Print this page
Wednesday, 23 June 2021 00:00

የእስራኤልና ሃማስ ግጭት ዳግም አገርሽቷል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ከሳምንታት በፊት ተቀስቅሶ ለ11 ቀናት ያህል የዘለቀውና በተኩስ አቁም ስምምነት ጋብ ብሎ የሰነበተው የእስራኤልና ሃማስ ግጭት ባለፈው ረቡዕ ዳግም ማገርሸቱንና እስራኤል ከጋዛ ሰርጥ የተላኩ ፊኛዎች ተቀጣጣይ ነገሮችን ይዘው ወደ ግዛቴ በመግባት የእሳት አደጋ አስከትለዋል በሚል በሀማስ ይዞታዎች ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሟን ማስታወቋን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ተቀጣጣይ ፊኛዎቹ በደቡባዊ እስራኤል 20 ያህል የእሳት አደጋዎችን ማስከተላቸውን ተከትሎ፣ ኔታኒያሁን ከ12 አመት ስልጣን አሰናብታ ናፍታሊ ቤኔትን ከሾመች ሳምንት ያልሞላት የእስራኤል የጦር ጀቶች፣ ባለፈው ረቡዕ በካን ዩኒስ እና ጋዛ ከተማ ውስጥ በሚገኙት የሃማስ ወታደራዊ ጣቢያዎች ላይ ድብደባ መፈጸማቸውን የአገሪቱ መከላከያ ኃይል ባወጣው መግለጫ ማስታወቁን የጠቆመው ዘገባው፤ሃማስ በበኩሉ በቃል አቀባዩ በኩል ባሰራጨው መልዕክት፣ ፍልስጤማውያን መብታቸውንና ኢየሩሳሌም ውስጥ ያሉትን ቅዱስ ቦታዎችን ለመከላከል የጀግንነት ተጋድሏቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ ማቅረቡን አመልክቷል፡፡
በተያያዘ ዜና፤ ላለፉት 12 ዓመታት እስራኤልን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ያገለገሉት ቤኒያሚን ኔታንያሁ ባለፈው ቅዳሜ ስልጣናቸውን ለአዲሱ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ያስረከቡ ሲሆን፣ የያሚና ፓርቲና የአዲሱ የአገሪቱ ጥምር ፓርቲ መሪ ናፍታሊ ቤኔት 36ኛው የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ቃለ መሃላ ፈጽመዋል፡፡ስምንት የአገሪቱ ፓርቲዎች የተካተቱበትን ጥምረት የሚመሩት የ49 አመቱ ቤኔት ለመጪዎቹ 2 ዓመታት እስራኤልን በጠቅላይ ሚኒስትርነት እንደሚያገለግሉ የዘገበው ሮይተርስ፣ ናፍታሊ ቤኔት ከዚህ ቀደም መከላከያን ጨምሮ በተለያዩ የሚኒስትር ሃላፊነቶች ማገልገላቸውንም አስታውሷል፡፡ከታዋቂው የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲ በህግ ሙያ የተመረቁት ቤኔት በአሜሪካ ለረጅም ጊዜ መኖራቸውንና ሳዮታ የተሰኘ የሶፍትዌር ኩባንያ በማቋቋም መተግበሪያ (ሶፍትዌር) አበልጻጊ ኩባንያ መስርተው ከፍተኛ ሃብት ማፍራታቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡

Read 7993 times
Administrator

Latest from Administrator