Print this page
Saturday, 01 September 2012 11:19

ዲጂታል የባክቴሪያ መግደያ የፈጠረው የቡታጅራ ወጣት

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

“ውስጤ ጀመርክ እንጂ አልጨረስክም፤ ብዙ ይቀርሃል፤ አስብ” ይለኛል

ዩኒቨርሲቲ ምንድነው የተማርከው?

በማኔጅመንት ነው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 6 ኪሎ ካምፓስ በ2000 ዓ.ም (በሚሊኒየሙ ዋዜማ) የተመረቅሁት፡፡

የፈጠራ ችሎታ እንዳለህ በምን አወቅህ?

ብዙ ሰዎች ልዩ ችሎታ እንዳላቸው የሚረዱት በተለያየ መንገድና አጋጣሚ ነው፡፡ አንዳንድ ሰው ፊልም ሲመለከት ወይም ሬዲዮ ሲያዳምጥ በውስጥ የሚያስደስተው ነገር ይኖራል፡፡ ያ ማንነቱ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሁልጊዜ ግን ላይሆን ይችላል፡፡ የሚያስደስተውንና የሚማርከውን ነገር መሆንና ማድረግ ይፈልጋል ማለት ነው፡፡ የእኔም እንደዚያው ነው፡፡ አልሞከርኩትም እንጂ የፈጠራ ችሎታ በውስጤ ነበር ማለት ነው - ስሞክረው ግን ወጣ፤ ማንነቴን አገኘሁ፡፡

እንዴት ነው ፈጠራ የጀመርከው?

እንደተመረቅሁ የቢሮ ሥራ በመፈለግ ጊዜዬን ማባከን አልፈለግሁም፡፡ መንግሥትም ሥራ ፈጣሪ እንጂ ሥራ ጠባቂ አትሁኑ አይደል የሚለው፡፡ በዚህ መሠረት ሥራ መናቅና ማማረጡን ትቼ፣ የቤተሰብ ወፍጮ ቤት ስለነበር እዚያ ገብቼ ማስፈጨት ጀመርኩ፡፡

የወዳደቁ ብረታ ብረት ከየመንደሩና ከየመንገዱ እየለቃቀሙ ለ“ቆሮያለሽ” (ቆርቆሮ ያለሽ) የሚያስረክቡ ልጆች አሉ፡፡ “ቆሮያለሾች” ደግሞ የራሳቸው ሚዛን አልነበራቸውም፡፡ ስለዚህ እኛ ጋ እያስመዘኑ ነበር የሚረከቡት፡፡ “እኔስ ለምን ትንሽ ጥቅም አላገኝም?” በማለት አሰብኩና፣ ከልጆቹ ብረታ ብረቶቹን አንዱን ኪሎ በ50ሳ. እየገዛሁ 20ሳ. አትርፌ ለቆሮ ያለሾች በ70 ሳንቲም ማስረከብ ጀመርኩ፡፡

ያን ሥራ ስትጀምር ካፒታልህ ምን ያህል ነበር?

በመጀመሪያው ቀን ሁለቱን ኪሎ በአንድ ብር ገዝቼ 40ሳ. ነበር ያተረፍኩት፡፡ ዋናውን ሥራዬን እየሠራሁ እንደ ቀልድ በጀመርኩት የብረት ግዥ የማገኘው ሳንቲም ስለጣመኝ ቀጠልኩበት፡፡ በሳምንቱ በፊት ከነበረኝ ጋር ተደምሮ 500 ብር ሆነልኝ፡፡ በዚያን ወቅት ተበላሽቶ የተቀመጠ የወፍጮ ዲናሞ ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ ያንን ዲናሞ “ገንዘብ ሳገኝ ኮፐር (መዳብ) ገዝቼ አሠራለሁ” የሚል ሐሳብ ነበረኝ፡፡

የዲናሞው ብልሽት የተጠቀለለበት ሽቦ (መዳብ) መቃጠል ነው፡፡ ያኔ ሽቦው እንዳሁኑ ውድ አልነበረም፡፡ የተቃጠለውን መዳብ አንስቼ በ500ው ብር አዲስ ገዛሁና ጠቀለልኩበት፡፡ ስሞክረው ያለ ምንም ችግር ሠራ፡፡ በጣም ደስ አለኝ፤ ሞራሌ ተነሳሳ፡፡ ዛሬ ለደረስኩበት ደረጃ መነሻ ካፒታሌ እንግዲህ ያቺ 500 ብር ናት፡፡

ከዚያስ በኋላ ምን አደረግህ?

