Print this page
Sunday, 11 July 2021 17:47

የኢዜማ የትግራይ ቀውስ ትንተና እና ምክረ ሃሳቦች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 "ሀገርንና ሕዝብን ለመታደግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ሊሰሩ የሚገባበት ወሳኝ ወቅት ላይ ደርሰናል!


         ሀገራችን  ኢትዮጵያ  በለውጥ  ሂደት  ውስጥ  ከገባች  ከሦስት  ዓመታት  በላይ  አስቆጥራለች።  በእነዚህ ሦስት  ዓመታት  በርካታ  የሀገርን ህልውና  እና  ቀጣይነት የተፈታተኑ  ችግሮች አጋጥሟታል።
ከነዚህ ችግሮች መካከል በዋነኛነት የሚጠቀሰው ባለፈው ጥቅምት ወር በሀገራችን ሰሜናዊ ክፍል
በትግራይ  ውስጥ የተከሰተው ግጭት ነው።
የሕወኃት አመራሮች የለውጡ ሂደት ከመጀመሩ በፊት  የነበራቸው  ድርጅታዊ   የበላይነት እየተሸረሸረ በመምጣቱ፣ ወደ ትግራይ ክልል በማፈግፈግ፣ አቅማቸውን ማጎልበትና የለውጥ አመራሩን በመፈታተን፣ በለውጡ አካሄድ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር
ሲዘጋጁ ነበር፡፡
በለውጡ አመራርና በሕወኃት መሪዎች መካከል ያለው ውጥረት በአደባባይ ወጥቶ መታየት የጀመረው ኢሕአዴግ የሚባለው ግንባር ፈርሶ፣ ብልጽግና በሚባል ፓርቲ ሲተካ ሕወኃት
የብልጽግና አካል ሳይሆን በቀረ ጊዜ ነበር፡፡  
የድርጅቶቹ ትንቅንቅ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰው በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሳቢያ የ2012 ዓ.ም ምርጫ መራዘሙን ተከትሎ ነው።
ሕወኃት የምርጫውን መራዘም ሕገ ወጥ ተግባር ነው በማለት በአደባባይ አቋሙን አሳውቆ በራሱ ክልል የፓርላማው የአምስት ዓመት ዘመን ከማለቁ በፊት ምርጫ እንደሚያደረግ ሲያሳውቅ፣ የሕወኃትን በክልሉ ምርጫ የማድረግ ውሳኔ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ሕጋዊ አይደለም
ብሎ ነበር። የሕወኃት መሪዎች ደግሞ "የትግራይን ሕዝብ ምርጫ የማድረግ መብት፣ ምርጫ ቦርድ ሊያግድ አይችልም፤ የምርጫ ቦርድ ምርጫን ለማስፈጸም የተቋቋመ ተቋም እንጂ የሕዝቦችን በመረጧቸው መሪዎች ለመተዳደር በሕገ መንግሥቱ የተሰጣቸውን መብት ለመከልከል ወይም ለመፍቀድ አይደለም" በማለት በጳጉሜ ወር 2012 ዓ.ም የራሳቸውን ምርጫ አድርገው፣ መንግሥት መስርተናል አሉ። የምርጫውን እወጃ ተከትሎ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ በትግራይ ክልል የተደረገው ምርጫ ሕጋዊነት እንደሌለው በማሳወቅ፣ ለትግራይ ክልል ከማዕከላዊ መንግሥት የሚሰጠው የበጀት ድጎማ ተመረጥኩ ላለው የክልሉ አመራር አካላት በማይደርስበት ሁኔታ ለሕዝቡ እንዲደርስ ውሳኔ አሳለፈ።
2
የሕወኃት መሪዎች ከመስከረም 30 በኋላ በብልጽግና ፓርቲ የሚመራው የማዕከላዊ መንግሥት ሕጋዊነት ስለማይኖረው፣ ከማዕከላዊ መንግሥት የሚመጣን ምንም ዓይነት ውሳኔ እንደማይቀበል
አስታወቀ።  
