Print this page
Wednesday, 07 July 2021 19:08

ግልፅ ደብዳቤ፡- ለጠ/ሚኒስቴር ክቡር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ - አዲስ አበባ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የኢትዮጵያ ወ.ወ.ክ.ማ የወጣቶችን የልማት ራዕይና ግብ በመደገፍና በማሳለጥ ረገድ በአእምሮ የጎለበተ፣ በመንፈስ የጠነከረና በአካል የዳበረ ወጣት በአዲስ አበባ፤ በኦሮሚያ፤ በአማራ፣ በትግራይ እንዲሁም በደ/ብ/ብ/ህ በሚገኙ አስር ቅርንጫፎች፣ ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ላይ የሚገኙ ሲሆን ከ30 ሺ በላይ አባላትና በጎ ፈቃደኞች እንዲሁም በየአመቱ 80 ሺ የፕሮጀክት ተጠቃሚ ወጣቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች አቅፎ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ በሲቪክ ተሳትፎ በአመራርነት ብቃት ላይ ሁለገብ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
ወ.ወ.ክ.ማ በደርግ ስርዓት ከአዋጅ ውጪ ያለ አግባበብ የተወረሰው 4 ኪሎ አካባቢ የሚገኘውን የቀድሞ የወ.ወ.ክ.ማ. ህንፃ እንዲመለስልን ከዚህ ቀደም ጥያቄ አቅርበን፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት በበጎ ታይቶ፣ ኮሚቴ ተቋቁሞ፣ ጉዳዩን ሲያጣራ ከቆየ በኋላ በ23/05/2004 ዓ.ም “ንብረቱ ለወ.ወ.ክ.ማ ይመለስለት” የሚል የውሳኔ ሀሳብ ቀርቦ፣ እልባት ሳያገኝ ጉዳዩ በእንጥልጥል መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ይህንንም አስመልክቶ በ10/03/2012 ዓ.ም እንዲሁም በ06/01/2013 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ የውሳኔ ሃሳብ ወደ አፈፃፀም እንዲሄድና እልባት እንዲሰጠን የጠየቅን ቢሆንም፣ እስካሁን ምላሽ አላገኘንም፡፡
በተመሳሳይ በአዲስ አበባ መስተዳድር ከንቲባ ጽ/ቤት በ12/12/2009 በ06/01/2013 እንዲሁም 19/9/2013 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ፣ ጉዳዩን ለማስረዳት ብንሞክርም እስካሁን አጥጋቢ ምላሽ አላገኘንም፡፡ ሆኖም የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን በቦታው ላይ ግንባታ ለማከናወን በዝግጅት ላይ መሆኑን አውቀናል፡፡ ይህም መላውን የወ.ወ.ክ.ማ. አባላትን፣ ደጋፊዎችና በውጭ ሀገርና  በአገር ውስጥ ያሉ አጋሮቻችን ጭምር ስጋት ላይ ጥሎናል፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፡- ኢትዮጵያ የወጣቶችን የታመቀ ሀብት፣ ጉልበትና ተስፋ ለሀገር እድገት፣ ሰላምና አንድነት ለመጠቀም በተነሳችበት በዚህ ወቅት ወ.ወ.ክ.ማ ለሚኖረው አስተዋፅኦ፣ የመንግስት ድጋፍ እንደማይለየን በማመን፣ ቀድሞ በኮሚቴው የቀረበውን የወ.ወ.ክ.ማን ንብረት የመመለስ የውሳኔ ሃሳብ ወደ አፈፃፀም እንዲሄድና የኢትዮጵያ ወጣቶች በአእምሮ በመንፈስ በአካል የሚዳብሩበት ማዕከላቸው ብሎም ለወ.ወ.ክ.ማ ቤተሰብ ሁሉ ምልክት የሆነውን ንብረት፣ እንዲመለስ አመራር እንዲሰጡልንና ታሪካዊ ሀላፊነትዎን እንዲወጡ በትህትና እንጠይቃለን፡፡
ከአክብሮት ሰላምታ ጋር
የወ.ወ.ክ.ማ ማኔጅመንት

Read 7444 times
Administrator

Latest from Administrator