Wednesday, 07 July 2021 19:28

ሁሉም ሊያነበው የሚገባ መፅሐፍ!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

 (አስደንጋጭ እውነቶች፣ አስፈሪ ገጠመኞች፣ አስገራሚ ሁነቶች)
                          

            እንደ ሸማኔ - መወርወሪያ ፈጣን በሆነው በዚህ ዘመን፣ጥሞና የሰማይ ያህል በራቀበት ጥድፊያ-መሀል፣ ሰው ሰውን ለማድመጥ ፋታ ብርቅ ሆኖበት፣ ከማሽን ጋር ፍቅር ላይ በወደቀበት፣ የዘመን ምድጃ ላይ ለተጣድነው ለእኛ በሰከነ ወንበር፣አርቆ በሚያስብ ጠቢብ የበሰለ ቁምነገርና ፍሬ ያዘለ ዕውቀት ማግኘት፣ የሙሴን ያህል የመሪነት ሚና ያለው ይሰማኛል፡፡ የጋዜጠኛና ፀሐፌ ተውኔት ቴዎድሮስ ተክለ አረጋይ “ፍልስምና ፭” የተሰኘ  የቃለ ምልልስ ጥራዝ፤ ያካተታቸውን ሀሳቦች የማየው በፓኬጅ እንደተቀመጠና በሀኪም ትዕዛዝ እንደሚሰጥ ክኒን ነው፡፡
ምክንያቱም እያንዳንዱ ባለሙያ በቃለ ምልልሱ ያካፈለው ጥሬ እውቀት፣ ልምድና ገጠመኝ የእያንዳንዳችንን ስሜት የሚኮረኩር፣ በየቤታችን ያለውን ፈተና፣ በየዕለቱ የሚያጋጥመንን የተግባቦትና የመኖር ጣጣ ፈልቅቆ የሚያሳየን ነው። ርዕስ ጉዳዩ ብቻ ሳይሆን፣ርዕስ ጉዳዩ የቀረበበት መንገድና መልስ የተሰጠበት ማስረጃ በእጅጉ ጠቃሚና ገራሚ ነው፡፡
እንዲያውም አንዳንዶቹ የባለሙያዎች ገጠመኞችና የሕዝባችን ችግሮች ከእኛ ሀገር ባህል፣ እምነትና ስነ ልቦና ጋር በእጅጉ የተራራቁና ከተገበዝንባቸው ኩራቶች ያፈነገጡ ስለሆነ- የጓዳችን ጉድ ያስደነግጣል።
በሁለት መቶ ስልሳ ዘጠኝ ገፆች የተቀነበበው መፅሐፉ፤ በውስጡ ሺህ ጉዳዮች እልፍ ምሬቶች፣ በበርሜል የማይሞሉ የእንባ ዘለላዎች አካትቷል፡፡ እነዚህ ደግሞ ጥሬ ሳይንሱንና በተግባራዊ ሥራ ላይ ብቅ ያሉ እውነታዎችን የያዙ ናቸው፡፡ በተለይ ተግባራዊ ተሞክሮ ያላቸው የእርቅ ማዕድ የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጆቹ እንዳልክ አሰፋና ትዕግስት የሚያጋሩን ገጠመኞች የሚገርሙ የሚያስደነግጡና የሚያስፈሩም ናቸው፡፡
