Print this page
Saturday, 19 June 2021 18:04

በደብረ ብርሃን 10 አምራች ኢንዱስትሪዎች ተመረቁ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ለ6 ሺ ሰዎች የስራ ዕድል ፈጥረዋል የባለ ኮከብ ሆቴልና የገበያ አዳራሽ የመሰረት ድንጋይ ተጥሏል
                   
         የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና መቀመጫ በሆነችው በደብረ ብርሃን ዙሪያ ሥራ የጀመሩ 10 አምራች ኢንዱስትሪዎች ተመረቁ፡፡ በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ የክልሉና የዞን ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተው፣ ፋብሪካዎቹን  ጎብኝተዋል፡፡ ፋብሪካዎቹም፡- ዋንዌይ ቴክስታይል እና ጋርመንት፣ ቻንግል ችፑድ ፋብሪካ፣ ሰን ዱቄት ፋብሪካ፣ ደብረ ብርሃን ፕሪ-ኢንጅነሪንግ የብረታ ብረት ፋብሪካ ፣ RZX ኮምፎርት ፋብሪካ፣  A1 ማርብል ፋብሪካ፣ JK የምግብ ማብሰያ ፋብሪካ፣  ሰለሞን ፋንቱ ወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ፣ ቫይሮ ጋርደን ፕላስቲክ ፋብሪካ እና ጁኒፐር ጠርሙስና ብርጭቆ ፋብሪካዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ፋብሪካዎች የ6 ቢሊዮን ብር ኢንቨስትመንቶች ሲሆኑ ለ6 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል እንደፈጠሩም ታውቋል፡፡ በዕለቱም የአንድ ባለኮከብ ሆቴልና የአንድ ግዙፍ የገበያ ሞል የግንባታ የመሰረት ድንጋይ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የተቀመጠ ሲሆን፣ በቅርቡም ግንባታቸው ይጀመራል ተብሎ ይቀመጣል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ ኢንቨስትመንቶችን እየሳበች የምትገኘው ደብረ ብርሃን፤ ለጥ ያለው ሜዳማ መልከአ ምድራዊ አቀማመጧ፣ ደጋማው የአየር ንብረቷና  ከዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ያላት  ቅርበት ይበልጥ ተመራጭ እንዳደረጋት የከተማዋ ተቀዳሚ ከንቲባ አቶ ደስታ አንደርጌ ገልፀዋል፡፡ በእለቱ ለፋብሪካዎቹ ስራ መሳካት ጉልህ አስተዋፅኦ ያደረጉት የመንግስት አመራሮች፣ የፋብሪካ ባለቤቶችና ባለድርሻ አካላት ሽልማትና እውቅና የተሰጣቸው ሲሆን በቀጣይ ከዚህ የበለጠ እንዲሰሩ ርዕሰ መስተዳድሩ አደራ ብለዋል፡፡
በዚሁ እለት አመሻሽ ደብረ ብርሃን ከተማን የቆረቆሯት የአፄ ዘርዓያዕቆብ ሀውልት በዘርዓያዕቆብ አደባባይ ላይ የተተከለ ሲሆን ይህም ለደብረ ብርሃን ተጨማሪ ድምቀት ሆኗታል፡፡
ከተማዋ እያስመዘገበች ባለችው ፈጣን እድገትና እንቅስቃሴ ወደ ሪጂዮ ፖሊታንት ከተማ አስተዳደርነት እንድትሸጋገር በህዝቡና በዞኑ በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲቀርብ የቆየ ሲሆን በዚሁ ዕለት የክልሉ መንግስት ጥያቄውን በመቀበሉና የከተማዋን ሁኔታ በመመርመር ወደ ሪጅዮ ፖሊታንት ከተማ አስተዳደርነት  እንድትሸጋገር መፍቀዱን ይፋ አድርጓል፡፡


Read 2396 times
Administrator

Latest from Administrator