Sunday, 11 July 2021 17:11

COVID-19 ክትባት ጡት ለሚያጠቡ ወይንም ለእርጉዞች፡፡

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

 በእርግዝና ላይ ያሉ ሴቶች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የከፋ ሕመም ሊደርስባቸው ይችላል፡፡
ክትባት መውሰድ የግለሰብ ውሳኔ ነው፡፡
በእርግዝና ላይ ያሉ ሴቶች በኮሮና ቫይረስ ቢያዙ ካልተያዙት ሴቶች ይልቅ ሕመሙ ሊበረታባቸው ይችላል የሚል ግምት አለ። እ.ኤአ. June 16, 2021 The Centers for Disease Control and Prevention (CDC) እና the Federal Drug Administration (FDA) ያወጡት መረጃ እንደሚጠቁመው አንዲት ሴት በእርግዝና ላይ ካለች ለኮሮና ቫይረስ የሚሰጠውን ክትባት እንድትወስድ ይመከራል። በእርግዝና ወቅት ክትባቱን መውሰድ በኮሮና ምክንያት ሊከሰት የሚችለውን የከፋ ሕመም ሊያስወግድ ይችላል፡፡ ክትባቱን በመውሰድ እና አለመውሰድ ጉዳይ ላይ ጥያቄ ካለ የህክምና ባለሙያን ማነጋገር ይቻላል፡፡
በእርግዝና ላይ ያሉ ወይንም በቅርብ ጊዜ እርግዝና ላይ የነበሩ ሴቶች ለኮሮና ቫይረስ የመጋ ለጥና ለከፋ ሕመም የመዳረጋቸው ደረጃ ሆስፒታል አልጋ ከመያዝ ጀምሮ ጽኑ ክትትል የሚያ ስፈልገው እንዲሁም የመተንፈሻ አገልግሎትን ማግኘት እስከሚያስፈልገው ሊደርስ ከዚያም ካለፈ ሞት ሊያስከትል ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የተረገዘው ጽንስ ጊዜውን ሳይጨርስ ሊወለድ እና በእርግዝና ላይ ካልሆኑት ሴቶች በተለየ ከእርግዝናው ጋር በተያያዘ ሌሎች ችግሮችም በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሊያጋጥም ይችላል፡፡
በእርግዝና ላይ እያሉ የኮሮና ቫይረስ ክትባትን ለመውሰድ የወሰኑ ሴቶች የሚከተሉትን ነገሮች አስቀድሞ መገንዘብ ይጠበቅባቸዋል፡፡  
በእርግዝና ላይ እያሉ ለኮሮና ቫይረስ የመጋለጥ አጋጣሚ ሊፈጠር እንደሚችል፤
በቫይረሱ ምክንያት ለከፋ ሕመም መጋለጥ ሊኖር እንደሚችል፤
ከክትባት ሊገኝ የሚችለውን ጥቅም ማሰብ፤
በእርግዝና ወቅት የኮሮና ቫይረስ ክትባትን መውሰድ ምን ያህል ለደህንነት እንደሚረዳና በቫይረሱ ቢያዙ እንኩዋን ለከፋ ህመም አለመጋለጥን በመረዳት ጥንቃቄ ለማድረግ ዝግጁ መሆንን መረዳት ይጠቅማል፡፡
በእርግጥ እስከአሁን ድረስ ባሉት የዳሰሳ ጥናቶች ክትባቱ ቫይረሱን ከመከላከል አንጻር በሰውነት ውስጥ የሚሰራውን ጥቅም መሰረት በማድረግ በእርግዝና ላይ ያሉ ሴቶች ክትባቱን ቢወስዱ ምን ጉዳት ይኖረዋል የሚለውን በሚመለከት እስከአሁን ውስን መረጃዎች ናቸው ያሉት፡፡ ቢሆንም ግን በእርግዝና ላይ ሁነው ክትባቱን የወሰዱ ሴቶችን ሁኔታ ከየሆስፒታሉ መረጃ በመሰብሰብ ጥናቶቹ በመሰራት ላይ ናቸው፡፡ እስከአሁን ግን በእርግዝና ላይ ካሉ እና ክትባቱን ከወሰዱ ሴቶች የተገኝ የተዛባ መረጃ የለም፡፡ ስለዚህ በእርግዝና ላይ ያሉ ወይም የነበሩ ሴቶች ክትባቱን መውሰድ እንደሚመከሩ መረጃው ይጠቁማል፡፡
ክትባት መውሰድ የግለሰብ ውሳኔ ነው፡፡
ማንኛዋም በእርግዝና ላይ ያለች ሴት የኮሮና ቫይረስን ክትባት መውሰድ የግል ውሳኔዋ ነው። ነገር ግን በመውሰድና ባለመውሰድ መካከል ያለውን አስቀድሞ መገንዘብ ይጠቅማል፡፡ ይህንን ውሳኔ ለመውሰድ መጀመሪያ ከእራስ ጋር ከዚያም ከቤተሰብ እንዲሁም ክትትል ከሚያደርጉበት የህክምና ተቋም ከሚገኝ የሕምና ባለሙያ ጋር መነጋገር እንደሚገባ (CDC) ይመክራል፡፡ ከህክምና ባለሙያው ጋር የሚመካከሩዋቸው ቁልፍ ጉዳዮች የሚከተሉትን ያካትታል፡፡
በCOVID-19 ኮሮና ቫይረስ ለመያዝ ምን ያህል የተጋለጥሁ ነኝ?
በእርግዝና ላይ እያለሁ በኮሮና ቫይረስ ብያዝ ለእኔና ላረገዝኩት ልጅ ምን ያህል አደጋ ያደርሳል?
