Monday, 07 June 2021 00:00

አስገራሚ አገር - አሜሪካ

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

  የስልጣኔ ውጤት ናት አሜሪካ፡፡ ከእውቀት ዘመን የተገኘች ደማቅ ፋና፣ ለእውነታ ከሚታመን አእምሮ የፈለቀች፣ ድንቅ አገር ናት፡፡ the age of reason enlightenment እንዲሉ፡፡
የስልጣኔ ውጤት ሆነች ማለት ግን፣ በአንዳች ቅጽበታዊ ሃይል፣ ተለወጠች ማለት አይደለም፡፡ ጭፍንነት፣ መከራና ውርደት ከበዛባት የኋላ ቀርነት ጨለማ ዓለም ውስጥ ተስፈንጥራ ወጣች ማለት አይደለም። በአንድ ዝላይ ወደ ብርሃናማ የእውቀት ዓለም ተሻገረች ማለትም አይደለም፡፡ ወደ ምርታማ የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የግል ንብረት ወደ ሚከበርበት የብልጽግና አለም ተቀየረች፤ የእያንዳንዱ ሰው የግል ህልውና ወደ ሚከበርበትና  የሕግ የበላይነት ወደ ሰፈነበት ወደ አዲስ ሰላማዊ ዓለም ዘልቃ ገባች ማለትም አይደለም፡፡
ይልቅስ፣ፋና ወጊ የስልጣኔ ተጓዥ ለመሆን የበቃች አገር ናት፡፡ የኋላ ቀርነት ገፅታዎችና መዘዞችን የማስወገድ፣ ጨለማውን የመቀነስ ነው- የስልጣኔ ጉዞው፡፡ በጨለማና በጠማማ ጉራንጉር ምትክ ብርሀናማና የተቃና መንገድ እየከፈቱ፣ የስልጣኔ መስኮችን እያስፋፉ፣ የጥረት ውጤትና፣ የስራ ፍሬዎችን የማበርከት ረዥም ጉዞ ነው የስልጣኔ ጉዞ፡፡
የኋላቀርነት ጨለማ፣ በአንድ ምሽት፣ ከሁሉም ቦታ አይወገድም፡፡ የስልጣኔ ብርሃን፣ በአንድ ንጋት በሁሉም ቦታ አይደምቅም፡፡
ለክፉም ለደጉም፣ ወደ ኋላቀርነትም ሆነ ወደ ስልጣኔ፣….ዘው ብሎ አይገባም። ነገር ዓለሙ ሁሉ በአንዴ ድግም ብሎ አይጠፋም ድንገት ቦግ ብሎ አይበራም፡፡ ቀስ በቀስ እየደበዘዘ፤ ወደ ጨለማ ወይም እየፈካ ወደ ብርሀን የሚያመራ ጉዞ፡፡ ቀስ በቀስ፣እየለመለሙ እየፈኩ፣አልያም፣ እየጠወለጉ እየደረቁ፤ ማዝገም ነው የታሪክ ጉዞ…. ወይ ፍሬያቸውን አሳምረው ያበረክታሉ፤ ወይ ፍሬያቸውን አምክነው እየረገፋ አፈር ይሆናሉ፡፡ በአንዴ ሳይሆን፣ውለው እያደሩ፣ ቁልቁል እየተዋረዱ፤ ወይም ወደ ከፍታ እየተመነደጉ። የሁሉም አገር የታሪክ ሂደት እንደዚህ ነው- የጎዞ  ታሪክ፡፡ አሜሪካም፤ የስልጣኔ ውጤት ናት ሲባል፣ ስልጣኔ ወደተሰኘው አድራሻ ተሻገረች ማለት አይደለም፡፡
በእውቀት መንገድ መጓዝ  የጀመረች አገር ናት፡፡ ነገር ግን፣ ከጭፍን እምነት ገፅዎችና ከመዘዞቹ ሁሉ በአንዴ ተገላገለች ማለት አይደለም፡፡ ከእውቀት መንገድ ጋር የማይነጣጠል ስልጡን የነፃነት ፖለቲካ የፈጠረች አገር ናት አሜሪካ፡፡  የሃይማኖት ፖለቲካን ወይም ፖለቲካዊ ሃይማኖትን የሚከለክል ህገ መንግስት ማፅደቋ፣…. ለአሜሪካ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም፣ ብሩህ የስልጣኔ መንገድ ከፍታለች። ነገር ግን፣ ሁሉም የጭፍን እምነት ጉራንጉር፣ሁሉም የሃይማኖት ፖለቲካ፣ ከነኮተቱ ተወገደ ማለት አይደለም፡፡
ይልቅስ ዋናው ቁምነገር፣በስልጣኔ ጉዞ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ፣በጥበብና በጥረት ፣ጣጣውን ከነጦሱ ማስወገድ፣የሚቻል መሆኑ ነው፡፡ ጎን ለጎንም የእውቀትና የነፃነት ብርሃንን ቀስ በቀስ ማፍካት ማስፋት ይቻላል በስልጣኔ ጎዳናው ፀንተው በመጓዝ፡፡
የአሜሪካ መስራቾች፣ የህገ መንግስት አዘጋጆችና አጽዳቂዎች፤ያንን የስልጣኔ መንገድ ቀይሰው፣ ጉዞውን ጀምረውታል፤  መስመር አስይዘውታል፡፡ነገር ግን፣የስልጣኔ ጉዞ ተሟልቷል ተጠናቅቋል አላሉም። የኋላቀርነት ጨላማን በድግምት መግፈፍ፣ የስልጣኔን ብርሃን በአስማት ማንገስ እንደማይቻል፣ በሃሳብም በተግባርም ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ለተፈጥሯዊ ዓለም እውነታን፣ የሰውን ህያውነት፣ አእምሮን አዋቂነት ጨብጠው የፀኑ፣ ሰዎች ናቸው ለእውነታና ለአእምሮ፣ ለሳይንስና ለእውቀት ከፍተኛ ክብር የነበራቸው ሰዎች ናቸው. ለጭፍን እምነት ያልተገዙ፡፡ የአሜሪካ መስራቾች ካስተማሩን ትልልቅ ቁምነገሮች መካከል አንዱን እንጥቀስ፡፡ “ሃይማኖት የግል ነው፤ አገር የጋራ ነው” እንደሚባለው፣ መንግስት በሰዎች ሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ መግባት የለበትም፡፡ በዚያው ልክ፣ ሃይማኖት በመንግስት  ቦታ ሊኖረው አይገባም፡፡ አንዱ ሃይማኖት ውስጥ በተዘረዘሩ ትዕዛዛት፣ ወይም በሌላኛው ሃይማኖት በተነገሩ ትንቢቶች አማካኝነት የተቃኘ ህግ አይታወጅም፡፡ ህልም ወይም ራዕይ፣ ስብከት ወይም ሃይማኖታዊ አንቀፅ እየተጠቀሰ፣ የሚከናወን ደሳኝነትና የቅጣት ፍርድ አይኖርም በስልጡን ፖለቲካ ውስጥ።
