Saturday, 01 September 2012 11:33

ጥላ ፍቅር

Written by  አገኘሁ አሰግድ
Rate this item
(4 votes)

ትናንት ረፋድ፡-

ቃል ልናገራት ድፍረት ያለኝ አይመስለኝም ነበር፡ እንዴት እንደሆነ ሳላውቀው፣ በሚተሳሰር አንደበት ይህንን ተናገርኩ “ሮሚ …ብዙ ጊ..ዜ እንዲህ ላለማሰብ ሞከርኩ… አልቻልኩም፡፡

ጊዜ በሄደ ቁጥር የማብድ ሁላ መሰለኝ፡፡ የትም ብሸሽ የማላመልጠው ፍቅርሽ ከውስጤ አለ፡፡ ቢያንስ … እንደ… ማትጠይኝ አውቃለሁ፡፡ … ምን መናገር እንዳለብኝ አላውቅም፡፡ ብቻ ጥልቅ ፍቅሬን ከተረዳሽ ደውይልኝ፡፡ … ስልክሽን እጠብቃለሁ… ቻዎ” የስንብት ስስማት ከንፈሬ ጉንጯ ላይ ተርበተበተ፡፡ “ምነው ባልሳምኳት” ይላል ውስጤ፡፡ እሷ ፈዛለች፣ ልትናገር ፈልጋ እንዳልቻለች አይነት፡፡

ማታ፡-

ዘላለም ከሆኑ ስቃይ ሰዓታት በኋላ ሮሜ ደወለች፡፡

ስሟን ስጠራው እንዴት ደስ እንደሚለኝ! የሆነ ኪናዊ ውበት አለው፡፡ እናንተስ ስትሰሙት ጆሮዋችሁ ላይ ጣዕሙ፣  አእምሮዋችሁ ላይ ውበቱ አይሰማችሁም? “ሀሎ” አልኩዋት፡፡ “አሸነፍከኝ” … አለች ሮሚ ከወዲያኛው ጫፍ፡፡ ለዓለም የሚበቃ ሀሴት ልቤ ውስጥ፡ “አሸነፍከኝ” የሰማሁት የዓለማችን ውዱ ቃል፡፡

ዛሬ፡-

ሮሚዬ ሰፈር ነው ያለሁት፡፡ ከቤታቸው ራቅ ብሎ ካለው ሜዳ፡፡ ትላንት “በ4 ሰዓት እዚህ እንገናኝ” ብላኛለች፡፡ አሁን 3 ሰዓት መሆኑን ብነግራችሁ ታምኑኛላችሁ?

3፡55

የዛሬው 4 ሰዓት በእርግጥ 4 ሰዓት ብቻ ነው ወይስ የእኔም ሕይወት? ሮሚ ልትመጣ ነው፡፡ ምዕት የሆኑ 5 ደቂቃዎች ብቻ ቀሩዋት፡፡

4፡05

ሮሚ አልመጣችም! መምጫዋን ደጋግሜ አያለሁ - የለችም፡፡ ምን ነካት? ኧረ ባካችሀ ፍጥረታት እንዴት እንደናፈቅሁዋት ሂዱና ንገሩዋት፡፡ ንፋሱ ምን ይሰራል እዚህ ከዛፍ ጋር የሚታገለው - ለምን ሄዶ አይነግራትም?

4፡10

ይኸውላችሁ… እስከ አሁን አልመጣችም፡፡ ደወልኩ፡፡ ስልኳ ጥሪ አይቀበልም፡፡ ጩህ ጩህ አለኝ፡፡ ለምን ታረፍዳለች? ልታገኘኝ አልጓጓችም ማለት ነው? አሸነፍከኝ ካለች በኋላ እኔን በምኞት መግደል ምን ይሉት ፈሊጥ ነው? እሺ ስልኳንስ ለምን ዘጋችው?

5፡00 ሰዓት

እኔ ይህንን አላምንም! “አሸነፍከኝ” ያለች ሴት እንዴት 1፡00 ሰዓት ሙሉ ትዘገያለች፡፡ ዛሬ ካላገኘኋት ነፍስና ስጋዬ መለያየታቸው ነው፡፡ ድፍረት ሰብስቤ ሄድኩ፣ ወደቤቷ - ንግስቴ ወዳለችበት፡፡

5፡05

ሰፈራቸውን ምን እንደረበሸው እንጃ - ደስ አይለም፤ ተሸብሯል፡፡ ቀጥታ ወደ እሷ ቤት ሄድኩ፡፡ ስደነግጥ ይሰማኛል፡፡

ሮሚ የቀረችው ለካ ወዳ አይደለም፡፡ የሚሰማ ለቅሶ፣ የሚታይ ድንኳን ግቢያቸው ውስጥ ከትሟል፡፡ የእኔ ቆንጆ ወዳ አይደለም የቀረችው፣ ምን አደርጋለሁ በቃ ወደ ሰፈሬ ልመልስ፡፡ አ…አ…ግን እኮ ሮሚ ሰው ሞቶባታል፡፡ ከቤተሰቦችዋ ወይም ከቅርብ ዘመዷ አንድ ሰው አጥታለች፡፡ አግኝቼ ላፅናናት ይገባል፡፡ ከዚህም በላይ ግን እሷን ማየት አለብኝ!!!

5፡10

በለቀስተኛው መሀል ገባሁ፡፡ ሮሚን በአይኔ እፈልጋት ጀመር፡፡ ብዙ ሳልፈልግ አየኋት…ያቻት…ወደ እኔ እያየች…ፈገግ ብላ…ፎቶዋ ተሰቅሎ በፈገግታ እያየችኝ፡፡ እስከ አሁን ያልሰማኋቸው “ሮሚዬ …ሮሚ “እያሉ የሚያለቅሱ ድምጾች ጆሮዬን ከበቡኝ፡፡….ብዥ አለብኝ…ደንዝዣለሁ፡፡ እየተወለካከፍኩ ወደ ውጪ ወጣሁ፡፡ አልቃሾቹ በእጥፍ በዙብኝ፡፡ ዓለም ሁሉ እያለቀሰ መሰለኝ፡፡ ለምን ለእኔ አያለቅሱልኝም? እዚህ ሮሚ በር ላይ ለሞትኩት እኔ የሚያለቅስልኝ ማነው? ከመሞት በላይ ለመሞቴ ምስክር ያሻል?

…ስንት ሰዓት ነው? ከዚህ በኋላ ጥቂት ወጣቶች ሳጥን ተሸክመው ወጡ፡፡ ሮሚ እዛ ውስጥ አንቀላፍታለች፡፡ ለዓለም ብርሃን የሚሰጡ አይኖቿ ተከድነው ዓለም ጨልማለች፤ ድቅድቅ ውጧታል፡፡

ሳጥኑን በመኪና ጫኑት፡፡ ማን ልብ ብሎ ያየኛል! በድፍረት መኪናው ላይ ወጣሁ፡፡…ከማላውቃቸው ሰዎች መሀል ተቀምጫለሁ፡፡ መኪናው ተንቀሳቀሰ፡፡ ሕዝቡ ይከተል ጀመር፡፡ ሮሚን ቀብረው ሊመለሱ፡፡ የሰፈራቸው ውበት ላይ አፈር ሊመልሱበት… ግን እንዴት አስቻላቸው? እንዴት ደፍረው በሕይወቴ ላይ አፈር ይጭናሉ?

…አንጀታቸው ጨከነ፣ ልባቸው ደፈረ…ሮሚን አፈር መለሱባት፡፡ ይሄ ሁሉ ሲሆን እዛው ነበርኩ፤ እያየሁ፡፡

ለቀረው ሰው ሮሚ ተፈፀመች፡፡ የመልስ ጉዞ ጀመሩ፡፡ እኔ ግን እዛው ቀረሁ፡፡ በማታውቃቸው ሰዎች መሀል ብቻዋን እንዴት ልተዋት? ለመጀመሪያ ጊዜ አለቀስኩ፣ ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ፡፡ ሮሚ ናፈቀችኝ…የጉንጮቿን ስርጉድ ማየት ተመኘሁ፡፡ “ለምን…ለምን ጥለሽኝ ሄድሽ!?” ብዬ ልጠይቃት ፈለግሁ፡፡

ፍቅሬን ስለነገርኩዋት የሞተች ሁሉ መሰለኝ፡፡ ታድያ እስከ ዛሬ ሕመም በፊቷ ያልዞረ፣ ፍቅሬን በነገርኩዋት እለት ምን ገደላት? ፍቅሬ ሟርተኛ ነበር እንዴ?...እውን አምላክ ምንም የማይሳነው ከሆነ ለምን ሮሜን አይመልስልኝም?!

መሸ፡፡ የማታናግረኝ ሮሜ አጠገብ ሳለሁ መሸ፡፡ ባትሰማኝም “ሮሚዬ ነገ እመጣለሁ..ደህና ሁኚ” ብያት ሄድኩ፡፡ “ና …ትተኸኝ አትሂድ” ያለች መሰለኝ ከኋላዬ፡፡ “እሺ” አልኩዋት፡፡ “እሺ ሮሚ….እመጣለሁ!”

እና ከመሄዴ በፊት እውነተኛ ፍቅር ከልባቸው ላደረ፣ ፍቅርን ለሚያምኑትም ይህችን መልዕክት መናገር ወደድኩ፡፡

“…ለምታፈቅሩት ሰው ልትነግሩት የምትሹት ካለ አታሳድሩ፣ ዛሬውኑ ንገሩት፡፡ ነገ የሚባል የለም፡፡ ነገ ላይ ጥሏችሁ ሊሄድ ይችላል - ሮሚ ጥላኝ እንደሄደችው፡፡

ዛሬን አትለፉ፣ ነገን አትመኑ …ተከትለዋችሁ ለሚመጡ ሁሉ መልዕክቴን አሳልፉላቸው፡፡ እኔ ወደ ሮሜ መሄዴ ነው፡፡ ናፍቃኛለች፡፡

በፍርሃት ታብቼ ያልነገርኩዋትን ሁሉ ልነግራት ነው፡፡ እሷ ሳታውቅ አፈቅራት የነበሩት አራት ዓመታት እንዴት እንደነበሩ ላጫውታት፣ ላሳዝናት፣ ላስቃት፣ መሄዴ ነው፡፡ ንፍቅ ብላኛለች፡፡

ምን ላድርግ? የትም ብዬ ሸሽቼ የማላመልጠው ፍቅሯ ልቤ ውስጥ አለ፡፡ እሷም ሳልናፍቃት አልቀርም፡፡ ኡፍፍፍ….መንገድ ሁሉ እንዲህ ደስ የሚል ቢሆን ሁሌ ተጓዥ እሆን ነበር…

 

 

Read 4752 times Last modified on Saturday, 01 September 2012 11:38