Sunday, 06 June 2021 00:00

በድንጋይና በካቴና

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

    በዚያ ሰሞን አቦይ ስብሃት ነጋ በመከላከያ ሰዎች ታጅበው፣ እጃቸው በካቴና ታስሮ የሚያሳየው  ፎቶግራፍ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ተለቅቆ ዋና መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡ ፎቷቸው እውነተኛ ማንነታችንን ያሳየን ይሆን? የፍትህ አምላክና የሕግ የበላይነት ጨርሶ እንዳልጠፉ ያስታውሰን ይሆን? ሰዎች ስንባል ከንቱነት የሚያጅበን ፍጡራን ነን። የህወሓት መሥራቹ አቦይ ስብሃት፣ እርጅናቸው በዚህ መልኩ ይቋጫል ብሎ ያሰበ መኖሩ ያጠራጥራል፤ እርሳቸውማ ገና ለልጃቸው መንግሥት ይመኙ ነበር… መንግሥት ግን የእግዚአብሔር ነች!
ከዚህ ምን እንማራለን?  ወይስ በሰው ውርደት ጣት እንቀስራለን? በሰው ውርደት መጨፈር የተጀመረው፣ ደርግ በቀየሰው የመደብ ቅራኔ ዘመን ነው። ያ ቅራኔ በህወሓት ዘረኛ ፖለቲካ ተባብሶ መደበኛ የሆነ ይመስላል! ፈሪሃ እግዚአብሔርና የሰው አክብሮት ልታስተምር የተገባት ቤተ ክርስቲያን፣ ከአናት እስከ ጅራት ተበክላለች! ትምህርት ቤቶች፣ ለዝንጀሮና ለዘር ተረት ተረት መደናቆሪያ ከዋሉ ሁለት ትውልድ አሳልፈዋል። እነዚህ ተቋማት ሳይቃኑ እንደ አገር የትም አንደርስም! ጥያቄው ይህ ነው፦ መሪዎቻችን፣ ያፈቀዳቸውን አድርገው አንጠየቅም የሚሉን እስከ መቼ ነው? እኛስ እስከ መቼ ነው ድልድይ ከማነጽ ይልቅ  የምናፈርስ?
መሪ ለመሆን የሚሹ፣ በድንጋይና በካቴና ተሸላልመው ቃለ መሓላ እንዲፈጽሙ ቢደረግ፣ እንደ ሕዝብ ከመገዳደል ይልቅ መደራደር፣አዋርዶ ከመዋረድ ይልቅ መከባበር እንጀምር ይሆን? ድንጋይ፣ የሕዝብን አደራ ስለ መሸከም። ካቴናው ካቴና ነው!
ሦስት ተኲል መንግሥት ያዩ ጥቂት ሚሊዮን ዜጎች ዛሬም በሕይወት አሉ። በስድሳ ስድስት፦ እውነት በመስቀል አይሁን፤ በማጭድና በመዶሻ፣ በምንሽርና ባካፋ ይሁን አልን፤በሰማንያ ሦስት በብሔር በቤልጂግ አልን። ለሁለት ሺ አስራ ሦስት ምን እያልን ይሆን? ከዚህ ቀደም የሞከርነው አንዱም አልጣመንም፤ አንዱም አልጠቀመንም። ዛሬ ለዘር፣ ለንዋይና ለጥላቻ ሃይማኖት እንጂ ለቀጭን እውነት ቆሞ የሚመሰክር ተመናምኗል።
ሦስት ተኲል መንግሥት፦ የአፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት። የጓድ ሊቀ መንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም መንግሥት። የሳሔል እና የደደቢት (ገ) መንግሥት። የህወሓት/ኢሕአዴግ ሦስት ጒርድ መንግሥት፦ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ህወሓት “ኮሌክቲቭ”፤ (መጽሐፍ፦ ስለ አገሪቱ ዓመፀኝነት አለቆችዋ ብዙ ሆኑ ብሏል)፤ እና የዶ/ር ዐቢይ አሕመድ/ብልፅግና መንግሥት። የህወሓት ኲርፊያ ክልላዊ መንግሥት ራሱን የቻለ ታሪክ ስላለው፣ እናሳድረው። ከእነዚህ ሦስቱ አልፈዋል፤ በሽል ያለው ብልጽግና ፍጻሜው ምን ይሆን?
