Saturday, 19 June 2021 17:13

የበቆጂ ልጆች ምስጢራቸው ምንድን ነው?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ምዕራባውያን፤ የኢትዮጵያውያንን የሩጫ ቅርስ - ሚስጥሩን ፍለጋ፤ የታቦቱን ፍለጋ ያህል ለፍተዋል፡፡ ዛሬም እየለፉ ናቸው፤(ተርጓሚው)
ከንጋቱ 11 ሰዓት ነው - የአዲስ አበባ ማለዳ፡፡ አዲስ አበባ ተኝታለች!
“አዲሲቱን” አዲሳባ በአንድ በሁለት ሰዓት ውስጥ ለመገንባት የሚንቀሳቀሱት የአዳዲስ ወጋግራ ማነጫዎችና የግንባታ ሥራ አንሺ - አውራጅ ክሬኖች፤ እንደ ጭለማ ምስሎች ሆነው፤ በሚያንፁት ግድግዳ አጠገብ ተሰድረ ዋል፡፡ የዚችን ህያው ከተማ መንገዶች በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚወሩት  ባለዲዜል ሞተር መጓጓዣዎች ገና ጉልበት ገዝተው፣ ትንፋሽ ፈጥረው አልተንቀሳቀሱም፡፡
ሯጮቹ ግን ነፍስ ገዝተው ሩጫቸውን ጀምረዋል!
መስቀል አደባባይ ላይ ጭለማ በዋጠው ሜዳ የስታዲዮም መቀመጫ በመሰሉት የድንጋይ አግዳሚዎች ጐን በፀጥታ ልምምዳቸውን ቀጥለዋል፡፡ በጃን ሜዳ (የንጉሡ ሜዳ እንደማለት) ሯጮች እየሮጡ ነው - በዚሁ ጠዋት፡፡ በቦሌ መንገድና ከቤተ መንግሥት በሚመጣው በዳግማዊ ሚኒሊክ ቁልቁለት ጐዳናም እየሮጡ ነው፡፡ የ3,200 ሜትር ከፍታውን የእንጦጦ ጋራ ሽቅብ ለመውጣት ጥቋቁር ጥላ የመሰሉ ሰዎች ከስለታሙ ቁልቁለት ጋር ተጋትረው በመሮጥ ላይ ናቸው!ከጐህ መቅደድ በፊት አዲሳባ በፀጥታ የሚንቀሳቀሱ ጥላዎች ከተማ ናት!
ከከተማይቱ እየራቃችሁ ስትነዱ፤ የመጀመሪያዎቹ የጧት ጨረሮች የተራሮቹን ጠርዞች ሲዳስሱ፣ አባጣ ጐርባጣውን ውበትና መልከ - ብዙውን ሻካራ ቁንጅና እያደመቁ ሲያጐሉት ታስተውላላችሁ፡፡
በተጨማሪም ከየባህርዛፎቹ ውስጥ ብቅ ጥልቅ የሚሉ ምስሎችን ትታዘባላችሁ፡፡
እነዚህ ምስሎች የ1960ው የሮም ኦሎምፒክ ወራሾች ናቸው! ያኔ የእረኛው ልጅ (“አበበ እንጂ መቼ ሞተ”፤ ያልንለት) አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ የማራቶን ድሉን ሲጐናፀፍ፤ ዓለምን ፀጥ እርጭ አሰኝቶ በድን ያደረገበት ጊዜ ነበር!
ከዚያን ጊዜ ወዲህ፣ አብዛኛዎቹ ለዘመናዊ ደረጃ የሥልጠና ግብዓቶች ያልታደሉ ሯጮቿን የወለደችው ኢትዮጵያ፤ ገና አንገቷን ቀና ማድረጓ ነበር፡፡
በዚህም የዓለም አቀፉን ህብረተሰብ የሩቅ ሩጫ መዘውር ጨብጣ መጫን የጀመረችበት ሰዓት ነበር! ከዚያ ማታ ጀምሮ የዓለም ህዝብ ሁሉ “እንዴት እንዲህ ሊያደርጉ ቻሉ?” ሲል መጠየቁን ቀጠለ!
