Saturday, 05 June 2021 13:19

የጉራጌ ልማት ማህበርና ዳይሬክተር ስለ ልማት ያወራሉ…

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 ማህበሩ ከ99 ሚሊዮን ብር በላይ ሃብት አለው

               ኬሮድ በቅርቡ በወልቂጤ ባዘጋጀው የጎዳና ላይ ሩጫ ማህበራችሁ የሰጠውን ድጋፍና በአጠቃላይ በስፖርቱ ውስጥ ያለውን ተሳትፎ በመግለፅ ውይይታችንን ብንጀምርስ…
ኬሮድ የአትሌቲክስና ልማት ማህበር ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ዋና አጋሩ ሆኖ የቆየው የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር ነው። በጎዳና ላይ ሩጫውም በሙሉ ሃላፊነት ሚናውን ተወጥቷል፡፡ ኬሮይድ በአዲስ አበባ የሚሰራበት ቢሮውን ያገኘው ከማህበራችን ነው፡፡ በወልቅጤ ደግሞ  በከተማዋ ዙርያ ወጣቶችን ላይ መልምሎ የሚያሰለጥንብትን ማዕከል የሚደረጅበትን ልማት ሰጥተናል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከዞኑ ትልልቅ አትሌቶች እየወጡ ናቸው፡፡ አትሌቶቹን ከልማት እንቅስቅሴያችን ጋር ለማስተሳሰር እንፈልጋለን፡፡ አካባቢው ለሩጫ ስፖርት የሚሆን ቶፖግራፊ አለው፡፡ በአሁን ወቅት በዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ውድድሮች የተሳካላቸውና በኦሎምፒክ የሚጠበቁ አትሌቶች መኖራቸውም ያነሳሳናል፡፡ ከኬሮድ ጋር በአጋርነት የምንሰራውም አካባቢው በአትሌቲክስ መልማት እንደሚችል ስላመንንበት ነው፡፡ ስፖርቱን ሊያድግ  የሚችለው ለማህበረሰቡ በአካባቢው የማሰልጠኛ ቦታ ሲገነባ ነው፡፡  ያለ ምንም ወጭ ያለምን ክፍያ ለማሰልጠኛ ካምፕ የሚሆነውን መሰረተ ልማት ሰጥተናቸዋል። በማሰልጠኛው አትሌቶች ገብተው በቂ ልምምድ እንዲሰሩበት ነው፡፡ በጎዳና ላይ ሩጫው ይህን አቅም ማስተዋወቅ ተችሏል። የስፖርትና ኮሚሽነርና የአትሌቲክስ ፌደሬሽን በከተማችን በመገኘታቸው መስተዳደሩ የማሰልጠኛ ማዕከል እንዲገነባ ጥሪ አድርጓል፡፡ በከተማዋ ግዙፍ የስፖርት እና የባህል ፌስቲቫሎችን በማዘጋጀት የጉራጌ ማህበረሰብ እንደመስቀል ሁሉ ወደ አካባቢው በብዛት የሚመጣበትን ሁኔታ ነው ወደፊት መፍጠር የምናስበው፡፡
እስቲ ስለ የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር በአጭሩ ይግለፁልኝ
የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር የተቋቋመው የማህበረሰቡን ዘርፈ ብዙ ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ነው፡፡ ማህበሩ ከተመሰረተ 12 ዓመታት ሆኖታል፡፡ እንደተቋቋመ ባወጀው ቴሌቶን በርካታ የልማት ስራዎችን አከናውኗል፡፡ ቴሌቶኑ ለብዙ የልማት ማህበሮች እንደ መነሻ ሆኗል፡፡ የገቢ ማሰባሰብ እንቅስቃሴን  በአገር አቀፍ ደረጃ አስተዋውቋል፡፡ በቴሌቶኑ ከጀመርናቸው የልማት ስራዎች  አንዳንዶቹን በማህበራችን አቅም እየሰራናቸው ነው፡፡  የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል ተብሎ ስራ የጀመረው ግዙፍ ልማት ያዘጋጀነው በቴሌቶን ውጤት ነው፡፡ ማህበራችን የሆስፒታሉን ግንባታ አስጀምሮ በርካታ  ምዕራፎችን ካለፈ በኋላ ለዩኒቨርስቲው