ያ ዲናሞ በአንድ ጊዜ ሙከራ በመሥራቱ ተደሰትኩ አይደለም፤ ሰከርኩ ማለት ይቻላል፡፡ ይህቺን ፍንጭ ሲያገኝ በውስጤ ያለው ስሜት “በል እንጂ ቀጥል፣ ሌላም ሞክር፣ ቀጥል፣ ቀጥል፣ …” እያለ ይገፋኝና ይጐነትለኝ ጀመር፡፡ ከዚያም የተለያየ መሳሪያ እውቀት ያላቸውን ሰዎች መጠየቅ፣ ኢንተርኔት ማሰስ፣ የተለያዩ መሳሪያዎች እንዴት እንደሚሠሩ የሚያስተምሩ ዶክመንተሪ ፊልሞች እያሳደድኩ ማየት፣ ስለፈጠራ ሰዎች ማንበብ፣ መከታተል፣ … ሥራዬ ሆነ፡፡

ይህ ብቻ አይደለም፤ የተለያዩ መሳሪያዎች እንዴት እንደሚሠሩ፣ የተበላሹት ደግሞ ምን እንደጐደላቸው እየፈታሁ ማየትና ማጥናት ያዝኩ፡፡

በቀጣይ ምን ዓይነት መሳሪያ ጠገንክ?

በሁለተኛ ደረጃ የሠራሁት የተበላሸ የሻይ ማፍያ መሳሪያ ነው፡፡ ከዚያ በኋላማ የተበላሸ ማቀዝቀዣ፣ የኬክ መጋገሪያ፣ ተሽከርካሪ የቶርታ ማሳያ፣ የድራፍት ቢራ መቅጃ፣ … በርካታ መሳሪያዎች ሠራሁ፡፡ የተበላሹትን ጠግኜ ብቻ አላቆምም - አዲስ ተመሳሳይ መሳሪያ እሠራለሁ፡፡

ይህን ችሎታ በማደበሬ አልተኮፈስኩም፡፡ አዳዲስ መሳሪያዎች ስሠራ፣ የማላውቀው ነገር ካጋጠመኝና ከቸገረኝ “በዚህ ጉዳይ ላይ እውቀት የለኝም” ብዬ ልምድና እውቀቱ ያላቸውን ሰዎች በግልጽ እጠይቃለሁ፤ አማክራለሁ፡፡

አንዳንድ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ደስ የሚል ነገር ታያለህ፡፡ ቅን ያልሆኑ ሰዎች የመኖራቸውን ያህል ከመጠን ያለፈና ከራሳቸው በላይ ለሰው ቅን የሆኑ ሰዎች አሉ፡፡ የቸገረኝን ነገር ከልባቸው በግልጽ የሚያማክሩኝ፣ የሚያስፈልገኝን ዕቃ የትና እንዴት እንደማገኝ፣ ምን ማድረግ እንዳለብኝ፣ … የሚነግሩኝ የሚጠቁሙኝ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ለእኔ እዚህ መድረስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስላደረጉ በጣም አመሰግናለሁ፡፡

እነዚያን ቅን ሰዎች እያማከርኩ ባደረጉልኝ ያልተቆጠበ ድጋፍ አዲስ የሻይ ማፍያ፣ የኬክ መጋገሪያ፣ ቶርታ ኬክ ይዞ የሚሽከረከር ፍሪጅ፣ የድራፍት ማቀዝቀዣና መቅጃ (ኢንስታንት ኩለር)፣ የአየር ማቀዝቀዣ (ፋን)፣ … በቃ በርካታ መሳሪያዎች ሠራሁ፡፡

እስካሁን የነገርከኝ በጥገና፣ ከውጭ የገቡትን ኮፒ በማድረግ፣ ቅን ሰዎችን በማማከር የሠራሃቸውን አዳዲስ መሳሪያዎች ነው፡፡ ፓተንት ወዳገኝህባቸው የፈጠራ ውጤቶች እንዴት ገባህ?

