Saturday, 05 June 2021 13:17

ለነፃና ፍትሐዊ ምርጫ፣ የመገናኛ ብዙኃን ሚና

Written by  በለው አንለይ
Rate this item
(0 votes)

     "--ለነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ዜጎች አይተኬ ሚና አላቸው፡፡ በርግጥም ዲሞክራሲ ጣዕም ይኖረው ዘንድ የህዝቡን ንቁ ተሳትፎ ይጠይቃል፡፡ ምርጫ በመሰረቱ ተመራጮች የሚመረጡበት ብቻ ሳይሆን ዜጎች በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ ይመክሩ፣ ይወያዩ፤ ይከራከሩና ይወስኑ ዘንድ የመጣ ዕድል ነው፡፡ ህዝብ በተለያየ መልክና መንገድ ይናገራል - ህዝብ በሰልፍ ይናገራል፤ በድምጹ ይወስናል፤ በዝምታው መልዕክት ያስተላልፋል፡፡--"
                    

              በዚህ ዘመን መገናኛ ብዙኃን፣ ሁሉም የሰው ልጅ ድርጊቶች የሚስተናገዱባቸው አደባባይ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ፣ የመድረኮች ሁሉ መድረክ (“ማስተር ፎረም”)፣ ግዙፍ ሜዳ (“ሜታ ፊልድ”) ተብለው እስከ መጠራት ደርሰዋል፡፡ በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ሁሉም ነገር ሚዲያዊ በሆነበት በዚህ ዘመን፣ በመገናኛ ብዙኃን የማይታጀብ ህዝባዊ ጉዳይ ይኖራል ለማለት አያስደፍርም፡፡ የዲሞክራሲ ዋና መገለጫ የሆነው ምርጫን እንደ ምሳሌ ብንወስድ እንኳን ያለ መገናኛ ብዙኃን ተሳትፎና እገዛ፣ ምርጫን የህዝብ አጀንዳ ለማድረግ አዳጋች ነው፡፡
ትርጉም ያለው ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ይካሄድ ዘንድ መገናኛ ብዙኃን ዜጎችን በማስተማር፣ በመቀስቀስና ንቁ ተሳትፎ ያደርጉ ዘንድ ህዝባዊ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። በምርጫ ወቅት መገናኛ ብዙኃን የተወዳዳሪ ፓርቲዎችን የፖሊሲ አማራጭና የቅስቀሳ ስራ በማቅረብ፣ የክርክርና የውይይት መድረኮችን በመፍጠር፣ ህዝቡ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን ተፈጥሮአዊ ሚናቸውን በአግባቡ መጫወት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ከመገናኛ ብዙኃን የሚጠበቁ ህዝባዊ ኃላፊነቶች በተለያዩ ሰዎች በተለያዩ ተምሳሌቶችና ዘይቤዎች ይገለጻሉ፡፡ አንዳንዶች መገናኛ ብዙኃን በተጨባጭ መሬት ላይ ላይ የሚደረገውንና የሚሰራውን ሁሉ ልክ እንደ መስታወት ቁልጭ አድርጎ ለህዝቡ ማቅረብ ነው የሚሉ ሲሆን፤ ሌሎች ደግሞ የመገናኛ ብዙኃን ዓይነተኛ ሚና የመንግስት ባለስልጣናትን ዘብ ሆኖ በመቆጣጠር ስልጣናቸውን አላግባብ እንዳይጠቀሙ ማድረግ ነው ይላሉ፡፡ በሌላ በኩል፤ የመገናኛ ብዙኃን ሚና የተለያዩ ሀሳቦች፣ አመለካከቶችና አስተያየቶች የሚንሸራሸሩበት የሀሳብ መድረክ ነው መሆን ያለባቸው በማለት አቋም ይዘው የሚከራከሩ በርካቶች ናቸው፡፡ ሁሉም ዓይነት ሚናዎች ወሳኝ የሚሆኑበት ወቅትና አግባብ ያላቸው ቢሆንም፣ በተለይ ዜጎች ሀሳባቸውን፣ ፍላጎታቸውንና ምኞታቸውን በነጻ እንዲያቀርቡ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር የዘወትር ተግባራቸው መሆን እንዳለበት የሚጠበቅ ነው፡፡