አበርክቶታል፡፡ ዩኒቨርስቲው ከመሰረተልማቱ  አቅራቢያ ያለ እንደመሆኑ የበለጠ ሊሰራበትና ሊጠቀምበት ይችላል። የህክምና አገልግሎት መስጭያ፤ የምርምር ማድረጊያ፤ ማስተማርያ መማርያ እንዲያደርገው፣ ለወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ፈቅደንለታል፡፡ ቡታጅራ ላይ ትልቅ  ህንፃ ገንብተን በተወሰነ መልኩ ስራ አስጀምረነዋል፡፡ አዲስ አበባ ላይ ልደታ አካባቢ በ2570 ካሬ ላይ ያረፈ የህንፃ ግንባታ ጀምረን ገና በዚህም ባናጠናቅቅም እየሰራን ነው፡፡
የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር አባላቱን በማስተባበርና በልማት ስራዎች ላይ ይሳተፋል፡፡ በሁሉም ወረዳዎች  አባላቶች ሰብስበናል፡፡ የመንግስት ሰራተኛው አርሶ አዳሩም አብረውን ናቸው፡፡ ማህበሩ ከሚሰበስበው መዋጮ 70 በመቶውን በየወረዳው ላይ ለሚከናወኑ ስራዎችን እንዲሁም እንደየፍላጎታቸው እንመድባለን። 30 በመቶውን ተቋም ለማስተዳደር የምንጠቀምበት ነው፡፡ ከዚያ በተረፈ ሌሎች ረጂ ድርጅቶች በማፈላለግ የልማት ስራዎችንም እንሰራለን፡፡ አሁን በቅርቡ ግሊመር ኦፍ ሆፕ ከተባለ ረጂ ድርጅት ጋር ተፈራርመናል፡፡ ደቡብ ሶዶ ላይ በ6 ወር የሚጠናቀቁ 16 የውሃ ጤና  እንዲሁም የትምህርት ፕሮጀክቶችን ለማከናወን ጨረታ አውጥተን ስራዎችን ጀምረናል። በሁሉም ወረዳዎች የጤና ኬላዎችንና ጣቢያዎችን በመገንባት የውሃ መስመሮችን በመዘርጋት ማህበራችን እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
ማህበሩ ከተቋቋመ ከሶስት ዓመት በኋላ የጀመረው ‹‹ጉዞ ወደ የአረንጓዴ ልማት›› የሚለው ፕሮግራምም አለ፡፡ በየዓመቱ በእያንዳንዱ ወረዳ የማህበሩን  አባላት በማስተባበር ችግኝ የመትከል ዘመቻ እናካሂዳለን ፡፡ ይህም አካባቢን መጠበቅ የማህበረሰቡ ተጨማሪ ባህል እንዲሆን ማድረግ ችለናል፡፡  የችግኝ ተከላውን ዘንድሮ ለዘጠነኛ ግዜ ነው ያከናወነው። ዓላማችን  ማህበረሱን ማቀራረብና በሁሉም ቦታ ሞዴል ሆኖ እንዲወጣ ነው። ውጤትም እያገኘን ነው፡፡ በስምንት ወረዳ ያከናወናቸው የችግኝ ተከላዎች ከ85 በመቶ በላይ እየፀደቁ ናቸው፡፡ የተተከሉ ችግኞችን ማህበረሰቡ እንዲንከባከብና እንዲጠብቃቸው ሃላፊነቱን ሰጥተናል፡፡ አካባቢውን እንዲያለማም እያስተባበርን ነው፡፡
ሌሎች የማህበሩ ተምክሮዎችስ…
የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር ከሌሎች ማህበራት ልዩ የሚያደርገው የመንግስት ድጋፍ ብዙ የለውም፡፡ ሌሎች የልማት ማህበሮች በአብዛኛው ስራዎቻቸውንና የሚያከናውኑት ከመንግስት በሚያገኙት  የተሟላ የበጀት ድጋፍ ነው፡፡ የጉራጌ ልማትና ማህበር ዛሬ በኦዲት የተጠና ሪፖርት ላይ እንደተቀመጠው ከ99 ሚሊዮን ብር በላይ ሃብት አለው፡፡ ይህ ሃብት በማህበረሰቡ ተሳትፎ የመጣ ሲሆን፤ ቡክ ቫሊውን ይዘህ ይህን ሃብቱን ወደገበያ ብታወጣው፣ ሶስት እጥፍ ይሆናል፡፡ ማህበረሰቡ በራሱ የገቢ ማስገኛ ተቋማትን አዋጥቶ በመገንባት፣ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡
በአሁን ወቅት ማህበሩ ወልቂጤ ከተማ ላይ ትልቅ ጋራዥ አለው፡፡ በዋናነት ለመንግስት ተቋማት አገልግሎት እየሰጠ ቢሆንም፤ ማንኛውም ህብረተሰብ አገልግሎቱን መጠቀም ይችላል፡፡ ለጥገና ሲባል መኪኖች ረጅም ርቀት ወደ አዲስ አበባና ሃዋሳ በመጓዝ ለሌላ ችግር እንዳይጋለጡ ነው ታስቦ በቅርባቸው የጥገና አገልግሎት የሚያገኙበት ሆኗል ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡ በጋራዣችን ጥራት ያለው ጥገና እየሰጠን እንገኛለን፡፡ በዓመት እስከ 200 መኪናዎችን ከቀላል እስከ ከባድ የጥገና አገልግሎት የምንሰጥበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ ወደሩቅ ከተማዎች በመሄድ ሊወጣ የሚችለውን አስተዳደራዊ ወጭ ይቀንሳል፡፡ ከጤናው ዘርፍ በተያያዘም ማህበራችን በርካታ የጤና ተቋማትን ገንብቶ ለማህበረሰቡ አስረክቧል፡፡ በቅርቡ ከፊስቱላ የህክምና አገልግሎት ጋር በተያያዘ የጀመርነው አሰራር አለ፡፡ ሴቶች ፤ እናቶች አስፈላጊውን ማስረጃ አቅርበው አዲስ አበባ ሄደው የሚታከሙበትን የትራንስፖርት ድጋፍ በመስጠት ከጤና ጣቢያዎች ጋር እየሰራን ነው፡፡
በመንግስት ደረጃ ሙሉ ድጋፍ ሳይኖረው ማህበረሰቡ በራሱ ብቻ እንዲህ መስራቱ፣ ማህበራችንን ልዩ ያደርገዋል፡፡ የልማት ማህበሩ አካባቢውን በመንከባከብና በመጠበቅ ትልቅ አስተዋፅኦ እያደረገ ነው፡፡ በዞኑ ውስጥ እና ከዞኑ ውጭ ያለውን ማህበረሰብ በማስተባበር ነው የምንተዳደረው፡፡
ማህበሩ ያሉት አባላቶች ብዛት ስንት ይሆናል ወደፊት ለማከናወን የያዛቸው እቅዶችና አቅጣጫዎች ምን ይመስላሉ?
በአሁን ሰዓት ከ450 ሺህ በላይ አባላቶች አሉን፡፡ አብዛኛዎቹ አባላት በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ ሲሆን በድሬዳዋ፤ በሃረር፤ በአዲስ አበባ፤ በሃዋሳ ላይአባላቶችን ይዘናል፡፡ በተለያዩ የውጭ አገራትም ዲያስፖራውን በማንቀሳቀስ እየተስፋፋን ነው፡፡ ሳኡዲ አረቢያ ላይ በየዓመቱ መዋጮ ሰብስበው ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉ አባላት አሉን፡፡ በቅርብ ጊዜ ደግሞ በመላው አሜሪካ የብሄረሰቡን ተወላጆችና ደጋፊዎች በማነሳሳት አባሎችን አፍርተን መዋጮ እየሰበሰብን ነው፡፡ እቅዳችንን የማህበሩን አባላት በእጥፍ ማሳደግ ነው፡፡
ማህበሩ በጉራጌ ዞን በአምስት ከተማ አስተዳደሮችና በ14 ወረዳዎች ላይ ይሰራል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ሁሉም አባላቶቻችን ወርሃዊ መዋጮዎችን የሚከፍሉ ናቸው፡፡ በሁሉም ወረዳዎች በጤና፤ በትምህርት፤ በውሃ፤ በአቅምን ግንባታ ስራዎች እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ በየዓመቱ  ቢያንስ ሶስት የልማት ስራዎችን በየወረዳው ስናከናውን እስከ 3ሺ ሰው እንዲጠቀም እናደርጋለን፡፡ በከተማው ማህበሩ ከሚያንቀሳቅሰው ጋራዥ ባሻገር  ገስት ሃውሶችም አሉት፡፡ ሁለቱም በወልቂጤ ከተማ የሚገኙ ናቸው፡፡ ከገስት ሃውሶች የምናገኘው ገቢ ለልማት ስራዎች ነው የምናውለው፡፡ በ14ቱም ወረዳዎች የምንሰራው አባላት በሚሰበስቡት፣ ሃብት በሚፈልጓቸው የፕሮጀክት እቅዶች ላይ ተንተርሰን ነው፡፡ ከረጂ ድርጅቶች በምናገኘው ፋይናንስ ግን በተወሰኑ 6 ወረዳዎች ነው መስራት የቻልነው።  ስለዚህም በየወረዳው የሚያስፈልጉትን ልማቶች በማጥናትና በማጥራት፣ ከረጂ ድርጅቶች በምናገኘው ድጋፍ እንሰራለን፡፡
ከወልቂጤ ባሻገር እንቅስቃሴያችሁ እንዴት ነወ?
