Sunday, 11 July 2021 17:15

የ"አረና" ም/ሊቀመንበር በትግራይ ቀውስ ዙሪያ ምን ይላሉ?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

በአዲስ አበባ የሚገኙት የአረና ትግራይ ሉአላዊነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ም/ሊቀመንበር አቶ ጎይቶም ፀጋዬ፣ በፌደራሉ የመከላከያ ሰራዊት ከትግራይ መውጣት፣ አሁን ባለው የክልሉ ቀውስ፣ በመገንጠል ጉዳይ እንዲሁም በዘላቂ መፍትሄ ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ባደረጉት ቆይታ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡  እነሆ፡-


        የመከላከያ ሰራዊት ትግራይን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ፣ በክልሉ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?
መከላከያ ትግራይን ለቆ ወጣ ሲባል ምን ማለት ነው? ትግራይ ግዛቷ የትኛው ነው? የትኛውስ የትግራይ አይደለም የሚለውን በሚገባ ማየት ያስፈልጋል። አሁን የምንተዳደረውስ በየትኛው ህገ-መንግስት ነው? በ1987 ነው? በሱ ከሆነ ክልሎች ወሰናቸው የት ነው? አማራ ክልልን የፈጠረው ይሄ ህገ-መንግስት ነው። ኦሮሚያ ክልልን ሌላውንም የፈጠረው ይሄ ህገ-መንግስት ነው፡፡ አሁንም በዚህ ህገ-መንግስት ነው የምንመራው ከተባለ፣ ህገ መንግስቱ እስካልተለወጠ ድረስ፣ በዚሁ ነው መመራት ያለብን፡፡ አንዱን የህገ-መንግስት ክፍል ወደ ሌላውን በራስ ህሊና ብቻ መዝኖ ጥሎ መሄድ እንዴት ይቻላል? ከዚህ አንፃር ትግራይ የሚባለው ማን ነው? መቀሌ ብቻ ነው? የሚለውን ስንመልስ ነው፣ መከላከያ ትግራይን በገዛ ፈቃዱ ለቆ ወጣ የምንለው። ዛሬ ላይ ትግራይ ማለት ይሄ አካባቢ ነው ተብሎ የወጣ አዲስ ህግ አለ? የለም፤ ይሄ በሌለበት ሁኔታ መከላከያ ከትግራይ ለቆ ወጣ የሚባለው አያስማማም። ለኔ የሚገባኝ ከመቀሌ ለቀው እንደወጡ እንጂ በሌላው አካባቢ መከላከያው እንዳለ ነው የሚገባኝ። እውነቱን ይዘን መነጋገር አለብን። የህግ ማስከበር ተብሎ የተጀመረው ዘመቻ አላማው ምን ነበር? ወልቃይትን፣ ራያን መውሰድ ነው? ሲጀመር 1987 ህገ-መንግስትን ጠቅሶ ወሎ ማለት አማራ ክልል ነው ካሉ በኋላ፤ ወልቃይት ትግራይ አይደለም፤ አማራ ክልል ነው ማለት እንዴት በመርህ ይገናኛል፡፡ አማራ ክልል ከመፈጠሩ በፊት ወሎ ውስጥ ኦሮሞዎች፣ አገዎች፣ አፋሮች፣ ትግራዋዮችና አማራዎች ነበሩ´ኮ። ትግራይ  ክፍለ ሃገር የተወሰነ አፋርንም ያጠቃልል ነበር፤ ጎንደር ወይም በጌምድር ወልቃይትንም ቅማንትንም አማራንም ያጠቃልላል፡፡ ጉዳዩ ወይም ጥያቄው የማንነት ነው ከተባለ፣ ለምን የአማራ ክልልን በፈጠረው ህገ-መንግስት መሰረት በህዝበ ውሳኔ አይፈታም፡፡ በዚህ ጥያቄ ላይስ የአማራ ክልል መንግስት ምን ግድ አለው? ይሄ ነገር አሳፋሪ አይደለም? ስለዚህ ትግራይን ለቀናል ማለት ለኛ መቀሌን ለቀናል ነው፤ መከላከያው አሁንም የትግራይን አካባቢዎችን እንደያዘ ነው ያለው፡፡
አሁን በትግራይ ምንድን ነው እየሆነ ያለው? በተለይ ጦርነቱ በማን ነው የሚመራው? የፖለቲካ ጎራ መደባለቆች ይታያሉ ይባላል፡፡ የእርስዎ ግምገማ ምንድን ነው?
