Saturday, 01 September 2012 11:26

ማምሻዎቹ

Written by  አንድነት ግርማ
Rate this item
(0 votes)

ብዙ አመት በምድር ላይ ኖሬያለሁ፡፡ አዎ ለአንድ ሰው ብዙ ነው፡፡ ሰባ አመት፡፡ አሁን መሰናበቻዬ ነው፡፡ ውልደቴን ይዛ ብቅ ያለችው ጸሃይ መጥለቂያዋ እንደተቃረበ ስለታወቀኝ፣ የቆየሁባትን፣ የኖርኩባትን ምድር እንድታሰናብተኝ ወዳለችበት ሄድኩ፡፡ ከምድር ጋር ለስንብት ከመገናኘታችን በፊት ሃሳብ ያዘኝ፡፡ ቆይ ተቃቅፈን ተሳስመን ነው የምንለያየው? … ወይስ እንደው “ቻው ቻው” ተባብለን? ምናልባት ታባርረኝ ይሆን? ከመምጣቱዋ በፊት ማውጠንጠን ጀመርኩ፡፡

እፀሃይ መኖሪያ ቤት ብዙዎች ሊሰናበቱ የመጡ አሉ፡፡ ግቢው መጠነኛ ነው፡፡ ከመግባቴ ክፉኛ የሚቀዘቅዝ ብርድ ነደፈኝ፡፡ ልክ እንደኔ እድሜ ጠግበው የሚሞቱ ሁሉ ሊሰናበቱዋት ይመጣሉ፡፡ ሽማግሌዎች ሰብሰብ ወዳሉበት ተጠጋሁ - ቢሞቀኝም ብዬ፡፡ ሆኖም ሁሉም በርዷቸዋል፡፡ ለአንዳንዶቹ መሸኛ ትጽፋለች፡፡ “እሱን ስለላክልኝ አመሰግናለሁ፡፡ የኖረው የብርሃን ህይወት ነው፡፡” ለብዙዎች ግን ምንም አትጽፍም፤ ዝም ብላ ነው የምታሰናብት፡፡ አንዳንዶች ይቅርታ ይጠይቋታል - ብልጣ ብልጦች ይመስላሉ፡፡ “ይህ ጊዜ ይመጣል ብለን ፈጽሞ አላሰብንም … ሁሌም የሚሞተው ሌላ ሰው ነበር የሚመስለን …” ይሏታል፡፡ እየተንከባለለች ወደኔ መጣች፡፡

አንድ ክፍል ገብተን ፊልም ከፈተችልኝ፡፡ ነብስ ካወቅሁ ግዜ ጀምሮ ያለውን የራሴን ህይወት የያዘ ነው፡፡ ተማሪ እያለሁ፣ ስራ ከጀመርኩ በኋላ፣ ከተማሪዎች ጋር፣ ከሰራተኞች ጋር፣ ከቤተሰቤ ጋር፣ ከጎረቤቶቼ ጋር … በተለያየ አጋጣሚ ከተገናኘሁዋቸው ሰዎች ጋር የነበረኝን ግንኙነት የሚያሳይ ፊልም፡፡ ፊልሙን ከፍታልኝ እሷ ወጣች፡፡ ፊልሙን ሳይ ሞቅ ሊለኝ እንደሚችል አስቤ ነበር፡፡ ሆኖም አይቼ ሳልጨርስ አስጠላኝ፡፡ አዲስ ነገር የለውም፡፡ የእጅ መዳፌን ያህል ጠንቅቄ የማውቀው እውነት ነው፡፡ በአጭሩ ለራሴ የኖርኩ ሰው ነኝ፡፡ የሚገርመው ይህ ሳይሆን ለራሴ የኖርኩት በሌሎች ኪሳራ ጭምር መሆኑ ነው፡፡ ሌሎችን እያከሳሁ የወፈርኩ፣ ሌሎችን እያጨራመትኩ የፈካሁ ነኝ፡፡ አሁን ግን ያ የደከምኩለት ህይወቴ በምንም መልኩ ሊቀጠል የማይችልበት ደረጃ ደርሷል፡፡ እንዳልኳችሁ የእድሜዬ ጀንበር አዘቅዝቃለች፣ ከልካይ የላትም፤ ዝም ብሎ ጥቁር ለብሶ መሸኘት ብቻ ነው፡፡ ፊልሙን ካየሁ በኋላ ብርዱ የበለጠ ወግቶ ያዘኝ፡፡

