Sunday, 11 July 2021 17:35

ዩኒቲ አካዳሚና የተማሪ ወላጆች ውዝግብ ላይ ናቸው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

  በዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ስር የሚገኘው ዩኒቲ አካዳሚ ቀራንዮ ቅርንጫፍ፣ የ2014 ዓ.ም መማር ማስተማሩን አቋርጫለሁ ማለቱን ተከትሎ፣ አካዳሚውና በአካዳሚው የሚማሩ የ1ሺህ 400 ተማሪዎች ወላጆች እየተወዛገቡ ነው ተባለ፡፡
ዩኒቲ አካዳሚ ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ ወረዳ 9 ውስጥ ከሚገኘው የኤልፎራ አግሮ ኢንዱስትሪ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በተከራየው ቦታ ላይ ከKG-8ኛ ክፍል፣ ከ9ኛ-12ኛ ክፍልና በከፍተኛ ትምህርት ደረጃ በዩኒቲ ዩኒቨርስቲ በመጀመሪያ ዲግሪ ላለፉት አምስት ዓመታት እያስተማረ የቆየ ሲሆን፤  ኤልፎራ ቦታውን ለሌላ አገልግሎት እፈልገዋለሁ በማለቱ የ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን እንደማይቀጥል አካዳሚው ለወላጆች በደብዳቤ ማሳወቁን ተከትሎ ነው ተማሪዎች፣ ወላጆችና መምህራን በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ መግባታቸውን የገለጹት፡፡
“አካዳሚው አሁን ባለው የኮቪድ ወቅት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ፣ ግንቦት 30 የፃፈውን ደብዳቤ ሰኔ 2 ቀን ለልጆቻችን መላኩ እጅግ አሳዝኖናል” የሚሉት ወላጆች፤ በዚህ አጭር ጊዜ ለልጆቻችን ት/ቤት ፍለጋ ብንሯሯጥም፣ በኮቪድ 19 ምክንያት ተጨማሪ አዲስ ተማሪ ለመቀበል ፍላጎት ያሳየ ት/ቤት በማጣታችን ተጨንቀናል ብለዋል፡፡
“ኤልፎራ ለቦታው ኪራይ ጨምሩ ብሎም ከሆነ አካዳሚው ወላጆችን ስብሰባ ጠርቶና አወያይቶ በጋራ መፍትሄ እንድንፈልግ ማድረግ ሲገባው “ልቀቅ ተብያለሁ” በሚል ብቻ 1 ሺህ 400 ተማሪ ያለ ዝግጅት  ሜዳ ላይ መበተን ከህግና ስርዓት ውጪ ነው” ሲሉ ወላጆች ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡
ወላጆች የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ ዘነበ ወርቅ አካባቢ በሚገኝ የቀበሌ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ባደረጉት ስብሰባ፤ ጭንቀታቸውንና የልጆቻቸውን የመለያየት ፍርሃት መንግስት አይቶ እልባት እንዲሰጣቸው ተማጽነዋል፡፡
“ዩኒቲ አካዳሚ ለማስተማር ስራ ሲጀምር የግቢውን ውበትና ስፋት አጠቃላይ ለመማር ማስተማር ያደረገውን ዝግጅት ስናይ ልጆቻችን ከሌላ ት/ቤት እያስወጣን ነው የመጣነው” የሚሉት ወላጆች፤ “ከተለያየ አካባቢ ቤታችንን ሸጠን፣ በት/ቤቱ አቅራቢያ ቤት ገዝተናልም ሲሉ በአካዳሚው ላይ የነበራቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
በስብሰባው ዕለት የተገኙ ተማሪዎችም “ይህንን ደብዳቤ ከተቀበልን ቀን ጀምሮ በመለያየት ጭንቀት ውስጥ ነን፣ መንግስትና ወላጆቻችን ተወያይተው የምንወደውና የለመድነው ት/ቤታችን ይቀጥልልን” በማለት የተማፀኑ ሲሆን ስለመለያየት ያቀረቡት መዝሙርም ወላጆችን በእንባ አራጭቷል፡፡
 ወላጆች ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤትና ለቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት የአቤቱታ ደብዳቤ አቅርበው መልስ እየተጠባበቁ እንደሆነ ጠቁመው፤ በዕለቱም ባለ አራት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተዋል፡፡ ወላጆች በአቋም መግለጫቸውም፤ መንግስት በዩኒቲ አካዳሚና በኤልፎራ መካከል የተፈጠረውን ችግር ከ1ሺህ 400 ተማሪዎች መጉላላት አንፃር ገምግሞ እልባት ይስጠን፣ ወላጆች ለልጆቻችን የሚስማማ ት/ቤት እስክናገኝ በጥቂቱ አምስት ዓመት የጊዜ ገደብ ሊሰጠን ይገባል፣ አሊያም የትምህርት ቤቱ መዋቅር እንዳለ ሆኖ የወላጆች ቦርድ ተቋቁሞ ትምህርት ቤቱ የሚቀጥልበት መንገድ ይመቻችል፤ ኤልፎራ ለግቢው ኪራይ ይጨመር የሚልም ከሆነ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ከፍለን  ልጆቻችን ትምህርታቸውን ይቀጥሉልን የሚሉት ይገኙበታል፡፡
ችግሮቻቸው እልባት ካላገኙ ግን ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ለጠቅላይ ሚኒስት፤ ለትምህርት ሚኒስቴርና በአጠቃላይ ለሚመለከታቸው አካላት እንገልጻለን ብለዋል -ወላጆች፡፡
ዩኒቲ አካዳሚ ቀራኒዮ  ቅርንጫፍ ለወላጆች በፃፈው ደብዳቤ፣ ኤልፎራ ቦታውን ለሌላ ጉዳይ እፈልገዋለሁ ማለቱን ተከትሎ ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲን በአቅራቢያው በሚገኝ ህንፃ ተከራይቶ ማስተማር መቀጠሉንና ለዩኒቲ አካዳሚ የሚሆን ምቹ ቦታ በማጣቱ የ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመንን መቀጠል እንደማይችል አስታውቋል፡፡
ወላጆች እስካሁንም የሚድሮክ ኢንቨስትምንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑትን አቶ ጀማል አህመድን ለማነጋገርና በጉዳዩ ላይ እልባት ለማግኘት ሙከራ እያደረጉ መሆናቸውን ገልፀው መንግስት ለነዚህ አገር ተረካቢ ህፃናት መፍትሄ እንዲሰጣቸው እየተማፀኑ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡



Read 1335 times