ዛሬም አልተማርንም። ጃንሆይ! በክብር ዙፋን ይልቀቊ ቢባሉ፦ አሳድገናቸው? (እንደ ሉሉ) ከእጃችን ላይ በልተው? ሕዝባችን እንዴት ይሆናል? ይህንስ አያደርጉብንም አሉ። ዘመን ጥሎአቸው እንደ  ነጎደ አላስተዋሉም። ለአልጋ ወራሹ ቀርቶ ለልጅ እንዳልካቸው መኮንን ሥልጣን ማዋስ አንገራገሩ። ይኸ ሲሆን ሻለቃ መንግሥቱና ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ በጭለማ ተቀምጠው ይዶልቱ ነበር። ወዲያው የጎባጣ ቮልስዋገን በር አዛጋ፤ ከዚያ ስድሳ እሩምታ ተሰማ! እሩምታው ባመቱ ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ሆነ! ጓድ መንግሥቱ ከአብዮት ኮረብታ ላይ ቆመው ግራ እጃቸውን አነሡ፦“ወይ እናት አገር ወይ ሞት!” አሉ፤ ሁሉም “ሞት!” ይሻለናል አለ፤ ሞት ተቸረው። እናት አገርን ያሰባት የለም! ለአስራ አምስት ዓመታት “በራዥ! አቆርቋዥ! ገንጣይ!” የወትሮ ፀሎት ሆነ። መንጌና አብዮቱ ታሪክ ቀድሟቸው፣ ወደ ኋላ እንደቀሩ ግን አላስተዋሉም። ደፍሮ የሚናገራቸው አልተገኘም፤ በፍጻሜ ላይ ብቻ ለምልክት ሦስት ተገኙ!
ያልታሰቡ፣ አንደበተ ርቱዑ አእምሮ ፈጣኑ ለገሰ፣ የህግ ስማቸውን ሰውረው መለስ አሉ። ለጋሱ መለስ፣ ከእንግዲህ በቀን ሦስቴ ትበላላችሁ ሲሉ ቃል ገቡልን። ተስፋ ለማድረግ ወይም ለመሳቅ ቸገረን። ቆይተው፦ “ያለ ህወሓት ብትሉ ግን መንገዱን ጨርቅ ያርግላችሁ፤ ማይ ዌይ ኦር ዘሃይ ዌይ! ያለ እኔ(ያለ ህወሓት) ዩጎዝላቪያ ነው መንገዱ፤ ሩዋንዳ ነው፤ ሶማልያ ነው፤ ቃሊቲ ነው፤ ኲርባጅ ዥዋዥዌ፤ ቂሊንጦ ነው፤ እርሳስ ነው። ከእኔ (ከህወሓት ጋር) ኮርያ ማሌዥያ፣ ጃፓን፣ ቻይና፣ ኤዥያ፣ ብሩህ ነው መንገዱ!” ማለት ጀመሩ።
ኃይለሥላሴ ያሉትን ብለው እንዳበቊ፣ ጨላልሞ ስለነበር አዳራቸውን ወደ አልጋቸው ወጡ፤ ሲነጋ የሆነውን ለማየት አልበቊም! የንጉሥ ሬሣ የገባበት ጠፋ። መለስ በአሜሪካኖች እርዳታ ከታላቅ ወንድማቸው ከኢሱ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው (አህያ አስቀድመው፣ ኦነግን፣ አዴፓን፣ ደቡብ ንቅናቄን በአሽከርነት አስከትተው፣በዑመር በሽር ጦርና መንፈስ) መናገሻዪቱን በጭለማ ወረሩ። የደርግን የጥይት ግምጃ ቤት ከጫፍ ጫፍ ድል! ድም! ደምደም! አደረጉት! መጥተናል! መጥተናል! ነው። በነጋታው የየሰውን ደጅና የዘር ኮቴ እየዞሩ አንኳኩ፤ በረበሩ! ለእነርሱ ፈንጠዚያ፣ ሲንገላታ ለኖረ ሕዝብ ስጋትና የትንቢት ቀጠሮ ነበር!
መለስ “መጪው ዘመን ብሩህ ነው!” ባሉ በሁለተኛው ዓመት በስውር ካገር ወጡ። ወጥተው የገቡበት ጠፋ። ከሁለት ወር በኋላ ቤልጂግ ሆስፒታል አልጋ ይዘው በቴሌቪዥን ታዩ። ይገርማል፣ ታመውም እንኳ ላገር ከመሥራት አልቦዘኑም! የሕዝባቸውን ስጋት ለማርገብ፦ "ህክምናችንን እንደ ጨረስን ወደ ምንወዳት አገራችን፣ ወደ ምንወደውና ወደ ሚወደን ሕዝባችን እንመለሳለን" አሉ።
ነሐሴ ፲፭/፳፻፬ በኢትዮጵያ ባንዲራ የተጠቀለለ የሬሣ ሣጥን፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጭኖ በጭለማ ቦሌ ደረሰ። ሣጥኑ ውስጥ መለስ አሉበት ተባለ፤ ሣጥኑ ውስጥ ለመኖራቸው ግን እርግጠኛ መሆን አልተቻለም። መለስ፣ እንደ አፄ ኃይለሥላሴ፣ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተቀበሩ። መካነ መቃብራቸው ማንም እንዳይደርስበት ቶሎ በእብነበረድ ታሸገ፤ የሥላሴ ደጅ በጠብመንጃና በሰንሰለት ታጥራ ከረመች። እርግጥ ነው፣ ኢትዮጵያዉያን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሬሣ መቆፈር ስላበዛን መጠንቀቁ አልከፋም!
