Sunday, 13 June 2021 00:00

የዘመናዊ እርሻ ፋና-ወጊው ግለ-ታሪክ!

Written by  አብዲ መሐመድ
Rate this item
(1 Vote)

  "--ለዚህም ይመስላል ረዳት ፕ/ር በቀለ መኮንን፤ ግለ-ታሪክ ሲበዛ የቀስቃሽነት ኃይል አለው፡፡ አሁኑኑ ተነስ-ተነስ፤ በል-በል ያሰኛል፡፡ ያስገርማል፤ የሰውን ልጅ ስራ በሌላ ተጨማሪ መነፅር ለመመልከትም ይጠቅማል፤ የሚሉን፡፡--"
              
          ረዳት ፕሮፌሰር በቀለ መኮንን በቀድሞ ‹‹አዲስ ጉዳይ›› መጽሄት ላይ ስለ ‹‹ግለ-ታሪክ›› አስፈላጊነት ባሰፈሩት አንድ መጣጥፋቸው፤ ‹‹እባካችሁ›› ሲሉ ይማፀናሉ፡፡ "... እባካችሁ፤ ታሪክ ዝጎ ተረት እንዳይሆን ሰው ሆነን የተፈጠረን ሁሉ ውሎአችንን እንፃፍ፤ የሁላችንም ህይወት የራሱ ፈላጊና ዋጋ ማግኘቱ አይቀርምና፡፡"
እርግጥ ነው ግለ-ታሪክ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች አሉት፡፡ በአንድ ሀገር የተሻለ ‹‹ማህበረሰባዊ ለውጥ›› ለማምጣት ግለ-ታሪኮች ተጠራቅመው የሚፈጥሩት ተጽዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ ብዙ ታላላቆቻችን አቅሙና ጊዜው እያላቸው ግለ ታሪካቸውን ላለመፃፍ የሚያሳዩት ዳተኝነት፣ በራሱ ተጨማሪ ጥናት የሚጠይቅ ጉዳይ ነው። ይህንን ማህበረሰባዊ ኪሳራ የሚያካክሱ አልፎ አልፎም ቢሆን ያጋጥማሉ፡፡ ለአብነት የጉዳዩ መክፋት አሳስቧቸው ይመስላል..ከራሳቸው ባሻገር የሌሎችንም ግለ-ታሪክ በመፃፍ የቤት ስራቸውን በአግባቡ ሰርተው፣ የሚያስደምሙን ጥቂት የማይባሉ ግለሰቦች አሉን፡፡ ከነዚህም ሰዎች መካከል ሌላው ተጠቃሽና ብርቱ ሰው ዶ/ር ጌታቸው ተድላ አንዱ ናቸው፡፡ እምብዛም አያጋጥመኝም እንጂ ወጣ-ባሉ የሙያ-ዘርፎች ውስጥ ተሰማርተው ሀገር እና ህዝብ ያገለገሉ ግለሰቦችን ታሪክ ማንበብ ከሚያስደስታቸው ተደራሲያን መካከል አንዱ ነኝ፡፡ ባለፈው ሰሞን ለግማሽ ክፍለ-ዘመናት በመሃል መርካቶ የሰዓት ንግድን ያሳለጡ፣ የዚህ ዘርፍ ፈር-ቀዳጅ ሚና የነበራቸውን ብርቱ ሰው፣ የሀጂ ኡመር ሰይድ የህይወት ጉዞ የሚያስቃኘውን “የጊዜ ነጋዴው ግለ-ታሪክ” የተሰኘ መጽሐፍ በአጋጣሚ አንብቤ መደሰቴን አስታውሳለሁ፡፡
ከሰሞኑ ሲቀናኝና ተደሰት ሲለኝ ነው መሰለኝ፣ እጄ ከገቡ ጥቂት ‹‹ግለ-ታሪኮች›› መካከል ዶክተር ጌታቸው ተድላ የፃፉት የአባታቸው ታሪክ የሆነው ‹‹ተድላ አበበ፤ የዘመናዊ እርሻ ፋና-ወጊ›› በሚል ርዕስ የተሰናዳ ግሩም ግለ-ታሪክ ነው፡፡ ዶክተር ጌታቸው ያባታቸውን ታሪክ ከመፃፋቸው ቀደም ብሎ የራሳቸው በሁለት ክፍል የተሰናዳ ግለ-ታሪካቸውን ለንባብ አብቅተው ነበር፡፡(የህይወት ጉዞዬ እና ትዝታዎቼ በውጪ ሀገር ክፍል አንድ ፤ የህይወት ጉዞዬ እና ትዝታዎቼ በውጪ ሀገር ክፍል ሁለት) በተለይ እነዚህን ሁለት የህይወታቸውን ጉዞ የያዙ ስራዎች ካነበብኩ በኋላ ለኚህ ግለሰብ ያለኝ ግምትና- አክብሮት ባያሌው ጨምሮ ነበር፡፡ በዚህ ስሜት ውስጥ ሆኜ ነው እንግዲህ ይሄንን የአባታቸውን ታሪክ የያዘውን መጽሐፍ ያገኘሁት፡፡ ..