Print this page
Sunday, 11 July 2021 18:16

ጦርነት “አብሾ” አለው - እንደ አውሬ ያደርጋል - ከበዛ፡፡

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 • ሕፃን አዋቂውን እየፈጀች ሰውን ከምድረ ገፅ ልታጠፋ ነበር - አንበሳዋ ሴክመት፡፡

          በጥንታዊቷ ግብፅ ውስጥ፣ ገናናው የጦርነት ጌታ ሄሩ ነው - በግሪክኛ ሆረስ ይሉታል። ግን፣ አስተዳዳሪ ንጉሥም ነው - ጦርነት መደበኛ የሁልጊዜ ስራው አይደለም። ሌሎች ሥራዎች አሉት።
ሴክመት ደግሞ አለች።
አንበሳዋ ሴክመት በሚል ስያሜ ትታወቃለች። ከሄሩ ጎን ለፆታ ተዋፅኦ ወይም ለፆታ እኩልነት በሚል ፈሊጥ አይደለም፤ የሴክመት ስም የሚነሳው። እንዲያውም በተቃራኒው ቀዳሚዋና ገናናዋ ሀርበኛ፣ ሴክመት ናት። የሄሩ ጦረኝነትን አግንነው ለመግለፅ ሲፈልጉ፣ “እንደ ሴክመት ነው” እያሉ ይፅፉ ነበር - ጥንት ከ3ሺ ዓመት በፊት።
በያኔዋ ግብፅ፣ ከአንበሳዋ ሴክመት በለጠ አስፈሪ ነገር አልነበረም ይላል - Sekhmet Bastet_ The Feline Powers of Egypt (2018) በሚል ርዕስ የቀረበው መፅሐፍ። ለነገሩ ስሟ፣ ያለ ቅፅል ለብቻው፣ ማንነቷን ይጠቁማል - “ሃያሏ፣ ከባዷ” እንደ ማለት ነው ስሟ። በግብፅ በብዛት የተሰሩ ሃውልቶች፤ የሴክመት ሃውልቶች ናቸው።
ሸንቃጣ ቆፍጣና ነው - ቁመናዋ። ፊቷን ግን የአንበሳ አድርገው ነው ሃውልት የሚሰሩላት። ቀስት ታጣቂ ናት። ለዚያውም ምርጥ ተኳሽ። “የሴክመት ቀስት፣ ሺ ገዳይ ነው” ተብሎላታል። ይሄ ብቻ ቢሆን ችግር አልነበረውም።
“የጨለማ እመቤት” ይሏታል - ፅልመትን ማውረድ ትችላለችና። “የእሳት የነበልባል ፍቅረኛ” ይሏታል - የቃጠሎ እመቤት ናትና። “የበሽታ ወረርሽኝ የምታመጣ፣ ሞትን የምትጠራ” በሚሉ ማዕርጎችም ትታወቃለች።
ምርጫዋ ግን፣ አጥንት መስበርና መዘንጠል ነው። ቁጡ አንበሳ አይደለች? “ደም የተጠማች” ብትባል፣ ያንሳታል እንጂ አይበዛባትም። ከሁለት ከሶስት ሺህ ዓመታት በፊት ብዙ ተፅፎላታል። ግን አንዷን ትረካ ብቻ ተመልከቱ። የሰው ልጆችን በሙሉ፣ ህፃን አዋቂውን ሁሉ እየፈጀች ከምድረ ገፅ ልታጠፋ ምን ቀራት? የዘግናኙ እልቂት እንዲህ ነው።
“ሰዎች፣ አማልክትን ረሱ፣ አፈነገጡ” የሚል ነው የነገሩ ሰበብ። “ሰዎች፣ አማልክት ላይ አመፁ” ተባለ። አጥፊዎችና አመፀኞች በዙ ለማለት መሆኑ ነው።
በዚህ አመፅ እጅግ ያዘነውና የተቆጣው “ረዓ” ወይም “ራ”፣ የተሰኘው የአማልክት አውራ፣ ጉባኤ ጠራ። ስብሰባ ተካሄደ። “አጥፊዎቹ ሰዎች ይጥፉ” ተብሎ ተወሰነ። በሰው ልጅ ላይ ጦርነት ታወጀ እንደ ማለት ነው።
ለዚህ የጦርነት ዘመቻ ማን ተመደበ? ምን ይጠይቃል! ክርክር ፉክክር አልነበረም። ለጦርነት ማን እንደሚመረጥ ይታወቃል።