ጓድ መንግሥቱ ያልሸኟቸውን፣ ያስተናገዷቸውን፣ ጥርስ የነከሱባቸውን፣ የጎሪጥ ያዩዋቸውን አንድ ባንድ ሸኛኝተው አሁንም በሕይወት አሉ! አርበኞች ጓዶቻቸው የጣልያን ጥገኛ ሆነው ከረሙ። አንዳንዶችም በስኳር፣ በአልኮልና በበርጩማ አለቊ።
መለስን፣ "ከወቅቱ ጋር ይራመዱ እንጂ፣ ሥልጣን አጋሩ እንጂ" ቢሏቸው፦ (እንደ አፄ ኃይለሥላሴና እንደ ጓድ ሊቀ መንበር መንግሥቱ) "ያለ እኛማ አይሆንም እኮ! አላወቃችሁም? ይልቅ የጀመርነውን እንጨርስ፣ ሥራ አታስፈቱን" አሉ። ህወሓት ሕዝብ ባስመረረ ቊጥር፣ አገሪቷን በሸነሸነ፣ ዘር ዘር ባለ ቊጥር፣ የጃንሆይ “ኢትዮጵያ ሆይ!” እና የመንግሥቱ ኃይለማርያም “ኢትዮጵያ ትቅደም!” ገበያቸው ደራ! ፈጣሪ የትኛውን በጎ ሥራ አይቶላቸው ይሆን? ይኸው፣ ያፈናቀሏቸው ተፈናቅለው፤ ከዋሻ ዋሻ ተንዘላዝለው፤ ለሌሎች በቆፈሩት ቃሊቲ ተጥለዋል። ወደ ኢምፔሪያሊስት አሜሪካና ወደ ደደቢት ተሰድደዋል። መንጌ ከዚምባብዌ እልፍኛቸው ይህን ሁሉ እያዩ (የሚናፍቊትን፣ የሚናፍቃቸውን ሕዝባቸውን እያሰቡ)፣ በፈገግታ፣ “ጓድ ስታሊን እንዳለው፣ እጠቅሳለሁ፦  ‘ይኸ ታሪካዊ ሂደት ነው!’” ሳይሉ አልቀረም! ይባስ፣ እርሳቸው ባቀጣጠሉት አብዮት፣ በአደባባይ አድኃርያንና ቀልባሾችን በጠርሙስ በቆሉበት፣ በስድሳ ስምንት በሻሻ ላይ የተወለደላቸው ወንድ ልጅ፤ በተሰደዱ በሠላሳ ዓመት፣ በእርሳቸውና በ“ኢትዮጵያ ትቅደም” ላይ ያሤሩትን ይበቀልላቸው ጀመር! ይህን በረከት ወይስ እርግማን እንበል?
እንዲያው ምንም አልተማርን? ስለ ሰው ከንቱነት? ስለሥልጣን ጊዜያዊነት? ስለ እግዚአብሔር ፍርድ? ምንም አልተማርን? ከአፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት። ከጓድ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም መንግሥት። ከሳሔል እና ከደደቢት (ገ)መንግሥት። ከህወሓት/ኢሕአዴግ ሦስት ጒርድ መንግሥት፣ ከህወሓት ኲርፊያ ክልላዊ መንግሥት። ምንም አልተማርን?
ሦስት ትውልድ፣ከረሃብና ከሰቆቃ እንቅልፍ ስንነቃ፣ ያልታሰቡ ሰዎች ጭለማ ለብሰው መንበር ላይ ቂብ ብለው አገኘናቸው! ሥልጣን አልለቅ ብለው አሰለቹን! ሞት ደርሶ ባይገላግልማ ከነልጅ ልጆቻችን ባርያ ባደረጉን!
ከሚያሠቃዩን እጅ ከሞት በስተቀር የሚገላግል የለም ማለት ግን አይደለም! ዋነኛው ገላጋይ ፀሎት ነው፤ ፀሎት! ፀሎት! ፀሎት! ሌላኛው ገላጋይ፦በሚኒስትር ደረጃ የሚሾሙ ሁሉ ቃለ መሓላ ከመፈጸማቸው አስቀድሞ ለወር ከርቸሌ ይክረሙ! በሳምንት ለአንድ ሰዓት ዥዋዥዌ ይለማመዱ! ሚስቶቻቸውም ወዲያው ስንቅ ማቀበል ይማሩ! ልጆቻቸው ያለ አባት፣ያለ እናት፣ያለአይፓድ ማደግ ይልመዱ! ወሩ ሲያበቃ፣ እጩዎቹ የእስረኛ ልብስ ለብሰው፣ በጫንቃቸው ድንጋይ ተሸክመው፣እጅ እግራቸው በካቴና ተጠፍሮ በሕዝብ ፊት ቃለ መሓላ ይፈጽሙ!
በዚህ ሰዓት፣ ወደ ሥልጣን እርካብ ለመውጣት አኮብኲበው፣ የዳኛ ብርቱካንን ፊሽካ የሚጠባበቊ ፓርቲዎች ቊጥር 50 ገደማ ደርሷል። የ50ዎቹ  ሤራና ግርግር እውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ምኞትና ምቾት ለማሳካት ነው? እንግዲያውስ በድንጋይና በካቴና ቃለ መሓላ ይፈጽሙ!
(ምንጭ፡- ኢትዮጵያን ኦብሰርቨር)


Read 2779 times