ቡታጅራ ላይ የገነባውን ህንፃ ምድር ቤቱን ጨርሰናል፡፡ እስካሁንም ለ14 ድርጅቶችና ተቋማት አከራይተን ገቢ እያገኘን ነው። ለሱቆች፤ ለባንክና ለሆቴል አገልግሎት የሚሆን ነው፡፡ በቀጣይ ሙሉ ግንባታውን ጨርሰን ከተማውንና ማህበረሰቡን በልማቱ ተጠቃሚ የሚሆንበትን እድል እንደጥራለን። በማህበራችን  በኩል የመንግስትን የልማት ክፍተቶችን እየተመለከትን በምናገኛቸው አማራጮች እየሰራን ነው፡፡
በወልቂጤ ከተማ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎች አሉ… እንዴት ይገለጻል?
ከዩኒቨርስቲውና ከሆስፒታሉ ጀምሮ እንዳይችሁት ጥሩ እድል ያለበት ነው። ማህበረሰቡ ስራና ስራን ብቻ ባህሉ ያደረገ፣ ሰርቶ መለወጥን በአገር አቀፍ ደረጃ ያስተማረ፤ የተረጋጋና ሰላም ያለበት ነው። በተለያየ መልኩ እዚህ አካባቢ መጥቶ መስራት የሚቻልባቸው እድሎች አሉ፡፡ ከተለያዩ ፖለቲካዊ ንትርኮች እና የዘረኝነት ችግሮች የወጣ ማህበረሰብ መሆኑን እንመለከታለን፡፡ ሁሉም ማህበረሰብ በነፃነት ያለምን ችግር ሰርተው ሊኖሩበት የሚችል አካባቢም ነው፡፡ ባለሙያውም፤ ባለሃብቱም መጥቶ መስራት ይችላል፡፡
የጉራጌ ህዝብ፤ ቢዝነስና አገር አቀፍ ተምሳሌትነቱ
የጉራጌ ብሄረሰብ በንግድ ስራ በመላው ኢትዮጵያ ላይ ሞዴል የሆነ ማህበረሰብ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆንም በሌሎች አገራትም የብሄረሰቡ ተመክሮ ቢቀመር እና ቢስፋፋ ይጠቅማል፡፡ ፈረንጆች ንግድ ከስክራች ይጀመራል ብለው ይናገራሉ። ይህ ማህበረሰብ ሳይማር ወይም ስልጠና ሳያገኝ ንግድን ከ0 ጀምሮ በመስራት በተግባር ያሳየ ነው፡፡ በመላው ኢትዮጵያ ተሰማርቶ ከሊስትሮ፤ ጀብሎ ከማዞር፤ አንስቶ እስከ ትልልቅ ህንፃዎች ግንባታ ኢንቨስትመንቶች ድረስ የተሰማራ የሰራ ማህበረሰብ ነው፡፡ ከ0 መጀመርን ያውቃል፤ ሰርቶ መለወጥን ለሌሎች አስተምሯል። በንግዱ እንደሞዴል የሚታይ ቢሆንም የጉራጌ ልማት በዚያ ደረጃ የሚመጥን ሆኖ አናገኘውም፡፡ አዲስ አበባ ላይ  እንዲሁም በሌሎች ከተሞችን ደብረዘይት፤ አዳማ ላይ ያለ በጉራጌ ባለሃብቶች ሃብትና ንብረት ከፍተኛ ቢሆንም፣ የጉራጌ አካባቢ ያለው ልማት ያን ያህል የሚያረካ አይደለም። የጉራጌ ልማት እና ባህል ማህበር ስራ አስኪያጅ እንደመሆኔና በአካባቢው ላይ በተለያዩ ስራዎች እንደተሰማራ ሰው እዚህ ጋር የማነሳው፤  ዞኑ በክልል ደረጃ አለመደራጀቱ ተፅእኖ አሳድሮበታል የሚለው ነው፡፡ በመላው ኢትዮጵያ በተለያዩ ከተሞች የጉራጌ ማህበረሰብ በመጠነ ሰፊ ኢንቨስትመንቶች የመሰማራቱን ያህል እንደመሰማራቱ በዞኑ ላይ ግን የኢንቨስትመንት ፍቃድ በመስጠት እየተሰራ አይደለም፡፡ ትልልቅ የኢንቨስትመንት ፍቃዶች ሲጠየቁ፣ በዞን ደረጃ ሰርተህ ኢንቨስትመንትን የምታስፋፋበት እድል የለም፡፡ ለነጋዴው ህብረተሰብ ውጤታማ እድሎችን ለመፍጠር አልተቻለም። በሌሎች ክልሎች ሰርቶ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው የመንግስት አስተዳደር፤ መንግስታዊ አገልግሎቶችን ስለሚያገኝ ነው። አሁን በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ፈቃድ ለማግኘት የምትሄደው ሃዋሳ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት አዲስ አበባ ላይ መስራቱን የአካባቢው ማህበረሰብ አማራጭ አድርጎታል፡፡ በተፈለገው ደረጃ አካባቢያችን ሊለማ ያልቻለው አስተዳደሩ በዞን ደረጃ በመወሰኑ ነው፡፡
መንግስት አሰራሩን ለመቀየር የሚችልበት እድል የለም ማለት ነው?