ኃቶር (ኃጦር) ተመረጠች። ለጦርነት ዘመተች። በእርግጥ፣ ለወትሮ፣ “የአዝመራና የደስታ፣ የፍቅርና የሙዚቃ እመቤት ናት” ኃቶር። የህዳር ወር እና የጥር ወር ከኃቶር ክብር ጋር ተያይዘው የመጡ ስያሜዎች ናቸው ይባላል። ተገጣጠመ ያስብላል። የአዝመራና የፍቅር እመቤት ከህዳርና ከጥር ወር ጋር ብትዛመድ፣ የተጣጣመ ጋብቻ ይሆናል። የአዝመራና የሰርግ ወራት አይደሉ?
ለማንኛውም፣ ጦርነት የኃቶር ዋና ሙያና መደበኛ ስራ አይደለም። ጦርነት ሲመጣ ግን ማንም አይስተካከላትም። ዋናዋ ዘማች ትሆናለች። የአዝመራና የፍቅር፣ የአበባና የልምላሜ፣ የሙዚቃና የጭፈራ እመቤት የሆነችው ኃቶር፣ ወደ ጦርነት ስትዘምት፣ ለጊዜው፣ “ኃቶር ሃያሏ” በሚል ስያሜ ይጠሯታል። “ኃቶር ሴክመት” ብለው ይሰይሟታል። የጦርነት ቅፅል ነው።
ኃቶር ሴክመት በማለዳው እንደ ፀሐይዋ ጨረር ወደ ጦር አውድማው ገስግሳ ትደርሳለች። ከዚያም ማን ይመስላታል? ቀስቷን ታስወነጭፋለች፤ በእሳተ ነበልባል ታጋያለች፤ በሽታ ታወርዳለች፣ ሞት ታዘንባለች። አንበሳነቷ ይነሳባታል።
እየዘለለች እየተወረወረች አጥንት ትሰብራለች፤ ከእግሮቿ ስር ታደቅቃለች። ትዘነጥላለች። እልቂት ይሆናል። ደሞ ይጎርፋል።
ያኔ፣ ደም ስታይ፣ ደም ሲሸታት፣ ይብስባታል። ደም ደም ይላታል። ደም ይጠማታል። ለምን እንደዘመተች ትረሳዋለች፤ “ይሄኛው ንፁህ፣ ያኛው አጥፊ” እያለች ነለየት ያቅታታል። መግደል፣ ደም ማፍሰስና መፍጀት ብቻ ነው የሚታያት። ማን እንደሆነችም ይጠፋባታል። ኃቶር መሆኗን ትረሳለች።
ለጊዜያዊ ጦርነት፣ “ኃቶር ሴክመት” የሚል ስያሜ የተሰጣት እመቤት፤ጠቅልላ ወደ “ሴክመት” ተለውጣለች - ከጦርነትና ከፍጅት ሌላ ምንም የማያረካት ቁጡ አውሬ ሆናለች። መቶ በገደለች ቁጥር፣ ሺ ገዳይነት ያሰኛታል። ሺ በገደለችም፣ ሚሊዮኖችን የመግደል ረሃብ ያንገበግባታል።
አጥፊዎችን በመቅጣት ብቻ የምትመለስ አልሆነችም። ህፃን አዋቂውን ሁሉ እየፈጀች፣ የሰው ልጆችን በሙሉ ከምድረ ገጽ ልታጠፋ ሆነች። የሚያስቆማት ጠፋ። “ማጣፊያው አጠረ”። አማልክት ሁሉ፣ እህት ወንድሞቿ ይፈሯታል። የአማልክት አውራ፣ የሁሉም አባት እንኳ፣ ከፍጅት ሊገታት አልሞከረም። ፊት ለፊት ሊጋፈጣት አልቻለም።
ምን ተሻለ? በ700 ጋን ሃይለኛ መጠጥ ተዘጋጀ። አጠማመቁ በልዩ ዘዴ ነው። በሚያቀላ ቅመም የተሰራ መጠጥ ነው። ደም ይመስላል። እንደ ደም የቀላውን መጠጥ ወስደው፣ ሰፊ ማሳ ላይ፣ አፈሰሱት። በሐሩር የነደደውን በረሃ የሚያረሰርስ የአባይ ጎርፍ ይመስላል።
አካባቢው በቀይ መጠጥ ተጥለቀለቀ - እስከ እግር ጉልበት ድረስ።
ጦረኛዋ እመቤት በሄደችበት ሁሉ፣ ሰውን እየፈጀች ስትገሰግስ ደረሰች። ማሳውን ስታየው ተጥለቀልቋል። ቅላቱ እንደ ሰው ደም ነው። በጦርነት “አብሾ” የሰከረችው አንበሳ፣ ደም ጠማት። ከማሳው እየላፈች እዚው ስትጠጣ ዋለች። መጠጥ መሆኑን አላወቀችም። ገና ከማለዳ ጀምራ ስትጠጣ ውላ ሰከረች፤ አንበሳነቷ ረገበ፤ ከብዙ እልቂት በኋላ።

Read 2189 times
Administrator

Latest from Administrator