Saturday, 01 September 2012 11:45

ተፅዕኖ ፈጣሪው ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሴ

Written by  ኤርሚያስ ጉልላት
Rate this item
(4 votes)

የአማርኛን ስነ ጽሁፍ ካሳደጉት ታላላቅ ኢትዮጵያዊያን መካከል ባለቅኔው ዮፍታሄ ንጉሴ ይጠቀሳሉ፡፡ ዮፍታሄ ንጉሴ የተወለዱት በጎጃም ክፍለ ሀገር በደብረ ኤልያስ በ1885 ዓ.ም ሲሆን በደብረ ኤልያስ ደብር የጥንቱን የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ትምህርት በሚገባ ተምረዋል፡፡ ዮፍታሄ በልጅነታቸው የዜማ ትምህርት ያስተማሯቸው መሪጌታ አደላ ንጉሴ ሲሆኑ የቅኔን ትምህርት ያስተማሯቸው የኔታ ገብረስላሴ ነበሩ፡፡ የኔታ ገብረስላሴ በደብረ ኤልያስ ደብር ታዋቂ የቅኔ መምህር ሲሆኑ ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስን ቅኔ እንዳስተማሯቸው በታሪክ ይታወቃል፡፡ ደብረ ኤልያስ ደብር የ”ፍቅር እስከ መቃብር” ደራሲ ሃዲስ አለማየው የተማሩበት ደብር ነው፡፡

አቶ ሙሉጌታ ስዩም በ1964 ዓ.ም በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዩኒቨርስቲ በመመረቂያ ጽሁፉ ላይ እንደገለፀው፤ በደብረ ኤልያስ ደብር የነበሩ መምህራን “ማህበረ ኤልያስ” በሚል ስም እግረ ኤልያስ ብለው ደቀመዛሙርት ተማሪዎቻቸውን ይጠራሉ፡፡ በዮፍታሄ የዜማና የቅኔ ችሎታ መምህራኖቹ ከመደነቃቸው የተነሳ ለአምስት ተከታታይ ዓመታት እግረ ኤልያስ የሚለውን ምርጥ ስም ሰጥተውታል፡፡ ለዮፍታሔ ገና በልጅነቱ የአባቶችን ማእረግ ቀኝ ጌታ ሾመውታል፡፡

ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ በ1911 ዓ.ም አዲስ አበባ እንደመጡ፣ ወዲያውኑ በአቦ ደብር በአጋፋሪነት፤ በመቀጠልም በደብረ አለቅነት ተሹመዋል፡፡ ከቤተክርስቲያን አገልጋይነት ቀጥለው በሊጋባ ወዳጆ ጽ/ቤት የጽሕፈት ስራ እየሰሩ ለተወሰነ አመት ቆዩ፡፡

በኋላም ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ ባልታተመ ጥናታቸው እንደገለፁት፤ ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ በዳግማዊ ሚኒሊክ ትምህርት ቤት በአስተማሪነት ተቀጥረው ልዩ ልዩ መዝሙሮችን እየደረሱ ማስተማር ጀመሩ፡፡ በቀድሞ ጊዜ ዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤት ያስተምሩ የነበሩ መምህራን በየጊዜው በትምህርት ቤቱ ቅጥር ጊቢ ልዩ ልዩ ትያትሮች እየደረሱ ለተማሪዎች ያሳዩ ነበር፡፡ ይህም ሁኔታ የመዝሙር መምህሩን ዮፍታሄን ከቲያትር ጋር አስተዋወቃቸው፡፡ ዮፍታሄም አዳዲስ ትያትሮችን በተለየ አቅጣጫ መድረስ ጀመሩ፡፡

ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሴ ከደረሷቸው በርከት ያሉ ትያትሮች መካከል “አፋጀሽኝ”፣ “የሆድ አምላኩ ቅጣት”፣ “የደንቆሮዎች ትያትር”፣ “እርበተ ፀሐይ” እና “ጎበዝ አየን” ይጠቀሳሉ፡፡

የትያትር መምህሩና ተዋናዩ ተስፋዬ ገሰሰ በጥናታዊ ጽሁፋቸው እንደገለፁት፤ ዮፍታሄ ንጉሴ በድርሰት ችሎታቸው ብዙ የተመሰገኑ እና ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ብዙ ሽልማቶችን ያገኙ ነበር፡፡

