Monday, 12 July 2021 00:00

“አባዬ ውሸት አስተምረን” የጥንት ተረት

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ድሮ በጣም ድሮ፣  አንድ በጣም ትልቅ ውሸታም ሰው ነበር። ውሸቱ ግን እንዲሁ ተራ ውሸት አልነበረም። “የዓለም መሪን እንኳን ውሸት ተናግሮ ያሳምናል” እየተባለ የሚነገርለት ዓይነት ነበር። አንዳንድ ሰዎች “እርሱ ዋሽቶ ማሳመን ያልቻለው ፈጣሪን ብቻ ነው” እያሉ አጋነው የሚናገሩለት ነበሩ። ስለዚህም “ስመ ገናናው ዋሾ” እያሉ የሚጠሩት ነበሩ። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ “ሊቀ መኳስ ወናፍ” በሚል ስም ይጠሩት ነበር። የጀግና ማዕረግ የሰጡት ደግሞ “ግንባር ቀደሙ” ለማለት “ፊታውራሪ ቱልቱላ፣ ቱሪናፋ “ይሉት ነበር። ብቻ ምን አለፋችሁ፤ ወደ አንድ ስፍራ ሲሄድ “ዛሬ ደግሞ ምን ይዋሸን ይሆን?” የሚባል ነበር።
ሰውየው ውሸት ተናግሮ ስለሚያሳምንም ብዙ ታላላቅ ሰዎች ሁሉ በመወሽከት እንዲተባበራቸው ይለምኑት ነበር። እርሱም ቢሆን “ከፍተኛ ገንዘብ ካልተከፈለኝ ምን በወጣኝ እዋሻለሁ” የሚል የመደራደሪያ ዋጋ ያቀርብ ነበር ይባላል።
“የሰውየው የውሸት ዋጋ ጣራ የሚነካው የሀገሩ ንጉሥ ወደ ውጭ ሀገር  መልእክተኛ ሆኖ ሄዶ ዋሽቶ እንዲያሳምንለት ሲፈልግ ነው” የሚሉም ነበሩ። ታዲያ ለሀገሩ ንጉሥ እንደሚዋሽ ሁሉ ለውጭ መንግሥትም  ከንጉሡ ጋር ከተዋዋለው ጋር ያልተያያዘ ውሸት በማቀበል የታወቀ ነበር።
ለንጉሡም ቢሆን የሚፈልገውን ውሸት ከውጭ እያመጣ  ይመግበው ነበር። በተለይ ንጉሡን በሐሰት በመካብ ከሌሎች ወሽካቶች ውስጥ አንድም እንኳን የሚስተካከለው አልነበረም። ስለሆነም ማንም ተራ ሰው የሚሠራውን በዚች ምድር ላይ ከእርሱ በስተቀር የሚሠራው አለመኖሩን ምሎ ተገዝቶ በመንገር፣ ጥፋቱን ልማት አስመስሎ በማቅረብ፣ የሚይዘው ነገር ሁሉ ወደ ወርቅ የሚቀየር መሆኑን በመመስከር፣ ህዝብ ዘላለም እንዲነግሥ ሌት እንቅፉን አጥቶ ቀን ሥራ ፈቶ እንደሚጸልይለት በማብራራት፣ ከንቱ ውዳሴውን ዜማዊ በሆነ ጥበብ ይነግረው ነበር።
መቼም ሰው በጎ ሥራም ይሠራልና ዋሽቶ የሚያስታርቅ ሰው ሲፈለግ፣ በቅድሚያ የሚጠራው እርሱ ነበር። በዚህ ምክንያት በጣም የናጠጠ ሀብታም ሆነ። ቤተ መንግሥት የሚያህል ቤትም ሠራ። እንደፈለገ የሚያረባቸው፣ የሚመገባቸው ብዙ ከብቶችም ኖሩት። በዚህም ምክንያት በትልቁ ግቢ በኩል አድርገው ሲያልፉም ሆነ ሲያገድሙ “እንዲህ ያማረና የገዘፈው ቤት የማነው?” ብለው ቢጠይቁ “የቦልቧላው ከበርቴ” የሚል መልስ ያገኙ ነበር።
ሆኖም ልጆቹ ሲጫወቱም ሆነ ጓደኞቻቸው “የታላቁ ውሸታም ልጆች” ስለሚሏቸው ይከፋቸው ጀመር። ሚስቱም በባሏ ውሸታምነት ምክንያት በየደረሰችበት “የሊቀ ጠበብት ዋሾ ባለቤት” እያሉ በመጥራት መከራ ያበሏት ነበር። ስለሆነም ልጆቹና እናታቸው በአንድ ላይ ሆነው በእረፍቱ ቀን ሊያነገጋግሩት ወደ ማረፊያ ክፍሉ ሄዱ።
