Tuesday, 29 June 2021 00:00

የምርጫው መጨረሻ፣ እፎይታ ነው - እንስራበት

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

- የምርጫው ውጤት፣አሻሚ አልያም ቅንጥብጣቢ አልሆነብንም
- የፓርቲዎች ፉክክር ጥሩ ቢሆንም፤ “ተቀራራቢና አሻሚ ውጤት” ግን ከባድ ፈተና ይሆንብን  ነበር፡፡
- የምርጫው ውጤት፣ውዝግብ የማያበዛ መሆኑ፣ ለአገራችን ጥሩ እድል ነው፡፡ መንግስት፣ የአገሪቱን ውጥንቅጥ በእርጋታ  ስርዓት የማስያዝ፣ የተጠራቀሙ ችግሮችንና ቅሬታዎችን የመፍታት ሃላፊነት ላይ ማተኮር ይኖርበታልና፡፡
1. ሰላምን መፍጠር ፣ህግና ሥርዓትን ማጽናት፣ አደገኛው የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካን  መሻርና  አስጊ የሃይማኖት ፖለቲካን መከላከል… ብዙ ስራዎች ይጠብቁናል-እፎይታን የሚሹ፡፡
2. የሰዎች ኑሮ ማገገም አለበት፡፡ የገንዘብ ህትመት መብዛቱና የኢኮኖሚ ምርት መደናቀፉ፣የዋጋ ንረትን እያባባሰ፣ኑሮን የሚያጎሳቁል ሆኗል፡፡
አለመረጋጋት፣ አመፅ፣ጦርነት፣የበሽታ ወረርሽኝ ተጨምሮበት፣ ከዚህም የከፋ ችግር ውስጥ አለመግባታችን፣ አንድ ቁምነገር ነው፡፡ ነገር ግን፣ መጪው ዓመት፣ የመፍትሄ ዓመት መሆን አለበት፡፡
ዋጋ ንረትን ማረጋጋት ቀዳሚው ስራ ነው። በዋጋ ቁጥጥር አይደለም፡፡ የገንዘብን ብዛት በመግታት እንጂ፡፡
ኢኮኖሚው የሚነቃቃበት፣ የስራ እድሎች የሚከፈቱበት መላ ያስፈልጋል-ማለትም፤ የነፃ የገበያ ስርዓትና የግል ኢንቨስትመንት እንዲያቆጠቁጡ፣  የህግ ዋስትናንና ሰላምን ማስፋፋት፣ በይደር የማይቆይ ሥራ ነው- አሁኑኑ የእፎይታ ጊዜን የሚጠይቅ፡፡
   

“የምርጫ ውጤት፣ ምንም ሆነ ምንም….” ብለው የሚናገሩ አሉ። እንደዚያ የምንልበት የስልጣኔ ደረጃ ላይ ብንሆን መልካም ነበር። ነገር ግን፣ ገና ለስልጡን ፖለቲካ እጅግ ሩቅ ነን። በዚያ ላይ፣ ዛሬ፣ ኢትዮጵያ፣ በእጅጉ እርጋታን የምትፈልግ፣ አልያም እርጋታ የሚያስፈልጋት አገር ናት። ለተከታታይ ዓመታት ብዙ ምስቅልቅል ተደራርቦባታልና። እናም፣ የምርጫ ዘመቻውና የምርጫው እለት ብቻ ሳይሆን፣ የምርጫው ውጤትም፣ ለሰላምና ለእርጋታ የሚያግዝ ቢሆንላት ይሻላል።
የአገራችን የፓርቲዎች ፉክክር፣ በቅንነትና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ስልጡን ፉክክር አይደለም፡፡ ባይሆንም ግን፣  ከጨዋነት ያልራቀ፣ በስድብና በዛቻ ያልተዘፈቀ ሰላማዊ ፉክክር እስከሆነ ድረስ፣ለአገር ለትውልድ ይጠቅማል፡፡ የመጠፋፋት ፉክክር ግን፣ከምርጫ ጋር ቢዳበልም ያው አጥፊነቱ አይለወጥም፡፡
ታዲያ፣ የመጠፋፋት ፉክክር፣ ቢቀር አይሻልም? በኦሮሚያ ክልል፣ 60% በሚሆኑ የምርጫ አካባቢዎች ላይ ፉክክር አለመታየቱ፣ ብዙ ቅሬታ ያላስከተለው በዚህ ምክንያት ይመስላል፡፡ ከመጠፋፋት ፉክክር ይልቅ፣ እርጋታና ሰላም ይሻላል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡
- አሻሚና ከቅንጥብጣቢ የምርጫ ውጤት አምልጠናል፡፡
ለምስቅልቅል የሚያጋልጥ ማንኛውም ሰበብ፣ ተቀራራቢና አሻሚ የምርጫ ውጤት ጭምር፣ ለአገራችን አይበጃትም። የፓርላማ ወንበሮችን፣ ለብዙ ፓርቲዎች የሚሸነሽን ቅንጥብጣቢ የምርጫ ውጤትም፣ ፈተናዋን ያከብደዋል።
በተቃራኒው፣ የምርጫው ውጤት፣ አለመረጋጋትን የሚያስቀርልን፣ አዳዲስ ስጋቶችን የማይጨምርብን፣ በሌላ ዙር “የለውጥ ውጣ ውረድ” አገሪቱን ትንፋሽ የማያሳጣ ሲሆን፣ ለአገራችን ሰላምና ለእርጋታ ይረዳል።
ቢያንስ ቢያንስ፣ የምርጫው ውጤት፣ አጠቃላይ አዝማሚያው፣ ተቀራራቢ የአንገት ለአንገት ፉክክር አለመሆኑ ወይም አሻሚ አለመሆኑ፣ ትልቅ እድል ነው። አገርን ያረጋጋል፡፡ መንግስትን ያረጋጋል፡፡
አዎ የፓርቲዎች ብርቱ ፉክክር ጥሩ ነው፣ አሸናፊውን ለማወቅ የሚከብድ “ተቀራራቢ ውጤት” ግን፣ ጣጣው ይበዛል። እንኳን ለኢትዮጵያ ቀርቶ፣ ለአውሮፓና ለአሜሪካም፣ ዛሬ ዛሬ፣ ተቀራራቢ የምርጫ ውጤት፣ አስቸጋሪ ፈተና እየሆነባቸው ነው። “የምርጫ ውጤት፣ ተቀራራቢ ወይም አሻሚ አይደለም” ማለት ግን፣ “የምርጫ ፉክክር አልነበረም” ማለት አይደለም።
በዘንድሮው ምርጫ፣ በብዙ ቦታዎች፣ ብርቱ ፉክክሮች ታይተዋል። ነገር ግን፣ የምርጫው ውጤት፣ በአብዛኛው ለውዝግብ የሚገፋፋ ወይም የሚያጋልጥ አዝማሚያ የለውም። በአንድ ከተማ፣ ገዢው ፓርቲ በሰፊ ብልጫ አሸንፎ፤ በሌላ ፣ከተማ ደግሞ ተቀናቃኙ ፓርቲ በሰፊ ልዩነት ያሸንፋል። እንደዚህ ሲሆን፣ የምርጫው ውጤት ተቀራራቢ ወይም አሻሚ አይሆንም። በየቦታው በየከተማው፣ የተፎካካሪዎች ውጤት በጣም ተቀራራቢ ሲሆን ግን፣ ….. “ማን ይሆን ያሸነፈው?” የሚል ስሜት ይራገባል፡፡ የተራገበ ስሜት ያለ ማርገቢያ፣ ያለ ምላሽ በእንጥልጥል ውሎ ሲያድር፣ ጥርጣሬ ሲበረታ፣ ወሬ ሲምታታ፣ አሸነፍኩ ተጭበረበርኩ የሚል ውዝግብና ውንጀላ እየተራባ አገር ይናጣል።
በየቦታው ማን እንዳሸነፈ ለማወቅ የማያስችግርና የማያሻማ የምርጫ ውጤት ይሻላል። ለእርጋታ ጥሩ ነው። ይህም ብቻ አይደለም።
የየቦታው የየመንደሩ የምርጫ ውጤት ብቻ ሳይሆን፣ በአገር ደረጃ፣ ጠቅላላ የምርጫ ውጤትም፣ ዘንድሮ ያን ያህልም አሻሚ አልሆነም። በተለይ የአዲስ አበባ የምርጫ ፉክክሮችና ዘመቻዎች በእርጋታ መቋጨታቸው፣ በየአካባቢው የተለጠፉ የምርጫ ውጤቶችም ወዲህ ወዲህ የማያማቱ የማያምታቱ፣ መሆናቸው፣ የእርጋታን መንፈስ ለከተማዋ ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱ የሚያነፍሱ ናቸው፡፡
 በአጭሩና በጥቅሉ፣ የዘንድሮው የምርጫ ውጤት፣ ለውዝግብና ለውንጀላ፣ ብዙም ሰበብና ክፍተት አይሰጥም። ተቃራኒውን ተመልከቱ፡፡ በአንድ በኩል፤….
