Sunday, 11 July 2021 17:22

“መንግስት ይሄዳል ይመጣል፤ አገር ግን አገር ነው”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 መቼ ነው ከቤትሽ የተወሰድሽው ንገሪን?
ሀሙስ ሰኔ 24 ጠዋት 2፡00 ላይ ነበር መኖሪያ ቤቴ የተንኳኳው፡፡ ማነው ብዬ በሬን ስከፍት፣ የታጠቁ ፌደራል ፖሊሶች ናቸው። አራት የፌደራል ፖሊስና ሁለት ሲቪል  የለበሱ የደህንነት አባላት በሬ ላይ፣ ሌሎች አራት ፌደራል ፖሊሶችና ሁለት ሲቪል የለበሱ ደግሞ ከህንፃው ስር በፓትሮል መኪና ቆመዋል፡፡ መጀመሪያ በተሳሳተ አድራሻ የመጡ ነበር የመሰለኝ፡፡ ስሜን ጠየቁኝ፡፡ ልክ ስነግራቸው ወዲያውኑ እጄ ላይ የነበረውን ስልኬን ወሰዱና “ለምርመራ ትፈለጊያለሽ፤ ጥቆማ ደርሶን ነው አሉኝ፡፡ የምን ምርመራ ነው ስል እሱን እንሂድና እዚያ ለሚጠይቅሽ አካል ምላሽ ትሰጪበታለሽ አሉኝ፡፡ “እሺ ልብሴን ልቀየር” ብዬ ልብሴን ቀይሬ አብሬያቸው ሄድኩኝ፡፡
መጀመሪያ ወዴት ነው የወሰዱሽ?
 ወደ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ነው የተውሰድኩት፡፡ ከዚያ አሻራ የመስጠትና መሰል ሂደቶች ተከናወኑ ማለት ነው፡፡
በምን ጉዳይ ነው አንቺ ላይ ጥቆማ የደረሳቸው?
በሽብር ወንጀል ነው የተጠረጠርኩት። ሀሙስ ከጠዋት እስከ 8፡00 እዛው ከቆየሁ በኋላ የፍተሻ ፈቃድ አውጥተው ወደ ቤቴ ይዘውኝ ከተመለሱ በኋላ ቤቴን ሙሉ ለሙሉ ፈተሹ፤ ምንም ያገኙት ነገር የለም። የምጠቀምበትን ላፕቶፕ፣ ስልኬን፣ መዝሙር የማዳምጥበትን ፍላሽና የባንክ ደብተሮቼን ይዘው “ለምርመራ አስፈላጊ ነው በሚል ተመልሰን ሄድን፡፡ እኔ ይህን ሁሉ አጣርተው ሀሙስ ማታውኑ እለቀቃለሁ፤ ወደ ቤቴ እመለሳለሁ የሚል ከፍተኛ እምነት ነበረኝ፡፡ ምክንያቱም የሰራሁት ወንጀልም ሆነ የምጠረጠርበት አንዳች ነገር ስለሌለ ከአሁን አሁን ያሰናብቱኛል እያልኩ ስጠብቅ ነበር፡፡
ከዚያስ ምን ተፈጠረ?
እንዳሰብኩት ሳይሆን አምስት ስድስት ቀን ነው የታሰርኩት፡፡
የፋና ሬዲዮና ቴሌቪዥን እንዲሁም የአሃዱ ሬዲዮ ጋዜጠኛ እንደነበርሽ  አውቃለሁ አሁን ምን እየሰራሽ ነው?
እኔ በአሁኑ ወቅት ከትግራይ ጊዜያዊ መስተዳደር ጋር በመሆን እየተቋቋመ ያለውን የትግራይ ቴሌቪዥን ሥራ በመስራት ላይ ነው የምገኘው፡፡ በአጠቃላይ ጊዜያዊ መስተዳድሩን እያገዝኩ ነው ያለሁት፡፡ ይሄንን መረጃ እዚህ እየመረመሩ፣ መደወል ያለባቸው አካል ጋር ደውለውም ሆነ በሌላ መንገድ ማጣራት ይችሉ ነበር፤ ይሄን አላደረጉም፡፡ በሌላ በኩል “በማህበራዊ ትስስር ሚዲያ ህዝብን ከህዝብ ብሔርን ከብሔር የሚያጋጭ የወንጀል ስራ በመስራት፣ በረሃ ካሉ ሰዎች መረጃ በመቀበልና በማሰራጨት ህገ-መንግስቱን በሃይል በመናድ ስራ ተጠርጥረሻል” ነው የተባልኩት፡፡ ይሄ በጣም ስለገረመኝ መሳቅ አማረኝ፡፡… ገረመኝ ሁሉ፡፡
እንዴት ለምን ገረመሽ?