የአሜሪካ መስራቾች በዚህ የስልጣኔ አስተሳሰብና  በብሩህ የእውቀት መንገድ ነው የተጓዙት፡፡ እናም፤ የትኛውንም የሃይማኖት ዓይነት ወይም ማንኛውንም የእምነት ቅኝት የማይጠቅስ፣ ስልጡን ህገ መንግስት አፀደቁ፡፡ መንግስት፣ የሃይማኖታዊ ተቋምን የሚመለከት አንዳችም ህግ ማወጅ አይችልም አሉ፡፡ የሃሳብን ነፃነት የሚለጉም ህግ ማውጣት የለበትም የሚል አንቀጽም በህገመንግስት ውስጥ በአጽንኦት አሰፈሩል። The First Amendment ይሉታል፡፡ ይሄ፣ ለአሜሪካ ብቻ ሳይሆን፣ ለመላው ዓለም፣ ደማቅ የስልጣኔ ፋና ነው፡፡ ነገር ግን፣ ህገ-መንግስቱ በፀደቀ ማግስት፣ ስልጣኔ ነገሰ የቀድሞ ሃይማኖት ነክ ፖለቲካና የአፈና ቅሪት ሁሉ ተጠራርጎ ጠፋ ማለት አይደለም፤ ጉዞው ተጀመረ እንጂ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜም ብዙ ፍሬ አስገኝቷል፡፡ ነገር ግን፣ ሃይማኖትንና ፖለቲካን መልሰው ማደበላለቅ የሚያምራቸው ሰዎች ከአባዜያቸው ተላቀቁ ማለት አይደለም፡፡ ዓለማዊ እውቀትንና የሃሳብ ነጻነትን በማንቋሸሽ የማይታክታቸው፤ በዚህም ብዙ ችግር የሚፈጥሩ፣ ጥፋትን የሚያስከትሉ ሰዎች አልጠፉም፡፡ ሁሌም መጠንቀቅ ይበጃል፤ መዘዙ ክፉ ነውና the closing of the western mind የሚለው መፅሐፍ ይህንን እውነታ ከታሪክ ያስረዳናል፡፡
ይህ ብቻ ቢሆን ባልከፋ፡፡
አሜሪካ፣ የእውነታና የአእምሮ፣ የእውቀትና የሳይንስ አርአያ እንዳልነበረች፤ ዛሬ ዛሬ፣ በእውቀት ምትክ “ትርክት”፣ በሳይንስ ምትክ “ውቅር” (Construct) የሚሉ ቃላት ነግሰውባታል፡፡ እውነትንና እውቀትን ከማንቋሸሽ ጎን ለጎን፣ የግል ነፃነትንና ህገ-መንግስትን፣ የአሜሪካ መስራቾችንና  የስልጣኔ ዘመናት ታሪኮችን፣ … በአጠቃላይ አሜሪካን የሚመለከት ማንኛውንም ነገር ማብጠልጠል፣ በአገረ አሜሪካ፣ እንደአሸን ፈልቷል፡፡ ገንኗል፡፡
“ስልጣኔ ጊዜው አልፎበታል” የሚል አስተሳሰብ በዩኒቨርስቲዎች ነግሷል post modernisim እንዲሉ::  የዚህ አስተሳሰብ ሰባኪዎች እንዲህ ይላሉ - ሁሉም ሃሳብ እኩል ነው፣ ሳይንስና ጥንቆላ ያው ናቸው ይላሉ፡፡ ሁሉም ባህልና ልማድ፣ ሁሉም ህግና ስርዓት ለየራሳቸው ትክክል ናቸው ይላል ፀረ ስልጣኔ ፀረ እውቀት የዘመናችን አስተሳሰብ የዚህ ቅዥት ምንነትና መጥፎ  መዘዞቹን የሚተነትን ታሪካዊ መፅሐፍ አለ the closing of theAmerican mind ይላል መፅሐፉ፡፡ በ allen bloom የተፃፈ ነው። በፀረ ስልጣኔ ምሁራን አባባል “እውነትና እውቀት”፣ የማይጨበጡ አፈታሪኮች  ናቸው፡፡ ሳይንስ፣ ከማንኛውም ጭፍን እምነት፣ ….የትርክት ዓይነት ነው እያሉም ያንቋሽሻሉ፡፡ የግል ነፃነትና የአሜሪካ ህገ-መንግስት፣ ነባር ገዚዎችን የሚያገለግሉ ድብቅ የጭቆና መሳሪያዎችና ውቅር ትርክቶች ናቸው በማለትም ያወግዛሉ። ሁሉም ነገር ምናባዊ ፈጠራ፣ ሁሉም ነገር ጭፍን እምነት፣ ሁሉም ነገር ማስረጃ አልባ ትርክትና የዘፈቀደ ውቅር ከሆነ፣……. እውነታ፣ እውቀት፣ ታሪክ፣ ሳይንስ የሚባሉ ነገሮች ባዶ አባባሎች ወይም የማታለያ ምናባዊ ፈጠራ (ውቅር) ከሆኑ፣ ምን ቀረ? ምን ያልፈረሰ ይገኛል? ሁሉም ነገር ተነቃሎ ተሰነጣጥቆ ይፍረከረካል፣ ይፈርሳል deconstruction እንዲሉ፡፡