ምርጫ የህዝብ ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን ከፓርቲዎች/እጩዎች ክርክርና ውይይት በተጨማሪ የህዝቡም ተሳትፎ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡ ሚዲያዎች ህዝቡ ድምጹን የሚያሰማባቸዉ ነጻ መድረክ ሆነው ሊያገለግሉ እንደሚገባ ይታመናል፡፡ እንደየ ሚዲያው አደረጃጀትና ኤዲቶሪያል ፖሊሲ፣ ህዝባዊ ነጻ መድረኮች የተለያየ መልክና ቅርጽ ሊኖራቸው ይችላል። የተለያዩ የጋዜጣ ነጻ አስተያየት አምዶች (ለምሳሌ አጀንዳ አምድ፣ ከአንባቢያን የሚላኩ ደብዳቤዎች)፤ አድማጭ-ተመልካችን ያማከሉ የራዲዮና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ የህዝብ አስተያየት ቅኝቶች፣ ኮንፈረንሶች፣ ህዝባዊ ድጋፍና ተቃውሞ ነክ የሆኑ ዜናዎች የሚያስተናግዱበት ገፆች እንዲሁም ማህበራዊ ሚዲያዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከህዝቡ የሚመጡ ሀሳቦችና አስተያየቶች በምርጫው ሂደትና ውጤት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያላቸው ሲሆን ህዝብ በንቃት ያልተሳተፈበት ምርጫ  ግን ከለበጣ የተውኔት መድረክነት ተለይቶ አይታይም፡፡
ለነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ዜጎች አይተኬ ሚና አላቸው፡፡ በርግጥም ዲሞክራሲ ጣዕም ይኖረው ዘንድ የህዝቡን ንቁ ተሳትፎ ይጠይቃል፡፡ ምርጫ በመሰረቱ ተመራጮች የሚመረጡበት ብቻ ሳይሆን ዜጎች በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ ይመክሩ፣ ይወያዩ፤ ይከራከሩና ይወስኑ ዘንድ የመጣ ዕድል ነው፡፡ ህዝብ በተለያየ መልክና መንገድ ይናገራል - ህዝብ በሰልፍ ይናገራል፤ በድምጹ ይወስናል፤ በዝምታው መልዕክት ያስተላልፋል፡፡ የመገናኛ ብዙኃንም የህዝቡን ተሳትፎ በማጉላት፣ በምርጫ ተዋናዮች መካከል (የፖለቲካ ፓርቲዎች/እጩዎች፤ ህዝብና ሚዲያ) የተሳትፎ ሚዛናዊነትን መጠበቅ አለባቸው፡፡
በአዲሱ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ (አዋጅ ቁጥር 1238/2013) አንቀጽ 71(2) ላይ በተደነገገው መሰረት፤ ማንኛውም የብሮድካስት አገልግሎት ባለፈቃድ በምርጫ ወቅት የሚያቀርባቸው የዜና ዘገባዎች፣ ትንተናዎችና የውይይት መሰናዶዎች ሚዛናዊና የተሟላ ዕይታ እንዲኖራቸው የመራጮችና የፖለቲካ ፓርቲዎችን ድምጽ ማካተት እንደሚጠበቅባቸው ተጠቅሷል። ሚዛናዊነት ብዙውን ጊዜ ከዜና ዘገባ ጋር የሚነሳ ጉዳይ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ በትንተናና የዉይይት መሰናዶዎች ላይ ሚዛናዊነትን እንዴት ማሳካት ይቻላል የሚለው ጥያቄ መነሳቱ አይቀሬ ነው።  በዜና ዘገባዎች ላይ እንደሚደረገው ሁሉ እንደ ክርክር ባሉ የሀሳብ ሙግቶች ላይም ለተሳታፊዎች ፍትሐዊ የተሳትፎ ዕድል፣ ጊዜና ቦታ በመስጠት ሚዛናዊነቱን በቀላሉ መጠበቅ ይቻላል፡፡  
በምርጫ ወቅት መገናኛ ብዙኃን የሚያቀርቧቸው በዜና ዘገባዎችና በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚደረጉ ክርክሮች ላይ ብቻ መወሰን አይጠበቅባቸውም፡፡ የተወዳዳሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ፖሊሲና ስትራቴጂ በዘርፉ ባለሙያዎች ማስተንተንን ጨምሮ አጠቃላይ የምርጫውን ሂደት በንቃት መከታተል፣ የህዝብ አስተያየት ቅኝት መስራት፣ ብልሹ አሰራሮችን ማጋለጥ፣ ህዝቡ ሃሰቡን የሚልጽባቸዉ መድረኮችን ማመቻቸት የመገናኛ ብዙኃን አብይ የትኩረት አቅጣጫቸው መሆን ይኖርበታል። የዲሞክራሲ ትርጉሙም ልዩ ልዩ ሀሳብና አመለካከቶች የሚስተናገዱበት፣ የንግግር ነጻነት የሚከበርበት፣ ሁሉም ዓይነት አስተያየትና ምልከታዎች ወደ ሀሳብ ገበያዉ የሚቀርቡበት ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1076 times