Tuesday, 13 July 2021 00:00

"በትግራይ የሲቪል ሰዎችን ሁኔታ ለማሻሻል አፋጣኝ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል"

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. የፌዴራል መንግስት በትግራይ ክልል የተኩስ አቁም ማወጁን ተከትሎ፣ የግንኙነት መስመሮች በመቋረጣቸው፣ የክልሉ ነዋሪዎች የሚገኙበት ሁኔታ እንደሚያሳስበውና መንግስት የነዋሪዎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ የሚረዱ እርምጃዎች በአፋጣኝ ሊወስድ እንደሚገባ ገለጸ።
በክልሉ የተቋረጡ መሰረታዊ አገልግሎቶችን መመለስና በትግራይ ክልል ስላለው ተጨባጭ የፀጥታ ሁኔታና የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት በቂ መረጃ መስጠት፣ በዚህ ረገድ ያሉ ክፍተቶችን ለማረምና የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ትብብር ለመፍጠር ቀዳሚ እርምጃዎች ናቸው።
ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ የሚደረገው ጥረት አስፈላጊነት እንደተጠበቀና በክልሉ ለሚደረጉ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቶች ጥበቃና ለተደራሽነቱ ትብብር እንደሚቀጥል መገለጹ የሚበረታታ ሆኖ፣ የሲቪል ሰዎች ደኅንነትና ሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። በአሁኑ ወቅት በአብዛኞቹ የትግራይ አካባቢዎች የመብራት፣ የስልክና የውሃ አገልግሎት በመቋረጡ በክልሉ ነዋሪዎች ላይ ከባድ የኑሮ ጫና እያስከተለ ይገኛል። የባንክ አገልግሎት መቋረጥና የጤና አገልግሎት አቅርቦትና ተደራሽነት ውሱንነት ችግሩን አባብሶታል።
በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ሀገራዊና ዓለምአቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች የኤሌክትሪክና የስልክ አገልግሎት መቋረጥን ጨምሮ የሌሎች አቅርቦቶች እጥረት የሰብአዊ ድጋፉን በከፍተኛ ደረጃ እንደጎዳውና በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችና ስደተኞች ስለሚገኙበት ሁኔታ ማወቅ አስቸጋሪ እንዳደረገው ይገልጻሉ።
በአዲስ አበባ ከተማ የትግራይ ክልል ተወላጅ የሆኑ ነዋሪዎችና የሚዲያ ሰዎችን ጨምሮ፣ ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል  ተጠርጥረው የታሰሩ ሰዎችን ሁኔታ ኮሚሽኑ በመከታተል ላይ ይገኛል። ይህም በነዋሪዎች ላይ ማንነትን በመለየት ለጥርጣሬና መድልዎ  የሚያጋልጥ ተግባር እንዳይሆን ስጋት የሚያሳድር ነው።
በተጨማሪም፣ በክልሉ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ወጣቶች ወላጆችና ቤተሰቦች፣  ተማሪዎቹ፣ በአሁኑ ወቅት ስለሚገኙበት  ሁኔታ ተገቢው ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጣቸው የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላት በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ። 
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የነዋሪዎችን ደኅንነት ማረጋገጥ ቀዳሚው የመንግስት ግዴታ መሆኑን አስታውሰው፣ “በክልሉ የሚገኙ ነዋሪዎች ስላሉበት ሁኔታ የተገቢው መረጃ ማነስ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ከሚደመጡ ዘገባዎችና ንግግሮች ጋር ተዳምሮ፣ ነዋሪዎችን ስጋት ላይ የሚጥል ነው። የተኩስ አቁሙ በሁሉም በግጭቱ ተሳታፊ በነበሩ ወገኖች ሁሉ በቁርጠኝነት መከበርና የመሰረታዊ አገልግሎቶች በአፋጣኝ መመለስ፣ አጠቃላይ ሁኔታውን ለማሻሻል፣ በትግራይ ክልል  ለተፈጠረው ችግር ዘላቂ መፍትሔ ለማፈላለግ፣ እንዲሁም ሰብአዊ አቅርቦቱ  እንዳይቋረጥ  የሚደረገውን  ጥረት የሚያግዝ  ነው። በተጨማሪም  ማንኛውም አይነት እስር ሁልጊዜም ሕጋዊ ሥርዓትን የተከተለ ሊሆን ይገባል” ብለዋል።
ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም፤ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙ የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ሁሉ ሁኔታውን የሚያባብሱ፣ በሕዝቦች መካከል ጥላቻና ጥርጣሬን ሊፈጥሩ ከሚችሉ ንግግሮች እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርበዋል።
(የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋዜጣዊ መግለጫ)
ሰኔ 26 ቀን 2013 ዓ.ም.


Read 4328 times