ከአጠገቡ እንደደረሱም ባለቤቱ ገለልተኛ በመምሰል “ልጆችህ ሊያነጋግሩህ ይፈልጋሉና አድምጣቸው” አለችው። ርዕሰ ውሸት የሆነው አባትም በፈገግታ ተቀብሎ “ደስ ይለኛል። ልጆቼ እንዲህ ተሰባስበው ሊጠይቁኝ ሲመጡ አጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ። አንዳንድ ጥንታዊ ሊቀ ሊቃውንት በመጻሕፍቶቻቼው እንደሚገልጡት “አባት እንዲህ እንደናንተ ሊጠይቁት ሲመጡ እንኳንስ ዕድለኛው ተጠያቂ አባት፣ ባናያት ነው እንጂ መሬት እራሷ ትደሰታለች። ጨረቃና ጸሐይም የበለጠ ይደምቃሉ። ትልልቅ ዛፎች ይለመልማሉ”  በማለት ጥያቄያቸውን እንዲያቀርቡ ነገራቸው። 
አንጋፋው ልጅም “በእውነቱ አባዬ ባንተ ውሸታምነት እኛ ልጆችህ ተቸግረናል። ከጓደኞቻችን ጋር ስንጫወት፣ በአንዳንድ በዓላት ከሰው ጋር ስንቀላቀል፣ ስንሠራ ‘የጀኔራል በጥረቄ ልጅ’ እያሉ ይጠሩናል። ስለዚህ እባክህ የሚበላና የሚጠጣ አልጠፋ ምነው ይህን ውሸትህን ለኛ ብለህ ብትተው” አለው። አባትየው የቀረበው ሐሳብ የልጆቹ ሁሉ መሆኑን ጠይቆ፣ የሁሉም መሆኑን ሲረዳ ወደ ሚስቱ ዞሮ “አንቺስ ምን ትያለሽ?” በማለት ጠየቃት።
ሚስትም “እኔም ብሆን በእርስዎ ምክንያት ገበያ ሄጄ መሸመት፣ ለቅሶ ሄጀ መድረስ፣ ሠርግ ሄጄ የደስታ ተካፋይ መሆን  አልቻልኩም። ‘የቢትወደድ ዋሾ ሚስት መጣች’ ብለው የሚንሾካሸኩብኝ ከሩቁ ነው። የሚበላና የሚጠጣ አልጠፋ ምነው ይህ ውሸተዎን ቢተውት” አለችና ጨመረችለት።
አባትየውም “በመጀመሪያ ሐሳባችሁን ስለሰጣችሁኝና በህብረተሰቡ የደረሰባችሁን መሸማቀቅ ስለነገራችሁኝ አመሰግናለሁ።  በእርግጥም ውሸታም ነኝ። በውሸታምነቴም ታውቄያለሁ። በመታወቄም ከፍተኛ ገንዘብ አገኛለሁ። በማገኘው ገንዘብም እናንተ የበለጠ ተጠቃሚ ናችሁ።” ካለ በኋላ “ለመሆኑ በዚች ምድር ላይ በአንድ ወይም በሌላ መልኩ የማይዋሽ ማን አለ? ከባለቤቴ፣ካንቺ  ልጀምር። ከእለታት አንድ ቀን ወደማልፈልገው ቦታ ሄደሽ አልሄድኩም አላልሺም? እናንተ ልጆቼስ አታድርጉ ያልኳችሁን አድርጋችሁ አታውቁም? ጓደኞቻችሁስ እናንተ ለኔ እንደዋሻችሁኝ እነሱም ለወላጆቻቸው አይዋሹም? የሃይማኖት አባቱ አትዋሹ እያለ እራሱ አይዋሽም?” እያለ ስለ ውሸትና ውሸታምነት ሁለንተናዊነት ጥበብ በተሞላበት መንገድ አስረዳቸው። ሲጨርስም በመካከላቸው ጸጥታ ሰፈነ።
