Sunday, 27 June 2021 16:46

32ኛው ኦሎምፒያድ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ከወር ያነሰ እድሜ ቢቀረውም የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን በዝርዝር አልታወቀም
በአትሌቲክስ 34  ፤ በብስክሌት 1   እንዲሁም በቴክዋንዶ 1  ኦሎምፒያኖች ተይዘዋል-ዊኪፒዲያ
9 ሜዳልያዎች (3 የወርቅ፤ 1 የብርና 5 የነሐስ) -ቤስት ስፖርት
7 ሜዳልያዎች (2 ወርቅ፤ 2 ብርና 3 ነሐስ) -ትራክ አዴንድ ፊልድ ኒውስ
8 ሜዳልያዎች (2 የወርቅ፤ 5 የብርና 1 የነሐስ) -ኦሎምፒክ ፕሪዲክሽንስ
7 ሜዳልያዎች (1 የወርቅ፤ 3 የብርና 3 የነሐስ) -ግሬስ ኖት



    ጃፓን ለምታስተናግደው 32ኛው ኦሎምፒያድ ከወር ያነሰ እድሜ የቀረ ቢሆንም የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን እና የልዑካኑ አጠቃላይ ዝርዝር በይፋ አልተገለፀም፡፡ ኢትዮጵያ በቶኪዮ 2020 ላይ ኦሎምፒክን የምትሳተፈው ለ14ኛ ጊዜ ሲሆን በተለያዩ የኦሎምፒክ ሜዳልያ ትንበያዎች ላይ በአጠቃላይ እስከ 8 ሜዳልያዎችን እንደምታገኝና ቢያንስ 2 የወርቅ ሜዳልያዎች ልታገኝ እንደምትችል ተገምቶላታል፡፡
በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድንና ልዑካኑ ዙርያ ግልፅ መረጃዎችን ለማግኘት አዳጋች ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በፌደሬሽንና በኦሎምፒክ ኮሚቴ መካከል ውዝግቦች መፈጠራቸው፤ የኦሎምፒክ ማጣርያ ውድድሮች በዝግጅት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መደረጋቸው እንዲሁም ስለኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች በብቃት የሚሰራ ድረገፅ እና የመረጃ ፍሰት አለመኖሩ ምክንያቶች ናቸው፡፡  በቶኪዮ 2020  ላይ ኢትዮጵያ  ስለምታሰልፈው ቡድን ትክክለኛ መረጃዎች በመላው አለም አለመሰራጨታቸው በትልልቅ ሚዲያዎች ለሚሰሩ ዘገባዎችና የሜዳልያ ትንበያዎች በቂ መረጃ የሚገኝበትን እድል አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ ከወር  በፊት በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ማህበር ድረገፅ በቀረበ ሃተታ ላይም ይህ ነው የተስተዋለው፡፡ በ32ኛው ኦሎምፒያድ የኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች ስኬታማነት የሚጠበቀው በረጅም ርቀት መሆኑን ድረገፁ ቢገልፅም በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ የሚፅፍበትን እድል ያገኘ አይመስልም፡፡ ሰለሞን ባረጋ በ5ሺ እና 10ሺ፤ ንብረት መላክ በ5ሺ ሜትር እና ሮዛ ደረጀ በማራቶን በቶኪዮ 2020 ላይ ይሳካላቸዋል በሚል የዓለም አትሌቲክስ ማህበር ኦፊሴላዊ ገፅ ግምቱን በደፈናው አስፍሯል፡፡ በ5000 እና በ10000 ሜትር የኦሎምፒክ ውድድሮች የ21 ዓመቱ ሰለሞን ባረጋ  ከፍተኛ ግምት እንደሚሰጠው የሚያብራራው ዘገባ በሀ18 እና በሀ20 በ5ሺ ሜትር የዓለም ሻምፒዮን መሆኑን በ2017 እና በ2019 በተካሄዱ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች 5ኛ ደረጃ እና የብር ሜዳልያን ማስመዝገቡን ጠቅሶ በ5000 ሜትር ምርጥ ሰዓቱ 12፡34.02 በመጠቆም የኦሎምፒኩ ድምቀት ሊሆን ይችላል ብሏል፡፡ በሌላ በኩል የዓለም አትሌቲክስ ድረገፅ በ5ሺ ሜትር ከፍተኛ ግምት መሰጠት ያለበት ለንብረት መላኩ እንደሆነና በሴቶች ምድብ ከኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች ልዩ ግምት የሚሰጣት የማራቶን ሯጯ ሮዛ ደረጀ መሆኗን አትቷል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከ800 እስከ 10ሺ ሜትር ርቀት ድረስ  በቶኪዮ 2020 ላይ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ኦሎምፒያኖችን በኔዘርላንድስ ሄንግሎ ከተካሄደው የማጣሪያ ውድድር በኋላ በደረጃቸው መሠረት እንደሚመርጥ ቢያሳውቅም እስካሁን በይፋ ያቀረበው ዝርዝር የለም፡፡ ከሄንግሎው ውድድር በኋላ ኢትዮጵያን በተለያዩ ርቀቶች የሚወክሉ ሦስት አትሌቶችና አንድ ተጠባባቂ እነ ማን እንደሚሆኑ ያልታወቀ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ቡድን ምርጫ ላይ በሁለት ርቀቶች ስለሚወዳደሩ ኦሎምፒያኖችም የተገለፀ ነገር የለም፡፡ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴም በኢትዮጵያ ተሳትፎ ዙርያ በቅርቡ  የሰጠው መግለጫም የለም፡፡
በ32ኛው ኦሎምፒያድ ላይ በ3 የተለያዩ የኦሎምፒክ ስፖርቶች  አትሌቲክስ፤ ብስክሌትና ቴክዋንዶ 36 ኦሎምፒያኖችን እንደምታሰልፍ በዊኪፒዲያ ድረገፅ ኢትዮጵያ በ2020 ኦሎምፒክ በሚል ርእስ ከተከፈተው ገፅ  ላይ  መጠቀሱን ግን ማመልከት ይቻላል፡፡ ዊኪፒዲያ ስለ ኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን በዝርዝር  ያቀረበውን መረጃ ከየት እንደሰበሰበውና ትክክለኛነቱን ለማረጋገጥ ባይቻልም፤ በአትሌቲከስ 34 ኦሎምፒያኖች 16 ወንድ እና 18 ሴት፤ በብስክሌት 1 ኦሎምፒያን በሴቶች እንዲሁም