እሺ መሞቴ አይቀርም፤ ግን የወዲያኛው አለም እንዴት ይቀበለኝ ይሆን? … አይኔን ጨፍኜ ዝም ብዬ ልግባበት? የመጣው ይምጣ ብዬ? … መቼም ከዚህኛው አለም እንግዳ መጣ ብለው ከመንገድ አይቀበሉኝም … እንደዚህ አይሸተኝማ፡፡ የታሰረ ውሻ ፈተው ቢያባርሩኝስ? … እሱማ በማን እድሌ! ወደ ምድር መጥቼ እኖር ነበር፡፡ ግን በድንጋጤ የምድር መንገድ ቢጠፋኝስ? ስለ ሁለተኛው አለም ምንም አይታወቅም ብዬ ልለፈው … ግን እኮ ወደዚህኛውም አለም ስመጣ የማውቀው ነገር አልነበረም … እንደው ድንገት ነው የመጣሁት፡፡ መምጣቴን እንኳ ያወቅሁት ከመጣሁ ከብዙ ግዜ በኋላ ነው፡፡ አይታወቅም ማለት ግን የለም ማለት አይደለም፡፡ ሰው ደግሞ የሆነ ጫፍ ሳይዝ አያወራም፡፡ ሁለቱ አለማትስ ጉርብትና የላቸው ይሆን?

አሁን ምድር እንዴት ታሰናብተኝ ይሆን ብዬ ማሰቤ ከሚመጣው አለም ጋር አያይዤው ብቻ አይደለም፡፡ መገናኘት በራሱ እንደሚያሳስብ መለያየትም እንዲሁ በራሱ ያሳስባል፡፡ ተጣልቶ ከመለያየት፤ ተቃቅፎ እየተላቀሱ መለያየት ይሻላል፡፡ አይቀሬ ከሆነ-መለያየቱ፡፡ እሺ ከአንድ ሰው ተጣልታችሁ ልባችሁ ሃዘኑን በተለያየ ምክንያት ይቋቋመው ይሆናል፡፡ ግን ከእናት ምድር ከራሷ ተጣልታችሁ ስትለያዩ ሃዘኑን እንዴት ትችሉታላችሁ?

ከሞት አፋፍ ላይ ሲሆኑ ሁሉም ነገር ያስገርማል፡፡ አሁን ያ ንጹህ፣ ለስላሳ፣ ቆዳን የሚያፍታታ አየር ብርቅ ሚሆንበት ጊዜ ይመጣል ቢሉ ማን ያምናል? …፡፡ ህልም ህልም ይመስላል፡፡ ምድር እውነት እውነት በማይመስሉ እውነቶች የተሞላች ናት፡፡ የሚሳሱላት እኮ ናት /ልክ እንደስለት ልጅ/ … ግን ስንኖር ጨካኝ የሚያደርገን ነገር ምንድን ነው? ታዲያ ይህችን ምድር በሃዘን መጥቶ መለያየት እንዴት አይከብድ? … እኔ የተወለድኩ ቀን የነፈሰው ንፋስ፤ ያን ቀን የነበረው ደመና፤ የዘነበው ዝናብ፤ ከጸሃይ ተልከው ወደ ምድር የመጡ ጨረሮች፤ የወጡ ኮከቦች ሁሉ ያዝናሉ፡፡ ምናልባትም “እኛ ሲመጣ ይህንን መች አወቀን … ህጻን ሲወለድ ሁሉ ደስ ይለዋል፤ በመሆኑም ደስ ብሎን ነበር፡፡ ለሞተ ሰው ሁሉ ግን አይለቀስም፤ አሁን ነው ያወቅነው” ይሉ ይሆናል፡፡ ምናልባት ከኔ ተምረው የሚወለድን ህጻን ሁሉ በእልልታ የመቀበል ልምዳቸውን ይቆጥቡ ይሆን? … ጉምሩክ ነገር፣ ኬላ ነገር … ያስቡ ይሆን? ቢጨንቃቸው ማለቴ ነው - መፍትሄ ሆነም አልሆነ፣ እንደው ሲጨንቃቸው እንደዛ ያስቡ ይሆን? … እኔም እኮ እንዲሁ የምለው ጨንቆኝ ነው፡፡ በርዶኝ፡፡ ቅዝቃዜ፣ ቆፈን ይዞኝ ነው፡፡ በዛ ላይ መንገደኛ፡፡

