Print this page
Saturday, 05 June 2021 12:48

ኢትዮጵያዊ ኩራታችንና የዲፕሎማሲ ፈተናዎቻችን

Written by  ደስታ መብራቱ
Rate this item
(5 votes)

      "-የአሜሪካንን ብሔራዊ ክብር የሚነካ ማናቸውም ንግግር በምንናገርበት ወቅት አብዛኛዎቹን ፍትሃዊ አስተሳሰብ ያላቸውን ነጭ ፖለቲከኞችን ብቻ ሳይሆን ብዙውን ጊዜ ለኢትዮጵያ ጥቅም የሚከራከረውን የአሜሪካውን ምክር ቤት የጥቁሮች ስብስብ (American Congress Black Caucus) አባላትንም እንደምናስቀይም መረዳት አስፈላጊ ነው።-"
                 
            ሃገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጫና ውስጥ ትገኛለች። ይህንን የዲፕሎማሲ ጫና በፊታውራሪነት እየመራ ያለው ከኢትዮጵያ ጋር በረዥም ዘመን ወዳጅነት የሚታወቀው የአሜሪካ መንግሥት መሆኑ ለብዙዎች ግርምትን ፈጥሯል። ነገር ግን፣ የአሜሪካ መንግሥትን የውጭ ፖሊሲ ዋነኛ የቅኝት መርሆች ለሚረዳ ሰው ብዙም አስገራሚ አይደለም። የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በሶስት አበይት መርሆች እንደሚመራ ተደጋግሞ ሲገለጥ ይሰማል። እነኚህም፣ ብሔራዊ ጥቅምን ማረጋገጥ፣ ሰብዓዊ መብትን ማስከበርና ዲሞክራሲያዊ እሴቶችን ማራመድ ናቸው። የኋለኞቹ ሁለቱ መርሆች፣ አስፈላጊ ሲሆን በማጣፋጫነት የሚጨመሩ እንጂ በሁሉም ሁኔታዎች ውስጥ ከልብ ተተግብረው እንደማያውቁ በርካታ ማሳያዎች ማቅረብ ይቻላል። የፊሊፒንሱን ፈርዲናንድ ማርኮስ እና የአፍሪካውን ሞቡቱ ሴሴኮ ጨምሮ በርካታ አምባገነኖች በህዝቦቻቸው ላይ ቁጥር ስፍር የሌለው ግፍ የፈጸሙት በአሜሪካና ምዕራባዊያን መንግሥታት ድጋፍ መሆኑ በግልጽ የሚታወቅ ነው። ወደ ቅርቡ ጊዜ የሃገራችን ሁኔታ ስንመጣም፣ ቁጥር ስፍር የሌለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸመውንና በተከታታይ ምርጫ ከዘጠና እስክ መቶ ፐርሰንት አሸነፍኩ እያለ ሲያፌዝ የነበረውን ህወሃት-ኢህአዴግ፣ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት አዋላጅ አድርገው ሲያቀርቡልን እንደነበር እናስታውሳለን። ከዚህ አኳያ፣ የውጭ ፖሊሲያቸው የምንጊዜውም ገዢ መርህ፣ የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ መሆኑ ግልጽ ነው።
በአሁኑ ወቅት፣ አሜሪካና ምዕራባዊያን ለምን ፊታቸውን አዞሩብን ለሚለው በርካታ ምክንያቶች ሲጠቀሱ ይሰማል። በዋነኝነትም፣ በመካከለኛው ምሥራቅ ካላቸው ብሔራዊ ጥቅም አኳያ ለግብፆች ማድላታቸው፣ አፍቅሮተ-ህወሃት የጠናባቸው ባለሥልጣናት በባይደን አስተዳደር ውስጥ መበራከታቸው፣ ዓለም አቀፉ ሚዲያና የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች በህወሃት ደጋፊዎች የሃሰት መረጃ መጠለፋቸውና የእጅ አዙር ቅኝ ገዢነት ፍላጎታቸው ይጠቀሳሉ። ምንም እንኳን እንደ ብዙዎቹ የውጭ ጣልቃ ገብነት ፖሊሲዎቻቸው፣ የአንዳንድ ጥያቄዎቻቸው አቀራረብ ቅጥ ያጣ ቢሆንም፣ ባሁኑ ወቅት በአሜሪካ መንግሥት በመወሰድ ላይ ያሉት እርምጃዎች፣ በሃገሪቱና በቀጠናው ያላቸውን ብሔራዊ ጥቅም ግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑ አያጠያይቅም። ይህ ደግሞ፣ ከአትዮጵያ ጋር ብቻ ተያይዞ የሚታይ ሳይሆን ከዓለም አቀፉ የጂኦ ፖለቲካ አሰላለፍና በተለይም ከአፍሪካ ቀንድና ከመካከለኛው ምሥራቅ ጂኦ ፖለቲካ ጋር የተያያዘ ነው። ይህ እና ሌሎቹም ከላይ የተጠቀሱት ምክንያቶች አሁን ለተፈጠረው ሁኔታ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ቢችሉም፣ ካንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በእንዲህ ዓይነት ፍጥነት ከወዳጅነት ወደ ጠላትነት ለመሸጋገር ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ለማለት ግን ያስቸግራል። በተለይም፣ ኢትዮጵያ በቀጠናውና በአፍሪካ ካላት ጉልህ ስትራተጂያዊ ስፍራና የዚህች ሃገር አለመረጋጋት በቀጠናውም ሆነ በአህጉሪቱ ሊፈጥር ከሚችለው ቀውስ አኳያ በአሁኑ ወቅት የአሜሪካን መንግሥት እየወሰዳቸው ያለው አደገኛ አቋሞች ከላይ ከተጠቀሱት ምክንያቶች የበለጠ ስውር ምክንያት ሊኖር እንደሚችል ያስገምታል። በእነርሱ በኩል ሊኖር የሚችለውን ተጨማሪ ምክንያት ጊዜ የሚገልጠው ቢሆንም፣ የእኛ ትኩረት፤ ‘እኛስ የት ጋ ነው የሳትነው ወይንም የተሳሳትነው?’ ብሎ የእርምት እርምጃ መውሰድ ላይ ቢሆን ፈተናውን ለመሻገር ያግዛል።
የማናቸውም ሃገር ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ዋነኛ መለኪያው ብሔራዊ ጥቅምን ከዓለም አቀፍና  ቀጠናዊ ሁኔታዎች ጋር አጣጥሞ በማራመድ አቅሙ ነው።  ይህ ደግሞ፣ ዓለም አቀፍ ጂኦ ፖለቲካውን፣ ድንጋጌዎችን፣ ስምምነቶችንና ልማዶችን (norms) በጥልቀት ተረድቶ ለራስ ሃገር ጥቅም በሚበጅ መልኩ የዲፕሎማሲ ጨዋታውን መጫወት ይጠይቃል። ወደ ኋላ መለስ ብለን ታሪካችንን ብንመለከት፣ አፄ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን ለመለወጥ የነበራቸው ታላቅ ጉጉትና አትዮጵያዊ ኩራት በታሪክ የሚዘከር ሆኖ ከእንግሊዝ መንግስት ጋር የነበራቸውን ግንኙነት በዲፕሎማሲያዊ አግባብ ሊመሩት ባለመቻላቸው ፍጻሜአቸው አሳዛኝ-ጣፋጭ (bitter-sweet) ሊሆን ችሏል። በተመሳሳዩ፣ አፄ ዮሐንስም ቀጠናዊ የሃይል አሰላለፉን ባግባቡ ሳያጤኑ በማሃዲስቶች የተከበበውን የግብጽ ጦር አጅበው ወደ ምፅዋ በማሳለፋቸው፣ ሃገሪቱ ለመሃዲስቶች ወረራ ልትዳረግና እርሳቸውም መተማ ላይ ሊሰዉ ችለዋል። ከዚህ በተቃራኒው፤ የኢትዮጵያ ወርቃማው የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ዘመን ተብሎ የሚጠቀሰውን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የነበረውን የአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን እናገኛለን። ይህ ዘመን፣ አትዮጵያ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ታላቅ ክብር የተጎናጸፈችበት ወቅት ነበር። ለዚህም አቶ አክሊሉ ሃብተወልድና አቶ ከተማ ይፍሩን የመሳሰሉት ዲፕሎማቶቻችን ታላቅ ባለውለታዎቻችን ናቸው። የዚህ ዋናው ሚስጥሩ፣ በማናቸውም ሁኔታ ውስጥ የማይዛነፈውን ኢትዮጵያዊ ሰብዕናቸውን ጥልቅ ከሆነው የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ዕውቀታቸው ጋር አጣጥመው መተግበራቸው ነው። ይህ ወርቃማ የዲፕሎማሲ ዘመን ለሃገራችን የውጭ ግንኙነት እንደ ታላቅ ምሳሌ ሊወሰድና ሊጠና የሚገባው ነው።
ባለፉት ጥቂት ወራት ከተፈጠሩት ዲፕሎማሲያዊ ቀውሶች ጋር በተያያዘ የሃገራችን የረዥም ዘመን ባለታሪክነትና ነፃነቷን ጠብቃ መቆየቷ እየተጠቀሰ፣ ዲፕሎማሲያዊ ትሁትነት (decorum) በጎደለው መልኩ አሜሪካንና ምዕራባዊያን ሃገራትን የሚሸነቁጡ ንግግሮች ከፖለቲካ መሪዎች፣ ተንታኞችና ሚዲያዎች በተደጋጋሚ ተደምጠዋል። እነኚህ ንግግሮች ከመንግሥታቶቹ አልፈው የየሃገራቱን ህዝቦች በአጠቃላይ የሚነኩ በመሆናቸው፣ ለመልካምና ሚዛናዊ ግንኙነት ሊቆሙ የሚችሉ ወዳጆቻችንንም እንዳሳጣን መገመት ይቻላል። የአሜሪካንን ብሔራዊ ክብር የሚነካ ማናቸውም ንግግር በምንናገርበት ወቅት አብዛኛዎቹን ፍትሃዊ አስተሳሰብ ያላቸውን ነጭ ፖለቲከኞችን ብቻ ሳይሆን ብዙውን ጊዜ ለኢትዮጵያ ጥቅም