Sunday, 13 June 2021 19:39

ከምርጫው ጋር በተያያዘ የኮቪድ-19 ስርጭት እንዳይስፋፋ ተሰግቷል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

 • በአሜሪካና ህንድ ከምርጫ በኋላ ስርጭቱ በእጅጉ መስፋፋቱ ተጠቁሟል
     • የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል መንግስት ቁርጠኛነት አላሳየም
     • ከባዱ ጊዜ ቢመጣ ልንወጣው እንደማንችል ተፈትነን አይነተዋል
                  
           በቅርቡ ከሚካሄደው 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ጋር በተያያዘ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭት ይስፋፋል የሚል ስጋት መኖሩ ተገለፀ፡፡ መንግስት የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል ቁርጠኛ እርምጃ እየወሰደ አይደለም በሚል ተወቅሷል፡፡
“ኢሮፕያን ሴንተር ፎር ኤሌክቶራል ሳፖርት” የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሰሞኑን ከኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድና ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመጣመር ከመገናኛ ብዙኃን  ባለሙያዎች ጋር ባካሄዱት  ውይይት ላይ እንደተገለጸው፤ መጪው አገራዊ ምርጫ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ስርጭት ሊያባብሰው ይችላል የሚል ስጋት እንዳለ ተመልክቷል፡፡
የበሽታው ስርጭት ከተከሰተ በኋላ አገራዊ ምርጫዎችን አድርገው የነበሩ አገራትን ዋቢ በማድረግ በተካሄደው የሰሞኑ ውይይት ላይ አሜሪካና ህንድ አገራዊ ምርጫቸውን ባካሄዱ ማግስት የበሽታው ስርጭት በከፍተኛ መጠን ማሻቀቡ ተጠቁሟል፡፡ አገራቱ የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል የሚያስችል በቂ ዝግጅት ሳያደርጉ ምርጫውን በማካሄዳቸው ብዙ ሺዎች የሚሆኑ ዜጎቻቸው በበሽታው ሲያዙ፣ ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ለህልፈት ተዳርገዋል ተብሏል፡፡ ይህ አሳዛኝ ክስተት በአገራችን እንዳይደገም ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባና መንግስት የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል እያሳየ ያለውን ዳተኝነት ማስወገድ እንዳለበት ተገልጿል፡፡
የበሽታው ስርጭት እየተስፋፋ መሄዱን ተከትሎ የጤና ሚኒስቴር ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የተለያዩ ህግና መመሪያዎችን ያወጣ ቢሆንም፣ የወጡት ህግና መመሪያዎች ተፈፃሚነት ሳያገኙ መቅረታቸው ተመልክቷል፡፡ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ህግና መመሪያዎችን የማስከበር ሃላፊነት ቢኖርባቸውም፣ ራሳቸው ህግና መመሪያውን ባለማክበር፣ ለህብረተሰቡ በጎ አርአያ የመሆን ሚናቸውን ሳይወጡ ቀርተዋል ተብሏል፡፡
በጤና ሚኒስቴር የሚኒስትር ዴኤታ ቢሮ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ዶ/ር ወንደሰን እሸቱ በዚሁ የውይይት መድረክ ላይ እንደተናገሩት ፣ አገሪቱ በሁለት የተለያዩ ወቅቶች የኮቪድ-19 በሽታ ስርጭት በከፍተኛ መጠን ያስተናገደች መሆኑን ጠቅሰው፣ እነዚህ ጊዜያት አገሪቱ ያላትን የመጨረሻ አቅም ያየችበትና እጅግ የተፈተነችበት ወቅት ነበር ብለዋል፡፡ ሁለቱም የበሽታው ስርጭት ከፍታ ያሳየባቸው ጊዜያት የህዝብ መሰባሰቦች የበዙባቸውና የበዓላት ወቅት እንደነበሩ አመልክተዋል፡፡ “ተፈትነን ልካችንን አውቀናል፣ ከዚህ የባሰ ሁኔታ ቢፈጠር መቋቋም  እንደማንችልም በሚገባ ተረድተነዋል፡፡ ስለዚህም ያለን ብቸኛ አማራጭ የበሽታውን ስርጭት መከላከል ብቻ ነው” ሲሉ ተናግረዋል አማካሪው፡፡
በቅርቡ በሚካሄደው አገራዊ ምርጫም በተመሳሳይ ሁኔታ ብዙ ሰዎች በአንድነት የሚገኙበትና የሚሰባሰቡበት ሁኔታ መፈጠሩ ስለማይቀር ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግበት እንደሚገባም ዶ/ር ወንደሰን አሳስበዋል፡፡
በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የኮቪድ-19 በሽታ ስርጭት መከላከል ኃላፊ ዶ/ር ኢማን አብዱልሐኪም  መጪውን ምርጫ ከኮቪድ 19- በሽታ ስጋት ነፃ ለማድረግ ከፍተኛ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ እያንዳንዱ መራጭ ራሱን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ እየተከላከለ ምርጫውን የሚያካሂድ ሲሆን የምርጫ አስፈጻሚዎችና በምርጫ እንቅስቃሴው ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ ሰዎች ሁሉ ራሳቸውን ከበሽታው ለመከላከል የሚያስችላቸውን እንደ ፊት ጭንብልና ሳኒታይዘር ያሉ መከላከያዎች ዝግጁ መደረጋቸውንም አመልክተዋልተደርገዋል ብለዋል፡፡
የኮቪድ-19 በሽታ ወደ አገራችን ከገባበት መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ 2.7 ሚሊዮን ሰዎች የተመረመሩ ሲሆን ከነዚህ መካከልም 272 ሺህ የሚሆኑት በሽታው እንደተገኘባቸው፣ 246 ሺዎቹ ከበሽታው ማገገማቸውን፣ 4200 የሚሆኑት ደግሞ በዚሁ ቫይረስ ሳቢያ ህይወታቸውን ማጣታቸውን የሚመለከተው የጤና ሚኒስቴር መረጃ፤ በአሁኑ ወቅት 22 ሺ ያህል ሰዎች በበሽታው ተይዘው እንደሚገኙ ይጠቁማል፡፡ 1.8 ሚሊዮን ሰዎችም የኮቪድ ክትባት መከተባቸው ታውቋል፡፡
የኮቪድ -19 በሽታ ስርጭት በአሁኑ ወቅት እየቀነሰ መምጣቱን የጠቆሙት በሚሊኒየም የኮቪድ- 19 ህክምና ማዕከል ሃኪም የሆኑት ዶ/ር ኢዮሲያስ በላይነህ፤ ይህ መረጃ ግን ፈፅሞ ሊያዘናጋንና ከምናደርጋቸው የጥንቃቄ እርምጃዎች ሊገታን ጨርሶ እንደማይገባ መክረዋል፡፡

Read 8612 times