በሕፃናት የባህሪ ጥናት ባለሙያ የሆኑት አቶ እድሜዓለም ገዛ በላይ ደግሞ ለእኔ ዓይነቱ የዘርፉ ባይተዋር፤  አዳዲስ መረጃዎችንና የዘርፉን ጥናት ወቅታዊ ቁመና በጥልቀት ያሳዩናል፡፡ በተለይ ወላጆች ገና ልጁን ወደዚህ ምድር የማምጣት ዕቅድ ሲጀምሩ በልጁ ሕይወት ላይ የሚኖራቸው ሕልም ያለውን ሚና በመግለፅ ጀምረው፣ በየዕድሜ አንጓው፣ያላቸውን ባህሪያት በመተንተን የሚያስተምሩንና ባለማወቅ ምክንያት የሚፈጠሩ የባህሪይ ዝብርቅርቆሽን በማሳየት ያኖሩልን ቁምነገር በእጅጉ የሚደንቅ ነው፡፡
ጠቅለል አድርገን ስናየው፣ የአቶ እንዳልክ አሰፋ ቃለ ምልልስ በአብዛኛው በተሞክሮ የታገዘ በመሆኑ ማመን የሚያዳግቱና ጉድ የሚያሰኙንን፣ምናልባት የሚሠቅቁንን ሀቆች አስፍረውታል፡፡
ልንቀበላቸው የሚከብዱን ገጠመኞች
(ገፅ 60 እንዲህ ሰፍሯል፡-)
ሚስቱ ወደ እኛ ቢሮ መጡ፡፡ ሚስት በጣም ነበር የምታለቅሰው…… "ከባሌ ጋር 4 ዓመት ኖረናል፡፡ አንድ አልጋ ላይ እናድራለን። ግን እስካሁን ድንግል ነኝ፡፡ ከባሌ ጋር ወሲብ ፈፅመን አናውቅም፡፡”
ይህ ለአንባቢ ግራ አጋቢ እንቅቅልሽ ነው። በሌላ በኩል፤ የትዳር ምሰሶ ወሲብ ነው ለሚሉት ወገኖች ደግሞ ፈታኝ ምስክር ነው…. ይሁንና ይህ ችግር በአማካሪዎቹ አማካይነት በህክምና ባለሙያዎች የተፈታ  መሆኑን መፅሐፉ ይነግረናል፡፡
2. ሌላው ለሚያነብበው ሁሉ የተዓማኒነት ጥያቄ የሚፈጥረው ቀጣዩ ምልልስ ነው፡፡ (ገፅ 65)
በአንደኛው ወገን ሊፈርስ የተጠጋ፣ውሳኔ የተሰጠበት ትዳር ነው፡፡ ሴትየዋ እርቅ ማዕድ የሬዲዮ አዘጋጅ ዘንድ ሄዳለች። ጋዜጠኛው ቴዎድሮስ ተክለ አረጋይ ለጠየቀው ጥያቄ ባለሙያው መልስ ሲሰጥ፣ ከደንበኛው ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ እንዲህ አስፍሮታል፡
“ለምንድን ነው ባልሽን መፍታት የፈለግሽው?” አልኳት፡፡
“ባሌ በወር የሚሰጠኝ ገንዘብ በቂ አይደለም”
“በወር ስንት ሰጥቶሽ ነው ያልበቃሽ?”
“300,000.00!”
“እ?……. ስንት አልሽኝ?”
“300,000.00!”
“በወር ሶስት መቶ ሺህ ብር?”
“አዎን፡፡ በዚህ ብር መኖር አልችልም፡፡ አይበቃኝም”   
ሶስት መቶ ሺህ  ብር እንዴት አይበቃትም ሊባል ይችላል?!
