Print this page
Sunday, 11 July 2021 17:39

ምክር ጠላት ሲያበዛ...

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ... ያለንበት ጊዜ ብዙዎቻችን ቅርቦቻችን ካሉ ሰዎች... አለ አይደል....እየፈጸምናቸው ካሉ አጓጉል ተግባራትና እየሄድንባቸው ካሉ የተሳሳቱ መንገዶች ሊመልሱን የሚችሉ ምክሮች ልናገኝበት የሚገባ መሆን ነበረበት፡፡ ምን ያደርጋል...ምክር መስጠት፣ ወዳጅ የሚቀንስበት፣ ጠላት የሚያበዛበት ዘመን ሆነና አረፈው!    
ስሙኝማ… በተለይ ቅልጥ ያለ ‘ላቭ’ ነገርዬ የያዘውን ሰው መምከር አስቸጋሪ ነው፡፡ የሆነ በጣም የቅርብ ወዳጃችሁን የሚመለከት ነገር አይታችኋል፡፡ ዝም ብላችሁ ካለፋችሁ ውሎ አድሮ ይኸ ወዳጃችሁ መጥፎ ችግር ውስጥ ይገባል፡፡ ደግሞ፣ ቀድማችሁ ልታሳውቁት ስትችሉ በእናንተ ዝምታ ወዳጃችሁ የሆነ ነገር ቢደርስበት ህሊና የሚሏት ነገር በትንሹም አለች አይደል! ስለዚህ አረጋግታችሁ ብትነግሩት እንደሚረዳችሁ ታስቡና ከተለመደው የመገናኛ ፕሮግራማችሁ ውጪ ትቀጥሩታላችሁ፡፡
“እንዲህ አጣድፈህ የቀጠርከኝ ምን ቢገኝ ነው? ብቻ መኪና ገዛሁ እንዳትለኝ!”
“አንድ አስቸኳይ ነገር ልነግርህ ፈልጌ ነው፡፡ ምን መሰለህ…”
“እሺ ንገረኛ…”
“እ…ምን መሰለህ… (ውስጣችሁ የሆነ ነገር መንጫጫት ይጀምራል፤ ‹ከቀዩ በፊት ‘ተጠንቀቅ’ ነው ምናምን የምትለዋ ቢጫ መብራት ትብለጨለጫለች፡፡ ምናልባት የመናገር ውሳኔያችሁ የተሳሳተ ሊሆን ይችላል።) “ብቻ ተወው... ይቅር፡፡”
የምን ማመንታት ነው! ወይ መጀመሪያውኑ ጎመን በጤና ምናምን ጭጭ ማለት ነበር፡፡ እንደውም የምር እኮ....ነካክቶ መተዉ የበለጠ ችግር አለው፡፡ ልክ ነዋ....“ከጀመረ በኋላ ሙሉውን ያልነገረኝ የሆነ ነገር እያሴረብኝ ነው፣” ብሎ ምናምኑን ‘መወልወል’ ሊጀምር ይችላላ!
“አንተ ሰውዬ፣ ምን ነካህ! ለምን ጀመርክ፤ ለምንድነው የሚቀረው?”
“ግዴለም፣ እዚህ ውስጥ መግባት አልፈልግም፡፡ ሌላ ነገር ብናወራ ይሻላል፡፡”
“ምን ማለት ነው! መጀመሪያውኑ አንተ አይደለህ እንዴ የምነግርህ አለ ብለህ አካልበህ ያመጣኸኝ! አንተው ካልነገርኩህ አልክ፡፡ እዚህ ውስጥ መግባት አልፈልግም ማለት ምን ማለት ነው!”
“እርሳው አልኩህ እኮ!”
“ለምንድነው የምረሳው? አልረሳውም! ምን ነበር ልትግረኝ የፈለግኸው?”
“ኦኬ...ስለ ጁዲ ስለ ገርልፍሬንድህ …ተወው ብቻ...”
እንዴት ነው ነገሩ! “ሥራ ነው፣ ጭቅጭቅ!” ያለው ማን ነበር! ስሙኝማ...የምር ግን እንዲህ አይነት ነገሮች እኮ... አለ አይደል...መጀመሪያ የምታስቡትና ነገሩን ስትጀምሩት የሚመጣባችሁ አይገናኝም፡፡ መጀመሪያ ላይ ብዙም ሳትጨናነቁ “ምን ጣጣ አለው! በቃ እነግረዋለሁ፣ ከሰማኝ ሰማኝ፣ ካልሰማኝም የራሱ ጉዳይ!” ምናምን ይባላል፡፡ መናገር ከጀመራችሁ በኋላ “ምን አገባህ ቢለኝስ!”፣  “ቢቀየመኝስ!“ “ደግሞስ እኔ ምን ቤት ነኝ!” ምናምን አይነት ሀሳቦች እየተግተለተሉ ይመጣሉ፡፡ እናማ... እንዲህ አይነት ነገሮች መጀመሪያ ላይ  እንደሚመስሉን ቀላሎች አይደሉም ለማለት ነው፡፡ ያውም በአሁን ጊዜ!