ሀገራዊ ኩራትና አርአያዎች
ኢትዮጵያ እንደሌሎቹ የአፍሪካ አገሮች ለረዥም ጊዜ በውጪ ወራሪዎች ያልተያዘች አገር ናት፡፡ ስለዚህም ህዝቦቿ በረዥምና አኩሪ ታሪካቸው በሞገስ ይኩራራሉ፡፡ ያ ኩራታቸው ደግሞ በሩጫ እስካገኙት ድል ድረስ የተንሰራፋ ነው!
ባለፉት ሦስት ኦሎምፒኮች፤ ማለትም ሲድኒ፣ አቴንስና ቤጂንግ - የኢትዮጵያ የረዥም ሯጮች (በ5ሺ፣ በ10ሺ እና በማራቶን) 22 ሜዳሊያዎችን አሸንፈዋል፡፡ በዚህ ድምር የሜዳሊያ ባለቤትነት ውስጥ ጐረቤቷ ኬንያ ተቀራራቢ ተፎካካሪዋ ናት፡፡ 11 ሜዳሊያ ከአንድ ወርቅ ጋር ይዛ - ኬንያ!
ለአለፉት ሁለት አሰርት ዓመታት የኢትዮጵያን ሩጫ የወከለው ቀዳሚ ፊት የሃይሌ ገብረስላሴ ገፅ ነበር፡፡ ሁለት ጊዜ የ10,000 ሜትር የአለም የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት! (1996 እና 2000 ዓ.ም) በዚህም ሆነ በዚያ ጊዜ የ27 የዓለም ሪከርዶች ጌታ ነው!
በኖቬምበር 2012 መጣጥፍ በSport Illustrated (በገላጭ ስዕል የታጀበ ስፖርት እንደማለት) ኃይሌን፤ “የቤት ውስጥ ሩጫን እንደፈጠረው እንደቤብ ሩት፤ ኃይሌ ገብረስላሴ የዘመናዊው የዓለም ረዥም ሩጫ ሪኮርድ ፈጣሪ ነው” ብሎታል! ሲያሞካሸውም “ዘመን ዘለል የስፖርት ሰው” ይለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሜዳሊያውን አቀበት በወጣችና ባንዲራዋ ከፍ ብሎ በተውለበለበ ቁጥር፤ አገሪቱ በጋራ ኩራት ደረቷን-መንፋቷ አያስገርምም!
ዛሬ ኃይሌ 39 አመቱ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜውን የንግድ ሥራዎቹን ለማሳደግ የሚጠቀም ሲሆን ሌላውን ጊዜውን መጪውን ኢትዮጵያዊ ሯጭ ለመቅረፅ ያውለዋል፡፡ በመጪው ትውልድ ላይ ኃይሌ ታላቅ ተስፋ ያያል፡፡ሌላዋ የኢትዮጵያ ጀግና የኃይሌ ዘመነኛ ደራርቱ ቱሉ ናት፡ ዛሬ ጡረታ ወጥታለች፡፡ በ1992ቱ የባርሴሎና ኦሎምፒክ የ10,000 ሜትር የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ናት፡፡
ከአዲስ አበባ 220 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በበቆጂ ከተማ የተወለደችው ደራርቱ፤ የሴት ሯጭ አርአያ አልነበራትም፡፡ “ለወርቅ ሜዳሊያ ስለሚሮጡ ሴቶች ምንም እውቀት አልነበረም” ትላለች እየሳቀች፣ አዲሳባ በሚገኘው ምቹ ቤቷ ውስጥ ዘና ብላ፣ በአስተርጓሚ እየተናገረች፡፡ “ሴቶች የሚሮጡት፤ ባል ለማግባትና ልጆች ለመውለድ ብቻ መሆኑን ነበር የሚያውቁት፡፡”
እሷ እንግዲህ ከሷ በፊት ይሮጡ የነበሩትን ወንዶች ነበር የምታየው፡፡
“አሰልጣኞቻችንም የሚነግሩን እነ ምሩፅ ይፍጠርና ማሞ ወልዴ የወርቅ ሜዳሊያ ለሀገራቸው በማስገኘት ኢትዮጵያን በአለም ማሳወቃቸውን ነበር” ብላ አከለችበት፡፡ “አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ መሮጡን እያወሱን ‘እናንተ የተሻለ ውጤት ማሳየት አለባችሁ’ ይሉናል፡፡
ደራርቱ በ16 ዓመቷ ወደ አ.አ መጣች፡፡ በቀጣዩ አመት ኮስተር ያለ የምር ልምምድ ማድረግ ጀመረች፡፡ ቀዳሚዎችን ጀግኖች ምሩፅንና ማሞን በአካል ያገኘቻቸው ይሄኔ ነው!