አባትየው በመቀጠልም “በመሠረቱ ውሸትና እውነት አይነጣጠሉም። እኔ ስዋሽ ሌላ የሚቀበል ካለ ውሸት እውነት ነው ማለት ነው። ጦርና አገር በውሸት እንደሚፈቱት ሁሉ በውሸት ሊተሣሠሩ ይችላሉ። ሌላውን ሁሉ ተውት የውሸትና የውሸታም ጠበቃ ሆነው፣ መንገድ ፈልገው፣ ውሸቱን እውነት በማስመሰል ሌላውን ለማሳመን የሚጥሩ የነገሥታት ወሽካቾች በጣም ትልልቅ ከሆነ ቤተ ሊቃውንት የተመረቁ አይደሉሞን? ያውም ትእዛዙ ፈጣን ስለሆነ  የሚዋሹት ጥበብን ባልተላበሰ፣ ማንም ሊረዳው የሚችል ደረቅ ውሸት አይደለምን? አስቡት እንግዲህ እነዚህ ሰዎችኮ “መጡ መጡ” ተብለው ከንጉሡ ቀጥሎ የሚከበሩ ናቸው። ‘እንደ ንጉሡ አጎንብሱ’ እንደሚባለው ሁሉ በአዋጅ ‘እንደ ንጉሡ ተንፍሱ’ የሚሉም አሉ። እኔም እንግዲህ የቀን ህልሜን እውን ለማድረግ መዋሸት፣ ቱልቱላና ጥሩምባ መሆን ተሰጥኦዬም ሥራዬም ነው። ከልጅነቴ ጀምሮ ጥርሴን ነቅዬ ያደግሁበት ጥበብ ነው።” ብሎ ከተናገረ በኋላ፣ ሁሉም በጥሞና እየሰሙ መሆናቸውን ሲረዳ እንዲህ አላቸው፡-
“እንድታውቁት ያህል ፀሐይ በመሬት ዙሪያ ትዞራለች ተብሎ በብዙዎች ይታመን ነበር፣ ቀላልና ከባድ ነገር እኩል አይወድቁም ተብሎ በጠቢባን ጭምር ይታመን ነበር። ዛሬ ያ ዕምነት ውሸት ሆኗል። ስለዚህ በአንድ በኩል ለመዋሸት ጥበብ የሚያስፈልግ ሲሆን ጠቢብም የውሸት ጥበብ ማወቅ አለበት። ስለዚህ ውሸት ጥበብም ጭምር ነው። እርግጥ ነው በሐቀኞች ዓይን ስነምግባር የጎደለው ተግባር ቢሆንም ጥበብ ነው። አዋራጅ ቢሆንም ጥበብ ነው።” ሲል አስረዳቸው።
የውሸት ጥበብነት ቆይቶ የገባቸው ልጆችም ሌላ ጥያቄ ለማቅረብ ወሰኑ። በስምምነትም የመጨረሻው ልጅ “አባዬ፣ ውሸት ጥበብ ከሆነ ለምን አታስተምረንም?” ሲል ጠየቀ።
አባታቸውም የሁሉ  ጥያቄ መሆኑን ከተረዳ በኋላ “መልካም፣ ውሸት ጥበብ መሆኑን አምናችሁ ለመሰልጠን ከፈለጋችሁ በመጀመሪያ የአእምሮ መመዘኛ ፈተና መውሰድ አለባችሁ። ከዚያም ለስልጠና ብቁ ከሆናችሁ ረቀቅ ያለው ትምህርት ይሰጣችኋል።” አለና መለሰላቸው።
እናትየው “ውሸትም ሥራ ሆኖ ልሰለጥን? በሉ ሥራ አለብኝ ልሂድ” ብላ ስትሄድ ልጆቹ የውሸት ጥበብ ለመማር የሚያስችለውን ስልጠና ለመውሰድ ይችሉ ዘንድ የመግቢያ ፈተና ለመውሰድ ተስማሙ።
በዚህ መሠረት አባትየው ከመጨረሻው ልጅ በመጀመር “ልጄ እዚያ በጭጋግ ከተሸፈነ ተራራ ምን ይታይሃል?” በማለት ከእነሱ ከሃያ ኪሎ ሜትር በላይ የሚርቀውን ተረራ አሳየው።
ትንሹ ልጅም ምንም ሳያሰላስል “አንዲት ጅግራ እንቁላል ከጣለች በኋላ ክንፎቿን ስታርገፈግፍ አየሁ። ካላመናችሁኝ ሄዳችሁ እዩ” ሲል መለሰ።
አባትየው የመጨረሻ ልጁን “ጎበዝ እንዲህ ነው ውሸት!” አለና ወደ ሁለተኛው ዞር አለና፣ በሆዴ ውስጥ ምን ድንቅ ነገር ይታይሃል?” አለና ጠየቀው።
ሁለተኛው ልጅም “ከአልማዝ  የተሠራ ዘውድ ይታየኛል።” ሲል መለሰ። አባትየውም ከውሸት ጥበብ ትርጉም አኳያ ሲታይ ይህ መልስ ሊሆን ይችል እንደሆነ ልጆቹን ጠየቀ። ልጆቹም ሆድ ያንን ያህል ዕቃ አይዝምና ሰው አያምነውም አሉ። ስለሆነም ሁለተኛው ልጅ “አንተ ከሐቀኞቹ ወገን  ስለሆንክ ጥበቡ አይገባህምና ከዚህ ጎራ መደመር አትችልምና ይቅርብህ” ተባለ።
