Print this page
Saturday, 19 June 2021 16:48

ዛሬ በመስቀል አደባባይ ታላቅ የፖሊስ ትርኢት ይካሄዳል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

 አዲስ የፖሊስ የደንብ ልብስና አርማም ይመረቃል
                           
              አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በዛሬው ዕለት በመስቀል አደባባይ ታላቅ ፖሊሳዊ ትርኢት የሚያቀርብ ሲሆን አዲስ የፖሊስ የደንብ ልብስና አርማ እንደሚመረቅ ታውቋል፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሚዲያ ሃላፊ  ዋና ኢንስፔክተር ማርቆስ ታደሰ ለአዲስ አድማስ እንደገለጹት፤ ዛሬ ከጠዋቱ 2፡30 ጀምሮ የሚካሄደው ፖሊሳዊ ትርኢት ሶስት ዋና ዋና ዓላማዎች ያሉት ሲሆን፣ አንደኛው ኮሚሽኑ ያደረገውን ሁለንተናዊ ሪፎርምና አጠቃላይ ቁመና ለማሳየት፣ ሁለተኛው አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለበርካታ ዓመታት ሲገለገልበት የነበረውን የደንብ ልብስና አርማ በአዲስ መቀየሩን ለማብሰርና ለማስመረቅ፣ ሶስተኛ ሰኞ ሰኔ 14 የሚካሄደው 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ሰላማዊና የተሳካ እንዲሆን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በየደረጃው የሰጠውን ስልጠና አጠናቅቆ ወደ ስራ መግባቱን አስመልክቶ የማጠቃለያ ስነ-ስርዓትም ጭምር እንደሆነ ዋና ኢንስፔክተሩ ተናግረዋል፡፡
 ዛሬ በሚካሄደው በዚህ ታላቅ የፖሊስ ትርኢት ላይ የፌደራል መንግስት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የፌደራል ፖሊስና የአዲስ አበባ ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮችና፣ የከንቲባው ካቢኔ አባላት እንዲሁም ታዋቂ ግለሰቦች ይታደማሉ ተብሏል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ አጠቃላይ አሰራሩን ለማሻሻልና ለማህበረሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማዘመን ምን መደረግ አለበት የሚለውን በባለሙያ አስጠንቶ አጠቃላይ ሪፎርም እያካሄደ መሆኑን የገለፁት ዋና ኢንስፔክተር ማርቆስ ታደሰ፣ ሰኞ  የሚካሄደው 6ኛ አገር አቀፍ ምርጫ በሰላማዊ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ የአዲስ አበባ ፖሊስ ምን ያህል ዝግጅት አድርጓል በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤ መላው የኮሚሽኑ አመራርና አባት መላ ትኩረታቸው በምርጫው ላይ እንደሚሆን ገልፀው፣ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ባሉ ፖሊስ ጣቢያዎች የሚገኙ የፖሊስ አባላት ከጥበቃ ጋር በተገናኘ ተገቢ የሆነ ስልጠና እንደወሰዱና  ስልጠናው ከላይ ከአመራሩ ጀምሮ እስከ ታች ድረስ በተዋረድ መሰጠቱን አስረድተዋል፡፡ከዚህ ጎን ለጎንም መደበኛ የሆነው የወንጀል መከላከል ስራ ስልጠና መሰጠቱን የገለጹት ዋና ኢንስፔክተር ማርቆስ፣ ኮሚሽኑ አጠቃላይ ምርጫውን የተመለከቱ ዝግጅቶችን አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱንም ተናግረዋል፡፡የዛሬውም ትርኢት አንዱና ዋነኛው ጉዳይ ፖሊስ አጠቃላይ ዝግጅቱን አጠናቅቆ ወደ ስራ መግባቱን ለህዝብ ለማብሰርና ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን የተሰጠውን ሃላፊነት በአግባቡ እንደሚወጣ ቃል ለመግባትም እንደሆነ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡





Read 12938 times