ከዚሁ   ውሳኔ ጋር በተያያዘ ለተለያዩ ጉዳዮች ከማዕከላዊ መንግሥት ወደ ትግራይ ክልል የሚላኩ ኃላፊዎችን ማጉላላት፣ ሲፈልገውም "ትግራይ ክልል አትገቡም" በማለት መመለስ ጀመረ። ይህ የሕወኃት ተግባር በሕወኃትና በማዕከላዊ መንግሥት መካከል እየተካረረ የሄደው
ውጥረት ወደ መጨረሻ ደረጃ መድረሱን ያመላከተ ነበር።
በመጨረሻም ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የትግራይ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ሠራዊት በትግራይ ክልል በሚገኘው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሰሜን እዝ በሰፈረባቸው በተለያዩ ቦታዎች ላይ ጥቃት በመፈጸም ከፍተኛ ጉዳት አደረሰ። ይህ ተግባር ሕወኃት በ2010 ዓ.ም የፌደራል መንግሥት ውስጥ የነበረውን የበላይነት
ካጣ በኋላ አጠቃላይ ሀገራዊ አለመረጋጋት እንዲፈጠር፣ ሌሎች ፅንፈኛ ኃይሎችን ጭምር በተለያዩ
መንገዶች በመደገፍ ሲያደርግ የነበረው ሙከራን ወደ ሙሉ ውጊያ የወሰደ ነበር። ሕወኃት የመከላከያ ሠራዊታችን ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ፣ የፌደራል መንግሥት የሕግ የበላይነትን የማስከበር እርምጃ መውሰድ የጀመረ ሲሆን ከሦስት ሳምንት ውጊያ በኋላ የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት መቐለ ከተማን ተቆጣጥሮ ነበር። መከላከያ ሠራዊቱ መቐለን ከመቆጣጠሩ
በፊት የሕወሃት አመራሮች ወደ በረሃ የገቡ ሲሆን የመከላከያ ሠራዊት የመቐለ ከተማን
ከተቆጣጠረ በኋላ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62/9  እና  የፌደራል  መንግሥት  በክልል  ጣልቃ የሚገባበትን አሠራር ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 359/1995 መሰረት፤ ጊዜያዊ መንግሥት
ክልሉን እንዲያስተዳደር ተቋቁሞ ነበር።
የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ላለፉት ስምንት ወራት የክልሉን ሕዝብ ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል ምንም ዓይነት የፖለቲካ ማረጋጋት ሥራ ያልሠራና ለችግሩ መባባስ ከፍተኛ
አስተዋጽኦ  ያደረገ መሆኑን  መገንዘብ  ይቻላል። እንደዚሁም ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሕዝቡን ከማረጋጋትና ችግሩን ከመቅረፍ ይልቅ ብልጽግና ፓርቲን ለመትከል የተደረገው መፍጨርጨር ችግሩን አወሳስቦታል። የሕግ ማስከበር እርምጃው ከተጀመረ በኋላ በክልሉ ውስጥ ዘላቂ ሰላም
ለማስፈንና ዜጎች ወደ መደበኛ ሕይወታቸው በተቻለው አጭር ጊዜ እንዲመለሱ ለማስቻል
ሕወኃት ላይ እርምጃ ከመውሰድ ባሻገር ታስቦበትና ታቅዶ የተተገበረ የተቀናጀ ግልፅ ተግባር አለመኖሩ፣ ግጭቱን በተበታተነ መልኩ ወደሚደረግ ሽምቅ ውጊያ ስልት የቀየረው ሕወኃት ውጊያ መቀጠሉ፣ በክልሉ ውስጥ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ እየጨመረ ከመሄዱ ጋር ተደማምሮ፣ በክልሉ ሰላምን ማረጋገጥና ዜጎችን ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ መመለስ ሳይቻል ቆይቷል።
3