የሚከራከረውን የአሜሪካውን ምክር ቤት የጥቁሮች ስብስብ (American Congress Black Caucus) አባላትንም እንደምናስቀይም መረዳት አስፈላጊ ነው። ዛሬ ባለንበት ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ማናቸውም ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ልማት ሊሳካ የሚችለው በሃይ ዘራፍ ስሜት (bravado) በሚመራ የውጭ ግንኙነት ሳይሆን ዕውቀትና ብልሃት ላይ በተመረኮዘ ክላልዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብር ብቻ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። በዚህ ሂደት ውስጥ ታላቁ ፈተናችን ደግሞ፣ ኢትዮጵያዊ ማንነታችንንና ኩራታችንን ከቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ እውነታዎች ጋር በማጣጣም፣ ብልጠት የተመላበት ዲፕሎማሲ (smart diplomacy) መተግበር ነው።
ሸንቋጭ ንግግሮቻችን ከምዕራባዊያኑ ጋር ብቻ ሳይሆን ከብዙዎቹ አፍሪካውያን ወንድሞቻችን ጋርም ሊያቀያይሙን እንደሚችሉ አያጠራጥርም። ስለ ኢትዮጵያ ታላቅነት፣ የረዥም ታሪክ ባለቤትነትና በቅኝ አለመገዛት አብዝተን በተናገርን ቁጥር ሌሎች አፍሪካውያን ወንድሞቻችንን ቅኝ ተገዢነታቸውን እያስታወስናቸው መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል። ባሁኑ ወቅት በዙሪያችን የሚገኙ ጎረቤት ሃገሮች ከግብጽ ጋር የሚፈራረሙት ወታደራዊ ስምምነቶች የሚያመላክቱት አንድ ዲፕሎማሲያዊ ህመም እንዳለ መረዳት ጠቃሚ ነው። የእነ አቶ አክሊሉ ሃብተወልድ ታላቅ የዲፕሎማሲ ሥራ መለያ ማህተሙ (signature diplomacy) ‘እኛ አፍሪካውያን አይደለንም’ የሚለውን የንጉሣዊያን አስተሳሰብ ቀይሮ የእኛ ኢትዮጵያውያን ዕጣ ፈንታ ከሌሎች አፍሪካውያን ወንድሞቻችን ነጻ መውጣት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ መሆኑን በማረጋገጥ ለአፍሪካ፟፟-አቀፍ (pan-african) ህብረትና ነፃነት ታጥቀው መስራታቸው ነው። ይህ ጥረታቸው፣ ከዓድዋ ድል ባልተናነሰ መልኩ፣ አፍሪካውያን ኢትዮጵያን የነጻነታቸው ተምሳሌት እንዲያደርጓትና በርካቶቹም ነፃነታቸውን ሲቀዳጁ የባንዲራ ቀለማችንን እንዲጋሩ አድርጓቸዋል። እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ፣ እኛ ኢትዮጵያውያን ከልባችን ልንኮራበት የሚያስችለን የቀደምት ሥልጣኔና ያልተቋረጠ የሃገረ መንግሥት ታሪክ ያለን ህዝቦች መሆናችን ጥያቄ ሊነሳበት የሚገባ ጉዳይ አለመሆኑ ነው። ነገር ግን፣ ይህንን ታላቅ ማህበራዊ እሴት (social capital) በሌሎች ላይ ልንታበይበት ሳይሆን ካለንበት አሳፋሪ የድህነት አረንቋ ለመውጣት በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል።         
አሁን ከምንገኝበት የዲፕሎማሲ አጣብቂኝ ውስጥ ለመውጣት፣ ከሁሉም በፊት ማናቸውም የመንግሥት ባለሥልጣን፣ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና ዲፕሎማቶች፣ ዲፕሎማሲያዊ ትሁትነት ከጎደላቸው አነጋገሮችና ውንጀላዎች በመቆጠብ፣ ሃገራዊ ልዕልናንና ብሔራዊ ጥቅምን ለሚያስጠብቅ ቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብር ዝግጁ መሆናቸውን ደጋግመው ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ፣ የኢኮኖሚ ልማት ትልሞቻችን በማንም ላይ የእኛን የበላይነት ለማስፈን ሳይሆን፣ በምግብ እህል ራሳችንን ለመቻል፣ በሃገራችን ተንሰራፍቶ የሚገኘውን ድህነት ለማስወገድ፣ የህዝባችንን አጠቃላይ ኑሮ ለማሻሻልና ለቀጠናዊ ልማትና እድገትም የበኩላችንን አስተዋጽ ለማድረግ መሆኑን አበክሮ መናገር ያስፈልጋል። ይህንንም ለማሳካት፣ አጎራባች ከሆኑም ሆነ ሌሎች አጋር ሃገሮች ጋር በቅርብ ትብብር ለመስራት ያለንን ቁርጠኝነት ማረጋገጥና ለተግባራዊነቱም ያለንን ሁለንተናዊ ዝግጁነት ማሳየት ይገባል። ከዚህም በላይ፣ ለዲፕሎማሲው ጫና እንደ ዋነኛ መሳሪያ የሚጠቀሙበትን በትግራይ ውስጥ ያለውን አሳሳቢ የሰብዓዊነት ቀውስና የመብት ጥሰት፣ በትግራይ ህዝብ ቀጥተኛ ተሳትፎ፣ አካታች መፍትሄ ለመሻት መንግሥት ወሳኝ እርምጃዎችን ሊወስድ ይገባል። በተጨማሪም፣ የዓለም አቀፋዊው ዘመቻ ትኩረት የሆነውን የኤርትራ ጦር በኢትዮጵያ ውስጥ መገኘት ህጋዊ መቋጫ መስጠት፣ ዲፕሎማሲያዊ ውጥረቱን በማርገብ ረገድ የራሱ የሆነ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል። ይህንን በተመለከተ፣ የኤርትራ መንግሥትም የጦሩ በትግራይ ውስጥ ለተራዘመ ጊዜ መቆየትና በተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መወንጀል፣ የኢትዮጵያ ህዝብ በህወሃት ጥቃት ወቅት ለተደረገው ታሪካዊ ድጋፍ የሰጠውን ታላቅ አክብሮት የሚያጠለሽ ከመሆኑም በላይ በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ሊኖር የሚችለውን ዘላቂ ሠላምና የልማት ትብብር ሊጎዳው እንደሚችል ማስገንዘቡ ጠቃሚ ይሆናል።
በመጨረሻም፣ አሁን ከምንገኝበት ዲፕሎማሲያዊ ቀውስ ውስጥ ለመውጣትም ሆነ የሃገራችንን የወደፊት ዓለም አቀፍ ግንኙነት ጤናማ መስመር ለማስያዝ፣ ኢትዮጵያ ያሏትን ማናቸውም የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ አቅም ማነቃነቅ፣ ማስተባበርና መጠቀም አስፈላጊ ነው። ለዚህም እንዲረዳ፣ ለዓመታት የካበተ ልምድ ያላቸውን ነባር (veteran) ዲፕሎማቶቻችንን፣ በሳል የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁራንን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን፣ የሃይማኖት ተቋማትንና በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ ኢትዮጵያውያንንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን የሚያካትት አንድ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምክር ቤት መመስረትና ከላይ የተጠቀሰውን አዲስ የግንኙነት ሥራ እንዲያግዝ ማድረግ ከፍተኛ ጠቃሜታ ይኖረዋል። ይህ ምክር ቤት ከአሜሪካና ምዕራባዊያን ሃገሮች ጋር በሚካሄደው ማናቸውም ውይይት ውስጥ በንቃት እንዲሳተፍ ማድረጉ፣ ባሁኑ ወቅት እየተካረረ የመጣውን የቃላት ምልልስ ለማለስለስና ለማከም ከማገዙም በላይ በመንግሥታዊ ባለሥልጣናት ከሚነገረው ውጭ ተጨባጭ ሃገራዊ ዕውነታውን ከሌሎች ወገኖች የሚረዱበትን ሁኔታም ይፈጥርላቸዋል።
በአጠቃላይ፣ ሁሉም የኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ያሳስበኛል የሚል ወገን ከፊት ለፊታችን እያስገመገመ ያለውን ዓለም አቀፋዊ ጫና ለመሻገር፣ ከስሜታዊነት ይልቅ ብልህነትን፣ ከፍጥጫ ይልቅ ትብብርንና ከቃላት እርግማን ይልቅ ስልጡን ንግግርን ጨብጦ ቢጓዝ ጠቃሚ ይሆናል።                    
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው  ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው ስታለንቦሽ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፈሰር ሲሆኑ የአፍሪካ ሳይንስ አካዳሚም አባል ናቸው።             



Read 1246 times