Sunday, 27 June 2021 19:14

በምርጫው በመሸነፋቸው የተደሰቱት አወዛጋቢው ፖለቲከኛ

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(5 votes)

 የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ መሪ ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት በብዙዎች ዘንድ በአወዛጋቢነታቸው  ነው የሚታወቁት ብል አልተሳሳትኩም፡፡ ከሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ-መንበርነታቸው የለቀቁት በሰላምና በፍቅር አይደለም፡፡ እንደተለመደው በውስጥ አመራር መካከል በተፈጠረ  ውዝግብ ሲናጡ ቆይተው “መፈንቅለ ፓርቲ” በሚመስል ሁኔታ ነው  ከመሪነታቸው የወረዱት፡፡  ከዚያ በኋላ የካበተ  ልምዳቸውን ተጠቅመው አዲስ ፓርቲ ስለማቋቋማቸው እርግጠኛ አይደለሁም፡፡
(ሳያቋቁሙ ግን አይቀርም!) ግን ብዙም ለውጥ የለውም፡፡ ቢያቋቁሙም አይታወቅም  ነበር፡፡ (ማን እንደ ሰማያዊ!) በተለይ በምርጫ ሰሞን ከ100 ምናምን በላይ ፓርቲዎች እንደ አሸን በሚፈሉባት ጦቢያችን፤ የፓርቲዎችን ስም ባናስታውስና ፓርቲዎችን ባናውቅ አይፈረድብንም፡፡ በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የሚመራው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምስጋና ይግባውና፣ ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን ፓርቲዎች  አጥርቶልናል። ይገርማል! “መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ደጋፊዬ ነው” እያሉ ሲፎክሩብን የከረሙ ፓርቲዎች ሁሉ  4ሺና 10 ሺ ፊርማዎችን ማቅረብ አቅቷቸው የሰበብ መዓት ሲደረድሩ ሰምተናቸዋል፡፡
ወደ ኢንጅነር ይልቃል ልመለስ፡፡  እንደነገርኳችሁ ለእኔ ኢንጂነሩ አወዛጋቢ ፖለቲከኛ ናቸው፡፡ (Controversial ማለቴ ነው!) የህወሃት አመራሮች ከፌደራሉ ሥልጣኑን መባረራቸውንና መቀሌ መከተማቸው ተከትሎ፣ አንድ ሰሞን በLTV “የቀወጠችው” ጋዜጠኛ፤  ኢንጂነሩን “አፋጣጭ” ለሚሉት ዓይነት (የሃበሻ Hard talk በሉት!) ቃለ መጠይቅ ጋብዛቸው ነበር፡፡
ቃለ መጠይቁ ሰፊ ቢሆንም ትዝ የሚለኝን ነው የማጋራችሁ፡፡ የጥያቄዋ መነሻ ኢንጅነሩ በፌስቡክ ገፃቸው የከተቧቸው ፅሁፎች ይመስሉኛል፡፡ በጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ናቸው፡፡
ጋዜጠኛዋ፤ እርስዎ “በጠ/ሚኒስትሩ ይቀኑባቸዋል እንዴ?” ስትል ፊት ለፊት ጠየቀቻቸው፡፡ ትንሽ ሳይደናገጡ አልቀሩም-ኢንጂነሩ፡፡
 “ምን ያስቀናኛል! እኔ ከሱ የበለጠ ብዙ ዓመት ለህዝብ ታግያለሁ”፤መስዋትነት ከፍያለሁ መለሱ-ፖለቲከኛው፡፡
“አይ ጠ/ሚኒስትሩ ብዙ ህዝብ ይወዳቸዋል፤ ብዙ ደጋፊዎችም አላቸው፤ በዚያ ይቀኑ እንደሆነ ብዬ ነው?” (ነገረኛ ጥያቄ ነው!)
“እኔ ከጠ/ሚኒስትሩ የበለጠ ብዙ ህዝብ ይወደኛል፤ ብዙ ደጋፊዎችም አሉኝ…” ፍርጥም ያለ ምላሽ ሰጡ፡፡
የጋዜጠኛዋ ጥያቄም ሆነ የኢንጂነሩም ምላሽ ሁሌም ያስገርመኛል፡፡ (አወዛጋቢ ናቸው ስል በምክንያት ነው!)
ኢንጂነሩ ከምርጫው በፊት ለጥቂት ወራት ያህል ወህኒ ቤት ነበሩ፡፡ ለዘንድሮው 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ግን ደርሰዋል፡፡ በእርግጥ የሚወዳደሩበት ፓርቲ አልነበራቸውምና ትንሽ የተንገላቱ ይመስለኛል፡፡ (ቦርዱ ሁለት ሦስት ፓርቲ ማቋቋም ቢፈቅድስ?)
የማታ ማታ ግን አንድ “አራዳ” ፓርቲ፤ እሳቸውንና ሌላውን አወዛጋቢ ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ አያሌውን ተቀበላቸው፤ በፓርቲው ታቅፈው በምርጫው እንዲወዳደሩ፡፡ (“ህብር” ሳይሆን አይቀርም!!) አቶ ልደቱ ከስንት ውጣ ውረድና ምሬት በኋላ ለልብ ህክምና ወደ አገረ አሜሪካ ተሻገሩ፡፡ (ከምርጫ በፊት ጤና ይቀድማል!!)
ወዳጃቸው ኢንጂነር ይልቃል ግን የትም አልሄዱም፡፡ በምርጫው ክርክር ወቅት አንድ ሁለቴ በቴሌቪዥን ሲከራከሩ ያየኋቸው ይመስለኛል። የምረጡኝ ቅስቀሳም አድርገዋል እንዲያም ሆኖ በቅርቡ ከአርት ቲቪ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ፤ “ለእኔ የምርጫው አስፈላጊነት ብዙም አይታየኝም” ሲሉ ሰምቼ ደንግጬ ነበር፡፡ አስፈላጊነቱ ባይታያቸውም ቅሉ ራሳቸውን ከውድድሩ ግን አላገለሉም፡፡ ምረጡኝ ብለው በፓርላማ እጩነት ተወዳድረዋል። ከሰሞኑ ታዲያ በምርጫው ሁለት ድምጽ ብቻ ማግኘታቸውን ያወቁት ኢንጂነር ይልቃል ብዙዎችን ያስገረመ አስተያየት ተናግረዋል፡፡
“በምርጫው ስለማላምን የምርጫ ካርድ አላወጣሁም ነበር፡፡ የሽግግር መንግስት ነው የሚያስፈልገው ስል ቆይቻለሁ፤ ከድሮ እስከ ዛሬ፡፡ የእኔ ወዳጆች ምርጫውን ቦይኮት አድርገዋል። በምርጫው ተስፋ ያልቆረጡ ግን የእኔ የሆነ ድጋፍ የነበራቸው ሰዎች  ለባልደራስ ነው ድምፃቸውን የሰጡት። ወዳጆቼ ለእኔ ድምጽ ቢሰጡኝ ኖሮ ነበር የምቀየማቸው፡፡ ብለዋል ኢንጂነሩ በምርጫ በዝረራ ተሸንፈው የተደሰቱ ብቸኛው ፖለቲከኛ ኢንጂነር ይልቃል፡፡ ሳይሆኑ አይቀርም ይመቻቸው፡፡

Read 1751 times