ምሩፅ ለኃይሌም አርአያ የሆነ ሯጭ ነው፡፡ ኃይሌ ደግሞ በፈንታው ለ18 አመቱ መሐመድ አሚን ሞዴል የሆነው አብሪ - ሯጭ (Inspiration) ነው፡፡ መሐመድ በ2012 የኢንዶር ቻምፒዮንሺፕ የ800 ሜትር አሸናፊ ነው፡፡“ኃይሌ ገ/ሥላሴ የኦሎምፒክ ባለድል ሲሆን ያየሁበትን ጊዜ አስታውሳለሁ” ይላል መሐመድ፤ “በጣም ወጣት ነበርኩ ግን ያ ድል ከአእምሮዬ ላይ ተትሞ ቀርቷል!”
 የተሻለ ኑሮ የተሻለ ህይወት
መሐመድ አሚን ቤተሰቦቹ ጫማ ሊገዙለት ባልቻሉባቸው፣ የመጀመሪያ ውድድሮቹ በባዶ እግሩ ነበር የሚሮጠው፡፡ ዛሬ ያለጥርጥር ጫማ የመግዛት አቅም ያለው የመካከለኛ ርቀት ኦሎምፒክ ሯጭ ነው፡፡ “እንደምገምተው ድህነት ከድል የሚያግድ እንቅፋት እንደማይሆን ነው የእኔ ማሸነፍ የሚያሳየው” ይላል መሀመድ፡፡የመሀመድ ኑሮ ውጤቱን ለሚያዩ ወጣት ሯጮች ሌላም የሚያረጋግጠው ነገር አለ፡፡ ሩጫ የህይወት ህልምን ለማሳካት የሚያገለግል ትኬት መሆኑን!
አንዳንዶቹ ባለህልሞች፣ ህልማቸው እውን ሲሆን ወደ ትውልድ መንደራቸው በመሄድ ኢንቨስት ያደርጋሉ፡፡ ለምሳሌ ከአሰላ ወጣ ብሎ 54 ኪ.ሜ ላይ ከበቆጂ በስተሰሜን ያደገው ኃይሌ፤ ቤተሰቡ አሁንም ትንሽ መሬት ይዞ በሚገኝባትና የተራቆተ ማህበረሰብ ባለባት፣ ሰማይ የተደፋበት አቧራና እዚህም እዚያም ግራር ብቻ በሚታይባት፤ በትንሿ ትውልድ መንደሩ ላይ ኢንቨስት እያደረገ ነው፡፡በወጣትነቱ፤ ሁሌ ይሮጥባት በነበረችው መንገድ አንዲት ቀጭን አለታማ የወንዝ ቦይ አቋርጦ ነበር የሚሄደው፡፡ የጫትና የቡና ዛፎች በአቅራቢያዋ አለ፡፡ በበጋ አንድ እዚህ ግባ የማይባል ጅረት እንደነገሩ ይፈስባታል፡፡ በክረምት ግን ያ ጅረት አታምጣ ነው፡፡ አጥፊ ጐርፉን ይዞ ሊደርስ ይችላል፡፡ አንድ ጊዜ ያ ጐርፍ እየተንደረደረ መጥቶ ውሃ ሙላቱን በያዘ ሰዓት አባትና ልጅ በማቋረጥ ላይ ሳሉ ይዟቸው እንደሄደ የሀገሩ ሰዎች በሀዘን ያስታውሳሉ፡፡ ስለዚህ ነው ኃይሌ እዚህ ወንዝ ላይ ድልድይ ያሰራው! ኃይሌ በአጠቃላይ በሀገሪቱ የተለያዩ ሆቴሎችን የገነባ ሲሆን ከአዲስ አበባ ውጪ የከፍተኛ ቦታ የሩጫ ልምምድ ማድረጊያ ቦታ ግንባታ ውስጥም ተሳታፊ ነው፡፡ (መለማመጃው ቦታ ያያ መንደር ነው)
“ትልቅ ህልም አለኝ፡፡ ኢትዮጵያ አንድ ቦታ እንድትደርስ እሻለሁ!! ድሌን ለሀገሬ በጋራ እፈልጋለሁ” ይላል ኃይሌ፡፡
ዮሴፍ ክቡርም፤ ሌሎች ሰዎች ህልማቸው ይሳካላቸው ዘንድ መርዳት የሚሻ ሌላ ሯጭ ነው! ዮሴፍ በ1993 የካናዳ አገር አቋራጭ ሻምፒዮንሺፕ አሸናፊ ነው፡፡ የኢንተርኔት ኢንተርፕረነርና የያያ መንደር መሥራች ነው፡፡
