Tuesday, 15 June 2021 18:58

የ‘ማስኩ’ ነገር!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ… ሰኞና ሰኔ ሊገጥሙ ለትንሽ ተላለፉ አይደል! ለነገሩ ቀኖቹ ሁሉ ሰኔና ሰኞ ከመሰሉ ከራርመዋል፡፡
እኔ የምለው…እንዴት ነው ነገሩ…ቱባ ቱባዎች የምንላቸው ምን እየሆኑ ነው!…ለምንድነው ማስክ  የማያደርጉት! ይህን ሰሞንማ ነገርዬው ብሷል፡፡ በርካታ ሰው በሚገኝባቸው ዝግጅቶች ላይ አብዛኛው ሰው ማስክ ሳያደርግ የሚታየው፣ የማናውቀው ነገር አለ እንዴ?! ለሁሉም አርአያ መሆን የሚገባቸው ሰዎች እንዲህ ሆነው ስናይ “ሁዋት ኢዝ ጎይንግ ኦን?” እንላለና፡፡ ልጄ እንኳን እንዲህ ከባድ ሚዛኖቹ ማስክ ሳያደርጉ ጎን ለጎን ተቀምጠው፣ እንደልባቸው እየሆኑ ታይቶ ቀርቶ በየታክሲው ላይ “ለምን ማስክ አታደርግም!” ሲባል “ምን አገባህ!” የሚለው ‘ብሶት የወለደው፣’ ጉልበተኛ መከራ አብልቶናል፡፡ አታበሳጩና! ወይም ወጣቶቹ እንደሚሉት... ‘ሀርድ አትስጡና!’ ወይስ እናንተም... “ምን አገባችሁ?; ትሉናላችሁ፡፡
አንድ ሰሞን ነጋዴዎቹ በየመድረኩ "ለምንድነው የሀገር ውስጥ ምርቶቻችንን የማትሸምቱት" ብለው ሲቆጡን ነበር። እኔ የምለው... ራሳቸው የጣልያን ሙሉ ልብስ፣ የእንትን ሀገር ሸሚዝ፣ የእንትን ሀገር ጫማ ግጥም አድርገው ምን የሚሉት ‘ፓትሪየቲዝም’ ነው! 
የምር ግን ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…አንዳንድ አለቆች የእልቅናቸው ማሳያ… አለ አይደል… ሠራተኞቹን ‘ሀርድ መስጠት’ ይመስላቸዋል እንዴ! ስሙኛማ ዋነኛ የሥራ ኃላፊነታቸው ለሠራተኞቻቸው ‘ሀርድ መስጠት’ የሚመስላቸው አለቆች አይገርሟችሁም! በቃ ዋናው ነገር ሠራተኛው የሀላፊነት ስሜት ተሰምቶት በሥራው እንዲተጋ ሳይሆን ‘ፌርማቶሪነት’ ተሰምቶት (ቂ...ቂ...ቂ...) ለእነሱ ወገቡ ሊቀነጠስ እስኪደርስ እንዲሰግድ፡፡ ኸረ ልክ አይደለም! ይሄ እኮ እንደ ድቡልቡል ማስቲካ ዘመን ያለፈበት ‘ማኔጅመንት ስታይል’ ነው! (አዎ፣ ለጠቅላላ እውቀት ያህል... "ድቡልቡል ማስቲካ የሚባል ነገር ነበር" እና በድቡልቡል ማስቲካ የተሠራው ‘አድቬንቸር’ አሁን ማህበራዊ ሚዲያዎቹና ስማርትፎኖቹ ሁሉ ተደማምረው እየሠሩ ካሉት በብዙ እጥፍ የበለጠ ነበር ለማለት ነው፡፡ እነ እንትና... አንድ ቀንማ፣ ያ ሁሉ ‘አድቬንቸር’...  አለ አይደል... የሆነ ተከታታይ ፊልም ምናምን ሊሠራበት ይገባል፡፡)
እናላችሁ...አንድ ጊዜ የሆነ መሥሪያ ቤት በአለቅነት የተሾሙ ትኩስ አለቃ ነበሩ አሉ…የሆነ እንደ ባላባትነት ነገር የሚያደርጋቸው ሰውዬ፡፡ ታዲያ…በማን እንደተሾሙ፣ እንዴት እንደተሾሙ፣ በምን መስፈርት እንደተሾሙ የበታች ሠራተኛ ሲንሾካሾክ ይሰነብታል፡፡
“ሰውየው እላይ በጣም ትልቅ ሰው አላቸው አሉ፡፡”
“ዘመዶቻቸው ጠፍር ቀጥ ማድረግ የሚችሉ ናቸው፡፡ እነሱ ናቸው ያሾሟቸው ይባላል፡፡”