“የማትነግረኝ ከሆነ ለምን ጀመርከው። ገርልፍሬንድህ እየሸወደችህ ነው ልትለኝ ነው!”
“እንደሱ አይደለም፡፡ ምን መሰለህ በቅርብ ጊዜ የያዘቻቸው ጓደኞች አሉ….”
“አውቃለሁ፡፡ ለእኔምአስተዋውቃኛለች…”
“እነዛ ሦስት ልጆች ጥሩ ባሕሪይ ያላቸው አይደሉም፡፡ ብዙ ልጆችን አበላሽተዋል፡፡ እና ጁዲ ሳታውቅ...”
እመኑኝ ይቺን ዓረፍተ ነገር አትጨርሷትም! ምላሳችሁ ላይ ተንጠልጥላ ትቀራታለች እንጂ እስከ አራት ነጥብ ድረስ እንድትሄድ አይፈቀድላትም፡፡
“ጁዲ ምን! በላ ጁዲ ምን! እንደሌሎቹ ተበላሽታለች ልትለኝ ነው?”
“አሁን እንደሱ የሚል ነገር ተናገርኩ?”
“ባትናገርም ልትለኝ የፈልግኸውን አውቄዋለሁ፡፡”
“እሺ፣ በቃ ተሳስቻለሁ፣ እርሳው…”
ምን አለፋችሁ... ነገር ተበላሽቷል፡፡ ከዚህ በኋላ “ቀኝ ኋላ ዙር!” “በደረትህ ተሳብ!” ምናምን ብሎ ነገር የለም፡፡ የአስርት ዓመታት የልብ ጓደኛችሁ የተለየ ሰው ይሆናል፡፡
“እንደውም እኮ አንተ ከመጀመሪያው ጀምረህ ለእሷ መልካም አመለካከት የለህም። የማላውቅ መሰለህ…” እመኑኝ፣ “የመሰል ምት...” “ተመጣጣኝ ምላሽ...” ቅብጥርስዮ ብሎ ነገር አያስፈልግም፡፡
እናላችሁ... ዘንድሮ የልብ ጓደኛ የምትሉትን ሰው ለመካለክል የምታደርጉት ሙከራ ብዙ ጊዜ ነጥሮ ወደ እናንተው ይመለሳል፡፡ “እኔ አልናገርም ብዬ በሆዴ ይዤ ነው እንጂ ዋነኛ ጠላቴ አንተ ነህ!” ማለት ይጀመራል፡፡ በእናንተ በኩልም “ለሌላ የማላደርገውን ጓደኛዬ ነው፣ የክፉ ቀን መመኪያዬ ነው፣ ሲጎዱት ተቀምጬ ማየት አልችልም ብዬ በነገርኩት፣ ይሄ ሁሉ ይደርስብኛል!” አይነት ቁዘማ ይጀመራል፡፡
እንበልና በስንት ልፋትና መንከራተት ሥራ ያገኘ ወዳጅ አላችሁ፡፡ ሚስቱና ልጆቹ በረሀብ የተነሳ ጎዳና ሊወጡ ትንሽ ሲቀራቸው ነው ጥሩ የሚባል ሥራ ያገኘው፡፡ ያን ጊዜ ሰው አየኝ አላየኝ ሳይል ህቅ ብሎ ያነባውን አትረሱትም። ታዲያ ምን ያደርጋል፤ ትንሽ ሲቆይና ለስንትና ስንት ዓመት ተከራይ ያጣ ቤት ሆነው የከረሙት ኪሶቹ አበጥ ማለት ሲጀምሩ፣ የሌለበትን ዓመል ያመጣል...መጠጥ፡፡ በዚህ የተነሳ ቤት ውስጥ ቀና ብሎ በዓይኑ ሙሉ ሊያያት ይሳሳላት የነበረችውን ሚስቱን ከፍ ዝቅ እያደረገ መሳደብ ጀምሯል። የምኖረው ለእነሱ ስል ነው ሲልላቸው የነበሩትን ልጆቹን በሆነ ባልሆነው ገጨት ማድረግ ጀምሯል፡፡
በመሥሪያ ቤት ደግሞ ከሥራ መቅረትና ማርፈድ በተጨማሪ የሥራው ጥራት እየቀነሰ፣ ጀማሪዎች አንኳን የማይሳሳቷቸውን ስህተቶች መሥራት ጀምሯል፡፡ አለቆች ደግሞ በስጨት ብለው እንደውም ቀይ ካርድ ሊሰጡት ነው እየተባለ እየተወራ ነው። ባለቤቱም “አለበለዚያ ልጆቼን ይዤ ጥርግ ነው!" ማለት ይዛለች፡፡
“ስማ አንተ ሰውዬ፣ ምን እየሆንክ ነው! ለምን አትረጋጋም!”
