Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 01 September 2012 10:54

‘መስመር ሲታለፍ…

Written by 
Rate this item
(0 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

ስሙኝማ…እዚህች የእኛዋ አገር ላይ ‘መስመር የሚያልፉ’ ነገሮች እየበዙ አይመስላችሁም? ምን የት ቦታ ላይ መቆም እንዳለበት፣ ግራ የተጋባን ነው የሚመስለው፡ነገሮቻችን ሁሉ ምርኩዝ ዝላይ ያለምርኩዝ አይነት እየሆኑ የእርስ በእርስ ግንኙነት ላይ…አለ አይደል…የሆነ ጫና እያሳደረ ነው፡፡እናላችሁ…በቀደም አንድ ሚኒባስ ታክሲ ላይ ከሆነ የሃሪ ፖተር ፊልም ላይ ዱብ ያለ የሚመስል ረዳት አንዱን በጎልማሳነት ሁለተኛ አጋማሽ ላይ የሚገኝ ተሳፋሪ ምን አለው መሰላችሁ… “ሠላሳ አምስት ሳንቲም ካለሽ ብሩን ልመልስልሽ፡፡” ሰውየው በጣም መናደዱ የሚያስታውቅ ቢሆንም የባሰ እንዳይመጣ በሚል ይመስላል የተባለውን አደረገ፡፡

ሚኒባስሶች ውስጥ እንደዚህ አይነት መስመር የሚያልፉ ነገሮች ብዙ ጊዜ በረዳቶች፣ አንዳንዴ በሾፌሮች ስታዩ በቃ “መስመር ሲታለፍ ሀይ ባይ ሊጠፋ ነው!” ያስብላችኋል፡ ይሄ የክላራ ዜትኪን ምናምን ጉዳይ ሳይሆን በቃ… አንተ “አንተ” ነው፣ አንቺም “አንቺ” ነች አለቀ፡፡

አማረልኝ ብሎ የሰውን ክብር ማዋረድ ስልጣኔም አይደል፣ “ለጨዋታ ያህል ነው…” የሚባልም አይደል፡፡

ደግሞላችሁ…የዘንድሮ ቃለ መጠይቆች ላይ ጠያቂም፣ ተጠያቂም መስመሩን በብዙ እጥፍ አልፈው ሲሄዱ ስትሰሙ፣ ስታነቡና ስታዩ አንዳንዴ…“ችግሩ ያለው እኔ ዘንድ ነው እንዴ?” ብላችሁ ትጠይቃላችሁ፡ ለምንድነው ትክክል ያልሆነው ነገር ለብዙ ሰው ትክክል የሚሆነው! ነገሩ ምን መሰላችሁ…መስመሩ የሚታለፍበት ነጥብ ወይ ጠፍቶናል ወይ መስመር መኖሩን ረስተነዋል፡፡

የምር…ብዙ ቃለ መጠይቆች ላይ…አለ አይደል…መላሾች እንደ ፈላስፋ ነገር መሆን ሲቃጣቸው፣ ምን አለፋችሁ፣ “በስንት ዘመኑ ፕሌቶ ራሱ ያሰለጠነው ደቀ መዝሙር ተገኘ” ምናምን ነገር ልትሉ ምንም አይቀራችሁ፡፡

ዓለም በአርሴ ተጀምሮ በማንቼ የሚያልቅ የሚመስለው ሰው ምን ተብሎ ሊጠየቅ ይችላል መሰላችሁ… “እንደው በአንተ እይታ ሰው ወደዚች ዓለም የመጣው ለምን ይመስልሀል?” የምር! ኩምክናው የሚጧጧፈው መላሹ በጥያቄው ሲመሰጥና አንድ ሁለቴ ጉሮሮረውን ማጥራት ሲጀምር ነው፡፡

“በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው የጠየቅኸኝ፡፡ እንደውም ይገርምሀል በቀደም ከጓደኞቼ ጋር በዚሁ ጉዳይ ስናወራ ይህን ጥያቄ መቼ ነው የምጠየቀው እል ነበር፡፡

ምን መሰለህ…እ…እ…ዋናው ነገር ወደዚች ዓለም የመጣነው…ምን መሰለህ…ብቻ ዋናው ነገር የመጣሁበት ዓላማዬ ምንድነው ብለህ ራስህ መጠየቅ አለብህ፡፡ ይሄኔ ነው የሚመስለኝ፡፡” ምኑ!

