Saturday, 19 June 2021 16:47

በጀነራል ሰዓረ ግድያ ጥፋተኛ የተባለው በሞት እንዲቀጣ ተጠየቀ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(3 votes)

   የቀድሞ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ኢታማዞር ሹም ጀነራል ሰዐረ መኮንንና ጓደኛቸው ሜጄር ጄኔራል ገዛኢ አበራን በመግደል ወንጀል ተከሶ ጥፋተኛ የተባለው አስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ፤ በሞት እንዲቀጣ ዐቃቤ ህግ ጠየቀ፡፡ የተከሳሹ ጠበቆች በበኩላቸው፤ የዐቃቤ ህግ ጥያቄ ከወንጅል ህግ ድንጋጌ ወጪ እንደሆነ በመግለፅ መቃወሚያቸውን አሰምተዋል፡፡
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረ ሽብርና የህገ መንግስት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ትናንት በዋለው ችሎት፤ የዐቃቤ ህግን ተከሳሹ በሞት ይቀጣልኝ ጥያቄንና የተከሳሹን ጠበቆች የቅጣት ማቅለያ አስተያየቶች ተቀብሎ፣ ጉዳዩን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ቀጠሮ ይዟል፡፡
ተከሳሹ አስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ፤ ጀነራል ሰዓረ መኮንን እና ሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራን ገድሏል የሚል ቀርቦበት ጉዳዩን ፍርድ ቤቱ ሲመረምር ቆይቶ ግንቦት 27 ቀን 2013 ዓ.ም ተከሳሹን ጥፋተኛ ነህ ሲል ውሳኔ  ሰጥቶበት ነበር፡፡ በዚህ ውሳኔ መሰረትም፤ ግራ ቀኙን  የቅጣት ማክበጃና ማቅለያ ሃሳቦቻቸውን እንዲያቀርቡ መሰረት፤ ዐቃቤ ህግ በተከሳሹ ላይ የሞት ፍርድ እንዲወሰንብት የጠየቀ ሲሆን የተከሳሽ ጠበቆች ጥያቄውን በመቃወም 4 ጠቅላላና ልዩ የቅጣት ማቅለያ ሃሳቦችን አቅርበዋል፡፡
ተከሳሹ መልካም ባህርይ ያለው፣ ቀደም ሲል የወንጀል ሪከርድ የሌለበት፣ የሁለት ልጆች አባት መሆኑንና ሽማግሌ አባቱንና እናቱን የሚጦር መሆኑን፣ በመግለጽ የቅጣት ማቅለያ፤ ሃሳባቸውን አቅርበዋል፡፡ የተከሳሽ ጠበቆች ባቀረቡት ልዩ የቅጣት ማቅለያ ተከሳሹ የአገሪቱ ኢታማዦር ሹም አጃቢ እንደነበር፣ድርጊቱ ከተፈፀመ በኋላ በደረሰበት ጉዳት በአንገቱ በኩል ጥይት ገብቶ በጭንቅላቱ የወጣ መሆኑን ለዚህም ህክምና ሲደረግለት ከነበረው የአገር መከላከያ ሰራዊት የጤና ማስረጃ ለማቅረብ የሚችል መሆኑን አመልክተው፣ ተከሳሹ አገሩን በውትድርና ሲያገለግል መቆየቱም በቅጣት ማቅለያነት እንዲያዝለት አስመዝግበዋል፡፡
የግራ ቀኙን የቅጣት ማክበጃና ማቅለያ አስተያየቶች የተቀበለው ፍርድ ቤቱ፤ ጉዳዩን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም ቀጠሮ ይዟል፡፡

Read 13220 times