Print this page
Saturday, 19 June 2021 16:55

ፌደራል ፖሊስ ምርጫው እንከን አልባ እንዲሆን ለባለ ድርሻ አካላት ጥሪ አቀረበ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(9 votes)

ማንኛውንም አጠራጣሪ ነገር ህዝቡ እንዲጠቁም አሳስቧል
                                    
          የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ከነገ በስቲያ ሰኞ የሚካሄደው 6ኛው አገራዊ ምርጫ ሰላምና ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ለኢትዮጵያ ህዝብና ለሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጥሪ አቀረበ፡፡
ኮሚሽኑ “ለኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ለ6ኛው አገራዊ ምርጫ በሰላም አደረሳችሁ” ብሎ በሚጀምረው መግለጫው፣ የምርጫው ሂደት ተጀምሮ አሁን ያለበት ደረጃ እስኪደርስ በጨዋነትና በትግስት ህዝቡ ላደረገው ድጋፍና ትብብር የላቀ ምስጋናውን አቅርቧል፣ በቀሪው የምርጫ ሂደትም ምርጫውን የሚያደናቅፉ አጠራጣሪ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ መረጃ በመስጠት  አስፈላጊውን ድጋፍ ለፀጥታና ለደህንነት ሃይሉ በማድረግ  ህዝቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ለተፎካካሪ ፓርቲዎችም ባቀረበው ጥሪ፤ የምርጫ ህጉንና የስነ-ምግባር ደንቡን አክብረው እስካሁን ድረስ ለምርጫው ሰላማዊነት በሰለጠነ መንገድ በመንቀሳቀስ ላደረጉት ገንቢ አስተዋፅኦ ምስጋናውን ያቀረበ ሲሆን ፣ ምርጫው ተጠናቅቆና ቆጠራው አልቆ ጥቅል ውጤቱ በምርጫ ቦርድ በኩል በይፋ እስኪገለጽ ድረስ በትዕግስት እንዲጠባበቁና በዚህም ለምርጫው ሰላማዊነት የበኩላቸውን  እንዲወጡ  ጥሪ አቅርቧል፡፡
ኮሚሽኑ ለፌደራልና የክልል የፀጥታና የደህንነት አካላት ባቀረበው ጥሪ፤ “መስዋዕትነት  በመክፈል ጭምር ፍፁም ገለልተኛ ሆናችሁ፣ ሌት ተቀን እያበረከታችሁ ላለው አስተዋፅኦ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ከፍተኛ አድናቆትና ምስጋናውን ያቀርባል” ካለ በኋላ፤ በቀጣይ በሚኖረው የድምፅ አሰጣጥ ሂደት እንዲሁም አጠቃላይ የምርጫው ውጤት እስኪገለፅ ድረስ የፀጥታና  ደህንነት አካላት የተሰጣቸውን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ሃፊነት  እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በአግባቡ እንዲወጡ  ከአደራ ጭምር አሳስቧል፡፡
 ኮሚሽኑ በመግለጫው፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ወሳኝ ምዕራፍ ከግምት ውስጥ በማስገባት የምርጫ ሂደቶች ከሁከትና ብጥብጥ የፀዱ እንዲሆኑ ከፀጥታና የደህንነት መዋቅሩ ጋር የተቀናጀ የምርጫ ደህንነት ዕቅድ በማዘጋጀት፣ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ዕለትና በድህረ ምርጫ ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ውስጣዊና ውጫዊ የፀጥታ ሁኔታዎችን በአግባቡ በመተንተንና በመለየት፣ አስፈላጊውን የሰው ሀይልና ግብአት በማሟላት በሀገርና በዜጎች ላይ ጥፋት ሳያስከትሉ ለማምከን፣ በጥብቅ ዲስፕሊን ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ  በአፅንኦት አስታውቋል፡፡ ኮሚሽኑ አክሎም፤ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫን ከዚህ አንፃር ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ማጠናቀቅ ለሀገራችን ሰላምና መረጋጋት ያለውን ጠቀሜታ የተገነዘበው የፌደራል ፖሊስ፤  የውጭና የውስጥ ፀረ-ሰላም ሃይሎች ጸጥታውን ለማናጋት፣ የምርጫውን ሰላማዊነት ለማደፍረስና ሁከትና ብጥብጥ ለመቀስቀስ እንደሚንቀሳቀሱ ከወዲሁ  በመረዳት፣ ምንም አይነት ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ በየትኛውም አካባቢ እንዳይኖር ከፌደራል እስከ ክልል ያሉ የፀጥታና የደህንነት መዋቅሮች በከፍተኛ ሃላፊነትና ተጠያቂነት የተሰጣቸውን ሃገራዊ ተልዕኮ ለመወጣት በቂ ዝግጅት ከማድረጋቸውም በተጨማሪ፣ ጠንካራ የመረጃ ልውውጥ ስርዓት በመዘርጋት፣ የቅድመ መከላከል ስራ በመስራት ላይ እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያን ሰላም መሆን የማይሹ ጸረ ሰላም ሃይሎች ከውስጥና ከውጪ ተደራጅተው፣ የምርጫውን ሰላማዊነት ለማደናቀፍ እየሰሩ እንደሚገኙ የሚታወቅ መሆኑን የገለጸው ኮሚሽኑ፤ ከዚሁ አንፃር መላው የሀገራችን ህዝብና የፀጥታ ሃይሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ በመቀናጀት ይህንን ታሪካዊ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ ማጠናቀቅ እንዳለበት አሳስቧል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ለህዝቡና ለምርጫው ስራ ከፍተኛ እገዛ የሚያደርጉ መሰረተ ልማቶች፡-  የስልክ፣ የመብራት፣ የውሃና የህክምና አገልግሎቶች በምርጫ ወቅት ያለ በቂ ምክንያት እንዳይቋረጡ የሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ያስጠነቀቀው የኮሚሽኑ መግለጫ፤ በመጨረሻም በድምፅ መስጫ እለትና በድህረ- ምርጫ ወቅት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሁሉ በህግ አግባብ ብቻ እንዲሆኑ ኮሚሽኑ በጥብቅ አሳስቧል፡፡

Read 12931 times