ምድር ቅዝቃዜው ያልበረገው ሽር ጉድ በዝቶባታል፡፡ ብዙ የምትሸኛቸው ተጓዥ ሽማግሌዎች አሉ፡፡ እሷ ከመመለሷ በፊት ፊልሙን ካየሁባት ክፍል ወጣሁ፡፡ እንዳታየኝ ተጠንቅቄ ነበር፡፡ ወጥቼ ሮጥኩ፡፡ ሃሳቤ ቤተሰቦቼን ለማግኘት ነው፡፡ ግን ከግቢው ሳልወጣ እሷን አገኘሁዋት፡፡

“ወዴት ይሮጣሉ…?”…

“ወደ ቤተሰቦቼ …” ከቅዝቃዜው ጋር እየታገልኩ፡፡

“ለምን?”

“ልክሳቸው … ልበድላቸው እንደማይገባ ተሰማኝ፡፡”

“ቤተሰቦችዎንም በድለዋል?”

“አዎ…”…

“ታዲያ ሌሎች በሩቅ ያሉትን መቼ ሊክሷቸው ነው?”…

“እንጃ፡፡ የግድ ግን አንድ ነገር ማድረግ አለብኝ፡፡ ለዛ ነው ምሮጥ”

“የበደሏቸው ሰዎች ምን ያህል ይሆናሉ?”

“እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ እንደ ባህር ዳር አሸዋ፣ እንደሰማይ ከዋክብት ናቸው፡፡ መፍትሄ የለውም፡፡” እንኳንስ በዚህ ብርድ በዚህ ሽምግልና ይቅርና …

“እስቲ አስቡበት … የአምስት አመት ጊዜ ያለዎት መሰለኝ …” ብላኝ ሊሰናበቷት ከኔ ቀድመው ወደመጡት ሌሎች የሽማግሌ እንግዶች ሄደች፡፡

የአምስት አመት ጊዜ ቢኖር ምን ይጠቅማል? … እጆቼ ዝለዋል፡፡ ማንምም መርዳት አይችሉም፡፡ አይኖቼ ፈልገው ማግኘት አይችሉም፡፡ እግሮቼ ሮጠው ማምለጥ፣ አባሮ መያዝ፣ ዘሎ ማውረድ አይችሉም፡፡ በወጣት እና በጎልማሳ ጉልበቴ ያፈረስኩትን በስተርጅናዬ እንዴት ልገነባው እችላለሁ? በትኩስ ጉልበቴ አፈረስኩ … በበረደ ጉልበቴ እንዴት አድርጌ ልገንባ … እድሜን እንደጋቢ ተከናንቤያለሁ፡፡ ግን ብርድ እያስገባ ቅዝቃዜው ክፉኛ በርዶኛል፡፡ እንዲሁም ብርድ የሚጠራ ነው የመሰለኝ - እድሜዬ፡፡ ድንገት ከቆላ ወደ ወይናደጋ አካባቢ የተወሰድኩ አይነት፡፡ የተከናነብኩት የእድሜ ጋቢ አስጠላኝ፡፡ ደጅ የተደቀነ የዝናብ ውሃ ውስጥ የተነከረ ጋቢ እንደተደረበብኝ ነው የሚሰማኝ - በሽማግሌ ቆዳዬ ላይ፡፡ እድሜ ጸጋ ነው … የሚለው ነገር እወነት አልሆነልኝም፡፡ ከላዬ አውልቄ በጣልኩት በወደድኩ፡፡ ግን አይሆንም፡፡ በጊዜ ውስጥ ወደ ኋላ መመለስን ይጠይቃል፡፡ ያውም የኔን ጊዜ ብቻ ሳይሆን የበደልኳቸውንም ሰዎች ጊዜ ወደ ኋላ መመለስ፡፡ ከዛ የሆነውን ሁሉ በላጲስ አጥፍቶ ሌላ ታሪክ መጻፍ ወይም መስራት፡፡ ቢቻል ነበር …

“ቅዝቃዜው ምን ያህል ላይ ቢሆን ነው … ያንዘፈዝፋል”… አልኳት እየተጣደፈች በአጠገቤ ወደ ሌሎች ስታልፍ፣ ስትንከባለል - ምድር፡፡

