Wednesday, 14 July 2021 00:00

የማይስማሙ ላይስማሙ መድከም

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(1 Vote)

  የታላቁ የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ከተጀመረ አንስቶ ግብጽና ሱዳን ለድርድሩ የሚመጡት ለይስሙላ እንደሆነ በተደጋጋሚ አረጋግጠዋል፡፡ አንድ ሰሞን ግብጽ “የእናቴ ቀሚስ ጠለፈኝ” ብላ ከድርድሩ ስትወጣ፣ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ሆና እስኪመቻት ትጠብቃለች፡፡ ሱዳን በተራዋ “ብርድ ብርድ አለኝ” ብላ ስትተኛ፣ ኢትዮጵያ ከግብጽ ጋር ሆና የምትነቃበትን ጊዜ ትጠብቃለች። ሌላ ጊዜ ሁለቱም የራሳቸውን ምክንያት ፈጥረው፣ ከድርድሩ ራሳቸውን ሲያገሉ፣ ኢትዮጵያ ብቻዋን የድርድሩን ጠረጴዛ አቅፋ በሯን ለድርድር ክፍት አድርጋ ትጠብቃቸዋለች፡፡ እነሱ ወደ ድርድሩ እንደፈለጉ ሲገቡና ሲወጡ፣ ይህ ካልተደረገ ብለው ላለመደራደር ሲያንገራግሩ ከቦታዋ ሳትነቃነቅ የምትጠብቃቸው ኢትዮጵያ ናት።
የኢትዮጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ በኋላ ስለ ግድቡ ከሁለቱ አገሮች ጋር ለመወያየትና ለመደራደር ኢትዮጵያ ስትነሳ፣  የግድቡ መሰረት በሁለቱ አገራት ላይ የከፋ ጉዳት እንደማያደርስ እንዲገነዘቡ ግንዛቤ እንዲይዙ እንዲያውም በየጊዜው ለሁለቱም  የተመጠነ ውኃ እንዲደርስላቸው በማድረግ እንደሚጠቅማቸው፣ በተለይ ደግሞ ሱዳንን ከደለልና ከከፋ የጎርፍ አደጋ እንደሚታደጋት ለማሳወቅና  በመካከላቸው መተማመን እንዲፈጥር በማሰብ ነበር፡፡
ኢትዮጵያ አንድ መቶ ሃምሳ የሚሆኑ ስለ ግድቡ የተደረጉ ጥናቶችን አሳልፋ ለሁለቱ አገራት የሰጠችው የምትፈልገውን መተማመን ለማምጣት እንደነበር ይታወቃል፡፡
ሆኖም ግብጽና ሱዳን የቀረበላቸውን ሃሳብ በቅንነነት ተቀብለው፣ኢትዮጵያ በውሃ ሃብቷ እንድትጠቀም ፈቃደኛ ሆኖ ከመገኘት ይልቅ፣እ.ኤ.አ በ1929 እና በ1959 የተደረጉ ውሎችን እንደ ጋሻ በመያዝ፣ ውኃው እንዳይነካ የእነሱም ጥቅም በነበረበት እንዲቀጥል መታገሉን ተያያዙት፡፡ ድርድሩም አስር ዓመት ሙሉ ባለበት ሲረግጥ ኖረ። እስካለፈው ዓመት ሐምሌ 2012 ድረስ ግብፆችም ሆኑ ሱዳኖች ድርድሩ አንድ እርምጃ ወደ ግቡ እንዲራመድ ሳይፈቅዱ ቀሩ፡፡ አሁንም ፈቃደኝነቱ እንደሌላቸው መናገር አዳጋች አይደለም፡፡ ኢትዮጵያም ብትሆን ይህን ያህል ግድ የሚሰጣት ጉዳይ አልነበረም፡፡
አምና ግን የሕዳሴው ግድብ የመጀመሪያውን ሙሌት እንደሚካሄድ ሲታውቅና ኢትዮጵያም ነገሩን ለወዳጅም ለጠላትም ግልፅ ስታደርግ ሁለቱ አገራት፡- ግብፅና ሱዳን፤ “ምንም አይነት ስምምነት ሳይደረግ ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ ውኃ መሙላት አትችልም” የሚል መግለጫዎችንና ማስጠንቀቂያዎችን ማዥጎድጎድ ጀመሩ፡፡ ለድርድር በጠረጴዛ ዙሪያ ሲቀርቡ የሚያግባባ ሃሳብ ሲቀርብ እየተቃወሙ፣ በአንፃሩ ነባር ጥቅማቸው  እንዲቀጥል የሚጠይቅ ሃሳብ እየደረደሩ ጊዜውን መግፋት ተያያዙ፡፡ “ያለ ስምምነት አይሞላም” እያሉ እየጮሁ ባሉበት ጊዜ ሐምሌ 2013 ገስግሶ ደረሰ፡፡ ኢትዮጵያ የእነሱን ስምምነት በመጠበቅ የሐምሌን ወር አይኗ እያየ ማሳለፍ ስላልፈለገች አምና  ከስምምነት ውጪ ግድቡን ሞልታ ጨረሰች። የአንድ የክረምት ወቅት ዝናብ ያለ ጥቅም እንዲያልፍ ለማድግ ግብጽና ሱዳን የሸረቡት ሴራ ከሸፈ፡፡