አዎ አለ፡፡ መንግስት እነዚህን አሰራሮች ሊያቀል የሚችልው የራሱ አስተዳደር ክልል ሲኖረው ነው፡፡ የአካባቢው መንግስት ኢንቨስትመንት እዚህ መጥቶ ሲጠየቅ ራሱ መስጠት ይችላል፡፡ ሌሎች ረጂ ድርጅቶች ሲመጡ ራሱ ውል መፈራረም ይችላል፡፡ አሁን ረጂ ድርጅቶች ሲመጡ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ከሆነ በዞን ደረጃ መፈራረም አይችልም፡፡ ኢንቨስትመንት በዞን ደረጃ ማንቀሳቀስ እይቻልም፡፡ እነዚህ አሰራሮች ካልተስተካከሉ፣ እዚህ አካባቢ ላይ ማህበረሰቡ ሌላ አካባቢ በሚሰራበት ልክ ሊንቀሳቀስ አይችልም፡፡
የጉራጌ ማህበረሰብ በመላው ኢትዮጵያ በሌሎች የውጭ አገራትም በስጋት መስራት ከ0 ጀምሮ ሰርቶ የአካባቢውን ማህበረሰብ መስሎና ተመሳስሎ የሚኖር ነው፡፡ እድርን በኢትዮጵያ ታሪክ ለማህበረሰብ ያበረከተ ነው፡፡ እቁብን በኢትዮጵያ ታሪክ በፋይናስ ተቋማት የብድር አገልግሎት ባልነበረበት ዘመን ፈጥሮ እቁብ ሰብስቦ እንዴት ተደጋግፎ ማደግ እንደሚቻል ለኢትዮጵያ ህዝብ ያስተዋወቀ ነው፡፡ አትዮጵያ ውስጥ በከተሞች ልማት ላይ የጉራጌ አሻራ ያለረፈበት የለም፡፡ ጉራጌዎች በየከተሞቹ ስሄዱ ከምንም ይጀምራሉ፡፡ ከሊስትሮ፤ ሰልባጅ በማዞር ይጀምሩና ቀን ከሌት ደከመኝ ሳይል እየሰራ ገቢውን እያጠራቀመ ራሱን ያሳድጋል፡፡ በአካባቢው ላይ ሱቅ ይከፍታል፤ ቡቲክ ይከፍታል፤ ሆቴል ይከፍታል፡፡ ከትንንሽ ንግዶች ጀምሮ እስከ ትልልቅ ኢንቨስትመንቶች ላይ ይሰማራል፡፡ ስልዚህም በአካባቢው መጥቶ በዚህ መልክ ሊሰራና ሊያለማ የሚችልበትን እድል አላገኘም፡፡ ነጋዴ መንገድ አይገነባም፤ ነጋዴ መብራት አያስገባም፣ ነጋዴ ስልክ እየዘረጋም እነዚህን መሰረተ ልማቶች ሲሟሉ፣ ነጋዴው ማህበረሰብ ሆቴል ይከፍታል፤ ሌሎች ኢንቨስትመንቶች ላይ ይሰማራል፡፡ የጉራጌ ዞን ከአዲስ አበባ 150-200 ኪ.ሜትር ተጉዘህ መጥተህ በሳምንት እንኳ ውሃ የማታገኝበት ነው፡፡ መብራት የሚባል ዞር ያለለበት ከተማ ነው የምታገኘ፡፡ ባለሃብቱ መጥቶ እንዲሰራ የመንግስት አካሉ የመሰረተ ልማቶች ላይ ችግሮች በመፍታት አለባቸው፡፡
በጉራጌ ዞን ካለው ሰላም፡ ስራ ወዳድ ብዛት ከሌሎች ምቹ ሁኔታዎች አንፃር  አስተዳደራዊ ምፍትሄ ያስፈልጋል፡፡


Read 1464 times