እሷም ተጐሳቁላለች፡፡ ክብ ፊቷ ማድያት ለብሷል፡፡ አረቄ ወይም ሌላ መጠጥ አብዝታ እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡ ምናልባት በጉንጭዋ የሚወርደውን እንባ አብዝታ ይሆናል፡፡ የሚወርደው ፈሳሽ ብዛት የጉንጭዋን እውነተኛ ቀለም ለውጦታል፡፡ የሷ እንቧ መጠን ለቅዝቃዜው አስተዋጽኦ ይኖረው ይሆን …. እኛንስ እሺ እሷ ታሰናብተናለች … የሷ ነገር እንዴት ነው? እንደዚህስ ማን ያስተዛዝናታል?

“ምንዎን ነው የሚበርድዎ …” ዝም ብላኝ ልትሄድ ፈልጋ ግን አላስችል ብሏት መለስ ብላ ጠየቀችኝ፡፡

“ሁለመናዬን፡፡ በተለይ ውስጤን ነው”

“እዚህ በአየር ላይ የሚነፍሱት እውነትና ፍቅር ናቸው … የእድሜ ማምሻ ላይ የሚረጩት ማለቴ ነው፡፡ ካለመዷቸው አይመቹም … የሚሰማዎን ስሜት የሚወስነው በእድሜ ዘመንዎ ከእነርሱ ጋር ምን ያህል ተለማምደዋል የሚለው ነው … ሰውነትዎ ውስጥ የተጠራቀመው … የኖሩት ኑሮ ነው የሚወሰነው” ብላኝ ሄደች፡፡

እንዲህ ነው እንዴ ነገሩ? አንድ አማራጭ አለኝ፡፡ ይህንን አምስት አመት ማሳጠር፡፡ አምስት አመት ሙሉማ በዚህ መልኩ መቀጠል አልችልም፡፡ የእግር እሶት ነው የሆነብኝ፡፡ እንደውም ቁርጡ የታወቀው እሳት ይሻላል፡፡ ገንዘብ አብሮህ አይቀበር፡፡ ዝና አብሮህ አይቀበር፡፡ በመጨረሻ ሰአት እውነት እና ህሊና ናቸው የሚያፈጡብህ፡፡ ከፎቅ ላይ መወርወር ወይም መኪና ጎማ ውስጥ መግባት ቀሪውን ቆይታዬን ለማሳጠር ያለኝ አማራጭ ነው፡፡ በስተርጅና፡፡ አይገርምም? … ለሱስ ቢሆን ጉልበት ከየት ተገኝቶ፡፡ ግን ሌላ ምን አማራጭ አለ? … ተረት ተረት የሆነ ኑሮ …

ባለዜማ ድምጽ ሰማሁ … ሃብት፣ ዝና፣ ክብር፣ ገንዘብ ሁሉ ሃላፊ፣

የዚህ አለም ውበት ሲያረጅ አብሮ ጠፊ፣

እንደ ጤዛ ታይተው ፈጥነው ይረግፋሉ፣

ሳይታሰብ ድንገት ከእጅ ያመልጣሉ፡፡

ቅዝቃዜው በረታብኝ፡፡ በስተርጅና፣ በሽምግልና ብርታትና ጽናት የሚሰጡ ነገሮች ምንድናቸው? … ምነው ከዘመናት በፊት በወጣትነቴ ተገንዝቤው፣ ትኩረት ሰጥቼው ቢሆን-ሃሳቡን፡፡ ማለቴ ይህንን ሃቅ … ለሃብት ስል፣ ለክብር ስል፣ ለዝና ስል የሆነውን ሁሉ አደረግሁ፡፡ እድሜዬን በነሱ ቀየርኩ፡፡ ሰዎችን በነሱ ለወጥኩ፡፡ ልብ አድርጌ ተነፈስኩባቸው፣ ደሜ ሆነው ደመቅኩባቸው … ዋርካ አድርጌ ተጠለልኩባቸው፡፡ አሁን ግን በወትሮ ማንነታቸው ከአጠገቤ የሉም፡፡ ዞር ብዬ የመጣሁበትን የህይወት መንገድ በሽማግሌ አይኖቼ ሳይ እንደሚያሳፍር የበኩር ልጅ ነው የሆነብኝ፡፡ አንገቴን ደፋሁ፡፡ ምናልባት የሚቀጥለው አለም “እጅ ከምን?” ይለኝ ይሆን … የምለውን በማጣት እንዳሁኑ አንገቴን ደፍቼ መንቀጥቀጥ - ምናልባት የኔ ምላሽ፡፡ አይ የሽማግሌ ጣጣ!