ምክንያቱም እኔ በስሜ የተከፈተ አንድ የፌስቡክ ገጽ ነው ያለኝ፤ ይህን ሁሉም ያውቃል፡፡ ከአምስት ሺህ ጓደኞች በተጨማሪ ከ44 ሺህ በላይ ተከታዮች አሉኝ፡፡ በዚህ የፌስቡክ ገጽ ፎቶዬ በግልጽ በተቀመጠበት ሁኔታ ነው ሀሳቦቼን የማንፀባርቀው፤ በብዕር ስምም ሆነ በፌክ አካውንት የምጠቀመው የተሰወረ ነገር የለም፡፡ ይህንን ሁሉም ያውቃል፡፡ ለዓመታት ስሜን ሳልደብቅ ፊቴን መልኬን እያሳየሁ፣ ፊልድ ብወጣ እንኳን ያለሁበትን ቦታ እየገለጽኩ፣ በነጻነት ሀሳቤን የማንፀባርቅ  ሰው ነኝ፡፡ ስደግፍም የምደግፈው ሀሳብን ነው፡፡ እኔን ከፍሎኝ አዕምሮዬን ተቆጣጥሮ የሚያሰራኝ አካልም የለም፡፡ ያደግሁትም ከኢትዮጵያዊነት የሚነጥል አመለካከት ባለው ማህበረሰብ ውስጥ አይደለም፤ መደጋገፍ መተባበርና ፍቅር ባለበት እንጂ፡፡
ካነሳሽው አይቀር ትንሽ  ስለአስተዳደግሽ አውሪኝ…የት? እንዴት?
ተወልጄ ያደግኩት ምዕራብ ሀረርጌ መኢሶ ውስጥ ነው፡፡ ምዕራብ ሀረርጌ ማለት ከአዋሽ በታች ሁሉም ኢትዮጵያዊ በፍቅር የሚኖርበት ሀገር ነው፡፡ ብሄራችንን እንኳን ሳናውቅና ሳንሰማ ነው አብዛኞቻችን ያደግነው፡፡ ለምን ብትይ… በዚያ አካባቢ ብሔር ጉዳይ ሆኖ የሚነሳበት ምክንያት አልነበረም፡፡ እኔ በአባቴ ትግሬ መሆኔን ያወቅኩት ከዩኒቨርሲቲ ከወጣሁ በኋላ ነው ብል እያጋነንኩ አይደለም፡፡
እኔ እናቴ ናት ያሳደገችኝ ልጅ እያለሁ እናቴ ከሞተች በኋላ ሃላፊነት ወስደው እናትም አባትም ሆነው ያሳደጉኝ የእናቴ ልጆች፣ ወንድሞቼ ናቸው፡፡ ከተለያየ ብሄር የተወለዱ የእናቴ ልጆች ናቸው፤ ተንከባክበው ያሳደጉኝ፡፡ ከአማራ የተወለዱ አሉ ከኦሮሞም የተወለዱ አሉ፤ እናቴ ደግሞ አገው ናት፡፡ ይህን የምልሽ… እንዴት የተሰባጠረ ቤተሰብ ውስጥና ማህበረሰብ ውስጥ እንዳደግሁ እንዲታወቅ ነው። ወቅቱም ስለሆነ ነው እንጂ እኔ ሳድግ ይህን ሁሉ አላውቅም፤ በአጠቃላይ በብሔርና በዘር ጠብቤና ተሸብቤ ያደግሁ አይደለሁም፡፡ ስለዚህ ከምንም በላይ አገርን ነው የማስቀድመው። መንግስት ይሄዳል ይመጣል፤ አገር ግን አገር ነው። የኔ ጉዳይ መንግስት አይደለም፤ ሀገር ነው፡፡ በእኔ እድሜ እንኳን ሶስት ጠቅላይ ሚኒስትሮች አይቻለሁ፡፡ አገሬ ግን ያቺው ናት፤ አትለወጥም አልተለወጠችም፡፡ አገርሽን የምታስቀድሚው ለህዝብሽም ለራስሽም ደህንነት ስትይ ነው፡፡  እኔ በዚህ ሁኔታዬ ለሀገር ስጋት ልሆን ቀርቶ ማስቡም ከብደኛል፤ ይዘገንነኛል “በሽብር ህገ-መንግስቱን በማፍረስ፣ ብሄርን ከብሄር በማጋጨት ወንጀል ተጠርጥረሻል ሲባል ሳቄን ነው የለቀቅኩት፡፡” መርማሪው፤ “ምን ስቅሻል ስራሽን ታውቂለሽ” ሲለኝ “አዎ እናንተ የዘረዘራችሁት ክስ ከእኔ ሁኔታና እውነታ ጋር የሚቃረንና እኔን የማይገልጽ ነው፤ እንዲህ መባሌ ለእኔ ስድብ ነው፡፡ አሁንም ሁሉም ነገር በእጃችሁ ነው አጣሩ፡፡ ንፅህናዬን ትደርሱበታላችሁ” አልኩኝ፡፡  እኔ ፊት ለፊት ወጥቼ የምጋፈጠውና እውነት ነው ላልኩት ሀቅ የምታገለው አባቴንና የአባቴን ቤተሰቦች አደጋ ላይ ጥዬ ነው፡፡
አባትሽ የት ነው ያሉት?