ዘንድሮም የተከተሉት ያው የአምናውን መንገድ ነው፡፡ የአፍሪካ ህብረት አደራዳሪ፤ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት ታዛቢ እንዲሆኑ ተስማምተው ሲደራደሩ ከቆዩ በኋላ ሶስቱ ታዛቢዎች ወደ ሙሉ አደራዳሪነት እንዲገቡ ግብጽና ሱዳን ጠየቁ፡፡ ኢትዮጵያ ጥያቄውን ውድቅ አደረገች፡፡ ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ቢወሰዱትም ያገኙት መልስ  ግን በጀመራችሁበት ቀጥሉ የሚል ሆነ፡፡ እነሱ ግን አሁንም በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ለመቀጠል አልፈለጉም፡፡ ድርጅቱን አቅመ ቢስ ነው እየከሰሱ የእነ አሜሪካን ሙሉ አደራዳሪነት ለማምጣት እየቃተቱ  እንደተለመደው “አንዳች ዓይነት አሳሪ ውል ሳያደርግ ኢትዮጵያ በራሷ ውሳኔ ብቻዋን ግድቡን መሙላት የለባትም፡፡ ያለስምምነት መሞላቱ በቀጠናው ሰላም ላይ ስጋት ይደቅናል” በማለት በማስፈራራት ቀጠሉ፡፡  ኢትዮጵያ በጉጉት የምትጠብቀው የዘንድሮው ሐምሌ 2013 በተለመደው ጉዞና ፍጥነት፣ ሲገሰግስ መጥቶ ደረሰ። ኢትዮጵያም ከሰሞኑ  ሁለተኛውን ዙር የግድቡን ሙሌት ጀመረች፡፡ የኢትዮጵያ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፣ ለግብፅ አቻቸው ሰኔ 27 ቀን 2013 ዓ.ም የሙሌቱን መጀመር በክብር አሳወቁ በደብዳቤ፡፡ ወዲያውኑ  ከግብፅ ወዲያው ተቃውሞው ጎረፈ፡፡ የሱዳንና የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፤ ኒውዮርክ ላይ ተሰባስበው ከመምከራቸውም በላይ እንደተለመደው ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት በመውሰድ አንዳች ተዓምራዊ ምላሽ መጠበቅ መረጡ፡፡
ጉዳዩ ወደ ተባበሩት መንግስታት ፀጥታው ምክር ቤት ተወሰደ፣ ዳግም ወደ አፍሪካ ህብረት ተመልሶ ወይም ሶስቱ አገሮች በክብ ጠረጴዛ ላይ ተቀምጠው በመደራደር፤ ከስምምነት  ላይ ይደርሳሉ ተብሎ አይታሰብም፡፡ ነገሩ የማይስማሙ ላይስማሙ መድከም ነው፡፡
ግብፅና ሱዳን ቀደም ሲል የተጠቀሱት ውሎች ተከብረው የነበረው የውሃ ተጠቃሚነታው እንዲቀጥል ይፈልጋሉ፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ መሬት ከፍ ሰማይ ዝቅ ቢል በውሃ ሃብቷ የመጠቀም መብቷን የሚገድብ አንዳችም ውል አትቀበልም መቀበልም አትችልም፤ መቀበልም የለባትም፡፡
ኢትዮጵያ እስከ አሁን እንዳደረገችው ሁሉ በአባይ ተፋሰስ ውስጥ የሚገኘውን የውሃ ሃብቷን ማልማቱን ለእድገቷ መጠቀሟን ትቀጥላለች፡፡ ይሄ ደግሞ ሁለቱ አገራት አለን የሚሉትን የ1959 ውል ሰጠን የሚሉትን መብት ነፋስ የገባው ገለባ ያደርገዋል፡፡ ለኢትዮጵያ የሚቀላት ከመደራደር ይልቅ ማልማት፣ ሃብቷን እያለማች ግብፆችና ሱዳኖች ሁኔታውን እንዲለማመዱት ማድረግ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ባለፈው  ሰኞ ሰኔ 28 ቀን 2013 ዓ.ም ለተወካዮች ም/ቤት አባላት ባደረጉት ንግግር ላይ ስላነሱት የችግኝ ተከላ፣ ግብጽና ሱዳን ስላላቸው ተጠቃሚነት የተሰማኝን ቅሬታ ልግለጥ፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ከዳር እስከ ዳር ተነስቶ በየአካባቢው ችግኝ የሚተክለው አፈሩ በጎርፍ እንዳይወሰድ፣ እርከን የሚሰራው ሳር የሚያለብሰው መጀመሪያ አፈሩን ለመጠበቅና የውኃ ሃብቱን ለመታደግ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ይህ ስራ ወደ መሬት የሚሰርገው የዝናብ ውሃ እንዲጨምር፣ ምንጮችና ወንዞች እንዲጎለብቱ ማድረጉ እውነት ነው። ወንዞች በጎለበቱ ጊዜ ሁሉ ተጨማሪ ውሃ ይዘው ወደ አደባባይ መግባታቸው የታወቀ ነው፡፡ በዚህ ትርፍ ውሃ ግን ግብፅም ሆነች ሱዳን በነፃ ተጠቃሚ ሊሆኑ ፈፅሞ አይገባም። ሊከፍሉበት ይገባል፡፡ እስካሁን የተደረገው ወደፊትም የሚደረገው የችግኝ ተከላ የሚያስገኘው ለውጥ እየተመዘገበ፣ የትርፍ ውሃው ተጠቃሚና ባለቤት የኢትዮጵያ ህዝብ መሆን አለበት፡፡

Read 6143 times