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ችግሩ ተባብሶ በቀጠለበት ሁኔታ ውስጥ የፌደራል መንግስት፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የተናጠል የተኩስ ማቆም ጥያቄን በመቀበል፣ መከላከያ ሠራዊቱን በቅጽበት ከአብዛኛው የክልሉ ክፍል አስወጣ። ይህ ሲሆንም በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ ሰላማዊ ዜጎችን (ተማሪዎች፤ የጊዜያዊ መንግሥት የታችኛው መዋቅር ሰራተኞች. ..ወዘተ) እና የአገሪቱ ሰላምና ሉዓላዊነት ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ችግር በቅጡ ከግምት ባላስገባና በተቻኮለ መልኩ መሆኑ፣ በትግራይ ክልል የደረሰው ቀውስ፣ ከክልሉም በላይ አንድምታ ወዳለው ከፍተኛ ምዕራፍ ሊሸጋገር
ችሏል፡፡
ከዚህ አንጻር የኢዜማ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ በወቅታዊ የትግራይ ክልል ሁኔታና ይበልጡንም ደግሞ ይህ የተፈጠረው አዲስ ሁኔታ ባጠቃላይ በሀገሪቱ ሰላም፤ የፖለቲካ መረጋጋት፤ ሀገራዊ አንድነት እንዲሁም በቀጠናው የወደፊት ሰላም ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ሀገራዊ ፈተናዎችንና የሚያስከትላቸውን አንድምታዎች  ከገመገመ በኋላ የሚከተሉትን የ"ቢሆንስ" ግምቶችና መውጫ መንገዳቸውን አስቀምጧል።
1. ቢሆንስ 1፤ አንደኛውና ከሀገሪቱ ዘላቂ ጥቅም አንጻር ጥሩ ሊባል የሚችል የቢሆንስ ግምት (scenario)፤ መንግሥት እንደሚለው፤ ይህ የተናጠል የተኩስ ማቆም፣ በክልሉ ያለውን የሰብአዊ ቀውስ ለመታደግና የእርሻ ጊዜው እንዳያልፍና ወደ ከፋ የችጋር ሁኔታ ውስጥ እንዳይገባ
በማሰብ የተደረገ እርምጃ መሆኑን በትግራይ ያሉት ታጣቂዎችም ሆነ ማኅበረሰቡ ተረድቶና አምኖበት በክልሉ ምንም ዓይነት የኃይል እንቅስቃሴ ቆሞና ሁሉም አካላት (የፌደራል መንግሥት፤ እርዳታ ሰጪ ተቋማት፤ የትግራይን አስተዳደር የተረከበው አካል... ወዘተ) ትኩረታቸውን ወደዚያ አድርገው በተቻለ መጠን በአጭር ጊዜ ችግሩን መቅረፍ የሚችሉበት፤ ከዚያም በኋላ ቀጣይ የፖለቲካ ጉዳዮችን በውይይት ለመፍታት ፍላጎት የሚታይበትና ወደ
ሰላማዊ መፍትሄ የሚኬድበት ቢሆንስ ነው። ምንም እንኳን ይህ ቢሆንስ ባጠቃላይ ሰላምን ከማንገሥና  የሰብዓዊ ቀውሱን ለመታደግ ጥሩ
የሚባል  ቢሆንስ ቢሆንም፣ እስከ ዛሬ በተለይም ባለፉት ሦስት ዓመታት ካየናቸው የባለድርሻ አካላት ባሕርይ አንጻር ሲታይ (ከመንግሥት፤ ከሕወኃት፤ ከእርዳታ ሰጪ አካላት ...ወዘተ) በተለይም ደግሞ ሕወኃት በእኒህ ሦስት ዓመታትም ሆነ ከዚያ በፊት ለ27 ዓመታት በማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ጭምር ሲጫወት የነበረውን አፍራሽ ሚና በቅርብ ለተመለከተ፤ እውን የመሆን ዕድሉ እጅግ የመነመነ ነው፡፡ ከሕወኃት ባለፈ ግን በትግራይ ውስጥ ሕወኀት ለረጅም ጊዜ ያሰረጸው ያስተዳደር ሥርዓት ነጻ አስተሳሰብ እንዲሰፍንና ይህንን መሸከም የሚችል ጠንካራ የሲቪክ ማኅበረሰብ ሊፈጠር አለመቻሉ፤ ይህ ቢሆንስ እውን እንዲሆን የሚያስፈልገው ማኅበራዊ ግፊት እንዲኖር ሁኔታው ስለማይፈቅድለት፣ ከሕወኃት