ከጦርነቱ በፊት በመናገሻ ቅጥር ጊቢ ውስጥ የጊዮርጊስ ትምህርት ቤት ሲባል ከነበረው ቀበና ከሚገኘው ሊሴ ኃይለ ስላሴ ትምህርት ቤት፣ ከተፈሪ መኮንንና ከዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ተመርጠው ልዩ ልዩ ትያትሮችን እያዘጋጁ ያበረክቱ ነበር፡፡ አቶ ሙሉጌታ ስዩም በጥናቱ እንደጠቆመው፣ አንድ ጊዜ ጃንሆይ ዮፍታሄን ትያትር በመመልከት ላይ እያሉ በጣም ከመደሰታቸው የተነሳ ከልዑል አልጋ ወራሽ አንገት ወርቅ አውልቀው፤ ለዮፍታሄ አድርገውላቸዋል፡፡

ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ በርካታ የመድረክ ድርሰቶች አዘጋጅተው አሳይተዋል፡፡ ነገር ግን ድርሰቶቹ ባለመታተማቸው የተገኙት በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ “ጎበዝ አየን” የሚባለው ድርሰታቸው የህትመት ብርሀን አይቷል፡፡

ለመድረክ ከቀረቡት ውስጥ የተመልካችን አድናቆት ያተረፈው “አፋጀሽኝ” የተባለው ድርሰታቸው ነው፡፡ ይሄን ድርሰት ዮፍታሄ የጀመሩት ከጣሊያን ወረራ በፊት ሲሆን ድርሰቱን የፈፀሙት ከወረራው በኋላ ነው፡፡

“አፋጀሽኝ” ድርሰት ምሳሌያዊ ሲሆን በወቅቱ የነበረውን የአለም ፖለቲካዊ አዝማሚያ የሚጠቁም ከመሆኑም በላይ በድርሰቱ ውስጥ የተመሰለችው እናት ሀገር ኢትዮጵያ በሚከጅሏት ዘንድ የነበራትን የፖለቲካ ሁኔታ የሚያሳይ ነው፡፡ “አፋጀሽኝ” ዋና ጭብጡ በጣሊያንና በኢትዮጵያ የነበረውን ጦርነት የሚያመለክት ነው፡፡ ይሄም የጊዜው አንገብጋቢ ፖለቲካዊ መልእክት ነበር፡፡ ድርሰቱ የዮፍታሄን ኪናዊ ችሎታ በቅጡ የሚያንፀባርቅ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡

በኢትዮጵያ የድራማ ታሪክ የመድረክ ተውኔቶችን ካቀጣጠሉት ፈር ቀዳጆች መካከል በቅድሚያ የሚጠቀሱት በጅሮንድ ተክለሀዋርያትና እና ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሴ ናቸው፡፡

ዮፍታሄ የድራማ ሰው የነበሩትን ማቲዎስ በቀለን አስተምረዋል፡፡ “ሙናዬ ሙናዬ” የተሰኘው ዘፈን የዮፍታሄ ግጥም ሲሆን ዜማው በአገር ፍቅር ማህበር ይገኛል፡፡

ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ከተውኔት ድርሰታቸው በተጨማሪ መዝሙሮችንና ግጥሞችን ደርሰዋል፡፡ የኢትዮጵያ አንድነትና የህብረት መዝሙር የሚገልጽልንን የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር (ተፈሪ ማርሽ)፣ ወላድ ኢትዮጵያ፣ አጥንቱን ልልቀመው፣ ድንግል አገሬ ሆይ የሚባሉ መዝሙሮችን ደርሰዋል፡፡ አጥንቱን ልልቀመው የሚለው ግጥም አርበኞቹን የዶጋሊውን አሉላ አባ ነጋ እና ራስ ጎበናን በማነፃፀር የገጠሙት ግጥም ሲሆን ድንግል ሀገሬ ሆይ የተሰኘውን ድርሰት የፃፉት በስደት ኢሊባቡር ሆነው በ1929 ዓ.ም ነበር፡፡ ይህ መዝሙር ከመጀመሪያ ረድፍ ከሚጠቀሱት ስራዎቻቸው ቀዳሚው ነው፡፡

ድንግል ሀገሩ ሆይ ጥንተ ተደንግሎ

ጥንተ ተደንግሎ ጥንተ ተደንግሎ

ህፃናቱ ታርደው ያንቺም ልብ ቆስሎ

ልጅሽ ተሰደደ አንቺን ተከትሎ

የህፃናቱ ደም አዘክሪ ኩሎ፡፡

አዝማች፤ አስጨነቀኝ ስደትሽ

እመቤቴ ተመለሺ እመቤቴ ተመለሺ

ይሄ ግጥም ዮፍታሄ ንጉሴ ህዝቡ በፋሺስት ወረራ የደረሰበትን ስደት የገለፁበት ስንኝ ነው፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም ከእስራኤል ወደ ግብጽ ያደረገችውን ስደት እና በኤሮድስ ህፃናት መቀላታቸውን ከኢትዮጵያ ስደት ጋር ያነፃፀሩበት ግጥምም ነው፡፡

የቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ግጥሞች ትንቢታዊ ሲሆኑ በአንድ ስንኝ የሚጽፉት ግጥም ተሰጦአቸው የላቀ መሆኑን ያሳየናል፡

የሰማይ አሞራ ልጠይቅሽ ወሬ፣

ተቃጥሏል መሰለኝ ሸተተኝ አገሬ፡፡

በጣሊያን ወረራ ወቅት ለፋሺስት ያገለገሉ ባንዳዎችን በማስመልከት የገጠሙት ምፀታዊ ግጥም እንዲህ ይላል፡-

ለጌሾ ወቀጣ ማንም ሰው አልመጣ

ለመጠጡ ጊዜ ከየጐሬው ወጣ፡፡

ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ በተለይ የግእዙን ቅኔ መንገድ ለአማርኛ ለማውረስና የግእዙን ኪነታዊ ጠባይ አማርኛ እንዲኖረው ለማድረግ ታላቅ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ከግጥሞቻቸው እንረዳለን፡፡ ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ በጥናታቸው እንደፃፉት፤ ይህም በግእዝ ቋንቋ ያላቸውን እውቀትና ብስለት የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ከሳቸው በፊት እንዲህ ያለ ሙከራ ያደረገ ሰው መኖሩም ያጠራጥራል፡፡ የተፃፈም ነገር አላጋጠመንም፡፡ ግን ኋላ ላይ ይህን መንገድ ብዙዎቹ ባለቅኔዎች ተከትለው ሰርተውበታል፡፡

ቆሞ የስኳር ጠጅ

ውስተ ደብረ ማሕው ልብነ ሀገሩ ስቃይ ወተድላ፤

ወደይነ በበተራሆሙ አረቄ ወጠላ፤

በውስተ በርሜል ልብነ ምስትግቡአ በቀለ አተላ፤

እሳተ አራዳ ኮኛክ እሷው ተቃጥላ፤

አወያይታ ለባቢሎን ገላ፡፡

ግማሽ አማርኛ ግማሽ ግእዝ አድርገው የሚያዘጋጇቸው ማህሌተ ገንቦ የተባሉት መዝሙሮቻቸው አድማጭ የሚስቡ ነበሩ፡፡ በተጨማሪም በቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሴ ድርሰት ላይ ጐልቶ እንደታየው የዮፍታሄ አፃፃፍ ከቀበሌኛ ወይም ከአገራቸው ከጐጃም አማርኛ የነፃ ነው፡፡ ለማንም አማርኛ ተናጋሪ ሳይቸግር ይገባል፡፡ የግእዝ ብስለታቸው ለዚህ አፃፃፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

ማሽላና ስንዴ በአንድ አብረን ስንቆላ፤

እያረረ ሳቀ የባህር ማሽላ፡፡

ከሰል የሚሆኑ ብዙ እንጨቶች ሳሉ፤

ዝግባ ለምን ይሆን ይቆረጥ የሚሉ፡፡

የቀኝ ጌታ ዮፍታሄ አፃፃፍ ለተከታዮቹ ደራሲያን ምሳሌ ስለነበር አንጋፋነታቸው ታላቅ ዋጋ የሚሰጠው ነው፡፡ ዮፍታሄ በግእዝ ቅኔ የበሰሉ ስለነበሩ አማርኛ የስነ ጽሑፍ ቋንቋ እንዲሆንና እንዲያድግ የላቀ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡

የአማርኛ ስነ ጽሑፍን ለማሳደግ በተውኔት፣ በግጥም፣ በዘፈን እና በመዝሙር ባደረጉት ጥረት በኢትዮጵያ ስነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ የክብር ቦታ አላቸው፡፡ ባለ ቅኔው ዮፍታሄ ከጣሊያን ወረራ በኋላ እስከ 1941 ዓ.ም የህግ መወሰኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ሲሰሩ ቆይተው በ1942 ዓ.ም አርፈዋል፡፡ የባለ ቅኔው ዮፍታሄ ስራዎች ግን ተጽእኖ ፈጥረው ከትውልድ ወደ ትውልድ ይሸጋገራሉ፡፡

 

 

Read 7544 times Last modified on Saturday, 01 September 2012 11:53