እስከዚያን ጊዜ ድረስ የሠራኋቸው ነገሮች አይጠቅሙም ማለት ሳይሆን በውስጤ ያለውን የፈጠራ ስሜትና ፍላጐት አላረካ አሉ፡፡ ውስጤ፣ “ጀመርክ እንጂ አልጨረስክም፡፡ ጅምርህ ጥሩ ነው፡፡ ግን ብዙ ይቀርሃል፡፡ ቀጥል፣ አስብ፤ አዳዲስ ነገር ፍጠር፣ …” እያለ ሹክ ይለኛል፡፡ የሠራኋቸውን ነገሮች ዞር ብዬ ሳይ በእርግጥም አነሱብኝ፡፡ የሕዝቡን መሠረታዊ ችግር የሚቀርፉ ሳይሆን፤ ከብዙኃኑ ሕዝብ አኳያ ሲታይ “የቅንጦትና የዘመናዊነት መገለጫ” ሆኑብኝና ውስጤ አልረካ አለኝ፡፡

ይኼኔ “ምን ብሠራ ነው አብዛኛውን ሕዝብ መጥቀም የምችለው? ውስጤስ የሚረካው? ዋነኛው የሕዝብ ችግር ምንድነው? የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫስ?...” እያልኩ ማሰብና ማሰላሰል ጀመርኩ፡፡ ከተማ ብወለድም፤ ዙሪያዬ ያሉትን የገጠር ሕዝቦች አኗኗርና ችግር አውቃለሁ፡፡ ዋናው ችግር የጤና ጉድለት ነው፡፡ የተቀረውም የገጠር ነዋሪ ችግር ተመሳሳይ ነው፡፡

መንግሥት ከነደፋቸው አመቺ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ውስጥ የሚጠቀሱት፤ ፋርማሲቲካል፣ ቆዳ፣ የቆዳ ውጤቶች፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ … ናቸው፡፡ መድኃኒት አምራች እንጂ ለጤናው ዘርፍ የሚያስፈልጉ መሳሪያዎችን ለማምረት የቀረበ ባለሀብት “የለም” ባይባልም ኢምንት ነው፡፡ ያለውን ክፍተት አየሁ፤ የጤና ጉዳይ የሚያስደስተኝና ትኩረቴም ስለሆነ በዚህ ዘርፍ አንድ ነገር ለመሥራትና አስተዋጽኦ ለማድረግ ወሰንኩ፡፡

ከዚያ በኋላ ስለ ሕክምና መሳሪያዎች ማገላበጥና ማንበብ ጀመርኩ፡፡ ከውጭ የሚገቡት የሕክምና መሳሪያዎች ምን ችግር አለባቸው? የጥራት ደረጃቸውስ ምን ይመስላል? የሚገዙበት የውጭ ምንዛሪስ ምን ያህል ነው? እንዴትስ ማዳን ይቻላል? ከሙያዬስ አኳያ ምንድነው ማድረግ የምችለው? … የሚሉ ጥናቶች አደረግሁ፡፡

በመቀጠልም የተበላሹ የሕክምና መሳሪያዎችን መጠገን ጀመርኩ፡፡ በዚያን ወቅት ለብልሽታቸው ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ጉድለቶች አየሁና ማሻሻል የምችልበትን መንገድ አሰብኩ፡፡ እነዚያን ጉድለቶች ለማጥፋት ሞከርኩና ተሳካልኝ፡፡

መጠገን የጀመርካቸው መሳሪያዎች ምንድናቸው? ችግሮቹ ምን ነበሩ? እንዴትስ አሻሻልካቸው?