በቴክዋንዶ 1  ኦሎምፒያን በወንዶች መያዛቸው የሰፈረ ሲሆን፤ የኢትዮጵያን ባንዲራ በማንገብ በድምሩ 17 ወንድ እና 19 ሴት የኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች እንደሚሰለፉ አመልክቷል፡፡ በዊኪፒዲያ የቀረበው የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን ዝርዝር እንደሚከተለው  ነው፡፡ በወንዶች 800 ሜትር ታደሰ ለሚ እና ሰለሞን ንብረት፤ በ1500 ሜትር ሰለሞን ባረጋ፣ ሳሙኤል ተፈራ እና ሳሙኤል አባተ ፤ በ5000 ሜትር ንብረት መላክ ፣ሚልኬሳ መንገሻ እና ጌትነት ዋለ፤ በ10ሺ ሜትር ብርሃኑ ኤጋዊ፣ ዮሚፍ ቀጀልቻ፤ በ3ሺ ሜትር መሰናክል ሃይለማርያም አማረ፣ አብርሃም ስሜ እና ቢቂላ ታደሰ  እንዲሁም በማራቶን ሌሊሳ ዴሲሳ፣ ሹራ ኪታታ እና ሲሳይ ለማ ናቸው፡፡ በሴቶች 800 ሜትር ሀብታም አለሙ፣ ወርቅ ውሃ ጌታቸው እና ወርቅነሽ መሰለ፤በ1500 ሜትር ፍሬወይኒ ሃይሉ፣ ለምለም ሃይሉ እና ድርቤ ወልተጂ፤ በ5000 ሜትር ጉድፍ ፀጋይ፣ ሰንበሬ ተፈሪና እጅጋየሁ ታዬ፤ በ10000 ሜ ለተሰንበት ግደይ፣ ፀሃይ ገመቹና ፅጌ ገብረሰላማ፤ በ3ሺ መሰናክል መቀደስ አበበ፣ ሎሚ ሙለታ እና ዘርፌ ወንድማገኝ  እንዲሁም በማራቶን ብርሃኔ ዲባባ፣ ሮዛ ደረጀና ትግስት ግርማ ናቸው፡፡
ከአትሌቲክስ ውጭ ኢትዮጵያ በ32ኛው ኦሎምፒያድ ላይ የምትሳተፈው በብስክሌት እና በቴኳንዶ ስፖርቶች ነው፡፡ የኢትዮጵያ የብስክሌት ቡድን በ2019 አዲስ አበባ ውስጥ በተካሄደው የአፍሪካ ሻምፒዮና ላይ በከፍተኛ ደረጃ ውጤት ማስመዝገቡ  በሴቶች የጎዳና ላይ ብስክሌት ውድድር አንድ ሴት ኦሎምፒያን የማሳተፍ እድል ተገኝቷል፡፡ በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሎምፒክ  በቴኳንዶ ስፖርት አንድ ኦሎምፒያን በወንዶች ምድብ የምታሰልፍም ይሆናል፡፡ በሞሮኮ ዋና ከተማ ራባት ላይ በተካሄደው የ2020 የአፍሪካ የኦሎምፒክ ማጣርያ ውድድር ላይ ሰለሞን ቱፋ በወንዶች ቀላል ሚዛን (58 ኪ.ግ) ምድብ ውስጥ አንድ ደረጃን አግኝቶ በማሸነፉ ይህን ታሪካዊ የኦሎምፒክ ተሳትፎ አስገኝቷል፡፡ ሰለሞን_ቱፋ በ2018 በተደረገው የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሽፕ  በ58ኪግ የቴኳንዶ ውድድር ላይ  በአንደኝነት የወርቅ ሜዳልያ የተሸለመ ሲሆን በቱርክ ኢስታንቡል በተደረገ ዓለም አቀፍ ውድድርም የነሐስ ሜዳልያም ተጎናፅፏል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኬንያ ከሳምንት በፊት 40 ኦሎምፒያኖች የሚገኙበትን የመጨረሻውን የኦሎምፒክ ቡድኗንና የልዑካኑን ዝርዝር