“ምን ለማለት ፈልገህ ነው?”
“ከመቼ ወዲህ ነው እንዲህ አይነት ባህሪይ ያመጣኸው?”
“ምን ባህሪይ አመጣ አሉህ?”
“ምናለ መጠጡን ብትቀንስ! መስሪያ ቤት እርምጃ ሊወስዱብህ እንደሆነ ነው የሰማሁት፡፡”
“ይሄን ወሬ ብለው ለአንተ አምጥተው ነገሩህ!”
“ባለቤትህ  ምርር ነው ያላት፡፡ እንደገና ልጆችህ...”
“የያዘኝ ይዞኝ ነው እንጂ፣ እኔ ከፈልግሁኝ አዲስ አበባን በአንድ እግሯ ማቆም የምችል ሰው ነኝ፡፡ ምድረ ምቀኛ ቢለፈልፍ ጉዳዬ አይደለም።”
“አሁን እያወራን ያለነው ስለእሱ አይደለም። ለምን አትሰማኝም! ስለወደፊት ህይወትህ እኮ ነው የማወራው፡፡”
ስህተት፣ ትልቅ ስህተት! ነገሩን ሁሉ ይጠመዝዘዋላ!
“ምን አልክ! ጭራሽ ስለ ወደፊት ህይወቴ አሳቢ ሆነህ አረፍከው! ከመቼ ወዲህ ነው አንተ ስለ እኔ ህይወት መጨነቅ የጀመርከው?”
እመኑኝ ነገርዬው እዚህ ቢቆም ይሻላል። አለ አይደል… ስህተቱን መቀበል ካልፈለገ ምን ማድረግ ይቻላል! “በቃ ነገርኸኛል። አሁን ወሬ ቀይር...” ብሎ ዝም ማሰኘት ይሻላል፡፡ ሰውየው እንዳጀማመሩ ዝም ብላችሁ ካዳመጣችሁት ብዙ ነገር ሊከተል ነዋ! ነገርዬው ወደ እናንተ ይዞርና አቅዳችሁ እንዳደረጋችሁት፡፡ ለአስርት ዓመታት በልብ ወዳጅነት ስንቱን ደግና ክፉ ነገር እንዳላሳለፋችሁ በአንድ ጊዜ… አለ አይደል…በዘመኑ ቋንቋ ‘ትርክቱ’ ይለወጣል፡፡ የጠላትነት ስፍራው ይለዋወጥና ቁጥር አንድ የነበረው አልሲሲ ይገነደሳል፡፡
“ድሮም እኮ አንተ ስለ እኔ ደግ ነገር አስበህ አታውቅም፡፡”
በቃ እዚህ ላይ ሁሉም ነገር ይለወጣል። የሀያና ሠላሳ ዓመት ወዳጅነት፣ አንዲት ትንሽዬ ምክር ለመስጠት በመሞከራችሁ ፍርስርሱ ይወጣል፡፡
እናላችሁ... አስቸጋሪ ነው፡፡ በቅርቡ ብዙ ነገር በሚወራባቸው መዝናኛ ቤቶች ከማምሸት ጋር ለቅርብ ጓደኛዋ ምክር ቢጤ ለመስጠት የሞከረች ልጅ፣ በዚሁ ሰበብ ጓደኛዋን አጥታ... “እኔስ ምን አቅብጦኝ ነው!” ስትል ነበር፡፡ እናላቸሁ አስቸጋሪ ነው። አሁን ሁሉም ለየልብ ወዳጁ፣ እንትናዬውና እንትናዋ፣ ከመጋረጃ ጀርባ ምን እየሠሩ እንደሆነ ቢናገር፣ ሰዉ ተስፋ ስለሚቆርጥ፣ የሰርግ አዳራሾች በገበያ እጦት ይከረቸሙ ነበር፡፡ ...ቂ...ቂ...ቂ...!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1532 times