የመላሹ ነገር “ወቸ ጉድ!” አሰኝቷችሁ ሳያበቃ ጠያቂው ምን ቢል ጥሩ ነው… “በእውነቱ በጣም አነጋጋሪ ነገር ነው ያነሳኸው፡፡

እኔ እንደሚመስለኝ…” ይልና ጠያቂው ደግሞ ‘ስማቸውን የማያስታውሳቸው’ ፈላስፎችን እየጠቀሰ ይቀጥላል፡፡ እና ይሄኔ ነው “መስመር ሲታለፍ ሀይ ባይ እንደጠፋ መቅረቱ ነው!” የሚያሰኛችሁ፡፡

ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ዘንድሮ ግርም ከሚሉኝ ነገሮች አንዱ ምን መሰላችሁ…‘በጉጉትና በናፍቆት’ የሚጠበቅ ግን እኛ የማናውቀው ነገር መብዛቱ!

“ሲጠበቅ የነበረው…” የምትባለዋን ነጠላ ዜማ “ነገ ደግሞ ለምን ይጠቀሙባት ይሆን!” ያሰኛችኋል፡፡ የምር እኮ የሚገርማችሁ ነገር ነው…ማን ሲጠብቀው እንደነበር፣ በምን ምክንያት ሲጠበቅ እንደነበር…የማታውቁት ነገር “በናፍቆት ሲጠበቅ የቆየው እንትን በአሁኑ ጊዜ ስለመጣ…” ምናምን የሚል ነገር በጣም እየተለመደ ነው፡፡

ስሙኝማ…አይደለም ከሱቅና ከሜዳም ለምናገኘው ነገር፣ እንትናዬ እንኳን በናፍቆት መጠበቅ ቀርቷል፡፡ አሀ…የፖፑሌሽኑ ሚዛን በአንድ ወገን እያዘነበለ ‘ፈላጊ ወደ ተፈላጊ’ ሳይሆን ‘ተፈላጊ ወደ ፈላጊ’ እየሄደ ነዋ!

እናላችሁ…እየተዋወቅን መተናነቅ ‘ናሽናል ስፖርት’ ነገር እየሆነ ነው፡፡ ነገርዬው ግን … አለ አይደል…የሚያነበውን፣ የሰማውን ነገር ሁሉ የሚያምን ስንትና ስንት የእኔ ቢጤ ምስኪን አለ መሰላችሁ! እናማ…“በናፍቆት ሲጠበቅ የቆየው…” ምናምን የሚለውን ሲያይ “ምንም ይሁን ምን ሰዉ በናፍቆት ሲጠብቀው የቆየው ጥሩ ነገር ቢሆን ነው…” አይነት ሱቁ ወይ አገልግሎት መስጫው ሳይከፈት በር ላይ ተገትሮ ልታገኙት ትችላላችሁ፡፡

ለምሳሌ… አዛውቱን ሰው “ሳንቲም የለሽም…” ከሚባልበት ውጪ ተሳፋሪ ሳይሆን ረዳትና ሾፌር ንጉሥ የሆኑባቸው ሚኒባስ ታክሲዎች ውስጥ አሪፍ፣ አሪፍ…አለ አይደል …ጥሩ መልእክት አላቸው የሚባልላቸው ጥቅሶች አሉ፡፡ በዛው ልክ ግን…በቅንነትም ይሁን ነገሮችን ጠለቅ ብሎ ባለማየት፣ ‘መስመር የሚያልፉ’ ተሳፋሪውን የሚዘልፉም ሞልተዋል፡፡

“የቤትሽን አመል እዛው” “አትንጣጪብን” ምናምን አይነት ነገሮች በሕዝብ አይነት ጥቅስ፣ በቃ አሪፍ አለመሆን ብቻ ሳይሆን መስመር ማለፍ ነው፡፡

የሚገርመው ደግሞ…እነዚህ አሉታዊ ይዘት ያላቸው ጥቅሶች በአብዛኛው ሴቶች ላይ ብቻ ማተኮራቸው፡፡

(“የእጅህን አትጣ፣” “ሰው በሰው ይተካል” እያላችሁ እኛ ብንሄድ ‘ፕላን ቢ’ እንዳላችሁ የምትነገሩን የሙዚቃ ሰዎች፣ እስቲ ይቺን እንኳን ነካኳትማ!)

እናማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… እዚህ አገር መስመር የሚያልፉ ነገሮች እየበዙ “ሀይ ባይ” ማን እንደሆነ ግራ እየተጋባን ነው፡፡

ለምሳሌ አንዳንድ (አሁን አሁን እንደውም ‘ብዙ’) ማስታወቂያዎች ‘መስመር ማለፍ’ ብቻ ሳይሆን ነገራቸው ሁሉ የሆነ ምርኩዝ ዝላይን ያለምርኩዝ መዝለል አይነት ሆኗል፡፡  በስዋስው የንግግር ክፍሎች ከምንላቸው አብዛኛው ማስታወቂያ በአንዱ ብቻ የሚነግርባት አገር የእኛዋ ብቻ ሳትሆን አትቀርም፡፡

በነገራችን ላይ ጥያቄ አለን… ለቅጽሎቻችን ጥበቃ ይደረግልን፣ ልክ ነዋ! በኋላ “…ሙልጭልጭ እያለ አስቸገረኝ ሰው…” እንደተባለው አይነት እንዳይሆን ነዋ! እናማ…መዝገበ ቃላት ላይ ላሉት ቅጽሎቻችን ይታሰብብት! አሀ…ልክ ነዋ! የምር እኮ “ከስምንቱ የንግግር ክፍሎች ለነጋሪ የተረፈው ቅጽል ብቻ ነው” የተባለ ይመስል አንዳንድ ማስታወቂያ ሥራዎች ኧረ እጄ ላይ ያሉት ቅጽሎች ሊያልቁብኝ ነው…የሚሉ አይነት ይመስላሉ፡፡ እናላችሁ…ማስታወቂያዎች መስመር ሲያልፉ የምርቱን ወይም የአገልገሎቱን ስምና አይነት እንኳን ሳናውቅ መታዘባችን ልብ ይባልልንማ፡፡

በየቦታው ሥርአት የሚያስከብሩ ሰዎች መስመር ሲያልፉ ትልቅ ትንሽ አይሉም፡፡ መጥቶ ወደዛ ጠጋ በሉ ሲል እግረ መንገዱን እየገፈተረ ነው፡፡

አንዳንዴ “ሀይ የሚል” እየጠፋ ነው እንጂ… “ጠጋ በሉ…” ተብሎም አልሰማ ብሎ ሰልፍ እያበላሸ ያለ ካለ አንድ ነገር ነው፡፡ ግን ትክክለኛ ቦታ ላይ ያለ የሚመስለው የአራት ልጆች አባት፣ በሰፈር በመሥሪያ ቤት በባህርዩና በሥራው የሚከበር ሰውን “ወደዛ ጠጋ በል!” ተብሎ ትእዛዙና ግፍትሪያው አንድ ላይ ሲመጡ አሪፍ ነገር አይደለም፡፡ ይህ መስመር ማለፍ ብቻ ብሎ ለመተው በጣም ያስቸግራል፡፡

ስሙኝማ…ትምህርት ቤቶች ሊጀመሩ ነው፡፡ እናላችሁ…የምር መስመር ማለፍና ሀይ ባይ የለበትም የሚያስብሉ ነገሮች የሚታዩት እዚህ ነው፡፡

የሚገርመው ነገር በተለይ መዋዕለ ህጻናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አካባቢዎች የሚታየው የምዝገባ ምናምን ጭማሪ፣…አለ አይደል… መስመሩን በብዙ ሜትሮች ማለፍ ነው፡፡

“የቤት ኪራይ ጨምሮብናል” እየተባለ ለሦስትና አራት ሺህ ብር የቤት ኪራይ ጭማሪ ሦስት መቶና አራት መቶ ብር መመዝገቢያና ዓመታዊ ክፍያ ላይ መጨመር የሚገርም ነው፡፡ ግን ምን ማድረግ ይቻላል… ‘መስመር አልፈሀል’ የሚል “ሀይ ባይ” በሌለበት እንዲሁ አፋችንን እየተመተምን እንኖራለን፡፡

እያንዳንዱን… መስመር እየታለፈ ያለበትን ነገር እንዘርዝር ብንል ሊሆንልን አይችልም…ችግሩ ያን ያህል ስር ሰዷልና!

ደህና ሰንብቱልኝማ!

 

 

Read 2710 times Last modified on Saturday, 01 September 2012 10:59