Tuesday, 08 June 2021 00:00

ራሳቸውን ከምርጫው ያገለሉ ሚናቸው ይታወቅ!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(1 Vote)


                     "ሥልጣን ድምጽ እንጂ ህይወት ሊገበርለት አይገባም"
                     
            በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት ወደ አንድ መቶ አስር ሚሊዮን እንደሚደርስ ይነገራል፡፡ ከዚህ ተነስቶ ሳይሆን አይቀርም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ለ6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ፣ ሀምሳ ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በመራጭነት ሊመዘገቡ ይችላሉ የሚል ግምት ያስቀመጠው፤ መጀመሪያ ላይ፡፡  
በኢትዮጵያ የህዝብ ብዛት ቁጥር ውስጥ ከፍተኛውን ቦታ የሚይዘው በወጣትነት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ከዚህም ውስጥ የሚበዛው ከ18 ዓመት በታች የሚገኘው እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ በትግራይ ክልል፣ በሱማሌና በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች ምርጫ እንደማይደረግም ተገልጿል፡፡
ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በህግ ቁጥጥር ስር ያሉ ሰዎች ለመምረጥ መመዝገብ እንደማይችሉ ቦርዱ አሳውቋል፡፡ እነዚህ ደግሞ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ በህግና በጤና ችግር ምክንያት አሁንም የመምረጥ መብታቸውን የሚያጡትን ስንጨምር፣ የቦርዱን ግምት  ጥያቄ ውስጥ እንድናስገባው ያደርገናል፡፡
በዘመነ ህወኃት ኢህአዴግ በተደረጉ አጠቃላይ ምርጫዎች፣ ህዝብ በተደጋጋሚ የታዘበው ሁኔታ፤ ወደ ምርጫ ምዝገባ ጣቢያ እንዲሄድ፣ ድምፁን ሰጥቶ የፈለገውንና የወደደውን መሪ ለስልጣን እንዲያበቃ የሚገፋፋው አልነበረም፡፡ ሕወሓት/አህአዴግና አጋሮቹ አሸናፊ እየሆኑ ስልጣናቸውን ሲያደላድሉ መኖራቸውን ነው የታዘበው፡፡ ብዙ የሚነገርለት የ1997 አገር አቀፍ ምርጫ ተደናቂ ያደረገው  ለመራጭነት የተመዘገበው የህዝብ ብዛት ከፍተኛነት  ሳይሆን  “ልሞክረው” ብሎ የተመዘገበውም ሰው በድምፅ መስጫ እለት ንቅል ብሎ መውጣቱ ነው፡፡ ለመራጭነት የተመዘገበውም ሆነ ያልተመዘገበው ሰው፤ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች በሚጠሩት የድጋፍ ሰልፍ ላይ በከፍተኛ ቁጥር በመውጣቱ፣ ያንን ምርጫ ቀለመ ደማቅ አድርጎታል፡፡
መምረጥ መብት ነው፡፡ “የፈለገው ሰው ይምጣ፤ የፈለገው ስልጣን ይያዝ፤  እኔ ምን ቸገረኝ” የሚል ወገን ለመራጭነት ላይመዘገብ ይችላል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰዎችንና ቀድመን የጠቀስናቸውን ጉዳዮች አዳምረን ስናይ፣ ቦርዱ የሰጠው ግምት እጅግ የተለጠጠ መሆኑን ለመረዳት አይከብድም፡፡
አሁን የመራጮች የምዝገባ ጊዜ በተደጋጋሚ ሲራዘም ቆይቶ  ተጠናቋል፡፡ ለመራጭነት ሰላሳ ስድስት ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች መመዝገባቸውን ቦርዱ በቅርቡ ይፋ አድርጓል፡፡ የሚጠበቀው ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም የሚደረገው የድምፅ መስጫ ቀን ነው። የተመዘገበው ሁሉ  ድምፅ ለመስጠት እንደማይወጣ ይታወቃል፡፡ ለመራጭነት የማይቀርቡት በሞትና በህመም ምክንያት ያልቻሉ ሳይሆኑ እስካሁን ባለው ምርጫ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ያልተደሰቱት ናቸው። ቦርዱ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሰጠውን ግምትም ሊያስበብት ይገባል፡፡
ስድስተኛው  አጠቃላይ አገር አቀፍ ምርጫ፤  በድምፅ መስጫ ዕለት፣ በየምርጫ ክልሉ በሚገኙ የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ተገኝተው፣ ለፈለጉት ግለሰብ ወይም ለሚደግፉት ፓርቲ እጩ ተወዳዳሪ፣ ድምፃቸውን የሰጡ ሰዎች ምርጫ እንጂ የሌላ የማንም እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡
የሚደግፏቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በልዩ ልዩ ምክንያት ወደ ምርጫ ወድድሩ ያልገቡላቸው፣ በዚህም ምክንያት ለመራጭነት ያልተመዘገቡ ወይም ተመዝግበው ቆይተው በድምፅ መስጫው ወቅት ድምፃቸውን ለመስጠት ያልፈቀዱ ወገኖች፤ ምርጫው የእነሱ እንዳልሆነ ሊረዱ ይገባል፡፡ በዚህም መሰረት የድምፅ አሰጣጥና ሂደቱ ላይ ተቃውሞ ማንሳት አይችሉም። አያውቁትማ፤ አልተሳተፉበትምና፡፡ በእርግጥ ይሄ በታዛቢነት የሚሳተፉትን አይመለከትም።
በመራጭነት ተመዝግበው በዕለቱ በድምፅ መስጫ ጣቢያ ተገኝተውና የድምፅ መስጫ ወረቀታቸውን ተቀብለው ማንንም ሳይመርጡ ድምጻቸውን አቃጥለው የወጡትም ቢሆኑ ምርጫው አይመለከታቸውም፡፡ እነሱ ለመራጭነት ካልተመዘገቡት የሚለዩት እስካሁን ባደረጉት ጉዞ ብቻ እንደሆነ መረዳት መልካም ነው፡፡
ምርጫው የኔ ነው ማለት የሚችሉቱ ለመራጭነት ተመዝግበው፤ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በየድምፅ መስጫ ጣቢያው ተገኝተው  በትክክል ድምጽ  የሰጡ ሰዎች ብቻ ናቸው። በምርጫው ውጤት ተደስተው ጮቤ ቢረግጡ ወይም አዝነው አንገታቸውን ቢደፉ እነሱ እንጂ ሌላው ሊሆን አይችልም። ከዚህ አንጻር ምርጫውና ውጤቱን ተከትሎ፣ በምርጫው ሳይሳተፉ፣ ግጭትና ብጥብጥ ለመቀስቀስ ብቻ የተዘጋጁ ወገኖች፣ ቡድኖች፣ የፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ፣ ከወዲሁ በግልጽ ሊነገራቸው ይገባል፡- “ይሄ የእናንተ ምርጫ አይደለም፤ አይመለከታችሁም!” በሚል! የምርጫ ጣቢያዎች አካባቢም ማንዣበብ  የለባቸውም፡፡ ሂደቱን ከማደናቀፍ በቀር ምን ይሰራሉ!?
በሌላ በኩል፤ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በአዲሱ የፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ አዋጅ መሰረት፣ የቆዩ ፓርቲዎች እንደገና እንዲመዘገቡ ሲያደርግ፣ መመዘኛውን ማሟላት ያቃታቸውን ፓርቲዎችን በመሰረዙ ምስጋና ይገባዋል፡፡ አዳዲስ ፓርቲዎች እየተመዘገቡ ወደ ፖለቲካ ትግል በመግባታቸው፤ የተቀነሱ ተቀንሰው፣ የተጨመሩ ተጨምረው፣ በአሁኑ ጊዜ 47 ፓርቲዎች በአገር አቀፍና በክልል ምርጫ እየተወዳደሩ ይገኛሉ፡፡ ከበቂ በላይ ነው፡፡
ፓርቲዎች ባደረጓቸው ክርክሮች፣ ማን ምን ላይ እንዳለ፣ መራጩ መገንዘብ የቻለ  ይመስለኛል፡፡  ይህ በምርጫ ውጤታቸው ላይ ተፅዕኖ ማስከተሉ የታመነ ነው። ራሳቸውን ከፍ ከፍ አድርገው የሚያዩ አንዳንድ ፓርቲዎች ምናልባት የጠበቁትን ድምጽ ባያገኙ ሊያኮርፉ፣ አመፅ ሊቀሰቅሱ ይችላሉ፡፡  ነገር ግን እውነቱን መጋፈጥ ነው የሚያዋጣቸው፡፡ ህዝብ ሁሉንም ነገር እኛ ከምንገምተው በላይ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ እናም አንዳንድ ፓርቲዎች #የተሸነፍነው ተጭበርብሮ ነው እንጂ ወዘተ; እያሉ ቢያለቃቅሱ፣ ህዝቡ ቤቱ ቁጭ ብሎ ሊስቅባቸው፣ አሊያም አስቂኝ ቲክ ቶክ ሊሰራባቸው ይችላል፡፡
እናም ተገፍተው ወይም ይሁነኝ ብለው ምክንያት በመደርደር፣ ራሳቸውን ከውድድሩ ያገለሉ ፓርቲዎች፤ የምርጫው ውጤት የሚመለከታቸው ባለመሆኑ፣ ከድህረ ምርጫ ውዝግቦች፣ ንትርኮች፣ክሶች፣ ቅሬታዎች ወዘተ-- ራሳቸውን  ማግለል ይጠበቅባቸዋል፡፡ የዘንድሮ ምርጫ አይመለከታቸውም፤ ይልቁንም ለሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ ራሳቸውን ያዘጋጁ፡፡
ዋናው ነገር በምርጫው ማግስት አላስፈላጊ የሆነ ብጥብጥና ግጭት እንዳይከሰት ከወዲሁ ጥንቃቄ ማድረግ ነው። ምርጫው ቢጭበረበር እንኳን ወደ ፍ/ቤት መሄድ እንጂ እንደተለመደው ህዝብን ለአመጽ አደባባይ ጠርቶ ሌላ ዙር "የምርጫ ማግስት ሞት" መደገስ ተቀባይነት የለውም። በህግም በታሪክም ያስጠይቃል፡፡ ሥልጣን ድምጽ እንጂ ህይወት ሊገበርለት አይገባም። የእስከዛሬው ይበቃል፡፡
ሁሉም የምርጫው ተዋናዮች  6ኛው አገራዊ ምርጫ የሞት ሽረት ጉዳይ አለመሆኑን ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል፡፡ የምርጫው ስኬታማነት አንዱ መለኪያው፣ አንድም የሰው ህይወት ሳይጠፋ፣ አንዲትም ንብረት ሳትወድም ምርጫው በሰላም መጠናቀቁ ነው፡፡ ነፃና ፍትሃዊነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው፡፡
ሥልጣን ድምጽ እንጂ ህይወት ሊገበርለት አይገባም!!

Read 10129 times