ባልየው የሰጠው መልስም ለማመን የሚያስቸግርና አስቂኝ ነው፡፡ እንግዲህ ለሀገራችንና ለእኛ ባዕድ የሆኑ፣ ለልምዳችን የራቁ ብዙ ነገሮች እንዳሉ ከሚያሳዩት አንዱ ይህ ትንግርት ነው፡፡ በእነ እንዳልክ ሰፈር ብዙ አስቂኝ ብዙ አስፈሪ ብዙ አስደንጋጭ ነገሮች አሉ፡፡ ከሀገራችን ባህልና ስነ-ልቡና ያፈነገጡ፣ በእምነታችን የሚወገዙ፣ ብዙ ነውር የተባሉ ነገሮች ተንፀባርቀውበታል። ፍፁም ጆሮ ጭው የሚያደርጉ፣እርግማን ውስጥ ነን የሚያሰኙና ፀያፍ ብለን የቆለፍንባቸው ድርጊቶች ይስተዋሉበታል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ሴት ልጆች በአባቶቻቸው አስገዳጅነት ወሲብ የፈፀሙበት/የተደፈሩበት አሳዛኝ ገጠመኝ፣ዓይኖቻችንን በእንባ ልባችንን በሀፍረት ይከድነዋል፡፡…… አንዳች ድንጋጤ ነፍሳችንን ይደበድባታል፤ እንፈራለን፤ እንሰጋለን፤ ጥርጣሬያችን ቆጥ ይወጣል!! …. ወድቀናል የሚል ድምፅ ውስጣችን ይጮሃል-- ያስተጋባልም፡፡
ለምሳሌ ይህን ትረካ እንይ፡-
የ14 ዓመት ልጅ ናት፡፡ አለባበሷ እንደ ትልቅ ሰው ነው፡፡  በውድ ዋጋ የተገዛ ሞባይል ይዛለች፡፡ ውድ ሽቶ ተቀብታለች፡፡ እንደ ትልቅ ሰው እግሯን አነባብራ ተቀምጣለች። እርሷ ራስዋ እንዲህ ተርካዋለች (ገፅ 104)፡-
“ይገርምሀል፣ እናትና አባቴ አይግባቡም፤ ይጋጫሉ፡፡ ሁሌም ስለሚጣሉ እሸሻለሁ፡፡ በተቻለኝ አቅም እደበቃለሁ፡፡ እነሱ ሲጋጩ ከቤት እወጣና በር ላይ እቆማለሁ፡፡ ከዚያ አባቴ እናቴን ሰድቧትም ሆነ ደብድቧት ሲወጣ፣ እኔን በር ላይ ያገኘኛል፡፡ “አባቴ” ስለው “አቤት” ብሎ ይዞኝ ይሄዳል፡፡ ወደ መጠጥ ቤት ነው የሚወስደኝ፡፡ መጠጥ ቤት ወስዶኝ አንድም ቀን መጠጥ ጋብዞኝ አያውቅም፤ ሁልጊዜ ሚሪንዳ ይጋብዘኛል፡፡ ለስላሳ እየጠጣሁ ከእሱ ጋር እቀመጣለሁ፡፡
“ሰው ሁሉ እየመጣ ይስመኛል፡፡ እነሱ አልኮል መጠጥ እየጠጡ፣እኔ ሚሪንዳ እየጠጣሁ አባቴና ጓደኞቹ ሞቅ ሲላቸው አውቃለሁ፡፡ ሳያዩኝ የእነሱን ጭላጭ እየሰረቅሁ መጠጣት ጀመርኩ፡፡ ቀስ እያልኩ አልኮል መጠጥ ለመድኩኝ፡፡ ከዚያ ሚሪንዳ አልጠጣም አልኩት፡፡ ምክንያቱን ሲጠይቀኝ፤ እኔም እነሱ የሚጠጡትን መጠጣት እንደምፈልግ ነገርኩት፡፡ ለጊዜው ፈቃደኛ አልሆነም፤ ግን እኔም የእነሱን ጭላጭ መጠጣት ቀጠልኩበት፡፡ ሁላችንም ሰክረን ወደ ቤት መግባት ጀመርን፤ እኔም አባቴም እንሰክራለን፡፡ ይህ ነገር እኔን ሱሰኛ አደረገኝ፡፡ ከዚያ ለአባቴ ያለኝ ፍቅር ጨመረ። ስለዚህ ከአባቴ ጋር ብቻ ነው የምሄደው፡፡ ሁልጊዜ ከእናቴ ጋር ባይጣሉም፣ ከአባቴ ጋር አብረን  እየሄድን መጠጣት ጀመርን፡፡;
አንድ ቀን 8 ወይም 9 ዓመትዋ ላይ  አባትና ልጅ ሰክረው ገቡ፡፡
ልጅቷ ቀጠለች፡-