“በፓርላማ ወንበር፣ የትኛው ፓርቲ ብልጫ ይኖረው ይሆን?” የሚያስብል፣ ተቀራራቢ የምርጫ ውጤት ቢኖር፣ይታያችሁ፡፡ ምን አይነት ስሜትና ድባብ በአገሪቱ ሊያንዣብብ ይችል እንደነበር አስቡት። የስልጣን አፋፍ ላይ፣ ስልጣን ለመያዝም ሆነ ለመልቀቅ፣ ለመሸነፍና ለማሸነፍ አፋፍ ጥግ የደረሱ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች፣ ምን ዓይነት ውጥረት ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ገምቱት።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ አስር ፓርቲዎች፣ በየመንደራቸው፣ በየጥጋጥጉ እያሸነፉ፣ ፓርላማ ውስጥ እያንዳንዳቸው  ሃምሳ ሃምሳ ወንበር ሲቀራመቱ ይታያችሁ። በምርጫው ማግስት፣ አገሪቱ ምን ይውጣት ነበር? የመከራዋ አይነት፣ መጠንና ፍጥነት ለመገመት ያስቸግራል። መከራ እንደሚበዛባት ግን እርግጥ ነው።
በብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ ሳቢያ የተዳከመች አገር ውስጥ፣ ቅንጥብጣቢ የምርጫ ውጤት ሲታከልባት፣ ተጨማሪ በሽታ ይሆንባታል፡፡ ቅንጥብጣቢ የፓርላማ ወንበር ቅርጫ፣ አገሪቱን የሚያመሰቃቅል እንጂ የሚያረጋጋ ሊሆን አይችልም።
ደግነቱ፣ ለጊዜው ተርፈናል። የምርጫው ውጤት፣ አሻሚ አልሆነም፤ ቅንጥብጣቢም አልሆነም። የእርጋታ እድልን የሚፈጥር ነው፤ በእውነትና በትጋት ከተጠቀምንበት፡፡
ከብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ ለማገገም ወይም የሃይማኖት ፖለቲካን ለመከላከል የሚፈልጉ ፓርቲዎች፣ ከዘንድሮው ምርጫ እንደገና ማረጋገጥ የሚችሉት አንድ ነገር አለ።
-ፓርቲዎች ሲበዙ፣ከቁጥረወ የማይገቡ ፓርቲዎች ይሆናሉ
በአንድ አካባቢ ውስጥ፣ ደርዘን ተፎካካሪ ፓርቲዎች እየተረባረቡ ቢደራረቡ፣ ቁም ነገር የለውም። አብዛኛው መራጭ፣ በየአካባቢው፣ ከሶስት በላይ ፓርቲዎችን የማስተናገድ ፍላጎት ወይም አቅም እንደሌለው፣ ዘንድሮም በድጋሚ አይተናል። እስካሁን በየቦታው ያየናቸውን ውጤቶች እናስታውስ፡፡
ሁለት ወይም ሶስት ፓርቲዎች፣ አነሳም በዛ፣ ከቁጥር የሚገባ የመራጭ ድምጽ ያገኛሉ።
ሌሎቹ ሰባት ስምንት ፓርቲዎች፣ ግን “ከቁጥር” የማይገቡ ይሆናሉ። የተለየ ድክመት ወይም ክፋት ኖሮባቸው አይደለም። ግን በቃ፤ አንድ ሺ መራጮች  የሰጡት ድምፅ ሲቆጠር፣ የአንዱ ፓርቲ ውጤት ዜሮ ነው። የሌላኛው ፓርቲ ሲቆጠር  4 ነው። ይህንን የሚበልጥ ፓርቲም አለ- የ6 መራጮች ድምፅ ያገኘ።
ምናለፋችሁ፣ ከመቶ በላይ ድምፅ የሚያስመዘግቡ ፓርቲዎች፣ ሁለት ወይም ሶስት ፓርቲዎች ብቻ ናቸው። በአንድ አካባቢ ውስጥ፣ ከሶስት በላይ ፓርቲዎች ቢንጋጉ፣ ትርጉም የለውም። እንዳሉ አይቆጠሩም።