አባቴ ከእነ ቤተሰቡ ትግራይ ክልል ነው ያለው፡፡ አባቴንና ቤተሰቡን ብቻ ሳይሆን ራሴንም አደጋ ላይ ጥዬ ነው “አሁን በትግራይ ህወኃት እያደረገ ያለው ነገር ልክ አይደለም፤ ለትግራይ ህዝብም ሆነ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ አይጠቅምም” እያልኩ ያለሁትና፤  ከኔ ይልቅ እኔ በዚህ እንድጠረጠር ያደረገውን ሰው ወይም አካል አጥብቃችሁ ብትመረምሩ የተሻለ ነው ብዬ የነገርኳቸው፡፡ ምክንያቱም እኔን በማሳሰር “ሁሉም ትግሬዎች እየተለቀሙ እየታሰሩ ነው” የሚል ውዥንብር እንዲፈጠር የሚፈልጉ አካላት፣ እኔን እንደጠቆሙኝ አልጠራጠርም፡፡ እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ ማመን አልፈለጉም፣ እያመላለሱ ይመረምሩኝ ነበር፡፡
ይህ ሁሉ ክርክር ሳይሰራ ከአዲስ አበባ ራቅ ወዳለ ቦታ ተወስደሽ ነበር ለመሆኑ የት ነው የተወሰድሽው?
ቦታውን መግለፅ አልፈልግም፡፡ ይህን የማደርገው ለሌሎቹም ተጠርጣሪዎች ደህንነት ሲባል ነው፡፡ እውነት ነው ከአዲስ አበባ ራቅ ወዳለ ቦታ ነው የተወሰድነው፡፡ እኔ ብቻ ሳይሆን በርከት ያሉ ጋዜጠኞችም በግርግር የሄዱም ሰዎች ነበር፡፡ የቦታው አለመገለጽ የእኔን ቤተሰብ ዘመድ ወዳጅ ጨምሮ የአብዛኛዎቹን ቤተሰቦች በእጅጉ ያስጨነቀ ጉዳይ ሆኗል፤ ይሄ ስህተት ነው። በተለይ የእኔን የተለየ የሚያደርገው፣ እኔ የምታወቀው በማህበራዊ ትስስር ሚዲያ፣ መንግስት አሸባሪ ብሎ የፈረጀውን ህውኃትን በመታገል ስለሆነ፣ ቤተሰብም የተጨነቀው አብዛኛው በማህበራዊ ሚዲያም እንደ ስጋት የተነሳው፤ “በህወሃት ሰዎች ታፍና ተወስዳለች” በሚል ነበር። በመንግስት አካል እጅ እንደሆንኩ በእርግጠኝነት ቢያውቁና ቢሰሙ የሰራችው ካለ ተጣርቶ ትፈታለች በሚል ይረጋጉ ነበር፡፡ ይህ ባለመሆኑ ቤተሰብ፣ ወዳጅና ጓደኛ በከፍተኛ ስጋትና ጭንቀት ውስጥ ወድቆ ሰንብቷል፡፡ በዚህ በጣም ነው ያዘንኩት፡፡ ወይ በ48 ሰዓት ፍርድ ቤት አልቀረብኩ፣ ወይም ያለሁበት አልተገለፀ? አስቸጋሪ ጊዜ ነበር፡፡ ወንድሞቼ ያልሄዱበት ያልገቡበት የለም፤ ጓደኞቼ ብዙ ቦታ ተንከራትተዋል፡፡ የመንግስት ሰዎችም ያለሁበትን ለማጣራት ጊዜ  ወስዶባቸዋል። በዚህ ጊዜ ነው “ህወሃቶች ወስደው ገድለዋት ነው” ወደሚለው ጭንቅ ውስጥ የገቡት እና ይሄ በፍጹም ትክክል አልነበረም። እኔ እንደውም መወሰዴንም ያወቀ ያለ አልመሰለኝም ነበር፡፡ ማህበራዊ ሚዲያው እንዲህ መነጋገሪያ ያደረገኝ መሆኑንም አላወቅኩም ነበር፡፡
አንቺን ጨምሮ በርከት ያሉ ተጠርጣሪዎች ከአዲስ አበባ ውጭ ነበራችሁ፡፡ እንዴት ነበር አያያዛችው? የደረሰብሽ የመብት ጥሰት አለ?
