Sunday, 27 June 2021 16:30

ኢዜማ ከ460 በላይ የምርጫ ቅሬታዎችን ለቦርዱ አቅርቧል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 ፓርቲው ምላሽ ካልተሰጠው ወደ ፍ/ቤት እንደሚያመራ አስታውቋል

   ኢዜማ ባለፈው ሰኞ በተካሄደው 6ኛ አገር አቀፍ ምርጫ ከ460 በላይ ቅሬታዎችን ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስገብቶ ምላሽ እየተጠባበቀ መሆኑን ከትናንት በስቲያ ሃሙስ የምርጫውን ሂደትና ቀጣይ የትግል አቅጣጫውን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ አመልክቷል፡፡
“ሰኔ 14 ቀን 2013 የተደረገው 6ኛው ሃገራዊ ምርጫ ሂደቱና ውጤቱ ሙሉ ለሙሉ ለሀዝብ የተገለፀ ባይሆንም በብዙ ግልጽ ችግሮች የታጀበ ነበር” ያለው ኢዜማ፤ በምርጫው የታዩና ፓርቲው ቅሬታ ያቀረበባቸውን ግድፈቶች ምርጫ ቦርድ የማያስተካክል ከሆነ ጉዳዩን ወደ ፍ/ቤት እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡ በምርጫው ከታዩ ግድፈቶች መካከል አንዳንዶቹ የምርጫ ውጤትን በቀጥታ ሊቀይሩ የሚችሉ ናቸው ያለው ፓርቲው፤ ከእነዚህም መካከል የኢዜማ እጩዎች ያልገቡባቸው የምርጫ ወረቀት  የማሰራጨት ጉዳይ ነው ብሏል፡፡
ፓርቲው ስለ ምርጫው ውጤት የምርጫ ቦርድን ይፋዊ መግለጫ እየጠበቀ መሆኑን ጠቁሞ፤ የቦርዱ መግለጫ ሳይሰማ በውጤቱ ላይ ምንም አይነት አቋም እንደማይዝ አስታውቋል፡፡
ይፋዊ ውጤት ከተሰማ በኋላ አጠቃላይ አካሄዱን ገምግሞ የራሱን አቋም እንደሚይዝም ነው ኢዜማ በመግለጫው የጠቆመው፡፡
አጠቃላይ የምርጫው ሂደትና ውጤት የሚገመግም ኮሚቴ ማዋቀሩንና ኮሚቴው የሚያቀርበውን የግምገማ ውጤትም ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ፣ የግምገማ ውጤቱን ተከትሎም በህጋዊ ማዕቀፍ ስር ያሉ ሂደቶችን እንደሚያስቀጥል ኢዜማ አመልክቷል፡፡
ለ6ኛው አገራዊ ምርጫ በመላ ሃገሪቱ 455 እጩዎችን ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አቅርቦ የነበረው ፓርቲው፤ በዚህም ለሃገሪቱ የዴሞክራሲ ሂደት መጠናከር አስተዋፅኦ አበርክቻለሁ ብሎ እንደሚያምን፤ በዚሁ ሰላማዊ መንገድ ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጫው ጠቁሟል፡፡ ምንጭ ሳይበግራቸው በጨዋነት ወጥተው ድምጽ የሰጡ ዜጎችን ያመሰገነው ኢዜማ፤ አሁንም ከምንም በፊት የሃገር አንድነትና ሰላምን እንዲያስቀድሙ ጥሪ አቅርቧል፡፡


Read 459 times