ለመላው ዓለም አስታውቃለች፡፡  በ5 የተለያዩ ስፖርቶች 84 ኦሎምፒያኖችን የምታሳትፍ ሲሆን በአትሌቲክስ 43 ኦሎምፒያኖች(24 ወንድ 19 ሴት) በቦክስ 4 ኦሎምፒያኖች (2 ወንድ 2 ሴት)፤ በራግቢ ሰቨንስ 24 ኦሎምፒያኖች (12 ወንድ 12 ሴት)  ፤ በቴክዋንዶ አንድ ኦሎምፒያን በወንዶች ምድብ እንዲሁም በሴቶች መረብ ኳስ 12 ኦሎምፒያኖች ተመርጠዋል፡፡ የኬንያ ኦሎምፒክ ቡድን ኦሎምፒኩ ከመጀመሩ 15 ቀናት ቀደም ብሎ ጁላይ 5  ላይ የኦሎምፒክ ቡድኑ በጃፓኗ ደሴት ክሩውሜላይ ወደየሚገኘው ካምፑ እንደሚያቀናም ተገልጿል።
ልዩ ልዩ የኦሎምፒክ ሜዳልያ ትንበያዎች
ቤስት ስፖርት ከሶስት ሳምንት በፊት ለኢትዮጵያ ባወጣው የሜዳልያ ግምት 9 ሜዳልያዎች (3 የወርቅ፤ 1 የብርና 5 የነሐስ) እንደምተሰበስብ አስፍሯል፡፡ የአሜሪካ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ልዩ ድረገፅ ትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ  በበኩሉ በዝርዝር ባቀረበው የቶኪዮ 2020 የአትሌቲክስ ውድድሮች የሜዳልያ ትንበያ ኢትዮጵያ 7 ሜዳልያዎች (2 ወርቅ፤ 2 ብርና 3 ነሐስ) ልታገኝ እንደምትችል ግምቱን አስፍሯል። በትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ ትንበያ መሰረት በወንዶች 800 እና 1500 ሜትር የሜዳልያ እድል ለኢትዮጵያ አልተሰጣትም፡፡ በ5ሺ ና በ10ሺ ሜትር የወርቅና የብር ሜዳልያዎችን ኡጋንዳውያን እንደሚወስዱ ተገምቶ በ5ሺ ሰለሞን ባረጋ በ10ሺ ሜትር  ዮሚፍ ቀጀልቻ የነሐስ ሜዳልያዎችን ለኢትዮጵያ ያስገኛሉ ተብሏል፡፡ በማራቶን ኤሊውድ ኪፕቾጌ የወርቅ ሜዳልያውን እንደሚያሸንፍ የጠቆመው ትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ በኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ቡድን የማይካተተውን ብርሃኑ ለገሰ የብር  ሜዳልያውን ሰጥቶ አሞስ ኪፕሮቶ ከኬንያ የነሐስ ሜዳልያውን እንደሚወስድ ገምቷል፡፡
በ3ሺ መሰናክል በሁለቱም ፆታዎች ለኢትዮጵያውያን የሜዳልያ ግምት ያልሰጠው ትራክ ኤንድ ፊልድ በተጨማሪ በሴቶች በ800 ሜትር የሜዳልያ ግምት አለመኖሩን ሲጠቅስ ጉዳፍ ፀጋዬ በ1500 የወርቅ ሜዳልያ እንደምትወስድ ጠብቋታል፡፡ በ5ሺ የኬንያዋ ሄለን ኦብሪ የወርቅ ሜዳልያ ስተጎናፀፍ የሆላንዷ ሲፋን ሃሰን የብር እንዲሁም የኢትዮጵያዋ ለተሰንበት ግደይ የነሐስ ፤ በ10ሺ ሜትር ለሲፋን ሃሰን ወርቅ እንዲሁም ለለተሰንበት ግደይ የብር ሜዳልያ ተሰጥቷል፡፡ በሴቶች ማራቶን ሜዳልያዎችን የኬንያ ሴት ኦሎምፒያኖች እንደሚጠቀልሉት በትራክ ኤንድ ፊልድ ትንበያ ተሰራጭቷል፡፡
