Sunday, 13 June 2021 19:46

እንደኔ አጠባለሁ ብለሽ ጥጃሽን አትግደይ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

 ከኤዞፕ ታሪኮች ውስጥ ጃክዶ ስለሚባል አንድ መጠኑ መካከለኛ የሆነ ቁራ - መሳይ ወፍ የሚከተለው ይገኛል፡፡ ጃክዶ በአውሮፓም በእስያም የሚገኝ ወፍ ነው፡፡ መልኩ የጥቁርና የግራጫ ቀለም ድብልቅ ነው፡፡ የሚያብረቀርቅ ነገር መልቀምና መስረቅ የሚወድ ለፍላፊ የወፍ ዘር ነው፡፡
ጃክዶ እርግቦችን ባየ ጊዜ በጣም አድርጐ ይቀናል፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት እርግብ ያገኝና ወዳጁ ሊያደርጋት ይጠጋታል፡፡
ጃክዶ - “እመት እርግብ” ይላታል
እርግቢት - “አቤት” ትላለች
ጃክዶ - “የእናንተ ቤተ - እርግብ (ቤተሰብ) እኮ በጣም የታደለ ነው”
እርግቢት - “እንዴት?”
ጃክዶ - “የሰው ልጅ ስለሚመግባችሁ የትም የትም ምግብ ፍለጋ አትንከራተቱም”
እርግቢት - “ዕውነትክን ነው - በሱስ እግዜር አድሎናል፤ ገላግሎናል”
ጃክዶ - “የሰው ልጅ የቤቱን ጣራ፣ የመስኮትና የበር ደፍ ሳይቀር ለመኖሪያ ቤት ሰጥቷችኋል።
እኛን ተመልከቺ፡፡ የምንኖረው በየቋጥኙ ሽንቁርና በየጭስ ማውጫው ጥላሸት ላይ ነው፡፡”
እርግቢት - “አዎን፡፡ የሰው ልጅ ባለውለታችን ነው”
ጃክዶ - “በዛ ላይ ከሶስት መቶ በላይ ዝርያ ስላላችሁ ጠላት ቢመጣባችሁ ለመከላከል
ትችላላችሁ፡፡ ሐዘን ቢደርስባችሁ ትስተዛዘናላችሁ፡፡ ብትፈልጉ ትመሣጠራላችሁ፡፡ ማሕበር ቢያሻችሁ ማሕበር መሥርታችሁ ትተጋገዛላችሁ፡፡ እኛ የጃክዶ ዝርያዎች እንደዛ ዓይነት መረዳዳት አናቅም፡፡ ስለዚህ በጣም ታስቀኑኛላችሁ፡፡
እርግቢት - “ልክ ነህ ብዙዎች የወፍ ዝርያዎች እንደሚቀኑብን ይነግሩናል፡፡ የተፈጥሮ ነገር ስለሆነ ምን ታደርገዋለህ” ትለዋለች፡፡
ጃክዶ በእርግቢቱ በኩል የእርግቦችን አኗኗር ሲያጠና ይቆያል፡፡ ከዚያም አንድ ቀን፤
