Saturday, 05 June 2021 12:42

እስክንድር ነጋ ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ሊወዳደር ነው

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(5 votes)

  የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ሊቀ መንበር አቶ እስክንድ ነጋ፤ በ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ሊወዳደር ነው፡፡ ፓርቲው እስክድርን በየካ ክፍለ ከተማ ለአዲስ አበባ ም/ቤት እንደሚያወዳድረው ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ ባልደራስ ለእወነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በእጩነት ያቀረባቸውን አቶ እስክንድር ነጋን  በህግ ቁጥጥር ስር የሚገኙ በመሆናቸው በምርጫው እጩነት ለመመዝገብ እንደማይችሉ ገልፀው ነበር፡፡ ውሳኔውን ያልተቀበለው ባልደራስ፤ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ክስ መስርቶ የነበረ ቢሆንም ፍረውድ ቤቱ የምርጫ ቦርድን ውሳኔ በማፅናት ሊመዘገቡ አይችኩን የሚል ውሳኔ ሰጥቶ ነበር፡፡
በውሳኔው ቅር የተሰኘው ባልደራስ፤ ጉዳዩን ወደ ፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት  ሁለተኛ ሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ ብሎ ፍ/ቤቱ ጉዳዩን ካየና ከመረመረ በኋላ ምርጫ ቦርድ እጩዎችን ሊመዝግብ ይገባል የሚል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ይሄን ተከትሎ ምርጫ ቦርድ ወሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚቸገር በተደገጋሚ አሳውቋል፡፡ ይሁን እንጂ ባልደራስ በምርጫ ቦርዱ ላይ የአፈፃፀም ክስ በመመስረቱ የምርጫ ቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ከትናንትና በስቲያ ጉዳዩን በሚመለከተው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ የምርጫ ጉዳዮች ችሎት ቀርበው፣ ፓርቲው ለምርጫው እንቀርቡለት የሚፈልጋቸውን እጩዎች የመመዝገቡ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በዚህ መሰረትም ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ መሪውን አቶ እስክንድ ነጋን ጨምሮ አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስመ፣ አስካለ ደምሴን በመጪው ምርጫ እንደሚወዳደሩለት ማስመዝገቡንና የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ እስክንድ ነጋ፣ በየካ ክፍለ ከተማ ለአዲስ አበባ  ምክር ቤት እንደሚወዳደሩ ገልጿል፡፡
የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት አባል አቶ ወግ ደረስ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ “ፍርድ ቤቱ የሠጠው ውሳኔ ለፓርቲው የተለየ ድጋፍ ለማድረግ አይደለም፤ ህጉ የሚፈቅደውንና በህግ የተረጋገጠውን መብታችንን ነው የጠየቅነው የተሰጠው ውሳኔም ይኼ ነው፡፡ ምርጫ ቦርዱ ህግን በመጣስ እንዳንመዘገብ ከልክሎን ነበር፤ የተከለከልንበት የህግ አግባብ ስህተት እንደሆነ የህግ ባለሙያ ለሁኑት ለሰብሳቢዋ መንገር ለቀባሪው እንደ ማርዳት ነው፡፡ ሁኔታው ከህግ ውጪ እንደሆነ በተደጋጋሚ እየጠየቀን ምላሽ ባለማግኘታችን በፍ/ቤት መብታችንን ልናስከብር ችለናል” ብለዋል፡፡ “አክለውም በሰጡት አስተያየት፤ ፕሬዝዳንታችንን አጥተን የምናደርገው ምርጫ የሚያጎድልብን ነገር ነበረው፤ አሁን ለእኛ ትልቅ ድል ነው፡፡ የብልጽግና ፓርቲ አባላት የሚያደርሱብንን ጫና ችለን መጪውን ምርጫ በአሸናፊነት እንወጣለን” ብለዋል፡፡
እነ እስክንድር ነጋ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር የአርቲስት ሃጫሉ ሑንዴሳ ግድያን ወቅት ከተቀሰቀሰው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ፣ በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል፡፡

Read 13495 times