በተቃርኖ ለዚህ ቢሆንስ የሚሠራ ኃይል ለማየት አስቸጋሪ ያደርገዋል።
2. ቢሆንስ 2፤ በትግራይ ያለው ያልጠራ ሁኔታ እንደቀጠለና የትግራይ አማጺዎች ከትግራይ ውጭ ሊያደርጉ የሚሞክሩት ግጭቱን የማስፋት ሙከራ (ወደ አጎራባች ክልሎች ወይም ከዚያም ዘልቆ ለመግባት) በፌደራል መንግሥቱ እየተመከተና እየከሸፈ የሚቀጥልበት፤ ግልጽ አሸናፊ የማይኖርበት ሁኔታ። ሁለተኛውና ከመጀመሪያው የተሻለ የመሆን ዕድል ያለው የቢሆንስ ግምት፣ ሕወኃት በአማራና በአፋር ክልሎች እንዲሁም በኤርትራ በኩል መጠነኛ ትንኮሳዎችን የሚፈጽምበት፣ በትግራይ ውስጥም ከፍተኛ  ቀውስ  የሚከሰትበት  ሁኔታ ከተፈጠረ፣ የፌደራል መንግሥት መከላከያ ሠራዊት ተመልሶ ለመግባት ሊገደድ ይችላል፡፡ ይህ ሁኔታ ከሕውኀት ባሕሪና ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር የመሆን እድሉ የማይናቅ ነው፡፡
በዚህ ሁኔታ፡-
- በአንዳንድ ከተማዎች ሕግና ሥርዓት የማስከበሩ ደረጃ ዝቅተኝነት የሚፈጥረውን አጋጣሚ በመጠቀም ዘረፋዎች ሊካሄዱ ይችላሉ።
-  የእለት  እርዳታ  የሚያስፈልጋቸው  የክልሉ ነዋሪዎች በሚፈለገው ደረጃ እርዳታ ሳያገኙ ቀርተው ለከፍተኛ አደጋ ሊጋለጡ ይችላሉ፣
- መሰረታዊ ለኑሮ የሚያስፈልጉ አገልግሎቶች፣ የውሃ፣ መብራት፣ ህክምና ግብዓቶች ማግኘት የማይቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር የሚችልበት ዕድል ከፍተኛ በመሆኑ፣ የክልሉ ሕዝብ ለችግር የሚጋለጥበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፣
-  የክልሉን አስተዳደር እንደገና ለማቋቋም ጊዜ የሚወስድና አስቸጋሪ ሊሆን ስለሚችል፣ የክልሉ ሕዝብ ለረጅም ጊዜ ምንም ዓይነት አስተዳደራዊ አገልግሎት ሊያገኝ የማይችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።
-  የዚህ ዓይነት የማያቋርጥ ግጭት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ብዙ ችግሮችን ስቦ ያመጣል፤ (ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ይቀንሳል፤ በዚህም የሥራ አጥ ቁጥር ይጨምራል፤) በሌላው የሀገሪቱ ክፍልም አለመረጋጋትን ያስከትላል።
-  ሕወኃት ታጣቂዎችንና  አባላቱን  መመገብ ስለማይችል፣ ህዝቡን ሊያስጨንቅና ሊዘርፍ
ይችላል፣
5
- መንግሥት የወሰደውን ክልሉን ለቆ የመውጣት እርምጃ የሚቃወሙና ተመልሶ እንዲገባ ጫና የሚያደርጉ ሀገራት ሊኖሩ ይችላሉ፣ ይህ ቢሆንስ የመሆን እድሉ የተሻለ ይሁን እንጂ በክልሉና ባጠቃላይ በሀገሪቱ ከብሄር ፖለቲካ ጋር ተያይዞ የመጣውን አደጋ በዘላቂነት የማይፈታ፤ ሀገሪቱን ቀስ እያለ ውስጧን እንደሚበላ በሽታ ከመግደሉ በፊት መፍትሄ የሚፈልግ ስለሆነ፣ ለሀገሪቱ የተሻለ መፍትሄ በፍጹም ሊሆን አይችልም። የተረጋጋ (stable) ሁኔታ ስላልሆነ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ወደ ከፍተኛ ግጭት ማምራቱ አይቀርም። ከዚህ የቢሆን ግምት በመነሳት የመፍትሄ ሃሳብ ይሆናሉ ያልናቸው ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፡-