ስለ ኮሮና ቫይረስ ምን የታወቀ ወይንም ምን መረጃ አለ?
ክትባቱ በሰውነቴ ውስጥ በመግባት ምን ያህል ቫይረሱን ሊከላከልልኝ ይችላል?
ክትባቱ ምን የጎንዮሽ ጉዳት ያደርሳል?
በእርግዝና ወቅት ክትባቱን መውሰድ ጠቃሚ መሆኑን ለማሳየት ምን መረጃ አለ?
ክትባቱ ከጽንሱ ጋር በተያያዘ ምን ጠቀሜታ አለው?… ወዘተ
ከላይ የተመለከቱትን እና ሌሎችም ተያያዥ ነጥቦች በማንሳት እርግጠኛ ለመሆን ምክር መጠየቅ ብልህነት ነው፡፡
The Centers for Disease Control and Prevention (CDC) የበሽታዎች መቆጣጠርና መከላከል ማአከል የሚመክረውን ተግባራዊ ለማድረግ ለሚችሉ የምክር አገልግሎት ከሚሰጡ ባለሙያዎች አንድ አድራሻ ጠቁሞአል፡፡ ይህ አድራሻ Mother To Baby የሚባል ሲሆን በእርግዝና ወቅት ክትባትን መውሰድን በሚመለከት ቢያማክሩአቸው በእንግሊዝኛ መልስ እንደሚሰጡ ይጠቁማል። በስልክ ቁጥራቸው 1-866-626-6847 ወይም በኢሜይል አድራሻቸው MotherToBabyexternal icon ጥያቄውን በመላክ መልስ ማግኘት ይቻላል፡፡ ክትባቱን ሙሉ በሙሉ ከወሰዱ በሁዋላ ካለምንም ስጋት ቀድመው የሚኖሩትን አኑዋኑዋር መቀጠል ይቻላል፡፡ ነገር ግን ከክትባቱም በሁዋላ መጠንቀቅ እንደሚገባ አለመዘንጋት ይገባል፡፡ ምናልባት ከአለርጂክ ጋር በተገናኘ ከሕክምና ባለሙያ ጋር መመካከር እንደሚገባም መረጃው ይጠቁማል፡፡
ጡት ማጥባትና የኮሮና ቫይረስ ክትባት፡-
በተለያዩ ሀገራት የኮሮና ቫይረስ ክትባት ጡት በማጥባት ላይ ላሉ ሴቶች አልተሰጠም፡፡ ለዚህ የተሰጠው ምክንያት ክትባቱ በሚያጠቡ ሴቶች ላይ የሚኖረውን ውጤትና ተከትሎም በሚያጠቡት ልጅ ላይ ሊኖረው የሚችለው አዎንታዊ ወይንም አሉታዊ ተጽእኖን የሚያሳይ ምንም የጥናት ውጤት ባለመኖሩ ነው፡፡
የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እናትየው የምትወስደው ክትባት ጡት በሚጠባው ልጅ ላይ ምን ተጽእኖ አለው?
ክትባቱ በልጁ ላይ  ምን ውጤት አለው ?
ክትባቱ የጡት ወተቱን በማምረት ሂደት ምን ያስከትላል ? …ወዘተ
የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ሲባል የሚወሰደው ክትባት በሰውነት ውስጥ የሚሰራውን የመከላከል ሂደት መሰረት ባደረገ መንገድ ለሚያጠቡ ሴቶች ወይንም ለሚጠቡ ልጆቻቸው ለጊዜው የጤና ችግር ይሆናል የሚል ምንም ማረጋገጫ የለም፡፡ ጥናቶች ግን እየተደረጉ ነው፡፡
ልጅ የመውለድ ፍላጎትና የኮሮና ቫይረስ ክትባት፡-
ማንኛውም ሰው ልጅ የመውለድ እቅድ ወደፊት አለኝ የሚል የኮሮና ቫይረስ ክትባትን ከመውሰድ የሚያግደው ምንም ነገር የለም፡፡
እስከአሁን ድረስ የኮሮና ቫይረስ ክትባትን ጨምሮ ማንኛውም ክትባት ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ቢከተቡ ከዘር ፍሬ ወይንም እንቁላልን ከማምረት ጋር በምንም የማይገናኝና ልጅ ማፍራትን የማይከለክል መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ክትባቱን ከወሰዱ በሁዋላ በማንኛውም ጊዜ ልጅን ማርገዝ ይቻላል፡፡ ሳይንቲስቶች ባለማቋረጥ ከኮሮና ቫይረስ ክትባት ጋር በተገናኘ ጥናትና ምርምር በማድረግ ላይ ስለሆኑ አዲስ ነገር ካገኙ እንደሚያሳውቁ ምንም ጥርጥር የለውም CDC እንደሚያረጋግጠው፡፡
የኮሮና ቫይረስ አንዳንድ የጎንዮሽ ጉዳቶች አሉት ቢባልም በእርግዝና ላይ ያሉ ሴቶችን በተለየ ሁኔታ የሚመለከት ምንም ጉዳት እስከአሁን አልተመዘገበም፡፡ ምናልባትም እንደማንኛውም ሰው ከክትባት በሁዋላ የሚሰሙ አንዳንድ ስሜቶች ቢኖሩ እንኩዋን ከእርግዝና ጋር በማያያዝ በተለየ በአደጋ መልክ የሚመዘገብ ሳይሆን እንደማንኛውም ሰው ሁኔታውን ተቀብሎ ለተሻለ ጤንነት መዘጋጀት ጠቃሚ ነው፡፡


Read 10050 times