Saturday, 05 June 2021 12:19

በእነ ጀነራል ሰዐረ ግድያ የተከስሰው አስር አለቃ ጥፋተኛ ተባለ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(0 votes)

   የቀድሞ የአገሪቱን ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም  ጀነራል ሰዐረ መኮንንና ሜጀር ጀነራል ጋዛኢ አበራን በመግደል ወንጀል ክስ ቀርቦበት ነበረው አስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ፤ በተከሰሰበት ወንጀል ጥፋተኛ ነው ሲባል የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረ ሽብርና የህገ-መንግስት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
ፍ/ቤቱ ትናንት በዋለው ችሎት በሰጠው ውሳኔ፤ ተከሳሹ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በጀነራል ሰዐረ መኮንን ላይ በመኖሪያ ቤታቸው ሊጠይቋቸው ከመጡት ሜ/ጀነራል ገዛኢ አበራ ጋር በሽጉጥ መቶ ገድሏቸዋል፡፡ በዚህም ወንጀል ተጠያቂ ነው ሲል የጥፋተኝነት ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ጀነራል ሰዐረ በዕለቱ ከወቅቱ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ከነበሩበት ኢንጂነር  ታከለ ኡማ ጋር ችግኝ ተከላ ውለው ወደ ቤታቸው ከተመለሱ በኋላ፣ አመሻሹን በባህር ዳር ከተማ በዶ/ር አምባቸው ላይ የተፈፀመውን ግድያ ተከትሎ፣ በመኖሪያ ቤታቸው ሆነው በስልክ አመራር እየሰጡ በነበሩበት ወቅት ተከሳሹ በሽጉጥ መቶ ገድሏቸዋል- ብሏል፡፡
የ1996ቱን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/1 ሀና ለ 35/38  እንዲሁም 238 በመተላለፍ በዋና ወንጀል  ፈፃሚነት ክስ ቀርቦበት ነበር፡፡ በዚሁ ክስ መሰረት ተከሳሹ  የመከላከያ ምስክሮችንና የሰነድ ማስረጃ አቅርቦ የተከላከለ ቢሆንም፣ ክሱን በተገቢው መንገድ ማስተባበል ባለመቻሉ ወንጀሉን መፈፀሙን ፍርድ ቤቱ ማረጋገጡ በፍርዱ ላይ ተገልጿል፡፡ የተከሳሹን የቅጣት  ማቅለያ ለመቀበልም ጉዳዩን ለሰኔ 11 ቀን 2013  ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Read 880 times