እነዚህን ፀረ እውቀትና ፀረ ስልጣኔ የቅዠት አስተሳሰቦች በአሜሪካ የመንገሳቸው ያህል፣ በአሜሪካ ታጥረው፣ አሜሪካን ብቻ አፍርሰው እዚያው አይቀሩም የአገራችን የኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች፣ ይህንኑን እወቀትና ፀረ ሳይንስ ቅዥት በሰፊው እያስተማሩ እልፍ አእላፍ እያስመረቁ ነው፡፡ በዩኤስኤ አይዲ የገንዘብ ድጋፍ የሚንቀሰቀ ሰው የትምህርት ሚኒስቴርም፣ እውነተኛ መረጃንና እውቀትን የሚያጣጥል ስርዓተ ትምህርት ሲያስፋፋ ቆይቷል፡፡
እውነተኛ መረጃንና እውቀትን ማስተማር ጊዜው አልፎበታል ይላል የዘመኑ ቅዠታም አስተሳሰብ፡፡ እንዲያውም፣ እውነትና እውቀት ላይ ያተኮረ ትምህርት፣ የአምባገነንነት፣ የጭቆናና የብዝበዛ ፕሮፖጋንዳ ነው ተብሏል፡፡ በተቃራኒው፣ የትምህርት አላማ፣ እውነትና እውቀት የመቃረን፣ የማጋለጥና የማፍረስ አላማ ሆኗል፡፡ ለምን?
እውነትና እውቀት፣ …. የገዢዎች ምናባዊ ፈጠራዎች ከሆኑ፣ ማታለያ ትርክቶች ከሆኑ፣ በጊዜ ብዛትም በሰው አእምሮ ላይ የታተሙ ውቅር እስር ቤቶች ከሆኑ፣የትምህርት አላማ፣ ነባሩን መዋቅር መቃረን ብቻ ሳይሆን፣ መነቃቀልና ማፍረስ ጭምር ይሆናል፡፡ ይህንን ነው ሞጋች አስተሳሰብ ብለው የሚያሞግሱት፡፡ critical thinking  ይሉታል፡፡ የቅራኔ አስተሳሰብ እንደማለት፡፡
ከዚያስ እያንዳንዱ ተማሪ የየራሱ የእውነት አይነትና የየራሱ የእውቀት አይነት ያዋቅራል ይላሉ፡፡ constructivism ይሉታል፡፡ እውነተኛ መረጃንና ቅጥ ያለው እውቀትን ማስተማር ግን፣…… ጊዜው ያለፈበት አምባገነንነት ነው ተብሏል፡፡
ሌው ቀርቶ፣ ፊደል ማስተማር፣ ሀ፣ ለ፣ ሐ፣ መ እያሉ ፅሁፍንና ድምፅን አዋህዶ ማስተማር ጭምር፣ አምባገነንነት ነው ብለው ፈርደውበታል፡፡ ተማሪዎች፣ እንደየ ዝንባሌያቸው፣ በየራሳቸው የድምጽ ምርጫ ያንብቡት በማለትም ይሰብካሉ፡፡ እናም፤ የንባብ ትምህርት፣ ከፊደል ትምህርት ቀስ በቀስ እየተፋታ ከቃላትና ከአረፍተ ነገር እንዲጀምር ሲደረግ ቆይቷል፡፡ የፊደል ትምህርት እየቀነሰ ሲመጣ፣ በዚያው መጠን፣ የንባብ ችሎታ ከተማሪዎች እየራቀ መምጣቱ ይገርማል?