ከምትቸኩልበት ቆም ብላ በሃዘኔታ አየችኝ፡፡ አንድ ቀጭን የማይመች መንገድ፤ ጨለማና ጭቃማ፤ አባጣ ጎርባጣ ቀጭን መንገድ - የምጋተር ሽማግሌ ሰው ሳልመስላት አልቀረሁም - ከቅዝቃዜ የማያስጥል ኮተት የደረብኩ፡፡ ከጭቃው መንገድ ላይ እጄን ይዛ ብታሻግረኝ … ምናለበት? የሽማግሌ ቆዳዬ ተኮማትሯል፡፡ የሰፋበት ቆዳዬን የያዘው የሰውነቴ አጥንት ይርገፈገፋል፡፡ በዛ ላይ ቅዝቃዜው በአጥንቴና በቆዳዬ መሃል ባለው ክፍት ቦታ ካልገባሁ ይላል፡፡

“አንድ ነገር ልምከርዎት…” … አይኖቹዋ ውስጥ የእናትነት ፍቅር አለ፡፡

“እሺ ምን” እናቴ …” ላጲስ አግኝታልኝ ይሆን?

“ቂም የያዙበት ሰው አለ?...”…

“ማለት?...”

“ለምሳሌ በድሎኛል ብለው የሚያስቡት፡፡ ሌሎች በእርሶ እንዳዘኑ፣ እርሶ ደግሞ ያዘኑበት…”

“እኔ በብዙ ሰው ህይወት ቀልጄያለሁ፡፡ በኔ የቀለዱ ደግሞ ሶስት ሰዎች አሉ፡፡ እነሱ በዚህ አሰቃቂ ቦታ ከኔ ጋር ቆመው ባይ ሃዘኑም አይሰማኝ፤ ይህ የቆምኩበት ቅዝቃዜ እንኳ የእጄ ነበር፡፡ ክፋትንም የተማርኩ ከነሱ ነው … እነሱ በኔ ነብስ ላይ መርዝ ረጩ፤ እኔም ከውስጤ አውጥቼ ሌሎች ላይ በብዙ እጥፍ አርከፈከፍኩት … የሁሉ መነሻ እነሱ ስለሆኑ እዚህ ቦታ አጠገቤ ቢቆሙ ቢያንስ ፍትህ ተገኘ እል ነበር…”

“ይሄማ ተያይዞ ገደል ነው”

“ታዲያ ምን ላድርግ ልጄ? … ብትጠይቂኝ እኮ ነው”

“ይቅር ይበሏቸው”

“ማንን? ማንን እናቴ? …” የበለጠ ብርዱ አንዘፈዘፈኝ

“እነሱን…”…

“እነዛን ከይሲ?”

“አዎ”

“እኮ ከዛስ?...”

“ከዛማ የአየሩን ሁኔታ ያዩታል…”

ብርዱ ስላርገፈገፈኝ ከአንገቴ ዝቅ አልኩ፡፡ የበደሉኝን ሰዎች እያንዳንዳቸውን አሰብኩ፡፡ ማሰብም አላስፈለገኝ፡፡ አይኖቼ ውስጥ ጎጆ የቀለሱ ይመስል አይኖቼን ሞሉት፡፡ ልቤ መላልሶ አቃረኝ፣ አጥወለወለኝ፡፡ ፊቴን ከሞሉት ከነሱ የተነሳ ልቤ ትቶኝ ሊበር ፈለገ፡፡

አቅቶኝ ቀና ብዬ አየሁዋት፡፡

“ይበሉ አባባ”… አይኖቹዋ ውስጥ የሚታየው እናትነት ደግሞ በተራው አሸነፈኝ፡፡ እንደምንም ድጋሚ አቀረቀርኩ፡፡ ጉልበት አግኝቼ አልኳቸው “ይቅር ለእግዚአብሔር” ከዛም አየሩን ለመፈተሽ በጉጉት ቀና አልኩ …

 

 

 

Read 3208 times Last modified on Saturday, 01 September 2012 11:33