“ቅርፄንና ቀለሜን እንደነሱ አድርጌ ከነሱ ተቀላቅዬ፤ የእነሱን ጥቅምና ምቾት ማግኘት
አለብኝ” ብሎ ያስባል፡፡ ከዚያም መላ አካሉን የነጭ እርግቦች ቀለም ይቀባል፡፡ ድምፁን በተቻለ መጠን በእነሱ ቅላፄ ለመቅረጽ ይለማመዳል፡፡ ሆኖም ብዙ ላለመናገር ይወስናል፡፡
አንድ ቀን በግሪሣ ከሚበርሩት እርግቦች ጋር ይቀላቀልና ይበርራል፡፡ ለብዙ ጊዜ እርግቦችን መስሎ፤ እርግቦችን አክሎ ኖረ፡፡ ሆኖም ከእነሱ ጋር ብዙ በኖረ ቁጥር ምቾት እየተሰማው፤ እንደ ጉራም እየተሰማው፤ የባለቤቱ ልጅ የሆነ መሰለው፡፡ ብዙ እርግቦች በተሰበሰቡበት ሸንጐ
ላይ ንግግር አደረገ፡፡ ብዙ በተናገረ ቁጥር የድምፁ ቅላፄ ወደ ጃክዶዎች ቅላፄ መምጣት ጀመረ፡፡
እርግቦቹ ተያዩና የነሱ ዝርያ እንዳልሆነ ለዩት፡፡ ወዲያው በአንድ ቅጽበት ሰፈሩበትና
እንዳይሞት እንዳይሽር አርገው ተክትከው ተክትከው አባረሩት፡፡
ጃክዶውም አዝኖና ቆሳስሎ ወደ ዘመዶቹ ሄደ፡፡ ዘመዶቹ ግን ነጭ ቀለሙን ሲያዩ፤“የእኛ ዝርያ ቤተሰብ አይደለህም፤ ዞር በል ከዚህ” ብለው አባረሩት፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ያ ጃክዶ ቤት አልባ
ሆኖ፣ ማረፊያ አጥቶ ይንከራተታል፡፡
* * *
መምሰል ክፉ በሽታ ነው፡፡ ለጥቅምም ሆነ ለአንዳች ግላዊ ዒላማ ብሎ ሌሎችን መስሎ፣ የሌሎችን ማሊያ ለብሶ፣ የሌሎችን ዜማ አጥንቶ፤ እንደሌሎች እሆናለሁ ብሎ ማሰብ፤ “የባዳ ሞኝ ከልጅህ እኩል አርገኝ” አለ፤ እንደሚባለው ነው፡፡ የተቀቡት ቀለም መደብዘዙ፣ ያጠኑት ዜማ መፍዘዙ እና የራስ ማንነት የማታ ማታ በዚህም ቢሉት በዚያ ብቅ ማለቱ አይቀሬ ነው፡፡
የሥነ - አዕምሮ ጠበብት እስስታዊ ባህሪ የሚሉት ነው፡፡ ፖለቲከኞች አድር - ባይነት ይሉታል፡፡
ገጣሚዎች ደሞ፤
“ያካባቢ ቀለም ብትለብስም፣ እስስት የኖረች መስሏት
የማይወላውል ባላንጣ፣ አድብቶ ለቀም አረጋት!
ቀን የተመቸን መስሎን፣ የኛ ካልሆነ መጠጋት
የጅሎች አጉል ብልጠት
ለ”አስብቶ - አራጅ” እጅን መስጠት
የሰው ቀለም ፍለጋ፣ የራስን ቀለም ማጣት!
