Sunday, 27 June 2021 16:44

የማህጸን በር ካንሰር

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

ማንኛዋም ሴት፡-
በወር አበባ መሃከል ወይንም በሁዋላ የተቋጠረ ወይንም ቀለል ያለ ደም መፍሰስ ካየች፤
የወር አበባ ረዘም ላለ ጊዜ ወይንም ከበድ ባለ ሁኔታ የሚፈስ ከሆነ፤
ከግንኙነት በሁዋላ የደም መፍሰስ ወይንም የጀርባ ሕመም ካላት፤
በብልት የሚወጣው ፈሳሽ መጠን የጨመረ ከሆነ፤
በወሲብ ግንኙነት ጊዜ ሕመም የሚሰማት ከሆነ፤
የወር አበባ ከተቋረጥ በሁዋላ በmenopause ጊዜ የደም መፍሰስ ካጋጠማት፤  
ሕመምዋ የማህጸን በር ካንሰር ወይንም ሌላ ሊሆን ስለሚችል ወደሕክምና በፍጥነት መሄድ አለባት፡፡ የማህጸን በር ካንሰር ወይንም በእንግሊዝኛው Cervical Cancer (CC) በማህጸን ጫፍ ላይ የሚከሰት እጅግ አደገኛ የሆነ በሽታ ነው ይላል በ2020/ ንጉስ ቢልልኝ ይመር (MSc, Clinical Midwifery) በኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ጉባኤ ላይ ያቀረቡት የተለያዩ ጥና ቶች ውጤት፡፡  
የተለያዩ ጥናቶች የዘገቡትን በመጥቀስ ያቀረቡት ወረቀት እንደሚጠቅሰው ከፍተኛ ትኩረት ሊሰ ጠው በሚገባው የሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ Human Papillomavirus (HPV) ምክንያ ትነት በሚከሰተው በዚህ የማህጸን በር ካንሰር ምክንያት በየአመቱ ወደ 530‚000 የሚሆኑ ማለትም 7.9 % ያህል አዳዲስ ታካሚዎች  በዚህ ካንሰር ሕመም ይያዛሉ፡፡ ከሴቶች ጤና ጋር በተያያዘ በአለም አቀፍ ደረጃ በ4ኛ ደረጃ ላይ ያለ ብዙ ሴቶች ላይ የሚታይ ሕመም ነው፡፡
የማህጸን በር ካንሰር 70 ከመቶ ያህሉ የሚከሰተው (HPV)  (16 እና 18 ) በተባሉት የሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ Human Papillomavirus (HPV) ምክንያትነት ነው፡፡ የማህጸን በር ካንሰር ሕክምና በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት 19 % ሲሆን ባደጉት ሀገራት ያለው ግን 63 % በመሆኑ ሲነጻጸር በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ያለው ሽፋን እጅግ አነስተኛ ነው። እ.ኤ.አ በ2017/ የማህጸን በር ካንሰር ሕክምናን ለመከታተል ወደ ሕክምና የቀረቡት ከሰሀራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት 10 % ብቻ ነበሩ፡፡  ለቀረበው ጥናት መረጃ ለመሰብሰብ ጥናት ከተደረገባቸው የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ኢትዮጵያም አንድዋ ነች፡፡
እ.ኤ.አ በ2020/ የወጣ መረጃ እንደሚጠቁመው በኢትዮጵያ በማህጸን በር ካንሰር ምክንያት የሚደርሰው ሕመም 26.4% ሲሆን ሞት ደግሞ 18.4/ ከ100‚000 መሆኑ ተመዝግቦአል። ይህ ምናልባትም ከንቃተ ህሊና ማነስ እንዲሁም ውስን ከሆነው የምርመራ አገልግሎትና ለዚያም የሚወጣውን ወጪ በታካሚዎች ዘንድ መቋቋም ካለመቻል ጋር ሲነጻጸር ቁጥሩ ትክክለኛው ነው ማለት አይቻልም፡፡ በተጨማሪም በብሔራዊ ደረጃ የካንሰር ሕመም ምዝገባ አለመኖሩም በትክክል መረጃውን ለማግኘት ያስቸግራል፡፡  
