Monday, 05 July 2021 00:00

የመጠማመድ ምንቸት ውጣ!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ... ከመሬት ተነስቶ ጥምድ የሚያደርግ ሰው ገጥሟችሁ አያውቅም! ፈተና እኮ ነው፡፡ ብቻ የሆነ ቦታ ላይ ስትተያዩ ወይ አጠገብ ለአጠገብ ስትተላለፉ በግልምጫ ሰማይ አድርሷችሁ ቁጭ ያደርጋችኋል፡፡ ደግሞላችሁ... ምክንያቱን የምታውቁት ግልምጫ እዳው ገብስ ነው፡፡
“እሷ ሆና ነው አንጂ በግልምጫ ብቻ ያለፈችህ ሌላ ነገር ብታደርግህም አይፈረድባትም፣” ስትባሉ ‘ኖ ኮሜንት’ ብሎ መጠጣት ነው፡፡ ምክንያቱን የማታውቁት ግልምጫ ግን...አለ አይደል... “እንዲህ ከምትገላምጠኝስ አንደኛውን በፍልጥ ብታንቆራጥጠኝ ይሻላል፣” ሊያሰኝ ይችላል። (‘ፍልጥ’ እና ‘ብታንቆራጥጠኝ’ የሚሉትን ቃላት ትርጉም ከመዝገበ ቃላት ማግኘት ይቻላል፡፡ ‘ጊዜውን ያማከለ ምክር’ ሊባልም ይችላል፡፡)  
“ከዚህ በፊት ትተዋወቃላችሁ?”
“ኸረ እኔ ምን ይሁን ምን አላውቀውም።”
“ምን ይሁን ምን ካላወቅኸው እንዲህ ጥምድ አድርገህ የያዝከው ለምንድነው?”
“እኔ እንጃ! ብቻ ሳየው የሆነ ጉሮሮዬ ላይ የሚተናነቀኝ ነገር አለ፡፡” (እዚህ ላይ ጣልቃ ለመግባት እንገደዳለን፡፡ ጉሮሮህን ከተናነቀህ ውሀ ጠጣበታ፡፡ ምን የሚሉት እንቁራሪቷን ዝሆን ማሳከል ነው! የሆነ የማታውቀውን ሰው ስታይ ከጉሮሮህ ላይ የሚሰነቀር ነገር ካለ ልዩ ችሎታ ነውና ‘አሜሪካ ጎት ታለንት’ ምናምን ላይ ተወዳደር፡፡ ደግሞ አንተ ገንዘብ ሳታጣ ‘ማይዘር‘ እየሆንክ፣ ምዳጃ አጠገብ የደረሰ የማይመስል ክክ ወጥ እየበላህ አይደለም ማነቅ ምላስህ ላይ ኮብልስቶን ቢነጠፍ ይገርማል እንዴ! ቂ...ቂ...ቂ...)
እናላችሁ እንዲህ አይነት ‘ከመሬት ተነስቶ’ የሚሉት ጥላቻ በፊትም፣ አሁንም አለ፡፡
እነ እንትና፣ እሺ እኛንስ...አለ አይደል...
“አጠገቡ ሆኖ እንጀራ አይበላም እኮ! ከእሱ ጋር ሲወዳደር ድራኩላ ሀንድሰም ነው...”
“የእሱ ቁመት ሆና ባንኮኒ ላይ ከእኛ እኩል መጠጣት ያምረዋል...”
“አቀርቅሮ የሚሄደው ለምን መሰላችሁ፣ ተንኮል ሲያስብ ነው እኮ!”
ምናምን እያላችሁ ልትጠምዱን ትችላላችሁ፡፡ ዘንድሮ በቁመቱም ቢሆን ከእናንተ ቢበልጡ እንጂ የማያንሱትን፣ በ‘ሀንድሰምነት’ እነብራድ ፒትን በቅናት የሚያንጨረጭሩትን፣ እንኳን አንገታቸውን  ሊደፉ ቀና ከማለታቸው የተነሳ እያንዳንዷ የአንገታቸውን ደም ስር የምትታየውን እነእንትናን ለምን ጠመዳችኋቸው! “መልሱ ግልጥ ነው፣” ያሉት ማን ነበሩ?
