Saturday, 05 June 2021 14:07

ቃል፣ ቀለምና ፊደል

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(3 votes)

  "-እኔ ሕይወትን ተጠቃላ ነጥብ አክላ ስረዳት ሦስት መከሰቻ መልኮች ብቻ አሏት፡- ቃል፣ ቀለምና ፊደል! ስለ ምንም ነገር አውሪኝ፤ እኔ
የምረዳሽ ወደ እነዚህ ሦስት ንዑሳን የሕይወት መገለጫ አንጓዎች እየመነዘርኩ ነው፡፡ ለእኔ ሕይወት ከቃል፣ ቀለምና ፊደልም አንሳ ነቁጥ አክላ ትቅረብ ከተባለች፣ ዝምታ ብቻ ትሆናለች፡፡ በእኔ እምነት ቃል፣ ቀለምና ፊደል አንድም ሦስትም ናቸው፡፡-"
                   

             ይህችን ታሪክ ደግሜ ልበላት…
‹ንባብ ለሕይወት› የተሰኘው የአንድ ሰሞን የንባብ ንቅናቄ መድረክ ላይ፣ ለጊዜው ስማቸውን የረሳሁት አንድ ዶክተር እንዲህ ሲሉ ሰማሁ፡- ‹‹ለስራ ጉዳይ ወደ ዳንግላ ከተማ ሄጄ መኪና ውስጥ ቁጭ ብዬ ሳነብ አንድ በሁሉ ነገሩ የተጎሳቆለ ሰው ወደ መኪናዬ መስኮት ተጠግቶ ቆመ፡፡ ያው እንደ አብዛኞዎቹ ገንዘብ ይጠይቀኛል ብዬ ስጠብቅ ግን ‹እባክህ የሚነበብ ነገር፣ የቆየ ጋዜጣም ቢሆን ካለህ› አለኝ፡፡ እጅጉን አዘንኩ፡፡ በአጋጣሚ እጄ ላይ የነበረው የማነበው የጀርመንኛ መጽሐፍ ብቻ ነበር። ከልጁ እንደተረዳሁት በከተማዋ ውስጥ የመጻሕፍትም ይሁን የጋዜጣ መሸጫ ብሎ ነገር የለም፡፡ አዲስ አበባ ዘመድ ቢኖረውም፣ መጽሐፍ እንደ ቅንጦት ስለሚታይ የሚልክለት አላገኘም፡፡›› የተራብነው እህል ብቻ ከመሰለህ ተሳስተሃል ወዳጄ፡፡
ይህን የመሰለው የመጻሕፍት ቅቅት ለንባብ ቅርበት የነበረን የአብዛኞቻችን የታዳጊነት ታሪክ ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያዊ ስትሆን ሌላው በቀላሉ በየደጁ የሚያገኘውን መጽሐፍ፣ አንተ ገንዘብ ከፍለህ እንኳን ልታነበው ይቸግርሃል፡፡ ዛሬም ድረስ ሺህ ብሮች እንኳን ከፍዬ ላገኛቸው የማልችላቸው፣ ግን የምጓጓላቸው፣ ሌላው ባህር ተሻግሮ እንደ መስቲካ በየደጁ የሚሸምታቸው በርካታ መጻሕፍት አሉ። አንድ ጊዜ እንደዚህ ሆነ… የሔርማን ኼሰን ‹‹ሲድሐርታ›› (ከ2001-2006 ዓ.ም) በአምስት ዓመታት ውስጥ ለአስራ አንድ ጊዜያት ማንበቤን ለገጣሚ ታገል ሰይፉ ነገርኩት፡፡ ግርምት እንኳን ሳያሳይ፤ ‹‹እንግዲያውስ…›› አለኝ…