Infectious Agents and Cancer የተባለው ድረገጽ በበኩሉ እ.ኤ.አ Nov/2019 ባወጣው መረጃ እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ በአብዛኛው የማህጸን በር ካንሰር ታካሚዎች ወደሕክምና የሚቀርቡት ካንሰሩ ከተባባሰ ወይንም ሕመሙ ከቆየ በሁዋላ ነው፡፡  
የማህጸን በር ካንሰር ሕመም እና በህመሙም ምክንያት የሚከሰተው ሞት ባደጉት ሀገራት ባለፉት አስርት አመታት በፍጥነት ቀንሶ ታይቶአል፡፡ የዚህ ምክንያት ሊሆን የሚችለውም ሴቶች በማህጸን በር ካንሰር ከመያዛቸው በፊት ምርመራ እንዲያደርጉ የሚያስችለው የንቃተ ሕሊና ማጎልበት በስፋት በተከታታይነት ስለተሰራበት እና የምርመራው አገልግሎትም በስፋት እና አመቺነቱ በተረጋገጠ ሁኔታ በመሰጠቱ ነው፡፡ ባደጉት ሀገራት ያሉ ሴቶች ለማህጸን በር ካንሰር ምክንያት የሚሆነውን የሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ HPV አይነትና አስከፊነቱን እንዲ ሁም መደረግ ያለበትን ቅድመ ጥንቃቄ ለህብረተሰቡ ትምህርት በመስጠታቸው ካንሰሩን በመከላከል ሂደቱ ላይ አርኪ ሊባል የሚችል ውጤትን ማስመዝገብ ችለዋል፡፡  
በታዳጊና በመካከለኛ ደረጃ በሚኖሩ ሀገራት ውስጥ የንቃተ ሕሊናን ግንዛቤ በመፍጠሩም ሆነ አገልግሎቱን በማስፋቱ ረገድ ያለው አካሄድ ከህብረተሰቡ ዘንድ በብቃት ባለመድረሱ ዛሬም እጅግ አስከፊ በሽታ ሆኖ ይኛል፡፡ በአለም ላይ ከተከሰተው 311‚000 የማህጸን በር ካንሰር ሞት በአደጉት ሀገራት የተመዘገበው ጥቂት ነው፡፡ በኢትዮጵያ በየአመቱ ወደ 6‚300 ያህል አዳዲስ ታማሚዎች ለምርመራ የሚቀርቡ ሲሆን 4‚884/ ሴቶች በማህጸን በር ካንሰር ምክንያት ይሞ ታሉ። በዚህም ምክንያት የማህጸን በር ካንሰር በአገሪቱ በብዙ ሰዎች ላይ አደጋ ከሚያደርሱ የካንሰር አይነቶች ሁለተኛውን ደረጃ ይይዛል፡፡
አንዳንድ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት የኤችአይቪ ኢንፌክሸን ያለባቸው ሴቶች በአብዛኛው የማህጸን በር ካንሰርን ለሚያመጣው የሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡ በተለይም በፍጥንት ወደህክምና ቀርበው ሳይታከሙ የካንሰር ሴሉ ደረጃውን አሳድጎ ለሕክምና አስቸጋሪ ከሚሆንበት ወይንም ሕክምናውን ማዳን ከማይችልበት ደረጃ ሊያደርስ እና ለሞት ሊዳርግ የሚችለው ብዙውን ጊዜ ከኤችአይቪ ኢንፌክሽን ጋር በተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማሉ፡፡አንዳንድ ለንባብ የበቁ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ኤችአይቪ ቫይረስ ባለባት ሴት ከ1.6/ እስከ 2.4/ ድረስ የካንሰር ሕመሙን ሊያባብስና አደገኛ ሊያደርገው ይችላል፡፡  ቢሆንም ግን በበለጠ በኤችአይቪ እና በማህጸን በር ካንሰር መካከል ያለውን ልዩነት ለማሳየት የሚችል ግልጽ የጥናት ውጤት እንዲኖር የዚህ ጥናት አቅራቢዎች ይመክራሉ፡፡  
ለማህጸን በር ካንሰር የመጋለጥና በጊዜው ሕክምናን አለማድረግ ከብዙ ነገሮች ጋር ይያያዛል፡፡
