Saturday, 12 June 2021 13:14

ኔቶ በቅድሚያ መዝመት ያለበት ወደ አሜሪካ ነው!

Written by  ጌታሁን ሔራሞ
Rate this item
(0 votes)

   በጦርነት ወቅትም ሆነ በድህረ ጦርነት በሲቪሎች ላይ የሚደርሱትን ሰብዓዊ ጥቃቶችን እቃወማለሁ፣ በተለይም በሴቶች ላይ የሚደርስ የትኛውም ዓይነት ጥቃት መወገዝ ያለበትና ጥቃት አድራሾቹንም ለፍርድ ማቅረብ አሌ የማይባል ነው። በዚህ ርዕሰ ጉዳይ በሰሜኑ ጦርነት ወቅትም ሆነ በድህረ ጦርነቱ ከአንዴም ሁለቴ የተቃውሞ ሐሳቤን አጋርቼአለሁ።
በአሁኑ ወቅት የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ በተፈጠረው ሰብዓዊ ጥቃቶች ዙሪያ የውጭ ሀገር መንግስታት ድምፃቸውን እያሰሙ ነው፣ ለዚህም ራሷን እንደ ዓለም አቀፍ ፖሊስ የምትቆጥረው አሜሪካ የአንበሳውን ድርሻ ትወስዳለች፤ አሁን ደግሞ በተለይም በሴቶች ዙሪያ የሚፈፀሙትን ጥቃቶች ተከትሎ የሰሜን አትላንቲክ ስምምነት ድርጅት (ኔቶ) በየትኛውም ሀገር ጣልቃ መግባት የሚችልበትን መንገድ እየጠራረገች ትገኛለች።
ሁሌም በተደጋጋሚ እንደሚባለውና የአሜሪካ መንግስትም ሰርክ እንደሚናገረው፣ የአሜሪካ የውጭ ፖሊሲዋ የተመሠረተው ገና ከመነሻው የአሜሪካን ጥቅም ከማስቀጠልና ከማስጠበቅ አኳያ ነው። ለዚህ ዋና አጀንዳዋ የአሜሪካ መነሻ ሰበቧ ግን ሌላ ሊሆን ይችላል። በእኔ ዕይታ በተለይም በጦርነት ወቅትም ሆነ በድህረ ጦርነት በሴቶች ላይ በሚፈፀሙ ወሲባዊ ጥቃቶች ዙሪያ አሜሪካ ራሷን ንፁሕ አድርጋ ሌሎችን ለመክሰስ ተፍ ተፍ የምትልበት ፍጥነት ትዝብት ላይ የሚጥላት ነው። ምክንያቱም በኢራቅና አፍጋኒስታን ከሴቶች ወሲባዊ ጥቃት ጋር በተገናኘ የአሜሪካ ወታደሮች የነበራቸው ስም እጅግ አሳፋሪና ዘግናኝ ነበር።
አሜሪካ በወታደሮች የሚፈፀሙ ጥቃቶችን በተመለከተ ሌሎችን ለመኮነን በአጭር ታጥቃ በተነሳች ቁጥር ትዝ የምለኝ የኢራቃዊቷ የ14 ዓመት ሕፃን “Abeer Qassim Hamza al-Janabi” የመደፈርና የመገደል ሰቆቃ ነው። ነገሩ እንደዚህ ነው፦ እ.ኤ.አ. በ2006 ዓ.ም. “Steven Dale Green” የተባለ የአሜሪካ ወታደር ከሌሎች ሦስት ባልደረቦቹ ጋር በመሆን ከባግዳድ 30 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ወደምትገኝ መንደር አብረው ከሄዱ በኋላ ከላይ የጠቀስኩላችሁ ሕፃን ልጅ ቤት ይገባሉ። እነዚህ የአሜሪካ አረመኔ ወታደሮች ወደ ቤት ከገቡ በኋላ የልጅቷን አባት እናትና ታናሽ እህቷን አስቀድመው ከገደሉአቸው በኋላ በተለይም “Steven Dale Green” የተረፈችውን የ14 ዓመት ሕፃን ከደፈራት በኋላ እሷንም ይገድለታል፤ ይህም አልበቃ ሲለው አስከሬኗን በእሳት አቃጠለ። “Steven Dale Green” ለፈፀመው ወንጀል የዕድሜ ልክ እስር ከተፈረደበት በኋላ እ.ኤ.አ.በ2009 ዓ.ም. ራሱን በታሰረበት ክፍል አጥፍቶ ተገኝቷል።