ተበላሽተው የጠገንኳቸው መሳሪያዎች፣ ጀርምና ባክቴሪያ፣ … በእንፋሎት ቀቅሎ መግደያ (ስትራላይዘር) ነበር፡፡ ችግሩ ምን ነበር? ውሃ የሚቀመጥበት ክፍል (ቻምበር) ሲለኮስ ጋዋን፣ ግላቭ፣ የመሳሰሉ ጨርቅ ነገሮችን ያቃጥላል፡፡ ከዚያም ጢስና ጉም ሆኖ ውስጥ ለውስጥ ሄዶ ቻምበር ውስጥ አሲድ ፈጥሮ ይቀመጣል፡፡ ሁለተኛ ጊዜ ሲለኮስ ቻምበሩ ላይ የቆየው ቆሻሻ (አሲድ) በእንፋሎት ይታጠብና መሳሪያዎቹ (መቀስ፣ መርፌ፣ …) ላይ ያርፋል፤ ቁሶቹ በአሲድ ተበከሉ ማለት ነው፡፡ ሐኪሞች፣ መሳሪያዎቹ በአሲድ መበከላቸውን ስለማያውቁ ይጠቀሙባቸዋል፡፡ በዚያን ጊዜ አሲዱ በቀላሉ ወደ ታካሚው ገላ በመግባት ጉዳት ያስከትላል፡፡

ታዲያ ችግሩ ተፈታ? እንዴት?

አዎ! የመጀመሪያው ዓይነት ችግር እንዳይከሰት ውሃ ማሞቂያውን ቻምበር ከውጭ አደረኩት፡፡ በዚህ ዓይነት ሁለት መሳሪያዎች አሻሽዬ ሠርቻለሁ፡፡ አንዱ Medical Steam Sterilizer ሲሆን ሁለተኛው Medical dray hot air sterilizer ይባላል፡፡ የእኔ መሳሪያዎች ዲጂታል ሲሆኑ ከውጭ የሚገቡት ማኑዋል ናቸው፡፡ በእነዚህ ፈጠራዎች ከኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት ሁለት ፓተንት ወስጃለሁ፡፡

የእነዚህ መሳሪያዎች ተፈላጊነት ምን ያህል ነው?

ተፈላጊነታቸው ከፍተኛ ነው፡፡ መንግሥት 5ሺህ የጤና ጣቢያዎች ለማቋቋም አቅዶ እየሠራ ነው፡፡ ለአንድ ጤና ጣቢያ ሦስት ስትራላይዘር ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ በአጠቃላይ 15ሺህ መሳሪያዎች ያስፈልጋሉ ማለት ነው - ለአዲሶቹ ጣቢያዎች ብቻ፡፡ ነባሮቹም ያስፈልጋቸዋል፡፡ ስለዚህ በከፍተኛ ደረጃ ይፈለጋሉ ማለት ነው፡፡

እነዚህ መሳሪያዎች ከውጭ ሲገዙና በአገር ውስጥ ሲመረቱ የዋጋ ልዩነት አላቸው?

አዎ! ከፍተኛ ልዩነት አላቸው፡፡ እነዚህን መሳሪያዎች ከኢትዮጵያ ብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ጋር በመተባበር ለማምረት የተስማማን ስለሆነ በቅርቡ እንፈራረማለን፡፡

ስለዚህ የዚህ አገር ዋጋ ይቆይና ከውጭ አንዱ መሳሪያ በ200ሺህ ዶላር ነው የሚገዛው፡፡ 15ሺህ ስትራላይዘሮች ከውጭ ለመግዛት 3 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፡፡

እዚህ ሲመረቱ ሌላ ምን ጥቅም ይገኛል?

ከውጭ አገር ሲገዙ በመርከብ ስለሚመጡ ከአምስት ወር በላይ ሊዘገዩ ይችላሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ብልሽት ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡ ዋናው ጥቅም ግን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማዳኑ ነው፡፡

 

 

 

 

Read 5236 times Last modified on Saturday, 01 September 2012 11:23