ዶክተር ጌታቸው እንደ ራሳቸው ግለ-ታሪክ ሁሉ የአባታቸውንም የኑሮ-ገድል ጥንቅቅ አድርገው እያዋዙ፣ ለዛ ባለው ውብ ‹‹የንግግር ቋንቋ›› ከትበውታል ለማለት ያስደፍራል፡፡ ...ሰውዬው ታሪክ ዘጋቢ ብቻ አይደሉም፤ የእለት ማስታወሻን በማስፋት ለግለ-ታሪክ ምንጭነት እንደ-ግብአት መጠቀምንም ተክነውበታል፡፡..ጌታቸው እያንዳንዷን ቅንጣት ገጠመኝ በመመዝገብና በማስታወስ ረገድ ያላቸው ችሎታ የሚደንቅ ነው፡፡ ..ይሄንን ደግሞ በራሳቸው ግለ-ታሪክ ውስጥም በበቂ ሁኔታ ያሳዩ ይመስለኛል ..በአባታቸው ታሪክ ውስጥም ደግመው አሳይተዋል፡፡ ጌታቸው በዚህ የአባታቸው ግለ-ታሪክ ውስጥ..አቶ ተድላ ያሳለፉትን የስራ፣የማህበራዊ ኑሮና ሌሎችንም ገጠመኞች መዝግበው፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር ያደረጓቸውን ቁም-ነገር አዘልና አንዳንዴም ቀልድ የተቀላቀለበት ምልልሶች በሚገባ ከትበው፣ አባታቸው የ‹‹ፎቶ ያህል›› ፍንትው  ብለው እንዲታዩ የላቀ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ..ሁላችንም የቤተሰባችንን ታሪክና-ገጠመኝ ጠብቀን በማቆየት ለሌሎች የማስተላለፍ ‹‹የትውልድ አደራ›› እንዳለብን ቆም-ብለን እንድናስብ የሚያስገድደን መጽሐፍ ነው፡፡ እኔን በተለይ ከአባቴ ጋር ያሳለፍኩትን እንደ-ዋዛ የምቆጥራቸውን ብዙ ትዝታዎች መለስ ብዬ እንዳስታውስ አንቅተውኛል፡፡ ..የአንድ ግለ-ታሪክ ትልቁ ሚናም ይሄ ይመስለኛል..በዚህ ረገድ ጌታቸው ያቀረቡልን የአባታቸው ታሪክ ግቡን መትቷል ማለት ይቻላል፡፡ በርግጥ አቶ ተድላ በእርሻው ዘርፍ ግንባር ቀደም ‹‹ፋና-ወጊ›› ይሁኑ እንጂ ከዚያ ጎን ለጎን ለቤተሰቦቻቸው ህይወት የከፈሉት መስዋዕትነት በቀላል የሚገመት አይደለም። ደርግ በተሳሳተ ፖሊሲዎቹ የአቶ ተድላን ራዕይና ህልም ቢያጨናግፍም፣ እሳቸው ያሳዩት ‹‹ሆደ ሰፊነትና-ጽናት›› ለማንም አርአያና-ተምሳሌት መሆን የሚችል ነው። ለዚህም ይመስላል ረዳት ፕ/ር በቀለ መኮንን፤ "ግለ-ታሪክ ሲበዛ የቀስቃሽነት ኃይል አለው። አሁኑኑ ተነስ-ተነስ፤ በል-በል ያሰኛል፡፡ ያስገርማል የሰውን ልጅ ስራ በሌላ ተጨማሪ መነፅር ለመመልከትም ይጠቅማል፡፡" የሚሉን፡፡ ጌታቸው ይሄንን የአባታቸውን ታሪክ በመፃፍ ከልጅ የሚጠበቀውን ‹‹ውለታ›› በመመለስ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል፡፡ አባታቸው በህይወት ኖረው ይሄንን የልጃቸውን ስራ ቢያዩ ምን ያህል ሊረኩ እንደሚችሉ መገመት አይገድም። ነፍሳቸውንም አሳርፈዋታል፡፡ በትውልዱ ውስጥ በብዙ መልኩ እንዲታወሱና እንዲዘከሩ ‹‹ትልቁን ስራ›› ሰርተውላቸዋል። ከእነ ፊታውራሪ አመዴ ለማ፣ከእነ-በቀለ ሞላ፣ከእነ-ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም እኩል.. አቶ ‹‹ተድላ አበበን››ም በኢትዮጵያ በዘመናዊ እርሻ ‹‹ፈር - ቀዳጅነታቸው›› እና በሌሎችም ታላቅ ተግባሮቻቸው የኔ-ትውልድ ምንጊዜም ቢሆን አይረሳቸውም፡፡ በርግጥ አቶ ተድላ አበበ የሁላችንም አባት ናቸው። ልጃቸው ዶክተር ጌታቸው፣ እኚህን አባት፣ የህይወታቸው ገጽ ላይ በነፃነት እንድንመላለስ አስችለውናልና ለሳቸው ‹‹ረጅም እድሜን ከጤና›› ጋር አለመመኘት አይቻለንም። ከላይ በመግቢያዬ የጠቀስኳቸው ረዳት ፕሮፌሰሩ ለመውጭያዬም የሚሆን የሁላችንም ግለ-ታሪክ ለሌላኛችን ምን-ያህል አስፈላጊና ጠቃሚ ስለመሆኑ እንዲህ ሲሉ በጽሁፋቸው  ያስረግጣሉ!
