Sunday, 27 June 2021 16:30

በአዲስ አበባ አብዛኛዎቹ የምርጫ ክልሎች የምርጫውን ውጤት እየተገለፀ ይፋ እያደረጉ አይደለም

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም የተካሄደው 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ውጤት በየምርጫ ክልሎቹ  ትናንትና ዛሬ ይፋ እንደሚደረግ ቢገልጽም፣ በአብዛኛዎቹ የምርጫ ክልሎች ውጤቱ ይፋ እየተደረገ አይደለም፡፡ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኙ  አብዛኛዎቹ የምርጫ ክልሎች የምርጫው ውጤት እየተገለጸ  አይደለም፡፡  
በከተማዋ በሚገኙ አብዛኛዎቹ የምርጫ ክልሎች የተጠቃለለ የድምፅ ቆጠራ ውጤት ከየምርጫ ጣቢያዎቻቸው ቢረከቡም ውጤቱን ለህዝብ  ይፋ እያደረጉ አለመሆኑ ታውቋል፡፡ በከተማዋ ወጤት ይፋ የሆነባቸው የምርጫ ክልሎች በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ ተዘዋውረን ያየናቸው የምርጫ ክልሎች አብዛኛዎቹ የምርጫውን ውጤት ይፋ አላደረጉም፡፡ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ምርጫ  ክልል 9፣ 10፣11 እና  12 ውጤት አልተገለፀም፡፡
በአራዳ ክፍለ ከተማ ከሚገኙት የምርጫ ጣቢያዎች መካከል የምርጫ ክልል 11 የ77 ምርጫ ጣቢያዎችን የቆጠራ ውጤት ቢረከብም፣ በ41ዱ ላይ  ችግር እንዳለባቸው በመታወቁ  ዳግም ቆጠራ ሊደረግ እንደሆነ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ዳግም ቆጠራውም የተፎካካሪ ፓርቲ ወኪሎችና ታዛቢዎች በተገኙበት ይደረጋል መባሉን እነዚሁ ምንጮች ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል። በዚሁ ክፍለ ከተማ የምርጫውን ውጤት ይፋ ያደረጉ ሁለት የምርጫ ክልሎች (ምርጫ ክልል 5 እና 6) ውስጥ የብልጽግና ፓርቲ እጩዎች ከፍተኛ ድምጽ ማግኘታቸው ታውቋል፡፡
አብዛኛዎቹ ምርጫ ክልሎች የምርጫ ውጤቱን የማደራጀት፣ የማመሳከርና የማዳመር ስራው ባለማጠናቀቃቸው ውጤቱን በተባለው ጊዜ ይፋ እያደረጉ አለመሆኑን ይገልጻሉ፡፡

Read 904 times