• በብዝኃነት ዙሪያ የሚነሱም ሆኑ ሌሎች ችግሮችን ለማስተናገድና ተረጋግቶ ወደፊት ለመጓዝ በመጀመሪያ ሀገር በጠንካራ መሰረት ላይ መቆም እንዳለባት ሁሉም ባለድርሻ አካላት አምነው የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች በሙሉ ይህን ከግንዛቤ ያስገባ መሆን ይገባዋል።
• በአንድ አካባቢ ሕዝብ ኪሳራ ሀገርም ሆነ ሌላው ሕዝብ ተጠቃሚ በመሆን የሚገኝ ሰላምና
ጥቅም እንደሌለ፣ ይህ ሁኔታ ሀገሪቷን ወደ ማያልቅ ግጭትና ውድመት እንደሚመራ
ኢዜማ በጥብቅ ማስገንዘብ ይሻል፡፡
• ሕወኃት፤ ትግራይ የራሷን መንግሥት ማቋቋም አለባት በማለት ሊያነሳ የሚፈልገው ሀሳብ፣ የትግራይን ሕዝብ ፍላጎትና ጥቅም እንደማያስጠብቅ ኢዜማ ያሳስባል።
• በዜግነት ላይ የተመሰረት ዴሞክራሲያዊ ፌደራሊዝም ሀገርን ማስቀጠልም ሆነ የብዝሃነትን ጥያቄ በአግባቡ ሊያስተናግድ የሚችል ሀገራዊ የፖለቲካ ሥርዓት መሆኑን
ኢዜማ ያስገነዝባል።
• ለሁሉም ችግሮች መፍትሄ የሚሆነው፣ ሁሉንም ዜጎች በእኩልነት የሚያስተናግድ፤
ተጠያቂነት ያለበት እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት የመመስረቱ ጥረት ላይ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ብርቱ ርብርብ ሲያደርጉ ብቻ ነው።
3. ሦስተኛውና እጅግ የከፋው የቢሆንስ ግምት፤  ሕወሃት  ክልሉን፣  አገሪቱንና ቀጠናውን ለማተራመስ ከሌሎች አክራሪ ሃይሎች ጋር ጥምረት የሚፈጥርበት ሁኔታና አልፎም ለሀገሪቱ የውጭ ጠላቶች መሳሪያ በመሆን በሀገሪቱም ሆነ ባካባቢው ፍጹም አደገኛ የሆነ ሁኔታ ሊፈጠር የሚችልበት ሁኔታ ነው፡፡
ኢዜማ፤ የሀገርን ህልውና እና ቀጣይነት ችግር  ውስጥ  የጨመረው  በትግራይና  በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች በየጊዜው የሚከሰተው ግጭት ዋነኛው መንስኤ፣ ማንነትን መሰረት ያደረገ የፍትህና የእኩልነት ጥያቄ፣ በሂደት ወደ ዘር የጥላቻና የግጭት ፖለቲካ በመቀየሩ መሆኑን ያምናል።  
ምንም እንኳን ለ30 ዓመታት ሲሰበክ የከረመ፤ በዚህ እንጠቀማለን ብሎ የሚያምን የዘር ልሂቅ በተፈጠረበት ሀገር፣ እንዲህ ዓይነት አመለካከት ባጭር ጊዜና በቀላሉ ይጠፋል ማለት ባይቻልም፤ የአደጋውን እምቅ አስከፊነት በመመልከት፣ ድርጅታችን፣ ኅብረተሰቡን፣ ከዚህ አደጋ እንዲጠነቀቅ ሲያሳስብ ቆይቷል። ይህ ሁኔታ ከሕወኃት የፀብ አጫሪነት ባሕሪ የተነሳ፣ አሁን ክልሉ፣ አገሪቱና ቀጠናው ካሉበት ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ሲታይና ከዚህም በተጨማሪ የውጭ አገራት፣ የአገራት ማኅበራት ሁኔታውን ባላገናዘበ መልኩ እያደረጉ ያሉት ጣልቃ ገብነት ሲታከልበት የመፈጠር ዕድሉ
አነስተኛ እንኳን ቢሆን፤ «የተሻለውን ተስፋ አድርግ፤ ግን ለመጥፎው ተዘጋጅ» እንደሚባለው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት፤ ሕዝብም ሆነ በፖለቲካ ጉዳይ ከመንግሥት ጋር ልዩነት ያላቸው ግን የሀገሪቱን ሰላምና አንድነት የሚፈልጉ ኃይሎች ሁሉ፣ በመተባበርና ያለ የሌለ አቅማቸውን በማሰባሰብ፣ ችግሩ ከመፈጠሩ በፊት ሊቀጩት የሚገባ ፍጹም አደገኛ ቢሆንስ ነው። የዚህ አደጋ ተጨባጭ አመላካች አንኳር ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው።
