Thursday, 15 July 2021 00:00

“ልጆቻችን በሚታነፁበት ስፍራ ጥቃት ሲፈፀም ማየትና መስማት ያማል”

Written by  ብርሃኑ በላቸው አሰፋ
Rate this item
(4 votes)

ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በመላው አለም እድሜያቸው ከ2-17 ዓመት ያሉ አንድ ቢሊዮን ልጆች የተለያዩ ጥቃቶች ይደርስባቸዋል፡፡ የጥቃቶቹ መገለጫዎች ደግሞ አካላዊ፣ ፆታዊና ስነልቦናዊ ናቸው፡፡
በማንኛውም ሰው፣ በማንኛውም ስፍራ በልጆች ላይ ጥቃት ሊፈጸም ይችላል፡፡ ጥቃቱ በቤተሰብ፣ በቅርብ ዘመድ፣  በባል፣ በወንድም፣ በመምህራን፣ በቢሮ ሃላፊዎች፣ በመሪዎችና በባለስልጣናት፣ በሃይማኖት አባቶችና በማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ሊፈፀም ይችላል፡፡ ይህም በቤት፣ በትምህርት ቤት፣ በስራ ቦታ፣ በመንገድና በማንኛውም ቦታ ይፈፀማል፡፡
ይህ ፅሁፍ በዋናነት የሚዳስሰው በትምህርት ቤት የሚስተዋለውን የልጆች ጥቃት ይሆናል፡፡ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፤ በመላው አለም 150 ሚሊዮን ልጆች በትምህርት ቤት ውስጥ የአቻ ለአቻ ጥቃት ተጋላጭ ናቸው፡፡ አንድ ሶስተኛ ልጆች በትምህርት ቤት ውስጥ ሞራልና ስሜታቸውን በሚጎዳ አጸያፊ ቃላት ስነ ልቦናዊ ቀውስ ይደርስባቸዋል፡፡
ልጆች በትምህርት ቤት ውስጥ ከሚደርስባቸው ጥቃቶች መካከል አካላዊ ጥቃት አንዱ ነው፡፡ አካላዊ ጥቃት በማንኛውም መንገድ በአካል ላይ የሚፈፀም የሃይል ጥቃት ነው፡፡ ለምሳሌ መምታት፣ መገፍተር፣ በጥፊ መምታት፣ በእርግጫ ማለት፣ በዱላ መምታት፣ በጥፍር መቧጨር፣ ጸጉር መንጨትን ያጠቃልላል፡፡
ሌላው ወሲባዊ ጥቃት ነው፡፡ ልጆችን በማታለል ወይም በማስገደድ ለፍላጎት ማርኪያ ሲጠቀሙባቸው ወሲባዊ ጥቃት ይባላል፡፡ ለአብነትም አስገድዶ መድፈር፣ የወሲብ ንግድ፣ ፆታዊ ትንኮሳ፣ ግብረ-ሰዶምና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ በሀገራችን ከ300 ወላጆች ጋር በተደረገ ዳሰሳዊ ጥናት፣ 40 በመቶ የሚሆኑ ቤተሰቦች፣ በሴት ልጆች ላይ በሚደርሰው ጥቃት ምክንያት ሴት ልጆቻቸውን  ትምህርት ቤት እንዳይልኩ ተስፋ እንደሚያስቆርጣቸው ተናግረዋል፡፡
 ልጆች በትምህርት ቤት ከሚደርስባቸው ጥቃቶች መካከል ስነልቦናዊ ጥቃት በሰፊው ይስተዋላል፡፡ ሥነልቦናዊ ጥቃት አስቦ አልያም በግድየለሽነት የልጆችን ሞራልና ስሜታቸውን በሚጎዳ ሁኔታ በማዋረድና በማሸማቀቅ የሚፈፀም ጥቃት ነው፡፡ ከእነዚህ ድርጊቶች መገለጫዎች መካከል ስድብ፣ ማንቋሸሽ፣ ማዋረድ፣ በማይፈልጉት ቅፅል ስም መጥራት ይገኝበታል፡፡ ይህን ተከትሎ ጥቃት የደረሰባቸው ልጆች የፍርሃት፣ የድብርት፣ ራስን የመጥላት፣ ያለመረጋጋት፣ በራስ ያለመተማመንና የብቸኝነት ስሜት ይስተዋልባቸዋል፡፡