“በፊት በነበሩበት መሥሪያ ቤት ሴቱን ሁሉ ጨርሰውት ጉምጉምታው ሲበዛ ነው፣ እስቲ  ለትንሽ ጊዜ ከዓይን ራቅ ይበል በሚል እዚህ ያመጧቸው አሉ፡፡”
እናላችሁ... ወንበራቸው እንኳን በቅጡ ሳይሞቅ ማእበሉን ለቀቁት አሉ…የቅጣት ደብዳቤዎች ማዕበል፡፡ ብቻ ማንም ይሁን ማን “እከሌ እንዲህ አደረገ!” “እከሊት እንዲህ ፈጸመች!” ከተባለ ሳያጣሩ፣ ሁለቱን ወገን ሳያዩ የቅጣት ደብዳቤ ማከናነብ ነው አሉ፡፡ እናላችሁ… ከሚገባው በላይ አበዙት መሰለኝ መንፈቅም ሳይደፍኑ አንስተው ሌላ ቦታ ወሰዷቸው፡፡ ለነገሩማ እንደ ደንቡ ከሆነ ከቅጣት በፊት የቃል ማስጠንቀቂያ፣ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ምናምን የሚባሉ ነገሮች ነበሩ፡፡ እንደልባቸው ለሚሆኑ ቦሶች ግን እንዲህ ብሎ ነገር የለም፡፡ ቅንነት ካለ ላለመስማማት መስማማት ይቻል ነበር እኮ!
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል...ይሄ ላለመስማማት መስማማት ብሎ ነገር የሆነ፣ የጎደለው ነገር ያለ አይመስላችሁም! "ዘ ቦስ" ካልወደደ አልወደደም ማለት ነዋ! በቃ፣ ሳዮናራ! ላለመስማማት መስማማት፣ ጉዳዩን በጠረዼዛ ዙሪያ መፍታት ብሎ ነገር የለም፡፡
“ጌታዬ፣ ይሄን ጉዳይ በጠረዼዛ ዙሪያ ብንፈታው ጥሩ ይመስለኛል፡፡”
“እውነት! እንዴት አይነት የተቀደሰ ሀሳብ አመጣህ እባክህ!”
“አዎ፣ ጌታዬ፡፡ ነገሩን በሰላም ለመጨረስ…”
“በቃ በቃ! ምክር ትፈልጋለህ!”
“እንዴታ ጌታዬ! ከእርሶ የሚመጣ ምክር ለመቀበል ዝግጁ ነኝ፡፡”
“በጠረዼዛ ዙሪያ የሚፈታ የታሰረ ነገረ ስለሌለ፣ ጓሮህ ሂድና ያሰርካት ፍየል ካለች እሷን ፍታ!” (ኪሎ ሥጋ ሰባትና ስምንት መቶ ብር በገባበት በፍየል ይቀልዳሉ እንዴ!)
እናማ... ላሊጋ ዲቪዥን ውስጥ ያላችሁ ያለ ማስክ አዳራሽ እየሞላችሁ አታበሳጩና!
ስሙኛማ…  ብዙዎቻችን ግን እኮ እንዲህ ነን፡፡ ሌሎች እንዳያደርጉ የምንሰብከውን እኛ ግን ያንኑ ነገር ደግመን ደጋግመን ስናደርገው እንገኛለን፡፡ …አለ አይደል…“በመጠጥ ደስታ ይገኛል ብላችሁ...” የምትለውን ከዳር ዳር ወጥተናት … ከምሽቱ አምስት ሠዓት ላይ ጎረቤት በር አንኳኩቶ “ጥምብዝ ብሎ መሄድ አቅቶት መንገድ ላይ አግኝተነው ነው…” ብለው ሲያስረክቧችሁ ይታያችሁማ!
እናማ… ባለስልጣኖች ማስክ ሳታደርጉ በየቦታው እየታያችሁ አታበሳጩንማ!
አንድ ወዳጅ አለን...ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ተጥዶ ውሎ ተጥዶ የሚያመሽ፡፡ እናላችሁ…ግን የእሱን ያህል መካሪ ማግኘት ያስቸግራል፡፡
“ፌስቡክ ላይ በቀን ከሠላሳ ደቂቃ በላይ ማጥፋት አያስፈልግም፡፡;
“አንተ ሃያ አራት ሰዓት አፍጠህ ትውልበት የለም እንዴ!” (እዚህ ላይ ነው ጨዋታው!)
“እኔ እኮ መጥፎነቱን እንዲህ ስለማየው ነው ለእናንተ እየመከርኩ ያለሁት፡፡ ካላየሁ እንዴት አድርጌ ልነግራችሁ እችላለሁ!”