‹‹እንግዲያውስ የዚህን ደራሲ ሌላኛውን የአማርኛ ትርጉም መጽሐፍ ‹ዕድል ፈንታ› ፈልገህ ብታነብ፣ ሲድሐርታን ሊያስንቅህ ይችላል፡፡›› ድንገት ሞትን ከሚያህል ጥልቅ እንቅልፍ እንደባነነ ሰው ሆንኩ፡፡ ጉጉቴ መቅበዝበዝ የታከለበት ነበር፡፡ ሽፋኑን በቅጡ የማላውቀውን መጽሐፍ ሳስስ ወራት ተግተለተሉ፡፡ አንድስ እንኳ መጽሐፉን የሚያውቀው የመጽሐፍ ነጋዴ ማግኘት አለመቻሌ ግን ደንቆኛል፡፡ በመጨረሻ ተፈላጊው ዓሳ ወደ መረቡ ገባ፡፡ መጽሐፉን በሰላሣ ብር፣ ለዚያውም በብድር ገንዘብ ገዝቼ ስመለስ፣ የተሰማኝ ደስታ፣ በሕይወቴ ሁሉ ተሰምቶኝ የማያውቅ የሚፈነቅል፣ የሚያስፈነድቅ ነበር፡፡ እንዳልተገራ ፈረስ ዝልል ዝልል እያልኩ አግድሜ ስሮጥ፣ ከደስታዬ ብዛት አለማልቀሴንም እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ አትፍረዱብኝ፤ ከመንጋ ትርኪምርኪ ጥራዝ መሀል ነፍስን የሚዳስሱ መጻሕፍት እኮ ጥቂትና ብርቅ ናቸው፡፡ ማንበብ ቀዳሚ ጉዳይ መሆኑን አልስትም… ምን አነበብክ የሚለውም ግን ወሳኝ መሆኑ መረሳት የለበትም፡፡ ከንባብም ንባብ ይለያላ! የዚህን ሰው ሌላ መጽሐፍ The Glass bead Game መጽሐፍ አግኝቼ ለማንበብ ሌላ አምስት ዓመት መጠበቅ ነበረብኝ፡፡
‹ዕድል ፈንታን› በጥንቃቄ እጅግ በታላቅ ጥንቃቄ ሰባት ጊዜያት ያህል ከማንበቤም በላይ ሊያጣጥሙት ይችላሉ ላልኳቸው ከሰላሣ በላይ ወዳጆችም ጠላቶችም እየገዛሁ አድያለሁ፡፡ መፅሐፉ በአስራ ስምንት ብር የጀርባ ዋጋ ለገበያ ቀርቦ፣ በቅናሽ በስድስት ብር ተጩሆበት፣ ለማለቅ አስር ዓመታት ፈጅቶባታል፡፡ እንዲያም ሆኖ በየአሮጌ መጻሕፍት መደብሩ ሁሉ ዞራችሁ ብትጠይቁ፣ አውቀዋለሁ የሚል ነጋዴ ማግኘታችሁን እጠራጠራለሁ፡፡ ኩርማን በምታህል ርዕስ የተቀነበበ፣ ዘመናትን ሁሉ የሚያቅፍ የሚጋፋ፣ እንደ የረጋ ወንዝ የሚብሰከሰክ፣ ሕልውናዊ አርምሞ የታተመበት የጥበብ ገጽ…
ዘወትር በሌሎች የምመሰጥባቸው አስደናቂ የኪነት ሥራዎች ላይ እንደማደርገው፣ ላለፉት ስድስት ዓመታት የዚህን ሰው ሥራዎች አንድም ገጽ አንብቤ አላውቅም፡፡ ጊዜ ሳገኝ እያሳደድሁ የማነበው ይልቁንስ መረዳቴን ለመፈተን በመፈለግ፣ ከተለያዩ የዓለም ማዕዘናት፣ የዚህን ሰው ድርሰቶች የሚያጥላሉ የሚያጠለሹ ሒሳዊ ንባቦች ነበር፡፡ ይህን፣ በካሙ፣ ቤኬት፣ ካፍካ፣ ፒካሶ… ሌሎችም ላይ አድርጌያለሁ፡፡
ሌላ ዓለም አላውቅም፡፡ ሕይወትን በቅጡ መመዘን ከጀመርኩበት ከአስራ ሦስት ዓመቴ ጀምሮ በአስፈሪ ሽሽት የታጀበ የመናኝ ሕይወቴን የኖርኩት መጻሕፍት ውስጥ ነው፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ከላይ የጠቀስኩትን የሚቀራረብ የደስታ ስሜት ያስተናገድኩት፣ ከወራት በፊት በፎቶግራፉ ላይ የምትመለከቱትን የስነ ስዕል ማስተማሪያ መጽሐፍ፣ በሦስት መቶ ብር ብቻ የገዛሁ ጊዜ ነው፡፡ እኔ ሕይወትን ተጠቃላ ነጥብ አክላ ስረዳት ሦስት መከሰቻ መልኮች ብቻ አሏት፡- ቃል፣ ቀለምና ፊደል! ስለ ምንም ነገር አውሪኝ፤ እኔ የምረዳሽ ወደ እነዚህ ሦስት ንዑሳን የሕይወት መገለጫ አንጓዎች እየመነዘርኩ ነው፡፡ ለእኔ ሕይወት ከቃል፣ ቀለምና ፊደልም አንሳ ነቁጥ አክላ ትቅረብ ከተባለች፣ ዝምታ ብቻ ትሆናለች፡፡ በእኔ እምነት ቃል፣ ቀለምና ፊደል አንድም ሦስትም ናቸው፡፡ ሊኦናርዶ ዳቪንቺ እንዲህ ይላል፡- ‹‹Paintings is poetry that is seen rather than felt, and poetry is painting that is felt rather than seen.›› ዞሮ ዞሮ ያው፣ ፊደልና ቀለም መንታ ገጽ አልሽልኝ፡፡
የእኛው ገብረ ክርስቶስ ደስታ በበኩሉ፣ በ1962 ዓ.ም African Art በተሰኘው መጽሔት ስለ ድርብ ጠቢብነቱ (ገጣሚነቱና ሰዓሊነቱ) ተጠይቆ ሲመልስ እንዲህ ብሎ ነበር፡- ‹‹… ሁለቱ ጥበባት(ፊደልና ቀለም) የሚነጣጠሉ አይደሉም፡፡ ቢያንስ ለእኔ። እንዲያውም አንዱ ሌላውን ይረዳዋል። በቃላት ልገልጸው ያልቻልኩትን ነገር በቀለማት እሞክረዋለሁ፡፡ በምስሎች ላሰፍራቸው ያልቻልኳቸውን ሀሳቦች ደግሞ አንዳንዴ በቃላት መግለጹ ይሆንልኛል።…›› ዞሮ ዞሮ በቃል፣ በቀለምና በፊደል የምትመረገደው፣ የምትወከለው፣ የምትባለው፣ የምትከወነው፣ የምትዜመው ራሷ ኪነት ነች፡፡ ከላይ ያነሳነውን ሔርማን ሔሰን ጨምሮ ገብረ ክርስቶስ ደስታ፣ ሚካኤል አንጄሎ፣ ካህሊል ጅብራንን የመሳሰሉ በርካታ ጠቢባን ከቀለም ወደ ቃል፣ ከቃል ወደ ቀለም እንደመራቸው የሚቅበጠበጡ ደቂቀ ጥበባት ነበሩ፡፡
ታዲያ በቃልና በቀለም (በሙዚቃና በስዕል) ነፍሴ የምትርበተበተውን ያህል፣ ስለ እነዚህ ጥበባት ልጻፍ ባልኩኝ ጊዜ ያኔ ብዕሬ ትተሳሰራለች፡፡ እኔ ነፍስን የሚገዛ ሙዚቃ ከሰማሁ በኋላ #ጥሩ ነው; ብቻ ብለው እንደሚያልፉት ሰነፎች መሆን አልፈልግም፡፡ ልምሰጥበት (meditate) ልተነትነው እፈልጋለሁ፡፡
ለዓመታት ሙዚቃን በንድፈ ሀሳብ ደረጃ አጭር ኮርስም ቢሆን ለመማር ያላንኳኳሁት ደጅ አልነበረም፡፡ ሁሉም የሙዚቃ ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩት ግን የሙዚቃ መሳሪያዎች ልምምድ ብቻ ሆነ፡፡ በዓለም ታሪክ በቀዳሚነት ሙዚቃን አራቅቀው በኖታ የጻፉ ህዝቦች ሆነን ሳለን፣ ከመንግስታዊው ‹የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት› ሌላ አንድስ እንኳን የሙዚቃ ትምህርት ቤት የለንም፡፡ ቢያንስ በእኔ መረጃ… በየጋዜጣው በየኢንተርኔቱ የሚጻፈው ሁሉ ፍላጎትን ከማባባስ ውጭ የሚያጠረቃ ግንዛቤ የሚሰጥ አልሆነልኝም። እሱንም ከተጻፈ እኮ ነው… የትኞቹ ጋዜጦቻችን ናቸው አምድ ሰጥተው የበሰሉ የሙዚቃ፣ የስዕል፣ የዳንስ፣ የኪነ-ሕንጻ ወዘተ ሒሶችን የሚሰሩት? የትኞቹም!