የዛም የዚህም ሳይሆኑ፣ ምላስ አርዝሞ መቅረት (Extensile Tongue) –
ሀምሌ 19 ቀን 2005 ዓ.ም (ለረዣዥም ምላሶችና ለልበ እስስቶች)
ረዣዥም ምላሶችና ልበ-እስስቶች የትም አሉ፡፡ በቢሮክራሲ ውስጥ፡፡ በፓርቲ ውስጥ፡፡
በኩባንያ ውስጥ፡፡ በንግድ ውስጥ፡፡ በወጣት ውስጥ፡፡ በአዋቂ ውስጥ፡፡ በሴት ውስጥ፡፡ ነቅተው ካልጠበቋቸው ለግንዱም ለቅርንጫፉም አስጊ የሚሆኑበት ጊዜ ይመጣል፡፡
ከላይ የተጠቀሰው የተረቱ ጃክዶ “በጳጳሱ ዙፋን ላይ በኩራት ይቀመጣል፡፡ ካህኑም፣
አባውም፣ ዲያቁንም ቢኖሩ ግድ የለውም” ይላሉ ፀሐፍት በምፀት፡፡ ለዚህም ነው የዱሮ ፖለቲከኞች፤“አድርባዮች ያሉበት አብዮት ከመቦርቦር አይድንም”የሚሉት፡፡
ጥንት የሀገራችን መሪ ባለስልጣናቱን ሰብስበው፤“ከዚህ ከዚህ ክፍለ ሀገር በሀገር ውስጥ ገቢ ያልተሰበሰበ ይሄን ያህል ሚሊዮን አለ ተብሏል። እሺ የክፍለ ሀገሩ አስተዳዳሪ ምን ትላለህ?” ብለው ጠየቁት አሉ፡፡ አስተዳዳሪውም ወታደር ነበረና ተነስቶ ግጥም አድርጐ ሰላምታ ከሰጠ በኋላ፤ “አለ ጌታዬ! አመጣለሁ!” አለ ይባላል፡፡
ከሰሞኑ ደግሞ አንዱ ለምርጫ የሚወዳደር  የፖለቲካ ፓርቲ መሪ፤ #ከምርጫ ቦርድ ለምርጫው ማስኬጃ ተብሎ የተሰጣቸውን ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ይዘው ተሰወሩ; የሚል ዜና በየማህበራዊ ሚዲያው ከተናፈሰ ከጥቂት ቀናት በኋላ ድምጻቸውን በማሰማት፤ #ኸረ እኔ አልተሰወርኩም፤ ብሩም አልጠፋም፤ለቅስቀሳ ፖስተር ለማሰራት የእጩዎችን ፎቶ እያሰባሰብን ነው; ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የምርጫ ቅስቀሳው ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት በቀሩበት በዚህ ሰዓት፣ እኚህ የፓርቲ መሪ ገና ፖስተር አለማሰራታቸውን ነው የሚነግሩን፡፡ በዚህ አካሄዳቸው ደግሞ ለቀጣዩ ምርጫ እንጂ ለዘንድሮው አይደርሱም፡፡ 1 ሚሊዮኑ ብር  ግን ደርሶላቸዋል፡፡  እኒሁ የፓርቲ መሪ ለቢሮአቸው ተብሎ ከመንግስት የተሰጣቸውን የኪራይ ቤት፣ ለሁለት ከፍለው መኖሪያ ቤት አድርገውታል በሚል የሚቀርብባቸውን ሃሜት በተመለከተ ተጠይቀውም፤  #እውነት ነው፤አባላቶቻችን ከክልል ሲመጡ ለአልጋ ከሚያወጡ ብለን ቢሮአችንን ለሁለት ከፍለን እንዲያድሩበት አዘጋጅተነዋል; ሲሉ አስገራሚ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ሙስና በተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ የለም ያለው ማነው?  
ቢሮክራሲና ካፒታሊዝም ቀለበት ካሰሩ ሰነባብተዋል፡፡ ሥልጣንና ንግድ ከተጋቡ ውለው አድረዋል፡፡ አሁን ጥያቄው Who guard the guards? ጠባቂዎቹንስ እነማን ይጠብቋቸዋል?
የሚለው ነው፡፡ አንድ የዘመኑ ማስታወቂያ አከል መልዕክት፡- “ማፍረስ ቀላል ባይሆንም፤ መገንባት የበለጠ ከባድ ነው!” (የደርግ መፈክር) ዛሬ በንግድ የሚተዳደሩ ቢሮክራቶች፣ የድርጅት መሪዎች እየበዙ ነው፡፡ የፖለቲካ መሪዎች ብዛትማ አይጣል! አስተዋይ ዐይን ተከፍቶ ቢያያቸው ይበጃል፡፡ “እንደኔ አጠባለሁ ብለሽ ጥጃሽን አትግደይ!” የሚለው የወላይትኛ ተረት ጡታቸው ላይ ማነጣጠር አለበት፡፡

Read 11366 times