አባታቸው ቀጠለና ሦስተኛውን ከፊት ለፊታችን ካለው ሜዳ በሬዎች እየታገሉ ነው። አየኻቸው? አሁን አንዱ ወደቀ። የወደቀበት ምክንያት ምንድነው ብለህ ትዋሻለህ? ሲል ጠየቀው። ሦስተኛው ልጅም፤ በዓይኔ በብረቱ እንዳየሁት የወደቀው በሬ በጣም ጉልበተኛ ነው። ጉልበቱ እንኳን አንድን በሬ ሁለት ሦስት በሬ ሊያሸንፍ ይችላል። ነገር ግን የገጠመው በሬ ጥሩ የእርሻ በሬ ስለሆነ እንዳይጎዳ ሲል ትንሽ አፈገፈገ። በዚህ ጊዜ ከኋላው የነበረው ጉቶ አደናቀፈውና ወደቀ። አወዳደቁም ለክፉ አሳልፎ አይሰጠውም፤ አንድ ሁለት ወር ከተቀለበ ጉዳቱ ሊድን ይችላል።” ሲል ጥበባዊ ውሸት ዋሸ።
ልጆቹና አባቱም ጥሩ ቀጣፊ ሊወጣው እንደሚችል ስላመኑ ስልጠናውን እንዲያገኝ ተወሰነ። አባትየው ቀጥሎም ወደ አምስተኛው ልጅ እያየ፤ “አንተ ደግሞ ስለ ውሸት ጥበብ ሐሳብህን በግጥም ገለጸ” አለው።
አምስተኛው ልጅም ትንሽ አሰበና፤
“እበጠረቃለሁ እንዳገሬ ልብስ፣
ምድረ ጉንጭ አልፌ የት እንዳትደርስ።
እተረተራለሁ እንደጥቅል ክር፣
ለኔ ሥራዬ ነው አንተ ተከራከር።
መዋሸት ጥበብ ነው፣ መበጥረቅ ጥበብ ነው፣
ሀብታም፣ ድሃ፣ ንጉሥ ሁሉ ‘ሚፈልገው።” አለና ገጠመ። በዚህ ጊዜ ሁሉም አጨበጨቡ።
ወደ ስድስተኛው ልጅ እያየም፤ “ላንተ ደግሞ አንድ ጥያቄ እጠይቅሃለሁ። ይህም ጥያቄ ጥንት የነበረ ልጅ አባቱን ውሸት እንዲያስተምረው ጠይቆ የመለሰው ነው።” ካለ በኋላ "በሰማይ ስለተወቃ አውድማ ሰምተሃል?” ሲል ጠየቀው። ልጁም እንዳልሰማ መለሰለት።
ስለሆነም አባትየው ወደ ሰማይ ቀና አለና “ሰማይ ላይ አውድማ ሲወቃ ታያለህ?” አለው። ልጁም በፍጥነት ዐይኑን ይዞ “ኧረ አባዬ እብቁ ዓይኔ ውስጥ ገባ። እስቲ እፍ ብለህ አውጣልኝ” አለና ወደ አባቱ ቀረበ። በዚህ ወንድሞቹ በጣም ሳቁ።
አባትዬውም “ጎበዝ የኔ ልጅ፤ ጥንታዊው ልጅም አንተ የሰጠኸውን መልስ ነበር የሰጠው።” ካለ በኋላ “በእውነቱ ውሸት እንዴት ጠቃሚ ጥበብ መሆኑን፣ ከእናታችሁና ከአንዱ ወንድማችሁ በስተቀር፣ በሚገባ ታውቃላችሁ። በመሠረቱ ብዙ ስልጠና አያስፈልጋችሁም። ትንሽ ሳይንሳዊ መንገዱን ባሳያችሁ ከኔ የበለጠ የውሸት ሊቃውንት ትሆናላችሁ። በመሆናችሁም ጠቃሚና ተጠቃሚ ትሆናላችሁ። ስልጠናው በቅርቡ ይጀመራል።” አለና አሰናበታቸው።
በዚህ ዓይነት የውሸት ጥበብ ተስፋፋ፡፡
አንደኛው ልጅ፡-
“እበጠረቃለሁ እንዳገሬ ልብስ፣
ምድረ ጉንጭ አልፌ፣ የት እንዳትደርስ።
እተረተራለሁ እንደጥቅል ክር፣
ለኔ ሥራዬ ነው አንተ ተከራከር።
መዋሸት ጥበብ ነው፣ መበጥረቅ ጥበብ ነው፣
ሀብታም፣ ድሃ፣ ንጉሥ ሁሉ ‘ሚፈልገው።”
ሲል የገጠመው ግጥም፣ ዜማ ወጥቶለት ተዘመረ ይባላል፡፡
ተረቴን መልሱ አፌን በዳቦ አብሱ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ተረቱን በኢሜይል ያደረሰንን ተሾመ ብርሃኑ ከልብ እናመሰግናለን፡፡


Read 3413 times