አሜሪካ የሴቶች ወሲባዊ ጥቃት ጠበቃ ሆና በምትቆምበት ቅፅበት ሁሉ ከኢራቃዊቷ “Abeer Qassim Hamza al-Janabi” በተጨማሪ ትዝ የምትለኝ አሜሪካዊቷ “Jessica” ነች። የአሜሪካ ወታደሮች የወሲባዊ ጥቃት ወንጀል ለገዛ ዜጎቻቸውም ጭምር የሚዳረስ ነው። “Jessica” የአሜሪካ ሚሊተሪ አባል ነች (ስሟ ለደህንነቷ ሲባል ተሰውሯል)፣ ነገር ግን በሚሊተሪ አለቆቿ ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባታል። በአሜሪካ የሚሊተሪ ተቋም ከሶስት ሴቶች በአንዷ በአለቆቻቸው ወሲባዊ ጥቃቶች እንደሚደርሱ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ (As many as one in three women in the US military are raped during their service, studies suggest [GALLO/GETTY])
ታዲያ ችግሩ በዚህ ብቻ የሚቆም አይደለም። ብዙዎቻችን አሜሪካ ፍትሕና ዲሞክራሲ የሰፈነባት ሀገር ስለሆነች ወሲባዊ ጥቃቱን በሚፈፅሙ የሚሊተሪ አባሎቿ ላይ ፈጣን እርምጃ እንደምትወስድ አድርገን እንቆጥር ይሆናል፣ ነገር ግን ጥቃቱ የደረሰባቸው የሚሉን ተቃራኒውን ነው። ይልቁን ወሲባዊ ጥቃቱ የደረሰባቸው ሴት ወታደሮች ጥቃቱን ሪፖርት በሚያደርጉበት ወቅት ፍትሕ ማጣታቸው እጅግ የሚዘገንን ነው። እስቲ ከላይ የጠቀስኳት የጥቃቱ ሰለባ የምትለውን ከራሷ አንደበት እንከታተል፦
“My experience reporting military sexual assault was worse than the actual assault.The command has so much power over a victim of sexual assault. They are your judge, jury, executioner and mayor: they own the law. As I saw in my case, they are able to crush you for reporting an assault.”
የአሜሪካ ወታደሮች በኢራቅና አፍጋኒስታን ቆይታቸው የፈፀሙአቸው ወሲባዊ ጥቃቶች ተቆጥረው የሚያልቁ አይደለም፣ አምኒስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዎች ቆጥረው ይዝለቋቸው። በወቅቱ የቡሽ አስተዳደር ይህን ገመናውን ለመሸፈን የተቀረፁትን ምስሎችንም ሆነ ቪዲዮችን ለመሰወር የማያደርገው ጥረት አልነበረም። ታዲያ ይህ ሁሉ ግፍ ሲፈፀም የዛሬው ኔቶ የት ነበር? አሜሪካ ዓይኗ ውስጥ የተሰነቀረውን ግንድ የሚያክል ገመናዋን ደብቃ የሌሎችን ጉድፍ ለማየት የሞራል ድፍረቱን ያገኘችው ከወዴት ነው? ወሲባዊ ጥቃትን ማውገዝና መቃወም በአሜሪካኖቹ አያምርባቸውም፣ ይልቁን የተሻለ ሞራልና ሰብዕና ያለውን የሚሊተሪ ተቋማትን የገነቡ ሀገራት ቢቃወሙ መልካም ነበር። ስለዚህም አሜሪካ ከሁሉ አስቀድማ ኔቶን በራሷ ላይ ታስዘምት! ፅዳቱ ከራስ ይጀምር!


Read 1996 times