ይህን መጽሐፍ በማግኘቴ ምክንያት ስለ ስነ-ስዕል ለመነሻ የሚሆን በቂ መረዳት ለመፍጠር የነበረኝ ጉጉት በማያሻማ ሁኔታ ተመልሶልኛል፡፡ ወደፊት ሌሎች ሺዎች ስዕልና ሰዓሊያንን የተመለከቱ መጻሕፍትን የማንበብ ፍላጎት ቢኖረኝም ቅሉ፣ ሁሉም የቅንጦት ንባቦቼ ይሆናሉ፡፡ ለመሆኑ የቀለማትን ያህል ኃያል ነገር ምን አለ? ስዕል ግን ከቀለማት፣ ከቅርጽ፣ ከጭብጥም በላይ ነው፡፡ ስዕል ማጠንጠኛ ምህዋሩ ሁሉ የዝምታ ጩኸት ነው፡፡ የሆነን ነገር በቃላት በገለጽሽው ቅጽበት፣ ያኔውኑ ለአለመግባባት በር ከፍተሻል፡፡ ትርጉሙን አዛብተሽዋል፡፡ ስዕልና ቅርጻ ቅርጽ ግን ይለያሉ፡፡ መከሰቻ ሁነታቸው የሆነ ዘለዓለማዊነትን የታከከ ረቂቅ ኑባሬ አለው፡፡ ከሺህ ቃላት አንድ ምስል ሲባል እኮ በምክንያት ነው፡፡
ስዕልን ከዘለዓለም ያነሱ ችኩል ሐሳቦችን ባሸከምሽው ጊዜ ያኔ ዘሙተሽበታል፡፡ ለፕሮፓጋንዳ አውለሽዋል፡፡ በጥልቀቱና ጊዜን በመገዳደር አቅሙ ስዕልን የሚበልጠው ዝምታ ብቻ ነዋ፡፡ ሆኖም ሂደቱ እንዲያው ትህፍስት (Harmony) የተሞላበት የሽርሽር ጉዞ ዓይነት አይደለም፡፡ ሲቃና ሰቆቃ ከግራና ከቀኝ የሚያላጉበት ጀብደኛ ጉዞ እንጂ… ፖሊሽ- ፈረንሳዊው ሰዓሊ Balthus እንዲህ ይላል፡- ‹‹painting is a source of endless pleasure, but also of a great anguish.›› ለምን አልከኝ? ሀዘን(ጭንቀት) እና ደስታ ወደረኞች ናቸዋ፡፡
አንተ ግን የክራሩን ክሮች በጣቶችህ ሳይሆን በነፍስህ ለመግረፍ ዝግጁ ካልሆንህ፣ አስቀድሞውኑ እዚህ ምን ትሰራለህ? ምክንያቱም ኪነት በእያንዳንዷ ጥቃቅን ኑረትህ ሁሉ የምትገለጽ የሕይወት መንገድ እንጂ የስራ ዘርፍ አይደለችማ! ከኪነት ከተወዳጀህ ቃል ኪዳኑን እንደሚሸከም ካህን መመረጥህን እወቀው፡፡ ጥቂት እንኳን መጓጓቱ ካለህ፣ የዓለምን የስነ ስዕል ልሂቅ በስስት ከሚነሳቸው ሁለት ወይም ሦስት ሰዓሊያን አንዱ የሆነውና በሕይወት ዘመኑ አንድ ስዕል ብቻ የሸጠውን የሰዓሊውን ቪንሰንት ቫን ጎ የመጨረሻ ስምንት ወራት የሚያሳየው አስደናቂ Biopic ፊልም At Eternity gate እንድትመለከት እጋብዝሃለሁ፡፡   
እኔ ግን ድምጽ ይሰማኛል፡፡ ከቃል፣ ቀለምና ፊደል ጋራ ምሽት፣ ተራሮች፣ ጊዜ፣ ወንዝ፣ ጥልቅ የሚያባባ ናፍቆት፣ መራመድ፣ sex, ዝምታና የጠየመች ሀዘን ሁሉ በአንድነት ሲነበቡ የሚያስተጋባ ውብ ሕብረ ዝማሬ ይሰማኛል፡፡ ነገርዬው ጥሪ ነው! ‹የነፍስ መፍገምገምን› የሚያስተጋባ ነጎድጓዳዊ ጥሪ። ቀርፋፋ ቢመስልም ጉዞው ግን ቀጥሏል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1506 times