አሁን እየሆነ ያለውን ለማወቅ ይከብዳል። መረጃ ማግኛ አማራጮች በሙሉ ተዘግተዋል፡፡ የባንክ፣ የመብራት፣ የስልክ አገልግሎት ተቋርጧል፡፡ ስለዚህ መረጃ ማግኛ አማራጮች የሉንም፡፡ ህዝቡ በከባድ ችግር ውስጥ ነው ያለው፡፡ የፌደራል ተቋማት አገልግሎት የተከለከለ ህዝብ በምን ሁኔታ ውስጥ እንዳለ ለማወቅ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ መንግስት ነገሮችን ክፍት ቢያደርግ፣ የተወሰኑ ነገሮችን አውቆ ቀጣዩን የፖለቲካ ሁኔታ ለመተለም ያግዛል፡፡ አሁን ግን ያለው ሁኔታ ያን ማሰብ የሚያስችል አይደለም፡፡ እዚህም አዲስ አበባ የተለያዩ የትግራይ ተወላጆች እየታሰሩ ነው፡፡ ስለዚህ የወደፊቱን ለማሰብ በጣም እያስቸገረ ነው ያለው፡፡ ችግሩ ብሶበት ህዝቡ ወደ አንድ አቅጣጫ ተገፍቷል፡፡ አሁን፣ ማን ምን አቋም አለው ለማለት ያስቸግራል፡፡ ሁሉም ወደ አንድ አቅጣጫ ተገፍቷል፡፡ አሁን ያለው እኮ የትግራይ መከላከያ ሃይል የሚባል እንጂ ህውኃት ብቻውን አይደለም፡፡ ህውኃት አንዱ አካል ነው እንጂ በውስጡ የቀድሞ ጀነራሎች እነ ጻድቃን፣ የባቶና፣ ሳልሳይ ወያኔ፣ ሳወት፣ የኛ አባላትም (በፓርቲ ደረጃ  ባንወስንም) በተለያዩ ተሳትፎ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ግማሹ ወደ ትጥቅ ሲገባ፣ ግማሹ እንደኛ ነገሩን በረጋ ሁኔታ ለማየት የሚፈልግ አለ፡፡ ስለዚህ የትግራይ ሁኔታ፣ የኛ ፓርቲ አባላትንም ውሳኔዎችና አቋሞች የፈተነ ሆኗል፡፡ ምንም እንኳ በአቋማችን የቀጠልን ሰዎች ብንኖርም፣ የኛ ፓርቲ አባላትን በእጅጉ የፈተነብን ሆኗል፡፡ ስለዚህ ትግራይ ላይ ያለው ሃይል ህውኃት ብቻ ነው ማለት አይቻልም፡፡
የመገንጠል አጀንዳ በስፋት እየተቀነቀነ ነው፡፡ የውጥረቱ መጨረሻ ምን ሊሆን ይችላል? የተወሰኑ ሴናሪዮዎች (የቢሆን ግምቶች) ማስቀመጥ ይቻላል?
በጎ ሴናሪዮዎችን እንመልከት ከተባለ፣ ምናልባት አለማቀፉ ማህበረሰብ እያደረገ ባለው ግፊት እውነተኛ የተኩስ አቁም ተደርጎ፣ ነገሮች በእርቅና መግባባት ሊጠናቀቁ ይችላሉ፡፡ ይሄ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ፣ የሃገሪቱን አንድነትም አስጠብቆ ሊያስቀጥል የሚችል ነው፡፡ ሌላኛው መጥፎ ሴናሪዮ፣ ውጊያው ሊቀጥል ይችላል፡፡ ነገር ግን አንዳቸው በጉልበት ቢያሸንፉ እንኳ ሃገሪቱን ወደ በጎ የፖለቲካ ሽግግር እንደማይወስዳት ጥርጥር የለውም፡፡ የመገንጠል ጉዳይ ግጭቱ በሰላም ቢያልቅም ጥያቄው መቅረቡ የሚቀር አይመስለኝም። ያው ህዝቡ እንዲወስን ይደረጋል፡፡ ይሄ ጥያቄ ከውጊያው በፊትም ሲነሳ ቆይቷል፤ በአንዳንድ ሃይሎች ሲቀርብ ነበር፡፡ ነገር ግን የህዝቡን ውሳኔ የሚወስነው ከፌደራሉ መንግስት ጋር ያለው ግንኙነት ወይም ለትግራይ ያለው አመለካከት ይሆናል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ህዝበ ውሳኔ ቢደረግ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው። ዞሮ ዞሮ፣ መጨረሻው ከእነዚህ ሁለት ሴናሪዮዎች አይወጣም፡፡
አረና በመገንጠል ጉዳይ ላይ አሁን ያለው አቋም ምንድን ነው?
እኔ አሁን እንዲህ ነው ብዬ የምናገረው አቋም የለም፡፡ አዳዲስ ነገሮች ተፈጥረዋል፡፡ በጣም ገፊ ነገሮች ተፈጽመዋል፤ ነገር ግን እኛ በፓርቲ ደረጃ ተሰብስበን የያዝነው አቋም እስካሁን የለም፡፡ አስቀድሜ እንዳልኩት አንዳንድ አባሎቻችን የነበሩ (TDF) ተቀላቅለዋል፡፡ ሌላው የሰፈሩን ኢህአዴግ ደግፎ እየተዋጋ ባለበት እኛም የሰፈራችንን ኢህአዴግን ደግፈን ለህልውናችን መዋጋት አለብን በሚል ነው እነዚህ አባሎቻችን የነበሩ ግለሰቦች በጦርነቱ እየተሳተፉ ያሉት። እናም በመገንጠል ጉዳይ ፓርቲያችን የያዘው አቋም የለም፡፡
ለትግራይ ቀውስ ምን ዘላቂ መፍትሄ ይታይዎታል?
በመጀመሪያ በትግራይ የተፈጸሙ ጉዳቶች በዓለማቀፍ ገለልተኛ አካላት መጣራት አለባቸው፡፡ አሁን በአገር ውስጥ ተቋማት የሚቀርቡ ሪፖርቶች ተአማኒነት የላቸውም፡፡ ስለዚህ አለማቀፍ ተቋማት የሚያቀርቡትን ጥናት ነው የምንቀበለው። ሌላው መከላከያው የያዘውን ቦታ ሁሉ መልቀቅ አለበት፡፡ ከዚያም ለእውነተኛ ድርድር መቀመጥ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ መንገድ ነው ወደ መፍትሄው መቃረብ የሚቻለው፡፡


Read 895 times