‘ዘ ቢተር ትሩዝ...’ እንዲል ፈረንጅ፣ መራራው እውነት በአሁኑ ጊዜ ምንም አይነት ተቀጥላ ምክንያት፣ ሰበብ  ምናምን ሳያስፈልገን...አለ አይደል... ርስት ሳንገፋፋ፣ ሚስት ሳንቀማማ፣ የአንዳችንን የፊት ለፊት ዳቦ ሌላኛችን በጓዳ ሰርገን ገብተን ሳንቀማማ በማንነታችን ብቻ የምንጠላላበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታም አይደል...ከመሀላችን የእውነት፣ ከልባቸው ንጹሀን የሆኑ ወገኖች ቢኖሩ... “ለዘመናት በዘራችሁት ጥላቻ መርዝ ህዝብና ትውልድን በክላችሁ ለዚህ መጠፋፋትና መቃቃር የዳረጋችሁን፣ አሁንም እንቅልፍ አጥታችሁ እዚህ ባህሪይ ላይ የሙጥኝ ብላችሁ ያለችሁት ሁሉ ለእስካሁኑ ጥፋታችሁ አንድዬ የእጃችሁን አያሳጣችሁ!” ብለው የውስጣችንን ለፈጣሪ ይነግሩልን ነበር፡፡
ስሙኝማ... እንግዲህ ጨዋታም አይደል... ይህ ችግር ልንሰማውና አምነን ልንቀበለው ከምንፈልገው በላይ የከፋ ነው፡፡ በአንድ በኩል ደግነቱ የጥላቻ ፖለቲካ የመረረውና ህልሞቹ ላይ ደንቃራ የሆኑበት፣ አንገቱን ወደ ኋላ እየጠመዘዘ ስለ ትናንትና ስለ ትናንት ወዲያ ደረቱን የሚደቃ ሳይሆን ዘመናትን አሸጋግሮ ለመመልከት እየሞከረ ያለ ትውልድ እየበረከተ መምጣቱ ለሀገር ተስፋ ነው፡፡
በአንድ በርካታ ሠራተኞች ባሉበት መሥሪያ ቤት ተቀጣሪ ወዳጃችን ነው፡፡ እና ከእነማን ጋር መቅረብ እንዳለበት፣ ከእነማን መራቅ እንዳለበት ግራ ገብቶታል፡፡ ይህ ብዙ ዓመት የኖረበት ተቋም የማያውቀው፣ የማያውቀው እየመሰለው ነው፡፡ “አንድም የማውቀው ሰው የሌለበት ክፍለ ሀገር ቢልኩኝም እንዲህ ባይተዋርነት የሚሰማኝ አይመስለኝም፣” ነው የሚለው፡፡
በፊት በአንድ መሥሪያ ቤት ባልደረብነት ሲተዋወቁ የነበሩ ሰዎች አሁን፣ አሁን ግንኙነታቸው የባዳ እየሆነ ነው፡፡ መተማመን ጠፍቷል፡፡ ሁሉም ሁሉንም ይጠራጠራል ነው የሚለው ወዳጃችን። ለነገሩ ምን መሰላችሁ... ይቺ ነገር በብዙ ስፍራዎች ያለች ነች፡፡ ለነገሩ እንግዲህ ጨዋታም አይደል... የአሁኑን ያህል አይሁን እንጂ በፊትም በየመሥሪያ ቤቱ እርስ በእርስ መጠራጠር የነበረ ነው፡፡ 
“እሱ ሰውዬ እኮ እዚህ መሥሪያ ቤት የተመደበው ሊሰልል ነው፡፡”
“በምን አወቅህ?”
“በፊት የነበረበት መሥሪያ ቤት መአት ሰዉ ነው ያስበላው አሉ!”
ቢሆንም፣ ባይሆንም እንዲህ የሚባሉ ነገሮች ነበሩ፡፡ ደግሞም እንክት ነዋ! ስለላ ነበራ!