ጥቃት የተፈፀመባቸው ልጆች አስፈላጊውን እንክብካቤና ምላሽ ሲያጡ ተበቃይ ሆነው በማደግ በቀጣይ የህይወት ዘመናቸው ጥቃት ፈፃሚ የመሆን ባህሪ ሊያዳብሩ ይችላሉ፡፡ ለተስፋ መቁረጥና ለሱሰኝነትም ይዳረጋሉ፡፡ ለጥቃት የተጋለጡ ልጆች በትምህርታቸው ዝቅተኛ ውጤት ያስመዘግባሉ፤ ከትምህርት መቅረት ያዘወትራሉ፤ ትምህርታቸውን ሙሉ በሙሉ የሚያsርጡም አሉ፡፡
በትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ልጆች ለጥቃት ከሚጋለጡባቸው ስፍራዎች መካከል፡- ሽንት ቤት፣ ጫካ፣ ኳስ ሜዳ አካባቢ እንዲሁም ክፍሎች ውስጥና ሰወር ያሉ ቦታዎች ይጠቀሳሉ፡፡ በእረፍት ሰዓትና በትምህርት ክፍለ ጊዜ ውጭ የሚገኙ ልጆች ደህንነትን መከታተል ይመከራል፡፡
ትምህርት ቤት ልጆቻችን የሚታነፁበት ስፍራ መሆኑ ቀርቶ የጥቃት መፈፀሚያ ሲሆን ማየትና መስማት ያማል፤ልብን ይሰብራል፡፡ በማንምና በምንም የማይተኩ ልጆቻችንን ደህንነት ለመጠበቅ ሰፊ ስራ ይጠበቅብናል፡፡ በተለይም ወላጆችና የትምህርት ቤት ማህበረሰብ፣ የልጆቻችንን ፍርሃትና ጭንቀት ተረድተን፣ የልጆቻችንን ስውር ትግል በነፃነት እንዲያወሩ እድል ልንሰጣቸው ይገባል፡፡  
ወላጆች ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ከመላክ ባለፈ ውሎአቸውን ለማወቅ በፍቅርና በትህትና መወያየት ማዳበር ይመከራል፡፡ ልጆቻችንን የመታደጊያ ቁልፉ ጆሮአችንን ከፍተን እነሱን ለመስማት ዝግጁ መሆን ነው:: ልጆች ለሚሰማቸው፣ ጊዜ ለሚሰጣቸውና ፍቅር ለሚያሳያቸው የልባቸውን ያጫውታሉ፡፡
ስጋታቸውንና ፍርሃታቸውን በመስማት መጋራታችን ብቻ ስነ ልቦናዊ አሸናፊነትን ያጎናፅፋቸዋል፡፡ ምክንያቱም በችግራቸው ወቅት የሚሰማቸው፣ የማይወቅሳቸው፣ የሚቀበላቸው፣ የሚያምናቸውና የሚቆረቆርላቸው እንዳላቸው መረዳታቸው ስነልቦናዊ ብርታት ይሰጣቸዋል፡፡ የአብሮነት ማረጋገጫችን የተስፋ ብርሃን እንዲታያቸው ያደርጋል፡፡
ትምህርት ቤቶች ለልጆች ደህንነት ምቹ ስፍራ እንዲሆኑ ማንኛውንም ጥቃት በቸልተኝነት አቅልሎ ማየት ዋጋ ያስከፍለናል። እናም ጥቃት ሲፈፀም ለሚመለከተው አካል ሪፖርት የማድረግ ባህል ልናዳብር ይገባል፡፡ ለመምህራንና ለወላጆች በልጆች ጥቃት ዙሪያ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ መስጠት ይጠበቃል። በትምህርት ቤት ለሚደርሱ ማናቸውም ጥቃቶች መንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የሃይማኖት አባቶችና መገናኛ ብዙኃን የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል። ሰላማችሁ ይብዛ!!
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 5450 times