ትምህርት፡- ሰዎች በተማሪ ቁጥር ለማወቅ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ያነባሉ፡፡ ይጠይቃሉ፡፡ የማያውቁትን ነገር ለማወቅ ይጥራሉ፡፡ ስለዚህም ሊደርስባቸው ስለሚችል የጤና መታወክ አስቀድመው ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡ ይህ ማለት ግን ያልተማሩ ሰዎች የምክር አገልግሎት ቢሰጣቸው ወይንም እውቀቱ እንዲኖራቸው ቢደረግ አይቀበሉም ማለት አይደለም፡፡ ከጤና ጋር በተያያዘ የተማሩትንም ሆነ ያልተማሩትን ሴቶች በባለሙያዎች የታገዘ ትምህርት በመስጠት እንዲያውቁት ማድረግ ይጠበቃል፡፡
መረጃ ማጣት፡- ታካሚዎች የት ሄደው መታከም ወይንም መመርመር እንዳለባቸው እና በሽታው ከመድረሱ በፊት የራሳቸውን እርምጃ መውሰድ እንደሚገባቸው ማስገንዘብ ይገባል፡፡ በተለይም ኤችአይቪ ያለባቸው ሰዎች ለሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑን አስቀድ ሞውኑ እንዲ ያውቁ ማድረግ ይጠቅማል፡፡
እድሜ፡-እድሜ ሌላው ጥንቃቄ ሊደረግበት የሚገባው ነው፡፡ ማንኛዋም ሴት እድሜዋ 21/አመት ሲደርስ ጀምሮ የማህጸን በር ካንሰር ምርመራ ማድረግ ይጠበቅባታል፡፡ እድሜአቸው ከ21-29 አመት የሆናቸው እንዲሁም ሌሎችም ሴቶች በየሶስት አመቱ ምርመራ በማድረግ ጤናቸውን ማረጋገጥ ይገባቸዋል፡
ትኩረት መንፈግ፡- ስለ ሂዩማን ፓፒ ሎማ ቫይረስ ማለትም የማህጸን በር ካንሰር ስለሚያመ ጣው ቫይረስ በተለያዩ መንገዶች ሲነገር እየሰሙ ችላ ማለት አንዱ በህብረተሰቡ ዘንድ መስተ ካከል ያለበት ነገር ነው፡፡ ምናልባትም የበሽታውን አስከፊነትና ገዳይነት እያደመጡ ነገር ግን ችግሩን የሌሎች ሰዎች ችግር አድርጎ መውሰድ አይገባም፡፡ ስለበሽታው አስከፊነት ተገንዝቦ እኔስ ምን ማድረግ አለብኝ የሚል አስተሳሰብ ይዞ መነሳት ብልህነት ነው፡፡
ሴቶች ከተለያዩ ሰዎች ጋር የወሲብ ግንኙነት የሚፈጽሙ ከሆነ እና በዚህም ሳቢያ በግብረስጋ ግንኙነት ለሚተላለፍ በሽታ ተጋላጭ ከሆኑ በኢንፌክሽን ሳቢያ የማህጸን በር ካንሰር ሊከሰት እንደሚችል አስቀድሞውኑ ማሰብ ይጠቅማል፡፡ የማህጸን በር ካንሰር ምርመራ ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ ዝቅተኛ ነው። ለዚህ በምክንያትነት ከሚጠቀሱት ምክንያቶች የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
ስለ የማህጸን በር ካንሰር ምንም እውቀት አለመኖር፤
የአኑዋኑዋር ሁኔታ፡- በገጠር የህክምና እርዳታውን በቅርብ ከማያገኙበት ቦታ ከሆኑ ወይንም አቅመ ደካማ እና ማንኛውንም ወጪ መሸፈን ካልቻሉ ወይንም ሊያማክሩት እና ወደሕክምና ተቋም እንዲሄዱ ሊደግፋቸው የሚችል ሰው የማጣት …ወዘተ፤
አገልግሎት፡- ለካንሰር ምርመራው ወደ ህክምና ተቋም ሊሄዱ ከሚችሉበት ክሊኒክ የሚያጋጥ
ማቸው ባህሪ ወይንም ተገቢ የሆነውን አገልግሎት አለማግኘት፤
የትምህርት ደረጃ እና ግንዛቤ፡- በህብረተሰቡ ውስጥ ከባህል ጋር በተያያዘ ወይንም በቀላሉ
ሊቀበሉት በሚችሉት መንገድ እውቀታቸውን ማጎልበት ካልተቻለ ችግሩን ሊያባብሰው ይችላል፡፡

Read 10131 times