አገራዊ ፓርቲዎች፣ ከቁጥር እንዲገቡና ቁም ነገርም እንዲሰሩ ከፈለጉ፣ ለዋና ዋና ሃሳቦች ቅድሚያ በመስጠት፣ በዋና ዋና እቅዶች ላይ በማተኮር፣ ወደ ሁለት ወይም ወደ ሶስት አውራ ፓርቲዎች መዋሃድ አለባቸው።
“ሰብሰብ ሰብሰብ በሉ” በማለት ጠ/ሚ አቢይ ሲናገሩ አልነበር? ለነገሩ፣ በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲከኞችም፣ እንዋሃዳለን እያሉ መናገራቸው አልቀረም። አንዳንዶቹም ለመዋሃድ ሞክረዋል፡፡ ግን፣ አሁንም የፓርቲዎች ቁጥር በጣም ብዙ ነው፡፡ በደርዘን በደርዘን ነው የሚቆጠሩት። ተዋህደው ሁለት ወይም ሶስት አውራ ፓርቲዎች  መሆን አለባቸው፡፡
“አይ” የሚሉ ከሆነ፣ … አንድም ከንቱ ልፋት፣ ከንቱ ብክነት ይሆናሉ። መቶ ፓርቲ ይቅርና፣ አርባ ወይም ሃምሳ ፓርቲም አይደለም፤ ደርዘን አገራዊ ፓርቲዎችም፤… ከመጠን ያልፋሉ። ከቁጥር የማይገቡ “ተረፈ ፖለቲካ” ከመሆን፣ በሁለት በሶስት ፓርቲ ቢዋሃዱና ትርፍ ያለው ፋይዳ የሚያመጣ ቁምነገር ቢሰሩ ይሻላል።
 “አይ፤ በጭራሽ” የሚሉ ከሆነ፣ በደርዘን፣ ከዚም በላይ በመቶ የሚቆጠሩ ፓርቲዎችን ማራባት ይሻለናል ካሉ ግን፣ በምርጫ ጊዜ ከቁጥር ሳይገቡ ይቀራሉ። ሌላኛው አማራጭ፣ የመንደር ፓርቲ መሆን ነው። በየወረዳው፣ ሶስት ሶስት የመንደር ፓርቲዎች ቢፈለፈሉ፣ … ከ3ሺ በላይ ፓርቲዎች ይኖሩናል።
 ደርዘን ከዚም በላይ መቶ ፓርቲ የፈለገ ሰው፣ በብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ፣ አገሪቱን ከመሸንሸን ውጭ፣ ሌላ አማራጭ የለውም። ይህም አልበቃ ሲል፣ በብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ ተሸንሽኖ በዘረኝነት የተበጣጠሰውን አገር፣ እንደገና በሃይማኖት ፖለቲካ በስላሽ ይሄድበታል-ቅንጥብጣቢውን ፖለቲካ እያደቀቀ ለመቀራመት።
ግን ምን ዋጋ አለው?
የአገርን መከራ የማራባት፣ መጥፊያዋ የማፋጠን፣ የተስፋ ጭላንጭሏን የማጨለም ጥረት ቢሳካ ምን ፋይዳ አለው?
ይልቅስ፣ የሚቀጥሉትን 5 ዓመታት፣ አገሪቱን ከመከራ የማቃለል፣ ከጥፋት ቁልቁለት የማውጣት፣ የስልጣኔ ተስፋን የማብራት ጥረት ላይ ለመትጋትና ለማሳካት ልንጠቀምባቸው ይገባል- አንደኛ፣ ከብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ ለመዳን፤ ሁለተኛ፣ የሃይማኖት ፖለቲካን ለመከላከል፣ ሶስተኛ “ሃብታም ድሃ” ከሚል የምቀኝነትና የዝርፊያ፣ የውድመትና የድህነት ፖለቲካ ለመገላገል መትጋት ይችላሉ፤ እንችላለን።

Read 2772 times