“ሰክሬ ከአባቴ ጋር ተኛሁ፡፡ ከዚያ ሌሊት ላይ ብልቴ አካባቢ የሆነ ጠቅ ሲያደርገኝ ተሰማኝ፤ አመመኝ በጣም፤ እናቴ  ተንደርድራ ስትመጣ  አባቴ እላዬ ላይ ሆኖ ወሲብ እየፈፀመ ነበር፡፡ እናቴም ስትጮህ ጎረቤት ተሰበሰበ፡፡ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱት። ፍርድ ቤት ቀርቦ 15 ዓመት ተፈረደበት፡፡”
 አንዱ አሰቃቂ ታሪክ ይህ ነው፡፡ ከዚህ የባሰ የደረሰባትና ከወላጅ አባቷ ጋር ወሲብ የለመደችው ሴት ልጅ በእንዳልክ ቃለ ምልልስ ውስጥ ትገኛለች፡፡ ይህንና ይህን  መሰል ብዙ ችግሮች አሉባት፡፡
በሌላ በኩል፤  ባለ ብዙ ህንፃ ባለ ብዙ ሀብት የሆነ ወላጅ፣ ልጆቹን የማግኘት ጊዜ አጥቶ፤ ሀብት፤  ፍለጋ ሲባዝን፣ ገንዘብ ስብሰባ ሲባትል፣ ልጆቹን  ዘንግቶ፣ አንድ ቀን በልጁ ልደት በዓል የተሰበሰቡት ህፃናት አንድ ላይ ሲወጡ የትኛዋ የእርሱ ልጅ መሆንዋን መለየት እንዳቃተው ባለሙያው ተናግሯል፡፡ ….. ብዙ ግር የሚያሰኙ፣ ለማመን የሚቸግሩ ቀውሶች--- በእንዳልካቸው አሰፋና በትዕግስት ዋልተንጉስ ቃለ ምልልሶች ውስጥ አፍጥጠው ወጥተዋል፡፡
የትዕግስት ዋልተንጉስ ቃለ ምልልስ ስለ አእምሮ ቁስለት የሚያነሳቸው ጉዳዮች በእውኑ ዓለም የሚንፀባረቁና ማህበራዊ ቀውስ የሚፈጥሩ ሆነው እናገኛቸዋለን። ለዚህ ማሳያ ከጠቀሰቻቸው ዓለማቀፍ ሁነቶች መካከል ስለ ቬትናም ጦርነት ተሳታፊዎች የአእምሮ ቁስለት እንዲህ  ተገልጿል (ገፅ 174)፡- “በተለይም በቬትናም ጦርነት ጊዜ የአዕምሮ ቁስለት ትልቅ እውቅና አግኝቷል፡፡ ከጦርነት ተመላሾች ወታደሮች በአሜሪካ መንግስት ገንዘብ ቤትና የመሳሰሉት ይሰጣቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ሲታዩ ሁሉም ኖሯቸውም ከቤተሰባቸውና  ከዙሪያቸው ካሉ ሰዎች ግራ መግባባት አልቻሉም፡፡ እንኳን ከባዱ የጦር መሳሪያ ጎማ ሲፈነዳም መደንገጥ ይታይባቸው ነበር። ራሳቸውን የሚያጠፉ ብዙ ወታደሮች ነበሩ፡፡ ይህ  ሁኔታ በተደጋጋሚ ሲያጋጥም፣ ለምንድን ነው ይህ የሚሆነው?” የሚል ጥያቄ ተነሳ፡፡ የአዕምሮ ቁስለት እንዳለባቸው ተደረሰበት፡፡
ትዕግስት የአእምሮ ቁስለትን በሚመለከት ሰባት ያህሉን ጠቅሳለች፡፡ እነዚህም በምንኖርበት ዓለም በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ የሚፈጥረውን ስሜትና ስሜቱ የሚያመጣውን ውጤት በምክንያት ለማሳየት ሞክራለች፡፡ እኛም  ከራሳችንና ከአካባቢያችን ጋር እያስተያየን ብዙ እንድንማርበት ሜዳውን ትታልናለች፡፡
