Saturday, 12 June 2021 13:11

የማለዳ እንጉርጉሮ

Written by  በእውቀቱ ስዩም
Rate this item
(0 votes)

አንዳንዴ ደሞ ጎህ ቀዶ
አብሮኝ ያደረው ደወል፤ ከራስጌዬ
ተጠምዶ
ከወፎች ቀድሞ ሲያመጣልኝ “ነግቶብሃል”
የሚል መርዶ
ብትት ብዬ፤ ደንብሬ
ግማሽ ፊቴን ትራሴ ውስጥ ቀብሬ
“እኮ ዛሬም እንደወትሮ
ካውቶብስ ወደ ቢሮ
ከኬላ ወደ ኬላ
ዛሬም በግንባሬ ወዝ ልበላ
እሺ ከዚያስ በሁዋላ?”
እያልሁ ልቤን ስሞግት፤ መልሱን
አያመለክተኝ
ይሄን ያህል ነው የታከተኝ፤
ጉዞዬ፤ ካዋላጅ እቅፍ፤ እስከገናዦች አልጋ
ባራት አግር ተጀምሮ፤ ባራት ሰው ሸክም
እስኪዘጋ
መንገዱ መንገድ እየሳበ
ትንንሹ ዳገት ፤ለትልልቁ እያስረከበ
እንደ ሀረግ ስጎተት፤ እንደ ጥንቸል ስፈጥን
“ምን ሽልማት ታሰበልኝ? ይህ ልፋቴን
የሚመጥን
እያልሁኝ ሳውጠነጥን፤
አንዳንዴ ደሞ ሲመረኝ
እንደ ለማዳ ፈረስ፤ ሞትን በፉጨት
መጥራት ሲያምረኝ፥
ዛፉን የተቀማ አሞራ
በኮረንቲ ምሶሶ ላይ፥ ጎጆው ባዲስ መልክ
ሲሰራ
ማርዋን የተዘረፈች ንብ፤ በየአበባው
ስትሰማራ
አይና
እንዲህ እንዲህ እላለሁ፤ እርስ በራሴን
ሳጽናና፡ -
ሺህ ጊዜ ብትራቀቅ ፤ ቃላት መርጠህ
ብትገጥም
ከዚህ አሞራ አታንስም ከዚች ንብም
አትበልጥም
ተፈጥሮ ትግልን እንጂ፤ የድል ዋስትናን
አትሰጥም
ቻለው!

Read 1986 times