“አብዛኞቹ ሯጮቻችን ለመኖር ያህል እርሻ ከሚታረስባቸው ገጠሮች የመጡ ናቸው፡፡ ከነዚህ አትሌቶች መካከል አንዱ አሸናፊ ሆኖ ሲመጣ መላው ቤተሰብ፤ አንዳንዴም አካባቢው ሁሉ፣ ከድህነት ይወጣል” ይላል ዮሴፍ፡፡
እነዚህ አትሌቶች የሚያገኙት ገንዘብ ምን ያህል ነው?
“የተሳትፎ ክፍያና የሽልማቱ ገንዘብ ይለያያል፡፡ እንደ ፐርፎርማንሳቸውና እንደ ውድድሩ አይነት፡፡ አይነተኛው አለም አቀፍ የማራቶን አሸናፊ ከ20ሺ-50ሺ ዶላር ይከፈለዋል፡፡ አንዳንድ ቦታ ግን ከፍ ያለ ክፍያ የሚከፍሉ አሉ፡፡ የዱባይ ማራቶን 250ሺ ዶላር ነው የሚከፍለው ለወንዶችና ሴት አሸናፊ ሯጮች!”
“ከአለም ከአንደኛ እስከ 10ኛ የሚወጡ ሯጮች ከክፍያቸው ሌላ ስፖንሰሮች ከ40ሺ እስከ 80ሺ ዶላር ይጨምሩላቸዋል”
ስለዚህ እንግዲህ ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው ሯጮች በመቶ ሺ የሚቆጠር ክፍያ ያገኛሉ ብንል ያዋጣናል፡፡ አንዳንዴ ደረጃቸው እንደ ኃይሌ የሆኑ ደሞ ሚሊዮኖችን ያፍሳሉ!
 “ውረድ - በለው ግፋ - በለው”
በሯጮች ዐይን
“የኢትዮጵያ አትሌቶች ኃይለኛ ሠራተኞች ናቸው!” ይላል መላኩ ደርሶ፤ የብሔራዊው ቡድን የረዥም ርቀት አሰልጣኝ፡ “ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የኑሮ ክብደትም ሆነ የማሰልጠኛ ግብአቶች እጦት ከማሸነፍ አያቆማቸውም!”
በኢትዮጵያ የትም ቦታ ቢኬድ ሲነገር የሚሰማ አንድ እውነት አለ፡- የሀገሪቱ ሯጮች ሁሌ የዓለም ምርጥ የመሆን ጥኑ ረሀብ አለባቸው!
ከጥቂት አመታት በፊት አንዲት ካናዳዊት የሺ አምስት መቶ ሜትር ሯጭ ልትለማመድ ወደ ኢትዮጵያ ትመጣለች - ሂላሪ ስቴሊንግዌርፍ ነው ስሟ፡፡ አንድ ቀን በ2700 ሜትር ከፍታ ላይ ከሀገሬው ሯጮች ጋር የ16 ኪ.ሜ ርቀት ትሮጣለች፡ እንደሚጠረጠረው የተራራው ውጣ ውረድ፤ የከፍታው አይበገሬነትና የርቀቱ ነገር ቅጣት ይሆንባታል፡፡ ስቴሊንግዌርፍ ሦስት ሳምንት ከተለማመደችም በኋላ፤ ወደ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለመግባት ካልበቃች ከአንዲት ሯጭ በስድስት ደቂቃ ወደኋላ ቀርታ ትጨርሳለች፡፡
“ካናዲያን ራኒንግ” በተባለው በግንቦት/ሰኔ እትም ባወጣችው ፅሁፍ፤ የሷ ቡድን ከ100 ከማያንሱ ሌሎች ሯጮች ጋር በርካታ መንገዶችን አቋርጦ እንደነበር ትገልፃለች!