- በሀገሪቷ ሌሎች ክልሎች የሚገኙ አክራሪ ብሄርተኞች፣ የሕወኃት ተመልሶ ክልሉን መቆጣጠር፣ እነሱም ለማሳካት ለሚፈልጉት አክራሪ ብሄረተኛ አጀንዳ የመንፈስ ጥንካሬ ስንቅ በመሆን የአመጽ ትግላቸውን አጠንክረው እንዲቀጥሉ ሊያበረታታ ይችላል፤ ይህ ምልክት በማኅበራዊ ሚዲያው አሁንም እየተንጸባረቀ ነው፤
- ሕወኃት ተወሰዱብኝ የሚላቸውን የወልቃይትና የራያ አካባቢ በኃይል ለማስመለስ ሊሞክር ይችላል። ይህ ግምት ሳይሆን መቀሌ ከተለቀቀ ጀምሮ ሕወኀቶች ቀጣይ ሥራቸው እንደሆነ
እየተናገሩ ነው። ይህ ሁኔታ ከደህንነት አስከባሪ ተቋማት አልፎ ሕዝብ ለሕዝብ የሚጋጭበትና ከፍተኛ ጉዳት ሊደርስ የሚችልበትን ሁኔታ ሊያስከትል ይችላል፤
- በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች በአመጽ ለሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ሕወኀት እገዛ በማድረግ የአመጽን ደረጃ ሊያሳድገው፤ ሀገራችንን ባጠቃላይ ለማተራመስ ሊጠቀምበት ይችላል፣ (ይህንን ባለፉት 3 ዓመታትም ያየነው ነው)
-  ውጭ ሀገር የሚገኙ የሕወኃት ደጋፊዎችን በመጠቀም፣ እንደተለመደው የተዛባ መረጃ በማቅረብ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የሚያደርጉትን ጫና አጠናክረው ሊቀጥሉ ይችላሉ፣
- ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች በእርዳታ ስም ሁኔታውን የሚያባብስ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ፣
-  የኤርትራ መንግሥት በራሱ ምክንያትም ሆነ ከህወኃት በሚደርስበት ትንኮሳ ከትግራይ ታጣቂዎች ጋር ግጭት ውስጥ ሊገባ ይችላል፣
በዚህ እጅግ ፈታኝ በሆነ ወቅት ላይ በሀገራችን ላይ የተደቀነውን አደጋ ለማለፍ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት የሚያስፈልጋቸውን ትዕግስት፣ ጥበብ፣ አርቆ አሳቢነትና ቁርጠኝነት ከግምት ማስገባት ያስፈልጋል። በዚሁ መሠረት ኢዜማ የሚከተሉት ባለ ድርሻ አካላት መወጣት የሚገባቸውን ኃላፊነትና ሚና ማስገንዘብ ይሻል።
1. የመንግሥት ኃላፊነት 1.1 መንግሥት ሀገርን በመምራት ሂደት ውስጥ በየቦታው የሚዝረከረኩ አሠራሮችን መስመር በማስያዝ ጥበብ በተሞላበት መልኩ ሀገርን ማስተዳደር ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ አንጻር ሁሉንም ባለ ድርሻ አካላትን ያካተተ ፖለቲካዊ መፍትሄ በሚያስፈልጋቸው አጀንዳዎች ላይ ለሀገራዊ ውይይት በሩን ክፍት ማድረግ ይጠበቅበታል። ለዚህም እንዲረዳ ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር የሚታዩትን ልዩነቶች በማጥበብ፣ በመቀራረብና በመመካከር፣ ሀገር የመምራት ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ በጥብቅ ማሳሰብ እንወዳለን፡፡