አዎ በርከት ያሉ ታሳሪዎች አሉ፡፡ እኔ የነበርኩት ከጋዜጠኞቹ ጋር ነው፡፡ አያያዝን በተመለከተ… ቤተሰባችን የት እንዳለን፣ በምን ሁኔታ እንደምንገኝ፣ ማወቅ ነበረበት፣ የማወቅም መብት አለው፡፡ ….. ከዛ በተረፈ አያያዛችን በጣም ጥሩ ነበር፤ ምንም የጎደለብን ነገር አልነበረም፡፡ ያው የፀጥታ አካል ሲባል በአዕምሯችን የሚመጣብን ነገር አለ፡፡ የሚደበድብ፣ የሚያንገላታ አለ አይደል…. ከዚህ በፊት ይዘነው የመጣነው አስተሳሰብ ስላለ. ብዙ ሰው ይጨነቃል፡፡ ነገር ግን አያያዝ ላይ የገጠመን ምንም ችግር የለም፡፡
እንዲያውም ትልቅ አባት የሆኑ ፌደራል ፖሊስ ነበሩ፡፡ ወጣቶችም ነበሩ፡፡ በተለይ ትልቁ ሰውዬ እንደ አባት “ልጆቼ አይዟችሁ” እያሉ ይጨነቁልን ነበር፡፡ ለገላ መታጠቢያ ውሃ እንኳን  ራቅ ካለ ቦታ የሚያመጡልን ፖሊሶች ነበሩ፡፡ ይህንን ሌሎቹም አብረውኝ የነበሩት ይመሰክራሉ፡፡ እውነት ለመናገር ለፌደራል ፖሊስ ያለንን አመለካከት ለውጠን ነው የወጣነው፡፡
እከሌ ነው ሊጠቁምብኝ የሚችለው ብለሽ የጠረጠርሽው ወገን አለ?
አዎ! በኋላ ላይ የፌደራል ፖሊሶችም ጉዳዩን ካወቁ በኋላ ሲያጠሩ ማን ማንን እንደጠቆመ ተነግሯቸዋል፡፡ በእርግጥ ለእኔ እከሌ ነው የጠቆመሽ ያለኝ አንድም ሰው የለም፡፡ ነገር ግን እኔን የጠቆመኝን ሰው በግሌ የጠረጠርኩትና፣ እርግጠኛ የሆንኩት ዛቻና ማስፈራሪያ ይልክብኝ ስለነበረ ነው። እነሱም “እከሌ ነው” ስል ዝም ነው ያሉት። መቼም ጋዜጠኞች ነን ከሁኔታዎች የምንረዳው ነገር አለ፡፡ ያ የጠረጠርኩት ልጅ በተመሳሳይ በማህበራዊ ሚዲያ ሃላፊነት ሊያስወስድ በሚችል አኳኋን በኔ የተጻፈ ፅሁፍ ስር መጥቶ የጻፈውን ነገር ከተፈታሁ በኋላ ተመልክቻለሁ፡፡ እኔ እዚህ ላይ አንድ ነገር ማለት የምፈልገው፣ አሁን ያለንበት ወቅት አስቸጋሪና ሁላችንም በተጠንቀቅ ልንቆምበት የሚገባ ጊዜ መሆኑን ከምንም በላይ እረዳለሁ፡፡ ነገር ግን አንድ ግለሰብ የደህንነት አካል ስለሚያውቅና “እከሌ እንደዚህ ነው ያዙት” ስላለ ብቻ ሰውን አንጠልጥሎ መውሰድ ተገቢ አይመስለኝም። የደህንነቱ አካል ያለ ድካም በቀላሉ ጉዳዩን ማጣራት ይችላል፡፡ አንድ ሰው የግል ቂምና ጥላቻ ስላለውና ስለጠቆመ ብቻ፣ ፖሊስም ያንን ቃል ብቻ አምኖ ሰውን ማጉላላት የለበትም፡፡ አንድ ሰው ስለጠላሽ ብቻ እንዲህ በቀላሉ የሚያጠቃሽ ከሆነ በጣም ከባድ ነው፡፡
