Saturday, 05 June 2021 12:17

ካገር እኖር ብዬ ከብት እነዳ ብዬ ልጅ አሳድግ ብዬ ለባሻ ዳርኩለት ሚስቴን እቴ ብዬ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

   ከዕለታት አንድ ቀን አንድ እንግዳ ወደ ገጠር ይመጣና አንደኛው ባለአገር ቤት ያርፋል፡፡ ለወትሮውም ወታደር ከሆነ በተሰሪነት ነበር የሚኖረው፡፡ ያም ተሰሪነት የተገባበት ባለሀገር የግዱን ነበረ ወታደርነት ይባስ ብሎም ያ ወታደር የባላገሩን ቆንጆ ልጅ አየና እንዲህ ሲል ጠየቀው፡-
“አንተ፤ ይህቺ እህትህ ስንት አመቷ ነው?” አለው፡፡
ነገሩ የክጀላ ነው፡፡
“ያም ባላገር ሚስቴ ናት” ማለት ፈርቶ “የእህቴ እድሜ ይህን ያህል ነው” ብሎ ተናገረ፡፡
ያም ጋጠወጥ ወታደር የባላገሩን ሚስት ይዞበት አደረ፡፡
በነገታው ያ ባላገር ደጁ ተቀምጦ፣ አቀርቅሮ እንደሚከተለው ገጠሞ አንጎራጎረ
ካገር እኖር ብዬ
ከብት እነዳ ብዬ
ልጅ አሳድግ ብዬ
ለባሻ ዳርኩለት ሚስቴን እቴ ብዬ
ይሄ የሆነው በሌሎቹ ነገስታት ዘመን እንጂ በሚኒልክ ዘመን አልነበረም፡፡ ከላይ የተጠቀሰው ታሪክ የተገኘው አፈወርቅ ገ/ኢየሱስ የተባሉ ደራሲ የጻፉት “ዳግማዊ አጼ ሚንልክ” ከተባለው  መፅሐፍ ነው፡፡  አሳጥረን አቅርበነው ነው፡፡
ለአያሌ የጀግንነት አይነቶች ምስክር ሆነናል፡፡ ገናም እንሆናለን፡፡ በየዘመኑ የየነገስታቱ አገዛዝና ስርዓት በሕዝብ ላይ የራሱን አሻራ ሲያሳርፍ እያየን ብዙ ዓመታት ገፍተናል፡፡ ምናልባትም ገና ዛሬም እንቀጥላለን፡፡  ከእያንዳንዱ ስርዓት የምናገኘው፣  በውስጡ እያለ የማይታየን  በርካታ ህፀፅ፣  ከስርዓቱ ወጣ ብለን ስናስተውል ፍንትው ብሎ ይታየናል፡፡
ትውልዱንም ለማብቃት አዳዲስ ጥርጊያ መንገድ እንከፍታለን፡፡ በዚህ ረገድ ስናየው መንገድ መዘርጋት ጀግንነት ነው፤ ትምህርት ቤት መክፈት ጀግንነት ነው፤ ጤና ጣቢያ መስራት ጀግንነት ነው፤ አለማችንን እያመሰ ያለው የኮሮና ቫይረስ መፍትሔ መሻት ቆራጥነት ነው፤ የስፖርት ማነቃቂያ ስራዎችን በጋራ ማደራጀት ጀግንነት ነው፤ ፓርኮችን ማልማት ጀግንነት ነው፤ የመኖሪያ የወላጆችንና የተማሪዎች ኮሚቴዎችን በሶስትዮሽ ስልት ማዋቀር ታላቅ ጀግንነት ነው፤ መማር ያልቻሉ ወጣቶችን በገጠርም በከተማም በማቴሪያልም በገንዘብም እየረዱ እድሜያቸው ለትምህርት ከማለፉ በፊት ማናቸውንም እገዛ ማድረግ ከጀግንነትም የላቀ ጀግንነት ነው፡፡ ዛሬ መሰረተ ልማትን ማንቀሳቀስ እንደ ታላቅ ጸጋ የሚታይበት የሀገርን ጥሪ ከድንበር እስከ መሃል ሀገር  እንደ ተገቢነቱ ውል ማስያዝና ጉዳዬ ብሎ፣ እኔንም ያገባኛል ማለት ታላቅ ኃላፊነትን መቀበል ነው፡፡ በስልጣን ላይ ያሉ አካላት ሂስ ሲያስፈልጋቸው ቸል ሳይሉ፣ ሙያዊ ድጋፍ መስጠትና ስነ-ምግባራዊ ተሞክሮን ማጋራት ዛሬም ወሳኝ ነው፡፡
ከላይ ለጠቀስናቸው ፍሬ ሃሳቦች ዋና መጠቅለያ የሚሆነን፣ የፍትህ አካላትን በተጠናከረ መልኩ አደራጅቶ መምራት መምራት ስለሆነ፣ እዚሁ ላይ ብርቱ ትኩረት የምንጠየቅበት አንገብጋቢ ወቅት ነው፡፡
ከሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ታዋቂ ድርሰቶች አንዱ ከሆነው ከ”ቴዎድሮስ” ቴአትር አንድ ስንኝ እንዋስ፡-
“ያለፈ ጥረታችንን፣ ሳስታምመው ትዝ ሲለኝ
ከሞከርነው ነገር ይቅ ያልሞከርነው ነው የሚቆጨኝ” የሚለውን ልብ ብለን እናስተውል፡፡
አንድም ድግሞ ከ”ማክቤል” የመጨረሻ ሰዓት በመጥቀስ፡-
“የነገ ውሎ የነገ ውሎ የነገ ውሎ
ከቀን ወደ ቀን ይሳባል፣ በእድሜ ንፉግ ጀርባ ታዝሎ
ትላንትናም ከትላንት በስቲያም፣ ለጅሎች ጥርጊያ አሳምሮ
ዛሬ ፈጥሮ ነገ ቀብሮ…
እግረ መንገዳችንንም  ከብራውን ጋር
“ደግሞም ማወቅ ማለት
ከውጭ ያለውን ሄዶ ከመፈለግ
ከውስጥ የበራውን እንዲወጣ ማድረግ” …ማለትንም አልዘነጋንም፡፡
ለመደምደሚያችንም…
ከኦቴሎ ጋር አንቺስ ሌላይቱ ጮራ አንቺ የጉም ፍንጣቂ
ከእብሪት ከተንኮል ዛፍ ፍሬ የተቀመምሽ ጭማቂ
እፍ ብዬ ባጨልምሽ ልጠፋብኝ ያንቺ ጮራ የለም
 መለኮታዊ ሃይል አንቺን የሚያበራ… እንላለን፡፡

Read 15138 times