... "የሰው ልጅ ግለ-ታሪኮች ወይም ባዮ-ግራፊዎች፤ ልክ እንደ-አንድ የምግብ አይነት ራሳቸውን የቻሉ ጣፋጭ ‹‹ጣዕምና ለዛ›› አላቸው፡፡ እውነተኛ ታሪኮች ከመሆናቸው በላይ እንደ ማንኛውም አንባቢ ስጋ የለበሱ ሰዎች የሆኑት፣ያደረጉት ድርጊት በመሆኑ ለራሱ ለ‹‹ሰው ልጅ›› ከምንም በላይ ጣፋጭና ተወዳጅ ይመስለኛል፡፡"
በዚህ ድንቅ ግለ-ታሪክ እልፍኝ ውስጥ ስንታደም፣ የአቶ ተድላ የአንድ ቀን ውሎ በሚያዝናና ሁኔታ እየተዋዛ እንዲህ ሰፍሮ እናገኘዋለን፡-
"…ገበሬው ተድላ ከእርሻ ኃላፊዎቻቸው ጋር ለመወያየትና የዘወትር ስራቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ከመኝታቸው የሚነሱት ገና ጎህ-ሳይቀድ ከሌሊቱ 11፡00 ሰዓት ባሉት ጊዜያት ነው፡፡ እንቅልፋም ሁሉ ተነሱ እንጂ፤ ሃያ አራት ሰዓት ነው እንዴ የምትተኙት? ይላሉ፡፡ ለብዙ አመታት ከጎናቸው ሳይለዩ አብረዋቸው የኖሩት ባለቤታቸው፤ ኤጭ! እንግዲህ ጀመራቸው፤ ብለው እያጉረመረሙ ጩኸታቸውን ላለመስማት አንሶላቸውን ይሸፋፈናሉ፡፡ አቶ ተድላም ባለቤታቸው የተበሳጩበት ነገር በደንብ እየገባቸው እያለ፤ ምን ሆነሻል? ይሏቸዋል፡፡ እባክዎን ይተዉ፤ ጥሩ አይደለም፤ እራስዎን እንቅልፍ እምቢ ቢልዎት ሌላውን ሰው እንቅልፍ ማሳጣት አያስፈልግም፡፡ ገና እኮ አልነጋም፣ሌሊት ነው፤ ብለው ለማስረዳት ይሞክራሉ፤ ወይዘሮ ንጋቷ፡፡ እንዳንቺ እኮ በአለም ላይ የደላው የለም ‹‹ንጋት›› ሰማሺኝ አንቺማ ተኚ ብለው ለማግባባት ይሞክራሉ፡፡
አለመንጋቱን ከተረዱ በኋላ አንዴ ሲያፋጩ አንዴ እንደ-መዝፈን እየቃጣቸው፣ አንዳንዴም ያረጁ ጋዜጦችንና አመተ-ምህረታቸው ያለፈባቸውን ወረቀቶች እያገላበጡ ለሊቱን ለመግፋት ይሞክራሉ.. አንዳንዴ ንጋቱ ሲርቅባቸው ‹‹ብሩ ይሙት፤ መጽሐፍ ማለት ይህ ነው›› ብለው ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ሀይለ ስላሴ በሚል ርዕስ በአቶ ተክለ-ፃዲቅ መኩሪያ የተዘጋጀውን የኢትዮጵያ-ታሪክ ሲያነቡ ይቆያሉ፡፡ማንበቡ ሲደክማቸው ወይም ሲሰለቻቸው፤
ያገር ፍቅር ትዝታው፣ ትዝታው
አይረሳም ለሚያውቀው ለሚያውቀው -- እያሉ በጎርናና ጽምፃቸው ያንጎራጉራሉ!" ገጽ 30፡፡
በዚህ አንድ አመት ከግማሽ ወራት ውስጥ ብቻ ከሌሎች የሙያ ዘርፎች በተለየ በሙዚቃና በሙዚቀኞች ላይ ያተኮሩ የህይወት ታሪክን የያዙ መጻህፍት በተከታታይ ታትመው በስፋት ተነበዋል። ከእነዚህም መካከል የእዮብ መኮንን "የሬጌው ንጉስ"፣ የአሊ ቢራ.. "የምስራቁ ዋርካ"፣ የኤልያስ መልካ "የከተማው መናኝ" ይጠቀሳሉ፡፡ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ከዚሁ በተጓዳኝ እንደ ተድላ አበበ ያሉ በሌላ የሙያ-ዘርፍ ተሰማርተው ሀገራቸውን ብዙ ያገለገሉ፣ እንደ-ዋዛ የትም ተረስተው የቀሩ ካሉበት ወጥተው ልናውቃቸውና ልንማርባቸው፣ እውቅናም ልንሰጣቸው ይገባል እላለሁ፡፡


Read 1189 times