የደህንነት ስራ እኮ ራሱን የቻለ ትልቅ ሥራ ነው፡፡ እኔን የጠቆመኝ ሰው እኮ ትግራይ ክልል ላይ ጊዜያዊ መስተዳድሩ እንዳይረጋጋ ካደረጉት አንዱና ዋናኛው ነው። እዛ የነበሩትን አመራሮች አንዱን ከአንዱ እያበላለጠ ሲሳደብና ሲዘልፍ የነበረ ሰው ነው፡፡ አንዱን አካባቢ እያገለገለ፣ ሌላውን ሲያገን የነበረ ነው፡፡ ክልሉ ባልተረጋጋበት ሁኔታ እሳት ላይ ጋዝ ሲጨምሩ ምን እንደተፈጠረ ….ትግራይ ዛሬ ያለችበትን ሁኔታ ሁሉም የሚያውቀው ነው፡፡ ህዝቡና ወጣቱ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር እንዳይተባበርና እንዳይሰራ፤  በጊዜያዊ አስተዳድሩ ላይ እምነትም እንዳይኖረው፣ ምሁራን ሁሉ “ከምንታሰር” እያሉ ጫካ እንዲገቡ ሲያደርጉ ቆይተው መጡ፡፡ ይህ ሰውና ግብረ አበሮቹ፡፡ አሁን ደግሞ እኔን በመጠቆም፣ “ትግሬ ሁሉ እየተለቀመ እየታሰረ ነው” ብለው ህዝቡን ለማሸበር ሆን ተብሎ ሲሰራ፣ መንግስት መንቃትና መመርመር አለበት፡፡ ይህ ሰው እኔ ላይ በዛተ በሶስተኛው ወይም አራተኛው ቀን ነው እኔ የተወሰድኩት፡፡ ሁኔታው ሲጣራ በከፍተኛ ደረጃ ያሉ እነ ኮምሽነር ተስፋዬ፣ ይቅርታ ጠይቀውኝ ነው የወጣሁት፡፡ ማንም ሰው በስህተት ይታሰራል፣ ተጣርቶ ይለቀቃል፡፡ ግን የእኔ አግባብ ስላልነበረ ነው ኮሚሽነሩ አክብረው ከተወሰድኩበት እስክመጣ ጠብቀው፣ “ሞራልሽ እንዳይነካ፣ እንዲህ አይነት ነገር ያጋጥማል” ብለው ይቅርታ የጠየቁኝ፡፡
እስቲ በእነዚህ ቀናት የገጠመሽን ፈገግ የሚያሰኝ ወይም የሚስገርም ነገር ካለ አጋሪን?
እንግዲህ ስላልተፈቀደልኝ የቦታም ሆነ የሰው ስም አልጠቅስም፤ ግን ጋዜጠኞችም ታስረዋል፡፡ እነዚህን ጋዜጠኞች ለመውሰድ የፀጥታ አካላት ወደዚያ ህንፃ ሲሄዱ፣  ከጋዜጠኞች ጋር ቡና ለመጠጣት በአጋጣሚ ከመጡት ውስጥ የህንፃው የማርኬቲንግ ክፍል ሰራተኛ ነበረችና “ኑ ውጡ” ሲባሉ፣ እሷ ደንግጣ ምን አለች “እንግዳም?” “አዎ ተነሽ” ብለው ከእኛ ጋር ነው የሰነበተችው። እነሱን ፖሊሶች ሊወስዷቸው ሲመጡ፣ ሌላዋ ሁለተኛ ፎቅ ላይ ሆና የምታይ ሴት ነበረች፡፡ የባህል ልብስ መሸጫ ተቀጥራ የምትሰራ ናት፡፡ ልክ ጋዜጠኞቹን ይዘዋቸው ሊወጡ ሲሉ ፎቶ ለማንሳት ስልኳን ስታነሳ፣ ፖሊስ ከታች ሆኖ ያያትና “ስልክሽን ቁጭ አድርጊው” ሲላት ደንግጣ ቁጭ ታደርግና፣ ደግማ ስልኳን ልታነሳ ስትል፣ ከመቅፅበት ፖሊሱ አጠገቧ ደርሷል፡፡
እሷም ተወሰደች?