ግዴላችሁም “ብልጥነትን” ሊያገኝ አይደለም በሰፈሯ ያላለፍነው ሁሉ ነን ዘንድሮ ብልጦች የሆንነው፡፡ (የፈለጉትን ነገር መሆን የሚቻልበት ዘመን!) ወይንም ብልጥነትን አስገድደን ልናግታት እየሞከርን ያለነው!)
“ተው እንጂ፣ ቀኑን ሙሉ ‘ቡአ የሚያስወርድ’ የዩቲዩብ ቪዲዮ ስታይ የምትውለው! አንድ ሁለቴ ካየሀቸው አይበቃህም እንዴ!”
“እዚህ ላይ ነው የማይገባችሁ፡፡ በየቀኑ የስድቡ አይነት ስለሚለዋወጥ ምን እያሉ እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ከዛ በኋላ ነው ሰዉን ማስጠንቀቅ የሚቻለው፡፡” (ይልቅ ያገትካትን ‘ብልጥነት’ ሌላ ነገር ሳይከተልህ ልቀቃት! አሀ… ተራችንን አታሳልፍብና! ቂ…ቂ…ቂ…)
ስሙኝማ… ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ …ይህ ማህበራዊ ሚዲያ ምናምን የሚሉት ነገር… ሁላችንም…አለ አይደል…“ምን አይነት ሰው ነው እንደዛ አይነት ነገሮችን የሚያየው!” እንላለን፡፡ ብዙዎቻችን ግን ራሳችን “ምን አይነት ሰዎች ናቸው!” የሚባሉት ውስጥ ነን፡፡ ልክ ነዋ…  እኛ ባንገባበት ያ ሁሉ መቶ ሺህ ‘ቪው’ እኮ ከባዶ አየር ዱብ የሚል አይደለም፡፡
እናማ… ላሊጋዎች፣ ማስክ ታደርጉ እንደሁ አድርጉ! አታበሳጩንማ!
“ስማ…ዩቲዩብ ላይ እንትና ትናንት የለቀቀውን ቪዲዮ አየኸው?”
“አላየሁትም፡፡”
“አትለኝም! እንዴት ነው የማታየው?”
“እኔ እንደዛ አይነት ነገር ካየሁ ቆየሁ። ዓመት፣ ዓመት ተኩል ባያልፈኝ ነው! ዩቲዩብ፣ ፌስቡክ የሚባሉ ነገሮች እርግፍ አድርጌ ነው የተውኩት፡፡”
“አመለጠህ ነው የምልህ! ማምለጥ የማይገባው ነገር አመለጠህ፡፡”
“ይህን ያህል …የካንሰር መድሀኒት አገኘሁ አለ እንዴ!”
“ቀልዱን ተውና፣ የሆነውን ልንገርህ፡፡ እነ እንትናን እንዳይሞቱ፣ እንዳይሽሩ አድርጎ ልክ ልካቸውን ነው የነገራቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ሰው ቀና ብለው የሚያዩም አይመስለኝም!”
“እናንተ ልጄ፣ ሥራ ስለፈታችሁ ነው፡፡ እኛ እንደ እናንተ አልደላንም፡፡”
“ስለማትከታተለው ነው፡፡ እዚህ ሀገር የሚሠራውን ጉድ እኮ ነው የሚያፍረጠርጠው፡፡ የዛሬ ሳምንት እነ እንትና ስለሠሩት ጉድ ያወራውን ብትሰማ ኖሮ፣ ሳትውል ሳታድር ልብስህን በፌስታል ቋጥረህ ወደ ናሚቢያ በእግርህ ታቀጥነው ነበር፡፡” (ደቡብ አፍሪካ ቦታ ሞላ እንዴ?!)
“አይ እነሱ ላይ በጣም ነው ያበዛው! እኔ የሆሊዉድ ፊልም የሚተርክ ነበር የመሰለኝ። ፊክሺን ቢጽፍ ይሻለው ነበር፡፡” (አንድ ጊዜ፣ ‘ታይምአውት!’ ፌስቡክና ዩቲዩብን እርግፍ አድርገህ ነው የተውከው ወይስ እቅፍ አድርገህ ነው የያዝከው!)
እናማ... ይሄ ማስክ ማድረጉ ላይ እንደልብ የመሆኑ ነገር....ሁሉም ሥራ የሚሠራው በእንደዛ አይነት ነው እንዴ!
እናማ… ላሊጋዎች፣ ማስክ ታደርጉ እንደሁ አድርጉ! አታበሳጩንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1750 times