“የእኛ አትሌቶች በማንም መሸነፍ አይሹም!” ሲሉ ያረጋግጣሉ የኢትዮጵያ አትሌቲክ ፌዴሬሽን የማራቶን አሰልጣኝ ዶ/ር ይልማ በርታ፡፡
“መወዳደር ከፈለጉ ማሸነፍ ነው እምነታቸው፡፡ የዚህ አይነት መነሳሳትና ፍቅር ነው ያላቸው”
 የከፍታ አገር ሰው መሆን ጠቀሜታ
አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ሯጮች የመጡት ከፍታ ካላቸው አካባቢዎች ነው፡፡ እንደ አርሲ ክልል በቆጂንና አርሲን ካቀፉ፤ ከፍታ ላይ ከሚገኙ ቦታዎች የመጡ አትሌቶች ሁሌም ተጠቃሚ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ አያስደንቅም፡፡ አንድም፤ እነዚህ ሯጮች በዚህ ከፍታ ቦታ ስለሚለማመዱ አነስተኛ የኦክሲጂን መጠን መተንፈስን ይለምዳሉ፡፡ ይሄ ማለት ሁሌም አብዛኛው ሩጫ ከሚካሄድበት ከባህር ወለል ወይም ከዚያ ዝቅ ካለ ከፍታ ከሚሮጡ ሯጮች የበለጠና የተለየ ከፍተኛ ጥንካሬ አላቸው ማለት ነው፡፡
አንድም ደግሞ በኢትዮጵያውያን አንፃር ስናየው በተራራና ሸንተረር ጠርዝ መሮጥ የእግር ጡንቻ ፍርጥምታና ጥንካሬ እንዲገነቡና ረዥም ርቀትን በፅናት መጓዝን እንዲለምዱ ስለሚያደርጋቸው፤ የሀገሪቱን ሯጮች ታሪካዊውን፤ የአጨራረስ ውረድ - በለው ግፋ - በለው ወኔ፤ ያጐናፅፋቸዋል!
በእርግጥ ግን ድል የከፍታ ቦታ ሩጫ ውጤት ብቻ አይደለም፡፡በአብዛኛው የኢትዮጵያ ገጠር ያለው የኑሮ ዘይቤ ጠንካራና ባህላዊ የጉልበት እርሻ መፃኢውን ሯጭ ለመፍጠር የተዘጋጀ እርሾ ነው፡፡ እና ደሞ በዚህ ህይወት ውስጥ በእግር መሄድ፣ መሄድ፣ መሄድ… የአገሬው ባህል ነው፡፡
 የመሮጥ ባህል
በየእለቱ ት/ቤት ሲመላለሱ በእግር የሚሄዱ ከሆነ፤ “ኢትዮጵያውያን ከመካከለኛው ምዕራባዊ ሯጭ፤ በ10 እና 15 አመታት የሚበልጥ የአካላዊ እንቅስቃሴ ፅናት (Aerobic endurance) ልምምድ እያደረጉ ነው ያደጉት ማለት ነው፡፡” ትላለች ሂላሪ ስቴሊንግዌርፍ፡፡
የበቆጂ መንደር 2800 ሜትር ከፍታ ላይ ነው የምትገኘው፡ አራት የኦሎምፒክ ባለወርቅ ሜዳሊያ ልጆች አፍርታለች፡- ደራርቱ ቱሉ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ቀነኒሳ በቀለ እና ፋጡማ ሮባ፡፡ ወደ ከተማዋ የሚያስገባው መንገድ፣ በኩራት፣ አየር ላይ የዘረጋው ባንዲራ መንደሯ ጋ መድረሳችንን የሚጠቁምና የሚያሳውቅ ሲሆን የአንዲት ሴት ሯጭ ምስልንም ያሳያል፡፡