አዎ! አምጪ ስልኩን ብሎ ሱቋን አዘግቶ ይዟት ሄደ፡፡ እኔ ስጠይቃት፤ “አሳዝነውኝ ለአለቃዬ ላሳይ ነበር ፎቶውን ላነሳ የነበረው” ነው ያለችኝ፡፡ ይህቺ ሴት ምንም አታውቅም፤ ትልቅና የልጆች እናት ናት፡፡ ከሄድንበት ቀን ጀምሮ ቀን ከሌት ስታለቅስ ነበር፡፡ ከእኛ ጋር ለምርመራ ፖሊስ ፊት ቀርባ “ለፌስ ቡክ ነው ፎቶ ያነሳሽው” ስትባል “ኧረ እኔ ስለ ፌስቡክም አላውቅ፣ ልጆቼ ናቸው ፌስቡክ የከፈቱልኝ፤ የሚያሳዝን ነገር ወይም አንድ ነገር ሳይ ላይክ ከማድረግ ሌላ አላውቅም” አለች፤ “አይዞሽ ይለቁሻል፤ ለመርማሪዎቹ እውነቱን ንገሪ ብለናት ሄዳ ስትመለስ፤ “ለምን ፎቶ አነሳሽ” ሲለኝ “ጊዮርጊስ ፈርዶብኝ አልኩት!” ብላ አሳቀችን፡፡ አሁን ፖሊስ ይችን ሴትዮ እዚያው አስጠንቅቆ ሊለቃት ይችል ነበር፡፡ ምንም በማታውቀው ነገር ነው፣ ልጆቿን ቤቷን ጥላ ወጥታ በዚያው ይህን ሁሉ ቀን የታሰረችው። ቤተሰቧን  ልጆቿን አስቢያቸው…. ያሳዝናል! ሴትዮዋም ታሳዝናለች፡፡ የደህንነት አካላት ሳይሆን የመሰሏት… ብልጽግናዎች አድርጋ ነው የወሰደቻቸውና “እኔ አብይን እወደዋለሁ” ሁሉ ብላቸዋለች… ብቻ ያሳዝናል፡፡ ከእኔ ጋር ተለቃ አብረን ነው ወደ አዲስ አበባ የመጣነው፡፡ ሌላው አንድ  ታሳሪ ጋዜጠኛ እዛው አግኝቶኝ “አንቺም ታሰርሽ? አብዮት ልጆቿን መብላት ጀመረች?” ብሎ ተናግሮኛል፡፡ እኔን የብልጽግና ደጋፊ ናት ነው የሚሉኝ፡፡ እኔ ጋዜጠኛ ነኝ ነገር ግን ትግራይ ካለችበት ችግር የምትወጣው ጊዜያዊ መስተዳድሩን በማገዝ ነው ብዬ ስለማምን ነው ከትግራይ ጊዜያዊ መስተዳድር ጋር እየሰራሁ ያለሁት እውነታው ይሄ ነው፡፡
ማህበራዊ ሚዲያው ስላንቺ በጣም ሲጮህና ሲሟገት ነው የሰነበተው፡፡ ይህን ጠብቀሽ ነበር?
በፍፁም! እኔ መወሰዴም የተሰማ አልመሰለኝም ነበር፡፡ ታማኝ በየነ ሁሉ ከአሜሪካ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሲደዋወል ነበር - በእኔ ጉዳይ፡፡  ለመተከልና ለትግራይ አብረን እርዳታ ስንሰበስብ ነው ከሱ ጋር የተዋወቅነው፡፡ በሶሻል ሚዲያ፣ እኔን ፍለጋ በመምጣት፣ በስልክ ሁሉ ስትደውሉ ስትጨነቁ ለነበራችሁ… ወንድሞቼም ጓደኞቼ፣ የሶሻል ሚዲው ማህበረሰብ… ሁሉ በእጅጉ አመሰግናለሁ፤ ድምፅና ጉልበት ሆናችሁኛልና ክበሩልኝ እላለሁ፡፡

Read 3351 times