Saturday, 12 June 2021 13:16

ብድር በምድር!!

Written by  ሔኖክ ኤ ም. ካ ሣ
Rate this item
(0 votes)

  የመሳፍንት ዘመን አብቅቶ አንዲቷን አትዮጵያ የማየት ህልም የነበረው ደጃች ካሳ (አፄ ቴዎድሮስ)፤ ራስ አሊንና ደጃች ጎሹን አሸንፎ ሀይሉን አጠንክሮ፣ሰራዊቱን አብዝቶ፣ የጎጃሙን ደጃች ብሩን “ግባ” ብሎ ሰደደበት። ደጃች ብሩ ልበ ደንዳና፣ ትዕቢተኛ ነበርና በንቀት “አንተ የኮሶ ሻጭ ልጅ፤ ወንድ ከሆንክ ግጠመኝ” ብሎ መልዕክት ልኮበት፣ እርሱ “ሶማ አምባ” የምትባል ቦታ ላይ ከተተ!
ደጃች ካሳም ወደ ጎጃም ዘልቆ፣ ሶማ አምባን ከቦ ተቀመጠ። ጉዳዩን በሰላም መጨረስ የፈለገው ደጃች ካሳ፤ ለመግባቢያ ይሆን ዘንድ አሽከሩን ወደ ደጃች ብሩ ልኮ፤ “የፈረስዎን ስም አባ ዳምጠውን ለኔ ይተውልኝ ፤ አይሆንም ያሉ እንደሆነ ለፈረሴ ሌላ ስም ያውጡልኝ” አለው።
ትዕቢተኛው ደጃች ብሩ “ፈረስህን "ትንጓለል በለው” ብሎ ላከበት፡፡ የዚህን ጊዜ ካሳ በብስጭት ፀጉሩን እስኪነጭ ድረስ ተናደደ።
የሶማ አምባ ምሽግ ጠንካራ እንደሆነ የተረዳው ካሳ፤ አዘናግቼ እይዘዋለሁ ብሎ ወደ ሜንጫ ተመለሰ። የካሳ የሰራዊት ብዛት ከጠበቀው በላይ የሆነበት ደጃች ብሩ፣ የካሳን ምሽግ መፍታት እንዳወቀ እግሬ አውጭኝ ቡሎ ወደ ኩታይ ኦሮሞ ሸሸ !! የኦሮሞ ፈረሰኞችም “በካሳ ታስፈጀናለህ፤ አንደብቅህም” ብለው ለካሳ ይዘው አስረከቡት። ደጃች ካሳም አርባ አምባ አስገብቶ ከሚስቱ ነጥሎ አሰረው!
የደጃች ብሩ ሚስት የሆነችው የውብዳር ከእስር ቤቱ አሽከሮች መካከል አንዱን መርጣ ውሽማ አደረገችው፡፡ ውሽማውም መሸት ሲል ጠብቆ እየገባ፣ የውብዳርን አጮጩሇ ይወጣ ጀመር። ይህንን ነገር ደጃች ብሩ በሰማ ጊዜ አዘነ! መጫወት በሚወደው በገናውም እንዲህ ብሎ አዜመ!
መከራን እንዲያ በሰው ላይ ሳቀለው
ምነኛ ከበደኝ እኔ ስይዘው
መከራ ሲመጣ አይናገርም አዋጅ
ሲገሰግስ አድሮ ቀን ይጥላል እንጅ
ደጃች ብሩ ይህንን የገጠመው እርሱ የጎጃም ገዥ በነበረበት ወቅት ህዝብ ላይ የሰራው ግፍ ትዝ ብሎት ነው። ደጃች ብሩ የጎጃም ህዝብ ላይ ከሰሩት ግፍ መካከል በጣም የሚያስገርሙትን ሶስቱን ልጥቀስ!
አሁን ላይ ከድታው በአሽከር ሞፈር የምትታረሰው የውብዳር፣ ቀድማ ቤተ ክርስቲያን ሳትገባ በፊት ማንም መግባት አይችልም ነበር። ገብቶ የተገኘ ሰው እንደ በረዶ ዱላ ይወርድበት ነበር!
ቤተ መንግስቱን ከምስጥ ለመከላከል ብሎ ህዝብን በወረዳ በወረዳ አደራጅቶ፣ አስር አስር እንስራ ጉንዳን እንዲያመጡ አዟቸው ነበር። ባላገሩ ጉንዳን እያደነ በሳምባ ሰብስቦ፤ እንስራውን ይዞ ሲሄድ ጉንዳኑ እየነከሰ ቢያስቸግረው በእንጉርጉሮ መከራውን እንዲህ ብሎ ገልጦ ነበር፡-
ከመከራው ሁሉ የጉንዳኑ ባሰ
የገባሪውን ጆሮና ትከሻ እየነከሰ
"ለበቅሎዬ የሆድ ቁርጠት መድሃኒቱ የሴት ብልት ፀጉር ስለሆነ አምስት አምስት መስፈሪያ ጠጉር አምጡ; ብሎ ህዝብን አስለቅሶት ነበር። ያን ጊዜ ሴት ዘመድ የሌለው ሰው፤ ጭገር ልመና በየሰው ቤት ተንከራተተ። እንግዲህ እኒህ እና ሌሎች ግፎቹ ትዝ ቢሉት ነው።
መከራን እንዲያ በሰው ላይ ሳቀለው
ምነኛ ከበደኝ እኔ ስይዘው
--ብሎ የገጠመው!

Read 2079 times