ከሦስት አስርት ዓመት በፊት መንግሥት ሲለዋወጥ አንዳንድ መስሪያ ቤቶች ግምገማ እየተባለ መአት ሰዎች ተባረው ነበር፡፡ በአንደኛው መስሪያ ቤት የነበረ አንድ ሰው ለመባረሪያ ከተጠቀሱበት ምክንያቶች  አንዱ ከማንነት ጋር የተያያዙ ቀልዶች ትቀልዳለህ ተብሎ ነበር፡፡ የሚገርመው ቀልዶቹ ሁሉም ሰው ማለት ይቻላል የሚቀልዳቸውና ምንም አይነት የማጣጣል፣ ክብር የመንካት ምናምን የሌለባቸው ናቸው፡፡ እና በሰውየው ቀልድ እግራቸውን ሰቅለው ሲስቁ የነበሩ ናቸው ጠቋሚ ሆነው እንዲባረር ያደረጉት። እናላችሁ... እንዲህ አይነት ጉድ ባለባት ሀገር፣ ሰዋችን እየሰለሉኝ ነው ብሎ ቢሰጋ አይገርምም፡፡
ታዲያላችሁ... ወዳጃችን ከመረሩት ነገሮች አንዱ ሰው እርስ በእርሱ የሚዘንብበት ነገር ነው፡፡ ለምሳሌ ቀደም ባሉ ጊዜያት በየመሥሪያ ቤቱ አዲስ ሰው ተቀጥሮ ሲገባ የተለመዱ መንሾኪያሾካዎች ነበሩ፡፡
“በምን መስክ ነው የተማረው?”
“ከዚህ በፊት የት ይሠራ ነበር?”
የሚሉና በቀጥታ ከሥራው ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ነበሩባቸው፡፡ አብሮ ደግሞ...
“ይሄኔ ትልቅ የባለስልጣን ዘመድ ይኖረው ይሆናል!” 
“የሥራ አስኪያጁ አበልጅ ነው ይባላል...” የመሳሰሉ ነበሩ፡፡ ደግሞ የ‘ፕሬሚየር ሊግ” ደረጃ ለማለት ሰበብ አለች...
“አባል ነው አሉ፡፡” (ለዚች ማብራሪያም፣ ምንም አያስፈልግም፡፡ “አባል ነው አሉ...” ከተባለ ጭጭ ምጭጭ ነው! የምር...እዚህ ሀገር በ‘አባልነት’ ስም በ‘ባለካርድነት’ ስም ሲካሄዱ በነበሩ ጣት ቅሰራዎች፣ ከእንጀራቸው የተፈናቀሉትን ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ 
እናላችሁ...አሁን ደግሞ መንሾኪያሾካችን እየጠፋ እየጠፋ ወደ ጥቂት ነገሮች ወርዷል። አዲስ ሰው በተቀጠረ ጊዜ የመጀመሪያው ጥያቄ ማንነቱ ላይ ነው፡፡
“የየት አካባቢ ሰው ነው?” የተለመደ አባባልን ለመጠቀም... “የየት ሀገር ሰው ነው?” ይባላል፡፡ አናሳዝንም! በዚህ አያያዝ አስር ሺህ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሀምሳ ሺህ ኮሌጆች ቢኖሩንስ ምን ዋጋ ይኖረዋል!
እና በእሱ ብቻ ካልበቃ “ሚስቱ የየት ሀገር ሰው ነች?” ወደሚል ይመጣል፡፡
ግን ደግሞ እነኚህ ነገሮች...አለ አይደል...ሁሉም በዞረ ድምር ዝም ብለው የሚወሩ የሰባተኛው ዙር ድራፍት ወሬዎች ናቸው ማለት አሪፍ አይደለም፡፡ አይደሉም፡፡ ብዙ ቦታ የአገልግሎት ጥራት መጓደል ዋናው ምክንያት ምንድነው ብሎ መጠየቁ ለበጎ ይሆናል፡፡   
ስሙኝማ....የምር ግን...በዚህ ቁጥር ጉዳይ ‘ኮቺንግ’ ሳያስፈልገኝ አይቀርም። ልክ ነዋ... ወዳጆቻችን አሁን እስከ ሰባተኛው ዙር ድራፍት ‘የሚገለብጡ’ ከሆነ  ወይ ቀድሞውን መካከለኛ ገቢ የሚባለው ደረጃ ላይ ደርሰዋል፣ ወይ ደግሞ ከዳያስፖራዎቻችን የምትመጣዋን አንዷን ‘ዶላሬ’ በስድስት ከምናምን እየመነዘሩ ነው! ቂ...ቂ...ቂ...
እናላችሁ... በማንነታችን የምንጠማመድበትን ዘመን አንድዬ ያሳጥርልን እንጂ ሌላ ምን ማለት ይቻላል! የመጠማመድ ምንቸት ውጣ!
አንዱ ወዳጁን ምን አለው አሉ መሰላችሁ... “ዓለም ላይ የምጠላቸው ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ሁሉም ሰዎች ደግሞ አንተ ነህ።” እንዴት ቢጠምደው ነው!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1561 times