1.2 ከሁሉ በፊት ሀገር እየመራ ያለው መንግሥት ቅድሚያ መስጠት የሚገባው ለሀገር ሕልውና እና ለዜጎች ደህንነት መሆኑን በሚገባ ማጤን ይኖርበታል፡፡
1.3   መንግሥት  ለዜጎች መግለጽ የሚገባውን ወቅታዊና ሀገራዊ ሁኔታዎች በየጊዜው እየተከታተለ በግልጽነት ማሳወቅ ይገባዋል።
1.4 መንግሥት ሀገራዊ ጉዳዮችን በሚገልጽበት ጊዜ ሀገርን የመምራት ኃላፊነት እንዳለበት አካል የሚመጥን ቋንቋ መጠቀም አለበት፣
2. የፖለቲካ ፓርቲዎች ኃላፊነት
2.1 የገዢውን ፓርቲ ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የፖለቲካ ፉክክር ሊኖር የሚችለው የሀገር ህልውና ሲረጋገጥ አና የሕዝብ ደህንነት ሲጠበቅ በመሆኑ፣ ለዚህ አላማ ሁሉም በጋራና በመቀራረብ መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል።
2.2 በትግራይ የተፈጠረው ችግር፣ የሁላችንም ሀገራዊ ችግር በመሆኑ፣ ችግሩን በጋራ ከመወጣት ውጭ የዘር ማንነትን መሰረት ያደረገ የችግሩ አፈታት፣ ችግሩን ከማባባስ በቀር መፍትሄ ሊሆኑ እንዳማይችሉ መገንዘብ ይኖብናል፣
8
3. የሕዝብ ኃላፊነት
ሀገራችንን አሁን የገጠማት ሁኔታ እጅግ አሳሳቢና በብርቱ የሚፈትነን በመሆኑ ለከፋ አደጋ ተላልፈን እንዳንሰጥ በጥንቃቄ የምንራመድበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ በዚህ ወቅት የሀገሪቱ ባለቤትና የችግሩ ገፈት ቀማሽ ሕዝቡ በመሆኑ፡-
3.1 መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በያለበት መሠረቱን ዜግነት ባደረገ መልኩ ተደራጅቶ ራሱን፣ ቤተሰቡን፣ አካባቢውንና ሀገርን ከተለያዩ ጥቃቶች መጠበቅ ግድ ይለዋል፡፡
3.2 ሀገርን ከመበታተን ለመታደግ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሚያደርገውን ብሔራዊ ጥሪ ተቀብሎ በመከላከያ፣ በፖሊስና በሌሎች የፀጥታ ተቋማት በመሳተፍ የዜግነት ድርሻውን ሊወጣ ይገባዋል፡፡
3.3 ከምን ጊዜውም በላይ ይህንን እጅግ ፈታኝ ወቅት በጥበብ ለማለፍ መላው የሀገራችን ሕዝብ ጥቃቅን ልዩነቶችን አስወግዶ፣ ከቀድሞ በበለጠ ተሳስቦና ተከባብሮ በአንድ እንዲቆም ሀገራዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
በመጨረሻም፤ በየደረጃው የምትገኙ የኢዜማ አባላትና ደጋፊዎች፤ በዚህ እጅግ ፈታኝ በሆነ ወቅት ከፓርቲያችን የሚጠበቀው የተለየ ኃላፊነት፣ ከምንጊዜውም ይልቅ የገዘፈ መሆኑን ልብ ልንል
ይገባል፡፡
ከዚህ አንጻር፣ ኢዜማ የሀገርና የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ባስቀደመ መልኩ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተጨማሪ ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ መሆኑንና ሀገርንና ሕዝብን ከሚያስቀድሙ ማናቸውም አካላት ጋር ተባብሮ ለመሥራት የአንበሳውን ድርሻ ለመውሰድ ቃል የምንገባበት ይሆናል፡፡
ሰኔ 26 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ

Read 1100 times
Administrator

Latest from Administrator