እዚህ አንድ ታሪካዊ አገርኛ አሰልጣኝ (Local Coach) አለ፡፡ ስንታየሁ እሸቱ ይባላል፡፡ መደበኛ ባልሆነ የስልጠና ዘዴ (Informal training) በዚህ ቀይና ዳለቻ አፈር የሩጫ ሰምበር (track) ላይ የሚካሄዱ ልምምዶችን ከተራሮቹ የርቀት መልክዐ-ምድራዊ እይታ ፊት ያካሂዳል፡፡ “አሰልጣኝ!” ይሉታል ስሙን - (እንደ ማዕረግ መሆኑ ነው - ኢታሊክ የእኔ)፡፡ ለ25 አመት አሰልጥኗል - በበጐ ፈቃዱ፡፡ እናም የሱ የልምምድ ክፍለ ጊዜ ወደ 250 የሚጠጉ ወጣቶችን ልቡናና ቀልብ ማርኳል (የበቆጂን ልጆች ሚስጥር የበለጠ ለማወቅ “Town of Runners” የሚለውን በቅርብ ጊዜ በታላቋ ብሪታኒያ የተለቀቀውን ዶክመንተሪ ፊልም ማየት ነው)
በበቆጂ፤ ሩጫ በሩጫው ሰምበር (Track) ላይ ብቻ አይደለም፡፡ ለበቆጂ ልጆች ሩጫ በመንገዱም፤ በተራራው ጠርዝም፤ በየፍየሎቹ ወይም በተጫኑት አህዮች መካከልም፣ የየመንገድ ዳር ገበያዎች በአጨቋቸው ቀለመ-ብዙ አትክልቶችና ቅጠላ-ቅጠሎች እንዲሁም የእጅ-ሥራ ዕቃዎች መካከልም ነው፡፡
እዚህ፤ በሌሎች የገጠር አካባቢዎች እንደሆነው ሁሉ፤ ሩጫ ማለት እጅግ በተቀላጠፈ መንገድ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ መሄጃ ዘዴ ነው፡፡ ከዚያ ደግሞ እግረ-መንገድን፤ ከቀላሉ የገጠር ህይወት ወደ ትልቅ ደረጃ መሳለጫና ማምለጫ ዘይቤ ነው፡፡
 ይሄ ነገር ከዝርያ ወይም ከዘረ-መል ጉዳይ (Genetic link?) ጋር ይገናኝ ይሆን?
አርሲን የሚያካትተው ታላቁ ስምጥ ሸለቆ ለ6000 ኪ.ሜ ያህል በምሥራቅ አፍሪካ ላይ ተንሰራፍቷል፡፡ አጥኚዎች የኢትዮጵያን ድል ሚስጥሩን ፍለጋ የሚመጡት እዚህ ነው፡፡
“ራኒንግ ኤንድ ፊትኒውስ” የተባለ በአሜሪካን ራኒንግ አሶሲየሽን የታተመ እትም የ114 ኢትዮጵያውያን አትሌቶችን የሩጫ ሰምበርና (track) የረዥም ርቀት እንቅስቃሴ በተመለከተ የብሪታኒያን የ2004 ዓ.ም ጥናት መሰረት አድርጐ ይገልፃል፡፡ ያ ጥናት እንዳመለከተው 73% የሚሆኑት የኢትዮጵያ አትሌቶች የመጡት ከሁለት ክልሎች ሲሆን አንደኛው ክልል አርሲ ነው!