ቀደም ሲል የጠቀስኩት  አቶ እድሜዓለም፤ የህፃናትን ሕይወት በሚመለከት በርካታና ጥልቅ መረጃዎችን አካፍሏል፡፡ ለምሳሌ  “የእምነት ጊዜ” በሚል የሚጠራው ህጻኑ ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ሰባት ዓመት ያለው ነው፡፡ ከ8-14 ዓመት ያለው ጊዜ የተግባር ጊዜ፣ ከ14-19 ዓመት ያለው የምክንያት፤ ከ20-28 ያለው የልብ ጊዜ፣ ከ28-35 የህሊና ጊዜ፣ ከ36-42 ያለው ደግሞ የሥራ ጊዜ ተብሎ እንደሚከፈል ባለሙያው ይነግረናል፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ ሌጣውን አልተቀመጠም፣ማሳያዎቹ አሉት።
ቴክኖሎጂን የሙጥኝ ማለቱም ጣጣው ቀላል እንዳልሆነ አቶ እድሜዓለም ያብራራል፡፡ (ገፅ 165)፡-
"መማር ማለት ምን መሰለህ? ጥያቄ አንስተህ መልሱን እስክታገኘው የሚቆይ ጊዜ ማለት ነው፡፡ ይህን ጊዜ ሊሰጥ የሚችለው ሰው ነው፡፡ ሞባይል ግን ፕሮግራም የተደረገ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ስትጠይቀው ወዲያው ትክክለኛውን ይነግርሃል፤ አይሳሳትም። በመሳሳት ስትማር መልሱን ታገኘዋለህ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ትውልዱ የመጨረሻ የመጨረሻውን መውሰድ ነው የሚፈልገው። አቋራጭ ነው የሚፈልገው፡፡"
እንግዲህ ይኸ ከማሽን የሚገኝ መልስ ምን ያህል ሳይደክሙ መቀበል እንደሚያስለምድና ወላጆች በልጆች አስተዳደግ ሚዛናዊ መሆን እንደሚገባቸው ጥንቅቅ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡
መፅሐፉ የብዙ ባለሙያዎችን ብዙ ጥበብና ብዙ ሙያዊ ገጠመኞች ይዟል፡፡ ግን ሁሉን ለማስቃኘት ጊዜና ቦታ ገደበኝ። ቢሆንም ፅሁፌን ከመቋጨቴ በፊት አንድ የገረመኝን ሀሳብ ባጋራ ደስ ይለኛል፡፡ ይህም ሀሳብ የአቶ እድሜዓለም ነው (ገጽ168)፡-
"ለምሳሌ፡- አለርጂ የስጋት ውጤት ነው። ስለዚህ ያን ስጋት እናጠፋዋለን፡፡ ፎሮፎር ለምሳሌ ወደ ኋላ ሄደን የምናስብ ከሆነና ከአሁን ጋር መገናኘት ካቃተን፣ ወዲያው ፎሮፎር  ይታያል፡፡ ስለዚህ ወደ ኋላ ያለውን እናነሳለትና እዚህ ላይ እንዲመጣ በማድረግ፣ ከራሱ ጋር እንዲዋሃድ ስናደርግ ፎሮፎር ይጠፋል፡፡ ነስር ለምሳሌ…. ከደም ጋር የሚገናኙ ነገሮች….. በነገራችን ላይ ከፍቅር ማጣት ጋር የሚገናኙ ናቸው፡፡ ….. ከደም ግፊት ከስኳር፣ከኩላሊት ድክመት፣ከጡት ካንሰር ጋር የሚገናኙ ሕመሞች በሙሉ በባህሪ ጥናት ሙያ ማዳን ይቻላል፡፡……”
እንግዲህ መፅሐፉን በግርድፉ እንዲህ ዳስሼዋለሁ፡፡ ….. ይህንን ዳሰሳ  በዋናነት የሰራሁትም አንባቢን ከመፅሐፉ ጋር ለማገናኘት ነው፡፡ እውነት ለመናገር  ሁሉም ሊያነበው የሚገባ መፅሐፍ ነው፡፡ ብዙ ያተርፋል፡፡


Read 672 times