Print this page
Sunday, 13 June 2021 19:41

በደንቢ ዶሎ ወጣቱን በአደባባይ የገደሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ ሂዩማን ራይትስ ዎች ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 “የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ህጋዊ ሽፋን እየተሰጣቸው ነው”
     የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሲፈፀሙ አፋጣኝ እርምጃ በመውሰድ አጥፊዎችን አለመቅጣቱ ዜጎች ህዝብ በተሰበሰበበት፣ በአደባባይ በጥይት ተደብድበው የሚገደሉበትን ሁኔታ ፈጥሯል ሲል ሂዩማን ራይትስ ዎች ወቅሷል፡፡
ላለፉት 3 ዓመታት የግጭት ቀጠና ሆኖ በዘለቀችው የኦሮሚያ ክልል ወለጋ ዞን፣ ደንቢ ዶሎ ከተማ፣ ግንቦት 3 ቀን 2013 ዓ.ም የ17 ዓመቱ ወጣት አማኑኤል ወንድሰን ከበደ፣ በአደባባይ በጥይት ተደብድቦ መገደሉን ያረጋገጠበትን የምርመራ ሪፖርት ከትናንት በስቲያ ያወጣው ዓለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች፤ የፀጥታ ሃይሎች ይህን ድርጊት ህዝብ በተሰበሰበበት እንዲፈጽሙ ያደረጋቸው በሃገሪቱ የተንሰራፋው የሰብአዊ መብት ጥሰት ልምምድ ነው ሲል ተችቷል፡፡
የአካባቢው ባለስልጣናት፤ ወጣቱ የመንግስት ባለስልጣናትን በመግደል የሚታወቀው “አባ ቶርቤ” የተባለ ቡድን አባል ነው በማለት መገደሉን ያረጋገጡ ሲሆን በአደባባይ ግን አልተገደለም ሲሉ ማስተባበላቸው ይታወሳል፡፡
ወጣት አማኑኤል ወንድሰን ከበደን የፀጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር ካዋሉት በኋላ ክፉኛ እንደደበደቡት፣ ከአካሉ ደም እየፈሰሰው በከተማዋ ውስጥ ህዝብ እንዲመለከተው በፀጥታ  ሃይሎች  ታጅቦ ሲዘዋወር መዋሉን፣ በከተማዋ በሚገኝ አደባባይ አንገቱ ላይ ሽጉጥ ታስሮበት ለህዝብ እንዲታይ መደረጉን፣ በኋላም ህዝብ በተሰበሰበበት በጥይት ተደብድቦ መገደሉን ሂዩማን ራይትስ ዎች በሪፖርቱ አመልክቷል- የዓይን እማኞችን በመጥቀስ፡፡
ወጣቱ ደም እየፈሰሰው በከተማዋ ሲዘዋወርና ሽጉጥ አንገቱ ላይ ታስሮ የሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስልም በከተማዋ መንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ድረ-ገፅ ላይ ተለጥፎ ህዝብ እንዲመለከተው መደረጉን የጠቆመው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ፤ ይህ መሰሉ ድርጊት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ህጋዊ ሽፋን እየተሰጣቸው መሆኑን ያመላክታል ብሏል፡፡
የፀጥታ ሃይሎች ወጣቱን ከገደሉት በኋላ ነዋሪዎች ወደ አስከሬኑ እንዳይጠጉ መከላከላቸውንና በፖሊስ ቁጥጥር ስር የነበሩት የአማኑኤል ወላጆች አስከሬኑ ወዳለበት እንዲመጡ ማድረጋቸውን የጠቆመው የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ሪፖርት፤  እናት የልጃቸውን አስከሬን አይተው  ማልቀስ ሲጀምሩ ፖሊሶች አባትና እናትን መደብደባቸውን ከአይን እማኞች መስማቱን አመልክቷል፡፡
የፀጥታ ሃይሎች በህግ እንጠየቃለን የሚል ስጋት ሳይኖርባቸው ታዳጊውን በአደባባይ በጥይት ደብድበው መግደላቸው ለሚፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የሚወሰደው አፀፋዊ የህግ እርምጃ በእጅጉ የተዳከመ መሆኑን ያመለክታል ብሏል- ሂዩማን ራይትስ ዎች፡፡
ሪፖርቱ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስም ወጣቱን በአደባባይ በህዝብ ፊት በመግደል ተጠርጥረው እንኳ የታሰሩ የፀጥታ ሃይሎች እንደሌሉና ይህም ለሰብአዊ መብት ጥሰቱ እውቅና የሰጠ አደገኛ አካሄድ መሆኑን ሂዩማን ራይትስ ዎች ጠቁሟል፡፡
መንግስት ለሰብአዊ መብት ጉዳዮች ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ የጠየቀው ሂውማን ራይትስ ዎች፤ መንግስት በ17 ዓመቱ ወጣት ላይ በአደባባይ የተፈጸመውን ወንጀል አምኖ ህዝብን ይቅርታ እንዲጠይቅና መሰል ድርጊት እንዳይደገምም በአጥፊዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ አሳስቧል፡፡

Read 9220 times