Saturday, 05 June 2021 14:14

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ከወለድ ነፃ ባንክ ሥራ ጀመረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  በአገራችን የመጀመሪያ የሆነውና ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን የሚሰጠው ዘምዘም ባንክ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ። ከትናንት በስቲያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ኡመር ኢድሪስ በተገኙበት ቦሌ በሚገኘው ጋራድ ህንፃ ውስጥ በይፋ የተከፈተው ባንኩ አጠቃላይ ካፒታሉ 876 ሚሊዮን ብር መድረሱ ተገልጿል፡፡
ባንኩ በአሁኑ ወቅት ከ11ሺ በላይ አባላት ያሉት ሲሆን በሸሪአ ህግ መሰረት ከወለድ ነፃ የሆነ አገልግሎትን ይሰጣል ተብሏል፡፡
በዚሁ የባንኩ የመክፈቻ ፕሮግራም ላይ የተገኙት የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶ/ር ይናገር ደሴ ፤በኢትዮጵያ የባንክ ተደራሽነትም ሆነ የባንኮች ቁጥር እንዲሁም አቅማቸው ዝቅተኛ መሆኑን ገልፀው፤ ይህ ሁኔታ እንዲሻሻል በትኩረት እንሰራለን ብለዋል፡፡ 17 ያህል ባንኮች ፈቃድ ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ እንደሆኑ ያመለከቱት ዶ/ር ይናገር፤ አስፈላጊውን መስፈርት ላሟሉት፤ በ6 ወራት ውስጥ ፈቃድ እንሰጣለን ብለዋል፡፡
የባንኩ ዋና ስራ አስፈጻሚ መሊካ በድሪ በነመክፈቻ ፕሮግራሙ ላይ እንደተናገሩት ባንኩ የሸሪአን ህግ ይከተል እንጂ አገልግሎቱ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የቀረበ ነው ብለዋል፡፡


Read 1750 times