ኦሎምፒክ ፕሪዲክሽን በሰራው የሜዳልያ ትንበያ ደግሞ ለኢትዮጵያ 8 ሜዳልያዎች (2 የወርቅ፤ 5 የብርና 1 የነሐስ) የተገመተ ሲሆን ለኬንያ ደግሞ 11 ሜዳልያዎች (5 የወርቅ፤ 2 የብርና 4 የነሐስ) ተመዝግቧል፡፡ 32ኛው ኦሎምፒያድ 100 ቀናት ሲቀሩት ግሬስ ኖት በሰራው ሳይንሳዊ ትንበያ ከአፍሪካ ትልቁን ስኬት ኬንያ በ15 ሜዳልያዎች (6 የወርቅ፤ 5 የብርና 4 የነሐስ ) እንደምታስመዘግብ ነው። ኢትዮጵያ 7 ሜዳልያዎች (1 የወርቅ፤ 3 የብርና 3 የነሐስ) በሁለተኛ ደረጃ ስትከተል፤ አይቬሪኮስት 2 የብርና 1 የነሐስ ግብፅ 1 የብርና ሁለት የነሐስ፤ ኡጋንዳ 1 ወርቅና 1 ብር ደቡብ አፍሪካ 1 ወርቅና 1 ነሐስ፤ ሞሮኮ 1 የወርቅ፤ ቦትስዋና 1 የብር እንዲሀም ናይጄርያ 1 የነሐስ ሜዳልያዎችን እንደሚሰበስቡ የተገመተላቸው የአፍሪካ አገራት ናቸው፡፡

ከቶኪዮ 2020 በፊት…
ከ32ኛው ኦሎምፒያድ በፊት ኢትዮጵያ በተሳተፈችባቸው 13 ኦሎምፒያዶች 54 ሜዳልያዎች (22 የወርቅ፣ 11 የብርና 21 የነሐስ ሜዳልያዎች) ሰብስባለች፡፡  የተቀሩት ውጤቶች 4ኛ ደረጃዎች 17 ጊዜ፤ 5ኛ ደረጃዎች 8 ጊዜ፣ 6ኛ ደረጃዎች 11 ጊዜ፣ 7ኛ ደረጃዎች 6 ጊዜ እና 8ኛ ደረጃዎች 32 ናቸው፡፡ በወንዶች 12 የወርቅ፣ 6 የብርና 12 የነሀስ ሜዳሊያዎች፣ 4ኛ ደረጃዎች 9፣ 5ኛ ደረጃዎች 3፤ እና 8ኛ ደረጃዎች 30 እንዲሁም በሴቶች10 የወርቅ፣ 5 የብርና 9 የነሐስ ሜዳሊያዎች፣ 4ኛ ደረጃዎች 8፤ 5ኘ ደረጃዎች 5፣ 6ኛ ደረጃዎች 1፣ 7ኛ ደረጃዎች 3 እና 8ኛ ደረጃዎች 2 ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ተሳትፎ ታሪክ ከፍተኛ ውጤት ያላቸው የኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች ከኢትዮጵያ አትሌቶች ለኦሎምፒክ ውጤቷ ቀዳሚ የሆነችው 6 ሜዳልያዎችን ያስመዘገበችው ጥሩነሽ ዲባባ ስትሆን፤ 3 የወርቅ 3 የነሐስ ሜዳልያዎች ናቸው፡፡ ቀነኒሳ በቀለ በ4 ሜዳልያዎች በ3 የወርቅና በ1 የብር በ2ኛ ደረጃ ይከተላታል፡፡ ምሩፅ ይፍጠር በ3 ሜዳልያዎች 2 የወርቅና 1 የነሐስ፣ ደራርቱ ቱሉ በ3 ሜዳልያዎች 2 የወርቅ 1 የነሐስ፣ መሠረት ደፋር በ3 ሜዳልያዎች በ2 የወርቅና 1 የነሐስ፤ እኩል 3ኛ ደረጃን ይጋራሉ፡፡ ማሞ ወልዴ 3 ሜዳልያዎች 1 የወርቅ፣ 1 የብርና 1 የነሐስ፣ ጌጤ ዋሚ በ3 ሜዳልያዎች 1 የብር፣ 2 የነሐስ፣ አበበ ቢቂላ 2 ሜዳልያዎች 2 የወርቅ፣ ኃይሌ ገ/ሥላሴ በ2 ሜዳልያዎች 2 የወርቅ፣ አልማዝ አያና በ2 ሜዳልያዎች 1 የወርቅና 1 የነሐስ እንዲሁም ስለሺ ስህን በ2 ሜዳልዎች 2  ተከታታይ ደረጃዎች ይወስዳሉ፡፡

Read 1060 times