ምናልባት የዝርያ ጉዳይ ይሆን? ይሄን እንዳንል 70 በመቶው ማራቶኒስቶች ወደ ት/ቤታቸው ከልጅነታቸው ጀምሮ የሚሮጡ ናቸው፤ ይላል ጥናቱ፡፡ግን ላይሆንም ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ የሚኖረውና ከአንዳንዶቹ ቀንደኛ ሯጮች ጋር የሰራው የሳይንስ ሰው፤ የደቹ ፊዚዮቴራፒስት ቪኔ ሎዝ እንኳ፤ ጉዳዩ የዝርያ ነገር መሆኑን ለመቀበል አሻፈረኝ ይላል፡፡ ሎዝ እንደሚለው ‘የአቺለስ መንፈስ አለው’ የሚባለውን ግምት የሚያሟሙቁ አስተሳሰቦችን የሚያራምዱ ቢኖሩም፤ የኢትዮጵያውያን አትሌቶችና የኬንያውያን አትሌቶች ከአንድ ወንዝ የተቀዳ፣ ከአንድ ስምጥ ሸለቆ የፈለቀ፤ ዝርያ (genes) መኖሩን ይገምታል፡፡
ባዮሎጂስቱ ያናስ ፒትሲላዲስ በዲ.ኤን.ኤ ዙሪያ ብዙ ጥናቶችን ያካሄደ ነው፡፡ ዋናው ትኩረቱን ያነጣጠረው በ10 ዓመታት ውስጥ በነበሩ የምሥራቅ አፍሪካ ዋና ዋና አትሌቶች ላይ ነው፡፡ ለድል የሚያበቃ ምንም የተለየ ጂን (ዝርያ) እንደሌላቸው ነው ያረጋገጠው!”
እስከዛሬ ማንም አጥኚ ምንም ልዩ አካላዊ የዝርያ አይነት ከአርሲ ልጆች ምርጥ ሯጭነት ጋር መዛመዱን እንዳላረጋገጠ ታውቋል፡፡ ይልቁንም እድሜ ልክ፣ በከፍተኛ ቦታ ላይ መሮጥ ያለጥርጥር የፈጣን አትሌቶች ተከታታይ ትውልዶችን ማፍራቱ የታመነ ነገር ሆኗል፡፡ እሺ ነገሩ እንዲህ ከሆነ፤ ለምንድነው በአጠቃላይ ከኢትዮጵያ፣ በተለይ ደግሞ ከአርሲ ብቻ ታላላቅ ሯጮች የሚፈልቁት? የዚችን የምሥራቅ አፍሪካን አገር ሯጮች፤ ወደ ድሉ ሰገነት መውጫ፤ ለሽልማት የሚያንደረድራቸው ምን ኃይል ነው?
ከላይ የጠቀስኳቸው ሁሉ ምክንያቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ምናልባት ግን ዋና ዋናዎቹ፡- ጀግንነት (ወኔ)፣ አርአያ የሚሆኑ ፈር - ቀዳጅና አንጋፋ ሯጮች መኖር፣ ከፍታ ቦታ፣ ጠንካራ ሠራተኝነት፣ የሩጫ ባህል እና ኑሮን የተሻለ ለማድረግ በቁርጠኝነት መታገል ናቸው፡፡ እነሆ ኢትዮጵያ የሩጫ የበላይነቷን እስከቀጠለች ድረስ የሯጭ ልጆቿን ሚስጥር ለማወቅ ያለው ፍላጐትም ይቀጥላል፡፡
 ለወደፊት አጥኚዎች አንድ ጥቆማ፡- ምናልባት ጥናቱን ከንጋቱ 11 ሰዓት ላይ ከመስቀል አደባባይ መጀመር፡፡ ከዚያ ጃን ሜዳን ወይም እንጦጦ ጋራን መዳሰስ፡፡
 የተርጓሚው ማስታወሻ፡-
እኚህ የውጪ አገር አጥኚ የአትሌቶቻችንን የድል ሚስጥር ለማወቅ ያደረጉትን ጥረት ሳይ፤ ለምን በሩጫ ብቻ እንደዛ ልንሆን ቻልን? በሌላ ህይወታችንስ ለምን እነዚህን እሴቶች አጣን? በፖለቲካው፤ በኢኮኖሚውና በማህበራዊ ህይወታችን ምን ነክቶን ተሸናፊ ሆንን? ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ፡፡
ጀግንነት አንሶን ነው?
ቀደምት አርአያ አጥተን ነው?
ከፍታ ቦታ ላይ ስለማንኖር ነው?
ጠንካራ ሠራተኛ ስላልሆንን ነው?
የሩጫ (የፍጥነት)ባህል ስላጣን ነው?
ኑሮን የተሻለ የማድረግ ቁርጠኝነት ጐድሎን ነው?
ወይስ መስቀል አደባባይ ጠፍቶብን ነው?
ኧረ ጐበዝ እንነጋገር! እንጠያየቅ! እንወሳሰን!!

Read 975 times