ከአገራችን የ2ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል፣ ግማሽ ያህሉ፣ አንዲት ቃል ማንበብ አይችሉም፡፡ ትልቅ የአገር ውድቀት ነው፡፡ የሚሊዮኖችን የወደፊት ህይወት የሚያበላሽ፣ ለአገርም የህልውና አደጋን የሚያስከትል ትልቅ ውድቀት፡፡
ይህንን ጥፋት በጊዜ ከማስተካከል ይልቅ፣ የቅዠት አስተሳሰብን ይባስኑ የሚያስፋፋ፣ የአገሪቱን ትምህርት ወደ ከፋ ትርምስ የሚመራ የትምህርት ፍኖተ ካርታ የተሰኘ እቅድ ተጨምሮበታል፡፡
ምናለፋችሁ! በአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች የተስፋፋው፣ የአገሪቱን ስረ-መሰረት እየሸረሸረና እያቃወሰ የሚገኘው ዘመኑ የቅዠት አስተሳሰብ፣ መላው ዓለምን፣ ከአውሮፓ እስከ ኤስያ፣ ከአረብ አገራት እስከ አፍሪካ፣ ኢትዮጵያንም ጭምር እያዳረሰ ነው፡፡  
ይህን ዓለማቀፍና ድንበር የለሽ ትልቅ አደጋ በጊዜ አለመገንዘብ፣ በጥንቃቄ አለመመልከትና በትጋት አለማስተካከል፣ ጥፋትን ያፋጥናል፡፡ የአፄ ሃይለስላሴ ዘመን የ1960ዎቹን ስህተት እንደ መድገም ይቆጠራል፡፡ ያኔ፣ የሶሻሊዝም አስተሳሰብ  ድንበር የለሽ አለማቀፍ አደጋ መሆኑን ለመገንዘብ፣ በጊዜም በርትቶ ለመመከት አለመቻላቸው፣ ምንኛ አገሪቱን እንደጎዳ ታሪክ ይመሰክራል፡፡
ፀረ እውነትና ፀረ እውቀት ዘመናችን አስተሳሰብም፣ የዚያኑ ያህል አደገኛ ነው፡፡ ያለ እውነትና ያለ እውቀት፣ ሌላ መግባቢያ የለማ፡፡ ስነ-ምግባርና ህግ፣ መከባበርና ፍትህ የተሰኙ ነገሮች ሁሉ ትርጉም እያጡ፣… አገር ምድሩ፣ በቅዠታም አስተሳሰብና በጭፍን እምነት እየተደናገረ መላተም ያዘወትራል፡፡
የሰው የግል ኑሮ፣ ምርትና ንብረት፣ ግብይትና መተባበር እየጠፋ፣… የዝርፊያ አስተሳሰብና የምቀኝነት ውድመት ይበረክታል። በድሮው የሶሻሊዝም አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን፣ “የአካባቢ ጥበቃ፣ የካርቦን ልቀት፣ ታዳሽ ሃይል፣ አረንጓዴ ልማት፣”… በሚሉ ፀረ ኢንዱስትሪና ፀረ ብልፅግና አስተሳሰቦች አማካኝነት፣ ድህነት ይበረታል፣  የአገር ህልውና ለአደጋ ይጋለጣል፡፡ የአካባቢ ጥበቃ የተሰኘው የዘመናችን አስተሳሰብም፣ መነሻውና መዛመቻው በአብዛኛው ከአሜሪካ ነው፡፡
ያቺ፣ የኢንዱስትሪና የምርታማነት፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራና የፋብሪካ፣ የነፃ ገበያና የብልፅግና ተምሳሌት የነበረች ድንቅ አገር፤ ዛሬ ዛሬ ፣ አጥፊ የአካባቢ ጥበቃ አስተሳሰብ አዛማች መሆኗ ምንኛ ያሳዝናል? ይህንን በዝርዝር ለማየት መሞከር አለብን፡፡ የዘመናችን ቁጥር 2 ዓለማቀፍ አደጋ ነውና፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፡፡ የእንዳንዱን ሰው ህልውና የሚያከብር፣ የግል ማንነትና  የግል ሃላፊነት ላይ የተመሰረተ፣ ዘረኝነትንና የጅምላ ፍርድን የሚቃረን፣ የፍትህና የህግ የበላይነት ስርዓትን እያሰፈነች የነበረች ድንቅ አገር፤ የግል ማንነትን በሚያንቋሽሽ የዘመናችን መንገኛ አስተሳሰብ ትጥለቀለቃለች…
The Closing of the liberal mind የተሰኘውን መፅሐፍ በማጣቀስ፣ የአደጋውን ትልቅነት ለማገናዝብና በአገራችን ምንኛ እየተስፋፋ እንደሆነ ለመመልከት መጣር ይገባናል፡፡

Read 12062 times